POWr Social Media Icons

Saturday, February 2, 2013


ምርጫ መጥቶ በሄደ ቁጥር ላለፉት 22 ዓመታት በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡
‹‹በግንባታ ሒደት ላይ ነው›› የሚባለው የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ከዜጎቹ፣ ከምሁራን፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ፍላጎት ካላቸው ሦስተኛ ወገን የውጭ አገር ተቋማትና አገሮች እንዲሁም ዜጎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሌሎች አካላትና ግለሰቦች የሚነሱትን ጥያቄዎች በሒደት የመመለስ ፍላጎት ያለው አይመስልም፡፡

ለማቀራረብ እንኳን የሚከብደው ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ኢሕአዴግ የሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም ላይ የሚቀርበው ጥያቄና የሚሰጠው ምላሽ አንዱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ርዕሰ ጉዳይ ኢሕአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቀራርበው ለመሥራት እንዳይችሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ሌላኛው ጥያቄ በኢሕአዴግና በመንግሥት መካከል ያለውን ግልጽ ያልሆነ ግንኙነት ወይም መቀላቀል ይመለከታል፡፡ ኢሕአዴግ የፓርቲውንና የመንግሥትን ሚና በመቀላቀልና ፓርቲው ያለአግባብ የመንግሥትን ሀብት እንዲጠቀም እንዳደረገው በተደጋጋሚ ቅሬታ እንዲቀርብበት በር ከፍቷል፡፡

የምርጫ ጉዳይ አስተዳዳሪ ተቋማትና በዲሞክራሲ ግንባታ ሒደቱ ላይ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ተቋማት ላይ የሚነሳው የነፃነትና የገለልተኝነት ጥያቄ ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድና የመንግሥት የሚድያ ተቋማት አሁንም የዛሬ 18 ዓመት ይባሉ እንደነበረው ኢሕአዴግን ብቻ በማገልገል፣ በሕግ ሁሉንም ተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩልነት እንዲያገለግሉ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ አይደለም ተብለው ይተቻሉ፡፡

ኢሕአዴግ በየትኛውም መስፈርት ጠንካራ ፓርቲ ነኝ ይላል፡፡ በአንፃሩ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተጠናክረው በመተባበር በመሥራት ለኢሕአዴግ ፖሊሲዎች አማራጮች ከማቅረብና ደጋፊና የድጋፍ መሠረታቸውን ከማደላደል ይልቅ፣ እርስ በርስ በመናቆር ባሉበት መርገጥ መቀጠላቸውም ሌላኛው ጥያቄ የሚነሳበት ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች አለመጠናከር በተወሰነ መልኩ ኢሕአዴግና ያልዳበረው የፖለቲካ ባህል አስተዋጽኦ ያላቸው ቢሆንም፣ ትልቁን ድርሻ የፓርቲዎቹ ቁርጠኛ አለመሆንና ጠንክሮ አለመሥራት ይወስደዋል፡፡

ከአባላት ብዛትና የገንዘብ አቅም ጋር ተያይዞ በኢሕአዴግና በሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት ለንፅፅር እንኳን ሊቀርብ አይችልም፡፡ ለዚህ የሕጉ ይዞታና የፖለቲካ ባህሉ የራሱ አስተዋጽኦ ቢኖረውም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ እነዚህን ችግሮች ተቋቁመው አባላት በማፍራት፣ የገንዘብ አቅማቸውን በማዳበርና በገንዘብ ኃይል የሚሠሩ ሥራዎችን ለመፈጸም ያደረጉት ጥረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

ምርጫ 2002ን ተከትሎ የመጣው የቅርብ ጊዜ አንገብጋቢ ጥያቄ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅን ተከትሎ የተቋቋመው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና ምክር ቤቱ ያወጣውን የስምምነት ሰነድ የመፈረምና ያለመፈረም ጉዳይ ነው፡፡

እነዚህን ጥያቄዎች የመመለስ ኃላፊነት የመንግሥት ወይም የኢሕአዴግ ብቻ አይሆንም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሌሎች የምርጫው ወይም የዲሞክራሲ ግንባታ ሒደቱ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የዜጎችም ኃላፊነት ነው፡፡ ይሁንና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ ሥር እንዲሰድ ኢሕአዴግ የሚፈልግ ከሆነ የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ተቋማዊ መሠረት እንዲኖረው፣ መጫወቻ ሜዳው ለሁሉም ሕጋዊ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተመቸ እንዲሆን በማድረግ ትልቅ ሚና መጫወት ያለበት ሲሆን፣ እንደ መንግሥት ለሌሎቹ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሕጋዊ ከለላ በመስጠት ተወዳዳሪዎቹ የሚጠናከሩበትን ሥርዓት የመገንባት ኃላፊነት እንዳለበትም ሊገነዘብ ይገባል የሚሉ አካላት አሉ፡፡

አማራጭ ፖሊሲዎችን ማቅረብ
የኢሕአዴግ ምክር ቤት ኃላፊና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ‹‹ከስፔን የመጣ የአውሮፓ ኅብረት ታዛቢ ሲናገር የፓርላማ መቀመጫ የሌላው ፓርቲ እንኳን የክርክር ሰዓት ሊሰጠው የፓርቲውን ስም ለመናገር ሁለት ሰከንድ አይሰጠውም ነበር ያለው፡፡ የትም አገር የሚዲያ የአየር ሰዓት የሚሰጠው ቀደም ሲል በነበረው ምርጫ ውስጥ በሕዝቡ ይሁንታ በተገኘው መቀመጫ ስልት ልክ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

እውነታው ግን በዓለም ላይ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አገሮች አውሮፓን ጨምሮ የሚድያ የአየር ሰዓት የሚሰጡት የፓርላማ መቀመጫን ብቻ ከግምት ወስጥ አስገብተው አለመሆኑን ነው፡፡ አንዳንዶች ለትልልቅ ፓርቲዎች መቀመጫቸውን ግምት ውስጥ ሳያስገቡ እኩል የመከራከሪያ ሰዓት ይሰጣሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ፓርቲዎቹ ባገኙት ተመጣጣኝ የመራጮች ቁጥር መሠረት የአየር ሰዓት ያከፋፍላሉ፡፡ ባቀረቡት የዕጩዎች ቁጥር ብዛት የአየር ሰዓት የሚሰጡም አገሮች አሉ፡፡ ፓርቲዎቹ ባሉዋቸው አባላት ብዛት ጭምር የአየር ሰዓት የሚያከፋፍሉ አገሮች አሉ፡፡ መንግሥት ለፓርቲዎች የሚሰጠው የገንዘብ ድጎማ ጉዳይም በተመሳሳይ ከላይ በተገለጹት የተለያዩ መስፈርቶች አማካይነት ይከፋፈላል፡፡

አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የራሳቸውን አማራጭ ፖሊሲዎች የማቅረብ ተነሳሽነት የላቸውም፡፡ ይህ ደግሞ አገር ከመምራት ግብ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም ይላሉ፡፡ እንደማሳያም በዘመነ ኢንተርኔት ከኢዴፓና ከአንድነት ፓርቲዎች በስተቀር አማራጭ ፖሊሲያቸውን በድረ ገጾቻቸው ላይ አልጫኑም፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ ኢሕአዴግ ‘አዲስ ራዕይ’ንና ድረ ገጹን በመጠቀም ርዕዮተ ዓለሙንና ፖሊሲዎቹን በስፋት እያሰራጨ ሲሆን፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሐሳቦች የሚያዋጡ እንዳልሆኑ ጭምር ተንትኖ አቅርቧል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን በዚህም እንኳን የነቁ አልሆኑም፡፡ የአንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ልሳኖችም ኢሕአዴግን ከመተቸት ተላቀው የራሳቸው አማራጭ ፖሊሲዎች ለሕዝብ ለማስተዋወቅ የቻሉ አይደሉም፡፡

ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ የራሱን ፖሊሲዎች ሲያቀርብ በአብዛኛው ፓርቲው በመንግሥት ደረጃ የፈጸማቸውን ነገሮች የእኔ ፖሊሲዎች በማለት ሲያቀርብ ይስተዋላል፡፡ በሥልጣን ላይ ላለ ፓርቲ የፓርቲው ፖሊሲዎች የአገሪቱ ፖሊሲዎች መሆናቸው ብዙም የሚገርም አይሆንም፡፡ ይሁንና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ፖሊሲ አመንጪዎችና ፖሊሲ አስፈጻሚዎች ሁሉ ከፓርቲው ጋር ሙሉ በሙሉ የተቆራኙ አለመሆናቸውን በመግለጽ፣ ሰፊ መሠረት ያለው መንግሥት ማዋቀሩን ለማሳመን ለሚጥረው ኢሕአዴግ የፓርቲውንና የመንግሥትን የተለያዩ አስተዋጽኦዎች ለያይቶ ማየት ያስፈልገዋል፡፡

ሌላው በአማራጭ ፖሊሲዎች ጉዳይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰከነ መንገድ እንዳይወያዩ ያደረጋቸው ነገር ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎቹ አንዳቸው ለአንዳቸው ፖሊሲ በጎ ጎን ዕውቅና ለመስጠት አለመቻላቸው ነው፡፡ ኢሕአዴግ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ የአገሪቱን ሥርዓት እንደ አዲስ ለመቅረፅ ያላቸውን ፍላጎት በከፍተኛ ሥጋት ነው የሚመለከተው፡፡ ይህ የኢሕአዴግ ሥጋት በምሁራንና በአንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር የሚደገፍ ነው፡፡ ይሁንና የኢሕአዴግ ሥጋት ፓርቲዎቹ ‘ፀረ ሰላም’ እና ‘የሕዝብ ጠላት’ እንዲሁም ‘አመፀኞች’ ናቸው የሚል ሲሆን፣ ምሁራኑና ተቋማቱ ግን ሥጋታቸው የፓርቲዎቹ ፍላጎት ሕገ ወጥነት ሳይሆን ለዘላቂ ልማትና ሰላም በተጀመሩ ሥራዎች ላይ መቀጠል እንጂ፣ የተከፋፈለ ፍላጎት ባለባት ኢትዮጵያ ሁሉንም ነገር እንደ አዲስ መጀመር የሚያዋጣ እንዳልሆነ ከመገንዘብ ነው፡፡ አገሪቱ ልትሄድ በሚገባት አቅጣጫ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ፓርቲዎቹ ያለውን ሥርዓት ጠብቀው እንዲጓዙ ማድረግ የኢሕአዴግ አንዱ አማራጭ ቢሆንም፣ በዲሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ ፓርቲዎቹ ለምን አማራጭና የተለየ አቋም ያዙ በማለት መኮነን ግን ጤናማ አካሄድ አይደለም፡፡

‹‹በኢትዮጵያ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዳዮች›› በሚል ርዕስ በ1994 ዓ.ም. በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የታተመ የመንግሥት ሰነድ ‹‹በዳበረ የዲሞክራሲ ሥርዓት ገዥ የነበረ ፓርቲ ተቃዋሚ፣ ተቃዋሚ የነበረውም ገዥ የመሆኑ ጉዳይ የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት የሥልጣን ሽግግር ያለ አንዳች ችግርና ቀውስ በሰላማዊ መንገድ የሚፈጸም ከመሆኑም ባሻገር ኅብረተሰቡ በሚመራባቸው መሠረታዊ አቅጣጫዎች ላይ ይህ ነው የሚባል ለውጥን የሚያስከትል አይሆንም፡፡ በመሠረቱ በአገር ግንባታና በአስተዳደር ጉዳዮች ላይ አንድ የጋራ አመለካከትና እምነት መፈጠሩ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ማበብ መሠረታዊ ተፈላጊነት ያለው ጉዳይ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ በአገራችንና በሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገሮች እንደዚህ ዓይነቱ የጋራ አመለካከትና እምነት አለመፈጠሩ በመካከላቸው ጤናማ ግንኙነት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይፈጠሩ ከፍተኛ እንቅፋት ይሆናል፤›› ይላል፡፡

ዶ/ር መረራ ጉዲና ኢሕአዴግ የተምታታ ርዕዮተ ዓለም እንዳለው ያምናሉ፡፡ የመድረክ አመራር የሆኑት ዶ/ር መረራ የኢሕአዴግ ርዕዮተ ዓለም በንድፈ ሐሳብና በተግባር እንዲሁም ከሶሻሊዝምና ከካፒታሊዝም ጋር ለመስማማት የተቸገረው ለሁለት የተለያዩ አካላት የቀረበ በመሆኑ ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ የዲሞክራሲና የመድበለ ፓርቲ መዘርዝሮች ለለጋሽ ድርጅቶች ብቻ የተዘጋጁ መሆናቸውን በመጠቆም፣ ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲን ለማስፈንም ሆነ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ጤናማ ግንኙነት ለመመሥረት ፈጽሞ ፍላጎት እንደሌለው በተለያዩ የጥናት ሥራዎቻቸው ዶ/ር መረራ ይተነትናሉ፡፡

‹‹Elections and Democratization in Ethiopia, 1991-2010›› በተሰኘ ሥራቸው ዶ/ር መረራ ኢሕአዴግ አማራጭ ፖሊሲ ያላቸውን ጠንካራ ፓርቲዎች በተቀነባበረ ሁኔታ የማዳከም ሥራ መሥራቱን ይከሳሉ፡፡ እስከ ምርጫ 2002 ዓ.ም. ድረስ ሕጋዊ ፓርቲዎቹን በሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም የማይከሰው ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎችን ‹‹የኒዮ-ሊበራል አቀንቃኞች›› በሚል የድጋፍ መሠረታቸውን ከአገር ውጪ ማድረግ መጀመሩን ይገልጻሉ፡፡

የአባላት ብዛትና የገንዘብ አቅም
በኢሕአዴግ የምርጫ 2002 ስትራቴጂ ውስጥ የሚከተለው ተካቷል፡፡ ‹‹ከኢትዮጵያ ሕዝብ ወስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ከ18 ዓመት በታች በመሆኑ የመራጩ ሕዝብ ቁጥር ከ30 ሚሊዮን በላይ ሊሆን እንደማይችል ይገመታል፡፡ ከዚህ ውስጥ ቢያንስ አራት ሚሊዮን የድርጅት አባላት ናቸው፡፡ እያንዳንዱ አባል በቀላሉ ሊቀበላቸውና ሊያሳምናቸው የሚችል ቢያንስ አራት ወዳጆችና ዘመዶች አሉት ብንል እነዚህ ተደማምረው 20 ሚሊዮን ይሆናሉ፡፡ በእነዚህ ብቻ ቢያንስ 2/3ኛው ድምፅ ማግኘት ይቻላል፡፡››

አሁን የኢሕአዴግ አባላት ቁጥር 6.5 ሚሊዮን መድረሱ በኢሕአዴግ እየተገለጸ ነው፡፡ በ‹‹አዲስ ራዕይ›› መጽሔት የሐምሌ 2000 እትም ላይ የቀረበው የኢሕአዴግ 7ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ሪፖርት ከምርጫ 97 በኋላ በተሠራው ሥራ የአባላትን ቁጥር በማስፋትና የአባላቱን አቅም በማጠናከር፣ የድርጅቱን ጥንካሬ ለመፍጠር የተሠሩትን ሥራዎች ይዘረዝራል፡፡ ትንታኔው ዜጎች ኢሕአዴግን ለመምረጥ ነፃ ሆነው ያለምንም ዓይነት ተፅዕኖ አባል የሆኑት በፓርቲው ጥንካሬ ብቻ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ዶ/ር መረራ ከላይ በተገለጸው ሥራቸው ኢሕአዴግ የአባላቱን ቁጥር በአጭር ጊዜ በስምንት እጥፍ ያሳደገው የመንግሥትን ሀብት በመጠቀም የሥራ ቅጥር፣ የሥራ ዕድገትና መሰል ጥቅማ ጥቅሞችን በመጠቀምና ጫና በማሳደር መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

ሃንጋሪ በሚገኘው የሴንትራል ዩሮፒያን ዩኒቨርሲቲ የፒኤችዲ ጥናት እያደረጉ የሚገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አቶ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፣ ‹‹Tackling Abuse of Incumbency and the Imperial Premiership: Ideas for Constitution Reform in Ethiopia›› በተሰኘ የቅርብ ጊዜ ሥራቸው ከሥራ ቅጥርና ዕድገት በተጨማሪ የትምህርት ዕድል፣ በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የሚሰጠው የብድር አገልግሎት የአባላቱን ቁጥር ለመጨመር ኢሕአዴግ እንደተጠቀመባቸው ይጠቁማሉ፡፡ አቶ ጌዲዮን በአካባቢ ምርጫ ቀድሞ የነበረው የምክር ቤት አባላት ቁጥር ከ15 ወደ 300 የተለወጠው ከምርጫ 97 በኋላ መሆኑን አስታውሰው፣ አሁን በመላው አገሪቱ የሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ በ3.6 ሚሊዮን ወንበሮች ላይ መወዳደር እንደሚጠበቅ ያስገነዝባሉ፡፡

ሌላኛው የመድረክ አመራር አቶ አሥራት ጣሴ አንድ ለአምስት የተሰኘው የኢሕአዴግ ስትራቴጂ የኢሕአዴግን አባላት በሕገወጥ መንገድ ቁጥሩ እየጨመረ እንዲመጣ እንዳደረገው ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል፡፡

ይህ የአባላት ቁጥር ወደ ተቃዋሚው ሲመጣ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ መኢአድ ወደ 100 ሺሕ የሚጠጋ አባላት አሉኝ ይላል፡፡ ኢዴፓ ወደ 40 ሺሕ የሚጠጋ አባላት እንዳሉት ይናገራል፡፡ በአጠቃላይ አባላቱ የፓርቲዎቹን የገንዘብ አቅም ለመጨመር ስላደረጉት አስተዋጽኦ ሲጠየቁ ፓርቲዎቹ ብዙም ግልጽ አይሆኑም፡፡ የኢሕአዴግ አባላት ግን ለሦስት ተከታታይ ወራት ካልከፈሉ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል፡፡ በቅርቡ የወጣውን የ’አዲስ ራዕይ’ ልዩ እትም ብቻ አባላቱ በ100 ብር እንዲገዙ ተደርጓል፡፡ በወር እያንዳንዱ አባል ከደመወዙ በመቶኛ የአባልነት መዋጮ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡ ይህ ለፓርቲው የሚሰጠው የገንዘብ አቅም ምን ያህል እንደሆነ ማሰብ ቀላል ነው፡፡

አቶ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ከላይ በተገለጸው ሥራቸው ኢሕአዴግ ከአባላቱ መዋጮ በተጨማሪ ፓርቲው የመንግሥት ሕንፃዎችን በጽሕፈት ቤትነት በመጠቀም፣ የመንግሥት ሠራተኞችን በመንግሥት ወጪ የፓርቲውን ርዕዮተ ዓለም ላይ እንዲሠለጥኑና የአባላት ምልመላ በማድረግ ሥልጣኑን ያለአግባብ እንደሚጠቀም ይጠቅሳሉ፡፡

በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 ላይ መንግሥት በፌዴራልና በክልል ምክር ቤቶች ውክልና ላላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕለት ተዕለት ሥራ ማከናወኛ ድጋፍ እንደሚሰጥ ተደንግጓል፡፡ በምርጫ ዝግጅት ወቅት ደግሞ ለፓርቲዎቹ ድጋፍ ለመስጠት በምክር ቤት ካላቸው መቀመጫ በተጨማሪ የማያቀርቡት የዕጩ ብዛትና የሴት ዕጩዎች ብዛት ከግምት ውስጥ ይገባል፡፡

ፓርቲዎቹ ከአባላት መዋጮና ከመንግሥት ድጋፍ ውጪ ከስጦታ ወይም ዕርዳታና ቀጣይነት ከሌለው ዝግጅት ላይ ገንዘብ በመሰብሰብ ገንዘብ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ሕጉ ከውጪ ዜጎች፣ አገሮችና ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከሃይማኖት ድርጅቶች፣ ከፍርድ እስረኞች፣ ከሕገወጥ ቡድን ወይም ሰው፣ ከሽብርተኛ ድርጅት፣ ከመንግሥታዊ ድርጅትና ምንጩ ያልታወቀ ስጦታ ወይም ዕርዳታ መቀበል የተከለከለ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ፓርቲዎቹ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ ባህልና ከኢሕአዴግ ጣልቃ የመግባትና የቁጥጥር አድማሱን ያለአግባብ የመለጠጥ ባህል አንፃር ስጦታና ዕርዳታ የሚሰጡ አካላትና ዜጎች ስማቸው በግልጽ እንዲቀመጥ ማዘዙ ይህም ለምርጫ ቦርድ በየጊዜው ሪፖርት እንዲደረግ መጠየቁ ትልቅ ተፅዕኖ እንደፈጠረ ይገልጻሉ፡፡

የሥነ ምግባር አዋጁና የጋራ ምክር ቤቱ አባልነት
የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 662/2002 አንቀጽ 16(2) ላይ በምርጫ ዘመቻ ወቅትና በማናቸውም ጊዜ የጋራ ጉዳይ በሆኑ ነጥቦች ላይ የመወያያ መድረክ ሆኖ የሚያገለግል የጋራ ምክር ቤት በፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚመሠረት ይደነግጋል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ የሚያወጣውን የስምምነት ሰነድ አዋጁ ሲቀረፅ በልዩ ልዩ ምክንያት ያልተሳተፉ ሌሎች ፓርቲዎች አባል ለመሆን መፈረም እንዳለባቸው የሚገልጽ አንቀጽ በአዋጁ ተካቷል፡፡ የጋራ ምክር ቤቱ በምክር ቤቱ የተደረሱትን ስምምነቶች የሚተገብር፣ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግና የሚቆጣጠር አካል ነው፡፡ በምርጫ ጉዳዮች አፈጻጸም ዙርያ የሚነሱ ጥያቄዎች ላይ መፍትሔ የመስጠት ኃላፊነትም አለበት፡፡ አዋጁ በሚጣስበት ጊዜ ቅሬታዎችን የሚያጣራ ኮሚቴ በማቋቋም ወይም በራሱ የሚያጣራ አካል ነው፡፡ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ደንቦችንና መመርያዎችን አስመልክቶ ረቂቅ ሐሳብ በማዘጋጀት ለምርጫ ቦርድ የማቅረብ ሥልጣንም አለው፡፡

ይህ በአዋጁ የተሰጠ ሥልጣን ያለው አካል አባል የመሆን ጉዳይ የመግባቢያ ሰነድ በመፈረም መገደቡ ምክንያቱ ግልጽ እንዳልሆነ የሚጠይቁ አሉ፡፡ መድረክ ከድርድሩ አቋርጦ በመውጣቱ ስምምነቱ ወደ አዋጅ መቀየሩን አላቆመውም፡፡ የአዋጁ ዓላማ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በጋራ በመወያየት የዲሞክራሲ ሥርዓቱንና የምርጫ ሥርዓቱን የተሻለ ዕድገት ማየት ከሆነ፣ በፓርላሜንታሪ ሥርዓት ፓርላማው ሕግ ላደረገውና ተፈጻሚነቱ ለሁሉም ፓርቲዎች ለሆነ አዋጅ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡ ስሜት የማይሰጠውን ያህል፣ መድረክ በፓርላማ ሕግ ሆኖ በሥራ ላይ ለዋለ አዋጅ ዕውቅና አልሰጥም ማለቱም ተመሳሳይ ውጤት ነው ያለው በማለት የሚተቹም አሉ፡፡      
  http://www.ethiopianreporter.com/index.php/politics/item/465-%E1%8B%AB%E1%88%8D%E1%89%B0%E1%88%98%E1%88%88%E1%88%B1-%E1%8A%A0%E1%8A%95%E1%8C%88%E1%89%A5%E1%8C%8B%E1%89%A2-%E1%8B%A8%E1%88%9D%E1%88%AD%E1%8C%AB-%E1%8C%A5%E1%8B%AB%E1%89%84%E1%8B%8E%E1%89%BD%E1%8B%AB%E1%88%8D%E1%89%B0%E1%88%98%E1%88%88%E1%88%B1-%E1%8A%A0%E1%8A%95%E1%8C%88%E1%89%A5%E1%8C%8B%E1%89%A2-%E1%8B%A8%E1%88%9D%E1%88%AD%E1%8C%AB-%E1%8C%A5%E1%8B%AB%E1%89%84%E1%8B%8E%E1%89%BD