POWr Social Media Icons

Monday, January 28, 2013


ሀዋሳ ጥር 20/2005 ሀዋሳ ከተማን ጨምሮ በሲዳማ ዞንና በሌሎች ከተሞች በመጪው ሚያዝያ ለሚካሄደዉ የአካባቢ ምርጫ ደኢህዴን ከ115 ሺህ በላይ እጩዎችን ማስመዝገቡን የዞኑ ምርጫ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በዞኑና በከተሞቹ ለሚካሄደዉ ምርጫ ከ1ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸውም ተገልጧል ። የጽህፈት ቤቱ አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ዱካሞ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ደኢህዴን ያስመዘገባቸው 115 ሺህ 368 ዕጩዎች ለዞን ፣ለወረዳ ፣ለከተማና ለቀበሌ ምክር ቤቶች ድርጅቱን ወክለው የሚወዳደሩ ናቸው። ደኢህዴን ለሲዳማ ዞን ፣ለሀዋሳ ፣ለይርጋለምና ለአለታ ወንዶ ከተሞች አስተዳደሮችና ለ21 ወረዳዎች ካስመዘገባቸው ዕጩዎች ውስጥ 105 ለዞን ምክር ቤት፣ 277 ለከተማ አስተዳደር ምክር ቤት፣ 1ሺ524 ለወረዳና ፣113 ሺህ 462 ለቀበሌ ምክር ቤት የሚወዳደሩ መሆኑን ተናግረዋል። ለምርጫው በዞኑና በከተማ አስተዳደሮች ፣በወረዳዎችና በቀበሌ ለመወዳደር ካስመዘገባቸው ዕጩዎች ውስጥ 53 ሺህ 289 ሴቶች ሲሆኑ ከነዚህ ዕጩዎች 38 ለዞን ምክር ቤት ፣110 ለከተማ ምክር ቤት፣ 484 ለወረዳ የሚወዳደሩ ሲሆን ቀሪዎቹ ለቀበሌ ምክር ምክር ቤት እንደሚወዳደሩ አስረድተዋል። በዞኑ ለመወዳደር ተመዝግበዉ የመለያ ምልክት ከወሰዱ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም ደኢህዴን፣ ፣ሲአን፣ኢዴአፓና ኢራፓ ውስጥ እስካሁን ዕጩዎቹን ያስመዘገበው ደኢህዴን ብቻ መሆኑን አስተባበሪዉ አመልከተዉ የዕጩዎች ምዝገባ የሚጠናቀቀው በነገዉ እለት በመሆኑ ፓርቲዎቹ ዕጩዎቻቸውን እንዲያስመዘግቡ አሳስበዋል። በተጨማሪም በዞኑ በተቋቋሙ 1648 የምርጫ ጣቢያዎች እስካለፈው አርብ ድረስ 1 ሚሊዮን 33 ሺህ መራጮች መመዝገባቸውንና ከነዚህ ውስጥ 472 ሺህ 764 ሴቶች መሆናቸውን አቶ ብርሃኑ አስታውቀዋል።
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=4932&K=1

ሃዋሳ ጥር 20/2005 በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞንና በሃዋሳ ከተማ በመጪው ሚያዝያ ለሚደረገው የአካባቢ ምርጫ ከ955 ሺህ በላይ መራጮች ተመዘገቡ፡፡ የሲዳማ ዞን ምርጫ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ዱካሞ እንደገለጹት በዞኑ በሚገኙ 21 ወረዳዎችና በሃዋሳና ይርጋለም የከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ 1 ሺህ 648 የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ ያለምንም ችግር በመከናወን ላይ ነው። እስከ ጥር 21 ድረስ በሚቆየው የመራጮችና የዕጩዎች ምዝገባ ከ1 ሚሊዮን 282 ሺህ በላይ መራጮች ይመዘገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። ከታህሳስ 22 ጀምሮ በመከናወን ላይ ባለው የመራጮችና የዕጩዎች ምዝገባ ለመራጭነት ከተመዘገቡት መካከል 446 ሺህ 699 ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል። በመጪው ሚያዝያ ወር በሚደረገው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ላይ በመራጭነት ለመሳተፍ የመራጮች ምዝገባ በመጪው ማክሰኞ ከመጠናቀቁ በፊት ህብረተሰቡ በመመዝገብ የመራጭነት ማረጋገጫ ካርዱን መያዝ እንዳለበት አስተባባሪው አሳስበዋል። በሃዋሳ ከተማ ሚሊኒየም ቀበሌና ዋጋኔ ዋጮ ቀበሌ ለመራጭነት በመመዝገብ ላይ ከሚገኙት መካከል ወይዘሮ በላይነሽ ደምሴና አቶ ታከለ ተሾመ በሰጡት አስተያየት ያገኙትን ዲሞክራሲያዊ መብት በመጠቀም የተሻለ ለውጥ በማምጣት ይሰራልናል ብለው ያመኑትን ዕጩ ለመምረጥ የመራጭነት ማረጋገጫ ካርድ ወስደዋል።
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=4931&K=1

ሃዋሳ ጥር 20/2005 የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በማሳካት የኢንዱስትሪውን ልማት ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የልማታዊ ባላሃብቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለዉ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ገባኤ አስታወቁ ፡፡ በሃዋሳ ከተማ ከሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የተገነባው ዳሎል ኦይል የነዳጅ ማደያ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ምክትል አፌ-ጉባኤ አቶ ማሞ ጎዴቦ ማደያውን መርቀው ስከፍቱ እንደተናገሩት ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በግብርና፣ በከተማ ልማት፣ በኢንዱስትሪ፣ በመልካም አስተዳደር እንዲሁም በሌሎችመስኮች በክልሉ አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ በየደረጃው ለተመዘገቡ ለውጦች መንግስታዊ አደረጃጀቶች፣ መላው ህብረተሰብ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የግል ባለሃብቶች በጋራ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል ። በተለይ ይላሉ አቶ ማሞ ሁሉም ዜጋ በሀገሪቱ ውስጥ በሚከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ መንግስት ያስቀመጣቸው ውጤታማ ፖሊሲዎችና ስትራቴጅዎች ለተመዘገበው ስኬት ቁልፍ ድርሻ አበርክተዋል፡፡ በዚህም በክልሉ ከ1986 ወዲህ ከ68 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ከአምስት ሺህ የሚበልጡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ መሰማራታቸውንና ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠራቸው ተናግረዋል፡፡ የሃዋሳ ከተማ ባለፉት ጥቅት አመታት ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ የሀገራችን ከተሞች አንዷ መሆኗን የጠቆሙት አቶ ማሞ የግል ባለሃብቶች ከከተማው ዕድገት ጋር የሚጣጣም የልማት አቅርቦት እንዲኖር ከመንግስት ጎን በመሆን እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል ። የዳሎል ኦይል አክሲዮን ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ደረጀ ዋለልኝ በበኩላቸው ኩባንያው ከአራት አመት በፊት በሰባት ኢትዮጵያዊን ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በርካታ አከሲዮኖችን ለህዝብ በመሸጥ ከ1ሺህ 230 በላይ ባለአክሲዮኖችያቀፈ ነዳጅና የነዳጅ ምርቶችን የሚያሰራጭ አገር በቀል ኩባንያ ነው ብለዋል፡፡ ኩባንያው በሃዋሳ አገልግሎት የጀመረውን ማደያ ጨምሮ በአርባምንጭ፣ በሃላባ፣ በአዲስ አበባ፣ በሰመራና በሌሎች አከባቢ ዘጠኝ ማደያዎችን በማስገንባት በየጊዜው እየተሻሻለ ለመጣው ለትራንስፎርት ዘርፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የነዳጅ ምርቶችን በማሰራጨት ላይ መሆኑን አመልክተዉ ከ580 ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠሩንም አስረድተዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=4934&K=1