‹‹የፖለቲካ ባህሉ መሠረት እንዲይዝ ብዙ ትግል ይጠይቃል››

አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን አባል የነበሩ
አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ከሃያ ዘጠኙ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ...
ኮሚሽን አባላት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት በዲግሪ የተመረቁት አምባሳደር ታዬ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ነበር ሥራ የጀመሩት፡፡ ይሁንና ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ በቆየው አገልግሎታቸው በዲፕሎማትነት፣ በቆንስላ ጄነራልነት፣ በአምባሳደርነትና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ውስጥ አገልግለዋል፡፡ በተለያዩ አገሮች ውስጥ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ውስጥ የሠሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ስዊዲንና አሜሪካ ይገኙበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ሰለሞን ጎሹ የዛሬ 19 ዓመት ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. ፀድቆ በሥራ ላይ የዋለውን የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሒደትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አምባሳደር ታዬን አነጋግሯቸዋል፡፡ 
ሪፖርተር፡- እርስዎ አባል የነበሩበት የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን አሁን በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት በማርቀቁ ሒደት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ የሽግግሩ ዘመን ቻርተር የሽግግር መንግሥቱ ሕገ መንግሥት በማርቀቅ እንደሚያበቃ ይገልጻል፡፡ አጠቃላይ ሒደቱ ምን ይመስል ነበር? አወቃቀሩስ ምን ይመስል ነበር? በማርቀቅ ሒደቱ ተጨማሪ ሚና ከነበራቸው ሌሎች ተቋማት ጋርስ የነበራችሁ ግንኙነት እንዴት ነበር?
አምባሳደር ታዬ፡- የሽግግር መንግሥቱ ዋነኛ ተግባር ሕገ መንግሥት አዘጋጅቶ ሥልጣኑን በሕዝብ ለተመረጠ አካል በሕገ መንግሥቱ መሠረት ማስረከብ ነው፡፡ በእርግጥ ወቅቱ የፖለቲካ ሥርዓት ሽግግር ስለነበር ሰላምና መረጋጋት ማምጣትም አንደኛው ተግባር ነበር፡፡ የሕገ መንግሥት ኮሚሽኑ በሚቋቋምበት ጊዜ ሁለት አማራጮች ነበሩ፡፡ አንደኛው አማራጭ ራሱ የሽግግር መንግሥቱ በሽግግሩ መንግሥት መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ሕገ መንግሥቱን ራሱ አርቅቆና ውይይት አድርጎ በጉባዔ ማፀደቅ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በወቅቱ በሽግግሩ መንግሥት የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ ከሽግግሩ መንግሥት ውጪ ያሉ አካላት ጭምር በማርቀቅ ሒደቱ መሳተፍ አለባቸው የሚል ነው፡፡ ያኔ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያየ የፖለቲካ ዓላማና ፕሮግራም በመያዝ በስፋት የተመሠረቱበት ወቅት ነበር፡፡ ሕገ መንግሥቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቃል ኪዳን ሳይሆን የሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎችና ሕዝባዊ ድርጅቶች አስተዋጽኦ የሚያስፈልገው ስለሆነ የሙያ ማኅበራትና ሕዝባዊ ማኅበራት መሳተፍ አለባቸው የሚል ክርክር ተደረገ፡፡ ሁለተኛው አማራጭ በስፋት ተቀባይነት ነው ያገኘው፡፡ የኮሚሽኑ አወቃቀር ሲደራጅ በሽግግሩ መንግሥት መቀመጫ ከነበራቸው ፓርቲዎች ውስጥ ሰባት፣ ከሽግግሩ መንግሥት ውጪ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ስብስቦች ሰባት፣ 15 ሰዎች ደግሞ ከሙያና የብዙኃን ማኅበራት ይህም የሠራተኛ ማኅበር፣ የመምህራን ማኅበር፣ የጤና ባለሙያዎች ማኅበር፣ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር፣ የሴቶች ማኅበራት ተወካዮችን ይጨምራል፡፡ በተወካዮች ምክር ቤት በሕገ መንግሥት ማርቀቁ ሒደት መሳተፍ የሚፈልጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሳተፍ እንፈልጋለን የሚል ማመልከቻ አስገብተው ነው የኮሚሽኑ አባላት የሆኑት፡፡ በአባላት ቁጥር፣ በተሳትፎና በወቅቱ በነበራቸው ሕዝብን የመምራት አቅም፣ የመደመጥ ችሎታን መነሻ በማድረግ ነው የተመረጡት፡፡ የሽግግር መንግሥቱ ዋነኛ ተዋናይ ኢሕአዴግ ነው፡፡ ከኢሕአዴግ ውስጥ ግን በወቅቱ ከኢሕዴን ብአዴን አቶ ዳዊት ዮሐንስ፣ ከኦሕዴድ ደግሞ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ብቻ ነበሩ የኮሚሽኑ አባላት፡፡ ከኢሕአዴግ ጋር ተመሳሳይ ፕሮግራም የነበራቸው ድርጅቶች ነበሩ፡፡ ሌሎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ ማለት ይቻላል የዓላማ መስማማት ብቻ ሳይሆን አንድ ላይ ተቀምጠው ለአንድ ተግባር ይሠራሉ ተብለው የማይገመቱ ነበሩ አንድ ላይ ሊሠሩ የሞከሩት፡፡ አንዳንዳቹ የዘውዱ ሥርዓት እንዲመለስ ፕሮግራም የነበራቸው ነበሩ፡፡ ሌሎቹ ሶሻል ዲሞክራቶች ነበሩ፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎች ደግሞ ማርክሲስት ሌኒኒስት ወይም ግራ ዘመም አተያየት ያላቸው ነበሩ፡፡ በዚያ ወቅት በማርቀቅ ሒደቱ ይደረጉ የነበሩ ክርክሮችን ያየ ሰው ይህች አገር በፈጣንና በተጠናከረ ሁኔታ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ያላት ይመስል ነበር፡፡ በሰሞነኛ አጀንዳ ሳይጠመዘዙ ያስቀመጧቸውን ፕሮግራሞች በበረታ ስሜትና መንፈስ፣ በግልጽነት ማንፀባረቅ የሚችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎች የነበሩበት ወቅት ነበር፡፡   
ሪፖርተር፡- ኮሚሽኑ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውጪ ከሕገ መንግሥት ጉባዔ ጋር በሒደቱ ላይ አብሮ ሠርቷል፡፡ የኮሚሽኑ አባላት ምርጫ ላይ መጠነኛ ቅሬታ ቢኖርም በጉባዔው አባላት ምርጫ ላይ ብዙ ቅሬታዎች አሉ፡፡ በማርቀቁ ሒደት ወሳኝ ሚና የነበራቸውን እነዚህን አካላት ስታዋቅሩ ልምድ ከየት ነው የወሰዳችሁት?
አምባሳደር ታዬ፡- ሕገ መንግሥት ተራ ሕግ አይደለም፡፡ መጀመሪያ ሕገ መንግሥትን ለማርቀቅ ምን ግብዓቶች ያስፈልጋሉ የሚለው ጥያቄ ወሳኝ የሆነና ተገቢ ምላሽ የሚያስፈልገው ነበር፡፡ በስፋት ለማየት የተሞከረው በቅድሚያ ለዘመናት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለእኩልነት፣ ለነፃነት፣ ለዕድገትና ከድህነት ለመላቀቅ ያደረጓቸውን ትግሎች ማጥናት ነበር፡፡ መሠረቱ ይኼ ነው፡፡ ሁለተኛ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን በመትከል ሰፊ ተሞክሮ ያላቸውን አገሮችና የሕገ መንግሥት ሥርዓትን ለመትከል ሞክረው ያልተሳካላቸው በዕድገት ከእኛ ጋር የሚመሳሰሉ አገሮችን ተሞክሮ ሁሉ ለመዳሰስ ተሞክሮአል፡፡ ሦስተኛ የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ፍላጎትና ዝንባሌ ለማጥናት ተሞክሯል፡፡ አራተኛ የኢትዮጵያን የቀድሞ ሕገ መንግሥቶችና ረቂቅ ሕገ መንግሥቶች ቻርተሩንም ጭምር ለማጥናት ተሞክሯል፡፡ አምስተኛ ለሕገ መንግሥቱ ግብዓት መሆን የሚችሉ ባህላዊ እሴቶችን፣ ልማዶችንና ወጎችን ሁሉ መርምረናል፡፡ እነዚህ ነገሮች ከተመለከትን በኋላ ነው ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሒደቱ ምን መምሰል አለበት ወደሚለው የሄድነው፡፡ በሽግግሩ ቻርተር መሠረት በሕገ መንግሥት ጉባዔ መፅደቅ አለበት፡፡ የሕገ መንግሥቱ ተቀባይነት የሚመሠረተው በአርቃቂዎቹ አይደለም፡፡ የተቀባይነት ምንጭ ሕዝብ ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ጉባዔ አባላት በሚመረጡበት ጊዜ የውድድር አጀንዳው በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያሉ አንኳር ጉዳዮች ነበሩ፡፡  
ሪፖርተር፡- የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንኳር አንቀጾች ከኢሕአዴግ ፕሮግራም ጋር በጣም የሚመሳሰሉ መሆናቸውን በመጠቆም የሕገ መንግሥት ማርቀቅ ሒደቱ በግንባሩ የበላይነት ስለመከናወኑ የሚከራከሩ አሉ፡፡ በማርቀቅ ሒደቱ ከኢሕአዴግ አቋም ውጪ የሆኑ አማራጭ ሐሳቦች በቂ የመወዳደር ነፃነት አግኝተው ነበር?
አምባሳደር ታዬ፡- የራስን ዕድል በራስ ከመወሰንና ከንብረት መብት ውጪ በሌሎች መሠረታዊ የሰብዓዊና የፖለቲካ መብቶች ዙሪያ ሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ስምምነት ነበራቸው፡፡ የፌዴራል የመንግሥት አወቀቀር ያስፈልጋል በሚለው ዙሪያ ልዩነት አልነበረም፡፡ በጣም ቀኝ ዘመም የሚባለው የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ እንኳን የፖለቲካ ድርጅት የፌዴራል አወቃቀሩ ላይ ልዩነት አልነበረውም፡፡ የሕገ መንግሥቱ አርቃቂ ኮሚሽን አባላትን ጥንቅር ስታይ ኢሕአዴግ የበላይነት የለውም፡፡ ኢሕአዴግ ያነሳቸው የመብት ጥያቄዎች ግን በወቅቱ የበላይነት ነበራቸው፡፡ ገዥ ሐሳቦች ነበሩ፡፡ የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል መብት እስካልተከበረ ድረስ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት የማረጋገጡ ነገር የሚጨበጥ አይመስልም ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ከዚህ የተለየ የተሻሻለ ሐሳብ ቢይዝ ኖሮ እንደ ድርጅት ተሸናፊ ነበር የሚሆነው፡፡ ጥያቄው የሚነሳው በአብዛኛው በልሂቃኑ ቢሆንም የአብዛኛው ሕዝብ ፍላጎት ነበር፡፡ በመሆኑም ይህ መብት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያስፈልገው ነበር፡፡ ብዴን (ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) የተሰኘ የከተማ ፓርቲና ይህ መብት ካልተረጋገጠ የሚለው ኦነግ በዚሁ መብት ዙሪያ የሚያደርጉት ክርክር ትኩረት የሚስብ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ እነዚያን ወቅታዊ ጥያቄዎች ባይዝ ኖሮ በዚያ ማዕበልና ወላፈን ውስጥ መቆም አይችልም ነበር፡፡ 
ሪፖርተር፡- ኦነግ ቢቆይ ኖሮ ሊለውጣቸው የሚችሉ ነገሮች ይነሳሉ፡፡ ቢያንስ ግን መጀመሪያ ላይ ኦነግ ተሳታፊ ነበር፡፡ በተማሪዎች ንቅናቄ ጉልህ ሚና የነበራቸው ኢሕአፓና መኢሶንን የመሰሉ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ግን ከመጀመሪያውም እንዳይሳተፉ ታግደዋል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች የወቅቱን ገዥ ሐሳቦች የመገዳደር አቅም እንደነበራቸው የሚከራከሩ አሉ፡፡
አምባሳደር ታዬ፡- ይኼ ትክክል ያልሆነ አስተያየት ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ከኢሕአዴግ በፊት የመሬት ባለቤትነትን በሚመለከት የጻፉና ያስተማሩ ናቸው፡፡ የብሔረሰብ መብትና የራስን ዕድል የመወሰን ጥያቄ እነዚህ ፓርቲዎች አንግበው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የመኢሶንና የኢሕአፓ በአካል የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ በወቅቱ አጠራጣሪ ነበር፡፡ እንደተደራጀ የፖለቲካ ቅርፅ የነበሩ አይመስለኝም፡፡ መኢሶን ሕጋዊ ህልውና አልነበረውም፡፡ ድርጅቱ ከመሥራቾቹ ጋር ነው አብሮ የጠፋው፡፡ ኢሕአፓም በወቅቱ ቅርንጫፍ (Fringe) የፖለቲካ ፓርቲ ነው የነበረው፡፡ ኢሕአፓና መኢሶን የሚያራምዷቸው ሐሳቦች ላይ ግን ክርክር ተደርጓል፡፡ እነሱ በአካል ባለመኖራቸው የሕገ መንግሥታዊ አማራጭ ሐሳብ አሳጥተዋል የሚባለው ስህተት ነው፡፡ ሐሳባቸው በአርቃቂ ኮሚሽኑ፣ በሕገ መንግሥት ጉባዔውና በሕዝቡ መካከል ተንሸራሽሯል፡፡ በ73 የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ አማራጭ ቀርቦ ነው ሕገ መንግሥቱ የተረቀቀው፡፡ ተራ በሚባሉ ጉዳዮች ሁሉ ሳይቀር እያንዳንዱ ሐሳብ አማራጭ ቀርቦለታል፡፡ ለምሳሌ በባንዲራ ጉዳይ ላይ ለሕዝብ አማራጭ ባይቀርብለትም በኮሚሽኑ ግን ከባድ ክርክር ነው የተደረገበት፡፡ አንዳንዱ ሰንደቅ ዓላማውን ከመለያ በላይ በመውሰድ ትርጓሜው የፍቅር፣ የአንድነትና አብሮ የመኖር መገለጫ እንዲሆን ይፈልጋል፡፡ ሌሎች ትርጓሜው የሚያሳምማቸው ነበሩ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩን ተቀብለው ሁለቱን ቡድኖች ለማጣጣም የሞከሩ ነበሩ፡፡ 
ሪፖርተር፡- ሕገ መንግሥቱ አንድ ዘመናዊ ደረጃውን የጠበቀ ሕገ መንግሥት ሊይዝ የሚገባውን መሠረታዊ ጉዳዮች ስለመያዙና ከሕዝቡና ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ የተቀዳ መሆኑን ለማረጋገጥ ልምድ መውሰድን ጨምሮ ምን ዓይነት ጥንቃቄ አድርጋችኋል?
አምባሳደር ታዬ፡- ዓለም አቀፍ የሕገ መንግሥት ባለሙያዎች በፓናል ውይይት እየተገኙ ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡ ከማስታውሳቸው መካከል ዲን ፓል፣ ፕሮፌሰር መርፊና ፕሮፌሰር ሳሙኤል ሃንቲንግተን ይገኙበታል፡፡ ሳሙኤል ሃንቲንግተን በተለይ “Clash of Civilizations” በተሰኘው ሥራቸው ይታወቃሉ፡፡ “The Third Wave” የተሰኘ ሌላ ታዋቂ ሥራና ሌሎች በርካታ ሥራዎች ያበረከቱ ታላቅ ምሁር ናቸው፡፡ በእነርሱ እሳቤ አንድ ሕገ መንግሥት ምን መምሰል እንዳለበት ሐሳብ አካፍለዋል፡፡ ሐሳባቸው ጎልቶ የወጣው በረቂቁ ሕገ መንግሥት ላይ በሰጡት አስተያየት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በልማዳዊና በተጻፈ ሕግ ስትመራ የኖረች አገር ናት፡፡ የራሳችን ልምድ አለን፡፡ የሕገ መንግሥት ዋናው መሠረት የኤክስፐርቶች አስተያየት ሳይሆን የሕዝብ ፍላጎት ነው፡፡ ከእነሱ እሴቶች ጋር በማይዛመዱ አንዳንድ አንቀጾች ዙሪያ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ የሕገ መንግሥቱ ዋነኛ ምንጭ የአገሪቱ ተጨባጭ እውነታ ነበር፡፡ እርግጥ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ በኮሚሽኑ ውስጥ ሰፊ ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያዊያን የሕግ ምሁራን ነበሩን፡፡ ብዙዎቹ አባላት ወይ የሕግ ባለሙያ አለዚያም የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያዎች ነበሩ፡፡ 
ፕሮፌሰር ሳሙኤል ሃንቲንግተን በወቅቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምን ሊመስል እንደሚችል ቀድመው አይተውት ነበር፡፡ አንድ ፓርቲ አውራ የሚሆንበት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንደሚፈጠር መገመት በወቅቱ ችለው ነበር፡፡ አንዳንድ የኢትዮጵያ ምርጫዎች ለውጭ ዜጎች አይገቡም፡፡ በልዩነቱ ውስጥ ከመለያየት ይልቅ አንድ የመሆን ፋይዳን የተገነዘበው ኅብረተሰብ መለየትን ወይም መገንጠልን ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ይሰጠኝ ሲል አንድነትን ለማረጋገጥ ነው እንጂ ተነጥሎ ሊሄድ አይደለም፡፡ ሃንቲንግተን በወቅቱ “The Third Wave” የተሰኘ መጽሐፍ ጽፈው ስለነበር ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ከ2,500 ዶላር በታች የሆኑ አገሮች ተሰባሪ (Fragile) በመሆናቸው ዲሞክራሲያዊ የመሆን ዕድላቸው የመነመነ ነው በማለት ነግረውን ነበር፡፡ የመጽሐፉም ጭብጥ በዚሁ ሐሳብ ላይ ነው የሚሽከረከረው፡፡ ከአቶ መለስና ከእኛ ጋር ይከራከሩ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲን ለማረጋገጥ ረጅም ጊዜ ስለሚወስድ አንድ አውራ ፓርቲና ሌሎች ትንንሽ ፓርቲዎች ያሉበት ልማታዊ አቅጣጫ ከተያዘ ኢትዮጵያ ጥሩ ዕድል እንደሚኖራት ነበር የተናገሩት፡፡ በልማት ውስጥ የመንግሥት ሚና ምን መሆን እንዳለበት አንዱ የሕገ መንግሥት ጉዳይ ነበር፡፡ በአውራ ፓርቲ ሥርዓት የመንግሥት ሚና ያይላል፡፡ የመንግሥት ሚና የጎላ ይሁን፣ የተመጠነ ይሁን ወይስ እስከነ ጭራሹ አይኑር የሚል ምርጫ ለሕዝብ ቀርቦ ነበር፡፡ አብዛኛው ሕዝብ የመንግሥት ሚና ከፍ ማለት አለበት የሚል ምርጫ ነው የነበረው፡፡ ከብዙ አገሮች በተመሳሳይ የሕገ መንግሥት ምሁራን መጥተው ክርክርና ውይይት ይደረግ ነበር፡፡ 
ሪፖርተር፡- በመጀመሪያው ረቂቅ ተካተው በኋላ ላይ የተተው ሐሳቦች እንዲሁም መጀመሪያ ያልነበሩና በኋላ ላይ የተጨመሩ ጉዳዮች እንደነበሩ ይነሳል፡፡ በተለይ ለእነዚህ ለውጦች አቶ መለስ የፓርቲውን አመራር በመጠቀም አልያም በግል የማሳመን ክህሎታቸው ስማቸው ከለውጡ ጋር ተይይዞ ይነሳል፡፡ በማርቀቅ ሒደቱ የአቶ መለስ ሚና ምን ነበር?
አምባሳደር ታዬ፡- በሒደት የተለወጡ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ የአቶ መለስ ሚና ጉልህ የነበረው በተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ኮሚሽኑ ካረቀቀ በኋላ ለተወካዮች ምክር ቤት ማቅረብ ነበረብን፡፡ ምክር ቤቱ ከተከራከረበትና ከተወያየበት በኋላ ነው ለሕገ መንግሥት ጉባዔ ቀርቦ የሚፀድቀው፡፡ ጉባዔው የኮሚሽኑን ረቂቅ ቢፈልግ የመቀበል፣ የምክር ቤቱን ረቂቅ የመውሰድ፣ ሁሉንም አልፈልግም ብሎ የራሱን የማርቀቅ ሥልጣን ነበረው፡፡ በነገራችን ላይ የኮሚሽኑ አባላት በምክር ቤቱ በሚቀርቡ ክርክሮችና ውይይቶች ተሳታፊ ነበርን፡፡ ከተወያየንባቸው ጉዳዮች መካከል እንደ ኢሕአዴግ አቋም የተያዘባቸው የሚመስሉ ነገር ግን ምክንያታዊ የሆኑ የአቶ መለስን አቋሞች አስታውሳለሁ፡፡ ለምሳሌ ሕገ መንግሥት ማሻሻልን በተመለከተ የኮሚሽኑ ረቂቅ ‹‹በዚህ ሕገ መንግሥት ውስጥ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች፣ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት፣ ስለሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ መርሆዎች፣ ስለመንግሥት ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ባህርይና ፌዴራላዊ አደረጃጀት የሰጡት ድንጋጌዎች የሕገ መንግሥት መሠረት ስለሆኑ በከፊል ወይም በሙሉ ማሻሻል አይቻልም፤›› ነው የሚለው፡፡ ይኼ በአብዛኛው የኢሕአዴግ አቋም ነው የነበረው፡፡ እኔ በግሌ የምቀበለው አንቀጽ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዓለም ላይ የማይሻሻል ነገር የለም፡፡ የአቶ መለስ አቋም ደግሞ ዛሬ የምናረቀው ሕገ መንግሥት መብቶቻችንን የሚያስከብር፣ የራሳችንን ዕድል ራሳችን መወሰን የሚያስችል፣ ፍላጎታችንን የሚያንፀባርቅ፣ በአንድነትና በጋራ ለመኖር ቃል ኪዳን የምንገባበት ቢሆንም ይህ አሁን በምናወጣው ሕግ የሚቀጥለውን ትውልድ ፍላጎት ማሰር እንችላለን ማለት አይደለም የሚል ነበር፡፡ በአጠቃላይ የማይሻሻል ነገር እንደሌለ ያምኑ ነበር፡፡ የሚሻሻለው ለበለጠ ጥቅም ሊሆን እንደሚችል ይከራከሩ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በቀላሉ መሻሻል የለበትም የሚለውንም ሐሳብ ደጋፊ ነበሩ፡፡ ይህ የአቶ መለስ ሐሳብ የሁሉም ኢሕአዴጎች ሐሳብ አይመስለኝም፡፡ ሌላው የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት ዙሪያ ተፃራሪ ድንጋጌዎች ነበሩ ለሕገ መንግሥት ጉባዔው የቀረበለት፡፡ አቶ መለስ እንደ ተወካይ ምክር ቤት ሊቀ መንበርነታቸው የሚያምኑበትን ሐሳብ ከገለጹ በኋላ የመጨረሻውን ውሳኔ የሕገ መንግሥት ጉባዔው እንዲወሰን አማራጮችን ከመላክ ውጪ ያልተገባ ተፅዕኖ አላሳረፉም፡፡ በነገርህ ላይ አቶ ክፍሌ ወዳጆ (የአርቃቂ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር ነበሩ) መገንጠል የሚለውን ቃል ስለማይወዱት መነጠል በማለት ነበር የሚጠሩት፡፡ ይህ መብት የሞራል መብት በመሆኑ በሕገ መንግሥት ውስጥ ቦታ ሊሰጠው አይገባም በማለት የሚከራከሩ ነበሩ፡፡ በሕገ መንግሥቱ አሰፈርከው አላሰፈርከው አንድ ሕዝብ መነጠል በሚፈልግበት ጊዜ ሕገ መንግሥቱንም አልፎ መገንጠል ይችላል የሚል አጥፊ አስተሳሰብ የነበራቸው ነበሩ፡፡ አቶ መለስ ተፅዕኖ አሳርፈዋል ከተባለ ተፅዕኖ የፈጠሩት የኢሕአዴግ አስተሳሰብ የበላይነት እንዲኖረው በማድረግ ሳይሆን ህሊናቸው የፈቀደላቸውን ምክንያታዊ ሐሳብ በመሰንዘር ነው፡፡ 
ሪፖርተር፡- በብዙ አገሮች ሕገ መንግሥት የሚገባው ቃል ኪዳን ‹‹እኛ የአገሩ ዜጎች ወይም ሕዝቦች›› ብሎ ነው የሚጀምረው፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ግን ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›› ብሎ ነው መግቢያው የሚጀምረው፡፡ በአንቀጽ 8 ላይም ሉዓላዊ ሥልጣን የተሰጠው ለእነዚህ ቡድኖች ነው፡፡ ይህ መብት የተሰጠው የመብት ጥያቄ አንግበው ለተንቀሳቀሱ ቡድኖች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ነው፡፡ ይኼ ውሳኔ የማንነት ጥያቄው መስፈርት በአንቀጽ 39(5) ከተገለጸበት ጋር ተዳምሮ የተለያዩ ቡድኖች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ የማንነት ጥያቄ በማንሳት ያላግባብ እየተጠቀሙበት ነው፣ አለመረጋጋት ያመጣል በሚል የሚቀርብ ቅሬታ አለ፡፡ እነዚህ ቅሬታዎች በማርቀቅ ሒደቱ ተነስተው ነበር?
አምባሳደር ታዬ፡- የመጀመርያው ረቂቅ ሕገ መንግሥት መግቢያ በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስሜት የተቃኘ አልነበረም፡፡ የፖለቲካ ድንጋጌ ነበር፡፡ የአንድን ፓርቲ ሐሳብ የሚያንፀባርቅ ነበር ማለትም ይቻላል፡፡ ያለፈውን ታሪክ በምሬት ይገልጽና ያለንበትን ሁኔታ ደግሞ በሥጋት መልክ ያስቀምጠውና ይኼንን ለመቅረፍ ሕገ መንግሥት አስፈላጊ ነው ብሎ ነበር የሚደመድመው፡፡ የአሁኑ መግቢያ የፀናው ከረጅም  ጊዜ ክርክር በኋላ ነው፡፡ የጋራ ጥቅምን መሠረት ያደረገ፣ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት፣ ድህነትን ለመሻገር ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የገቡትን ቃል ኪዳን የሚያመለክት ነው የአሁኑ መግቢያ፡፡ እኛ በእውነቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነን፡፡ ብዙና የተለያየን ነን፡፡ በዕድገታችን ተመሳሳይ ነን፡፡ በራሳችን መለኪያ ደግሞ የተለያየን ነን፡፡ አንዱ በውስን አካባቢ ተረጋግቶ ይኖራል፣ ሌላው ተንቀሳቃሽ ማኅበረሰብ ነው፣ አንዱ ቋንቋው ያደገ ነው፣ አንዱ በቋንቋው እንዲጠቀም አልተደረገም ወዘተ. የመጀመርያው ፈተና እኛ ማን ነን የሚለውን ማወቅ ነበር፡፡ እውነታው ብዙና የተለያየን መሆናችንን መረዳታችን ነው፡፡ እያደግንና እየበለፀግን ስንመጣ ይኼ ይጠፋል ወይ? እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ሕገ መንግሥቱ እኛ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች ብሎ መጀመሩ ተገቢ ነው፡፡ ሁሉም ቡድን በስም ሁሉ መጠራት ነበረበት የሚል ጥያቄ ነበር በወቅቱ፡፡
ሪፖርተር፡- የመንግሥት ቅርፅን በተመለከተ በፓርላሜንታሪያዊና በፕሬዚዳንታዊ፣ በአሃዳዊና በፌዴራላዊ፣ በብሔር ተኮር ፌዴራላዊ መዋቅርና አካባቢ ተኮር ፌዴራላዊ መዋቅር መካከል አማራጭ ውይይቶች ቀርበው ነበር?
አምባሳደር ታዬ፡- ፌዴራላዊ አወቃቀሩ አከራካሪ አልነበረም፡፡ አሃዳዊ አወቃቀርን በጽሑፍ ደረጃ አየነው እንጂ እንደ ምርጫ አልቀረበም፡፡ ሥልጣን በአንድ ማዕከል እየተቆረቆረ ኢትየጵያን እንደ አገር ጠብቆ ማቆየት የማይቻልበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ የፌዴራል ሥርዓት በሞአ አንበሳ ተወካዮችም ዘንድ ተቀባይነት ነበረው፡፡ ንጉሥ፣ ንጉሠ ነገሥት የሚለውን አወቃቀር እየገለጹ ድሮም ቢሆን ፌዴራላዊ አወቃቀር ነበር የሚል ክርክር አቅርበዋል፡፡ በፓርላሜንታዊና ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት መካከል ግን ሰፊ ክርክር መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ፓርላሜንታሪያዊ ሥርዓት የተመረጠበት ዋነኛ ምክንያት አንደኛ በፓርላሜንታሪያዊ ሥርዓት አስፈጻሚው ከፓርላማ ነው የሚወጣው፡፡ ስለዚህ ፓርላማው የሚቆጣጠረው መስተዳድር ያስፈልገናል የሚል ስምምነት ነበር፡፡ ሕዝብ በተወካዮቹ አማካይነት አስፈጻሚውን እንዲቆጣጠር ፍላጎት ነበር፡፡ በመሠረቱ ዲሞክራሲያዊ የመሆንና ያለመሆን ነገር በመንግሥት ቅርፅ አይወሰንም፡፡ ወሳኞቹ ምንጮች የማኅበራዊ ዕድገትና የፖለቲካ መብቶችን የማክበር ጉዳይ ናቸው፡፡ ፓርላሜንታሪያዊ ሥርዓትን ከመረጡ በኋላ መሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆን ፕሬዚዳንት እንዲሆን አማራጭ ያቀረቡ ነበሩ፡፡ በተጨማሪም ሁለት ምክትል ፕሬዚዳንቶች እንዲኖሩ ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡ አንዱ ምክትል ፕሬዚዳንት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሌላኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ እንዲሆን አማራጭ ቀርቦ ነበር፡፡ ለፓርላማው ተጠሪ የሆነ ፕሬዚዳንት ነበር እንደ አማራጭ የቀረበው፡፡ አሁን ያለው ፕሬዚዳንት የአስፈጻሚ አካል አይደለም፡፡ የአንድነት መገለጫ ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አሁን ሕግ አውጪ አካል አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱን የሚተረጉም አካልና ከብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች ጋር የተያያዙ ሌሎች ሥልጣኖች ያሉት አካል ነው፡፡ ነገር ግን በማርቀቅ ሒደቱ ቀርቦ የነበረው አንድ አማራጭ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር የወል ሥልጣን እንዲኖረውና በአገሪቱ የውጭ ግንኙነት፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ ዜግነት፣ ብሔራዊ መከላከያና ደኅንነት፣ በሁለትና ከሁለት በላይ በሆኑ ክልሎች የንግድ እንቅስቃሴ፣ ብሔራዊ ባንክና የፋይናንስ እንቅስቃሴ ላይ፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ የብሔራዊ ኢንቨስትመንት ፖሊሲና የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ የወል ሥልጣን እንዲኖረው ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡ ይኼ ያልተመረጠበት ዋነኛ ምክንያት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ተመራጭ አካላት ባለመሆናቸው ነው፡፡ እርግጥ አባላቱ በሕዝብ የሚመረጡበት አግባብ በሕገ መንግሥቱ ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን ተቋሙ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተወካይ ነው፡፡ 
ሪፖርተር፡- ሕገ መንግሥትን የመተርጎም ሥልጣን በፖለቲካው ተሳትፎ ካለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይልቅ ነፃ ለሆነ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት መሰጠት ነበረበት በማለት ጠንካራ ክርክር የሚያነሱ በጣም በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሕገ መንግሥት ምሁራን አሉ፡፡ ሥርዓቱ የሚጠበቅበትን ያህል ያልዳበረው በዚህ የዲዛይን ችግር እንደሆነና ምርጫው የሦስቱን የመንግሥት አካላት የእርስ በርስ ክትትልና ቁጥጥር ደካማ እንዳደረገ ግምገማ የሚያቀርቡም አሉ፡፡ በሥራ ላይ ያለው አማራጭ በምን ምክንያት ተመረጠ?
አምባሳደር ታዬ፡- የሕገ መንግሥት ትርጉም በሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ወይም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ይከናወን የሚሉ ሁለት አማራጮች ነበሩ፡፡ ሕገ መንግሥት ነክ ክርክሮች በሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ይታዩና አስተያየት ተሰጥቶባቸው የመጨረሻ ውሳኔ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይወስን የሚል አማራጭ ነበር፡፡ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽኑና የተወካዮች ምክር ቤት የሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት አወቃቀርን በተመለከተ ተመሳሳይ አቋም ነው የነበራቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የተባለው በቀደሙት ረቂቆች የሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ይባል የነበረው ነው፡፡ የሰረዘው ሕገ መንግሥት ጉባዔው ነው፡፡ ተገቢ የሆነ ምክንያት ነበረው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ቢቋቋምም አወቃቀሩ ከሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው ጋር ተመሳሳይ ነበር፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትና የተመረጡ ከፍተኛ የሕግ ባለሙያዎችን ነው በአባልነት የሚይዙት፡፡ ልዩነቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካዮች በረቂቁ ላይ ስድስት ሲሆኑ፣ አሁን ሦስት ብቻ ሆነው የሕግ ባለሙያዎች ደግሞ ስድስት እንዲሆን መደረጉ ነው፡፡ ሁሉም የሕግ ባለሙያዎች በመሆናቸው ብዙዎቻችን አልተስማማንም ነበር፡፡ ሕገ መንግሥት ሲተረጎም በሕግ አዋቂ ብቻ አይደለም የሚተረጎመው፡፡ የማኅበራዊ ሙያ ያለው፣ የፖለቲካ ሙያ ያለው፣ ከሕግ ውጪ የተለያየ ሙያ ያለውን ሰው ሊያሳትፍ ይገባል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሕግ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ሰነድ ነው፣ የማኅበራዊ ጉዳይ ሰነድ ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ጉባዔው ክርክር የሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ውሳኔ በራሱ የፀና ካልሆነና በሌላ አካል እንደ አዲስ የሚተረጎም ከሆነ እንደ ፍርድ ቤት መቁጠር አይቻልም የሚል ነበር፡፡ ለዚህም ነው ስሙን ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ብሎ የቀየረው፡፡ የዚህ ሐሳብ መሠረታዊ መነሻ የኢፌዲሪ መሠረቶች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመሆናቸው ፍላጎታቸውን ሕገ መንግሥቱ ማረጋገጥ ስላለበት በሕግ አተረጓጎምም ሆነ በመብት አጠባበቅ እነሱ የሚወከሉበት ተቋም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥበቃ እንዲያደርግ ኃላፊነቱ ሊሰጠው ይገባል የሚል ነው፡፡ ሕገ መንግሥት በመተርጎም ሳቢያ መብቶቻቸው እንዳይሸራረፉ ለመከታተልም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተመራጭ ነው፡፡ በግሌ ግን በጣም ንቁ የሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቢኖር ጥሩ የነበረ ይመስለኛል፡፡ አሁን በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ ነው የሚሰበሰበው፡፡ ሕግ በማውጣትና የታችኛውን ምክር ቤት በመቆጣጠር ደረጃ ተጨማሪ ሥልጣንና ኃላፊነት እንዲኖረው የሚመኙ ነበሩ፡፡ ይኼ መጥፎ ሐሳብ የነበረ አይመስለኝም፡፡ 
ሪፖርተር፡- የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የክልል ሕጎች ላይ ጭምር የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥበት አግባብ አለ፡፡ ይኼ ከፌዴራል አወቃቀሩና ራሱ ሕገ መንግሥቱ ከተመሠረተበት የራስን ዕድል በራስ ከመወሰን መርህና ከብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት ጋር የሚጋጭ እንደሆነ የሚተቹ አሉ፡፡
አምባሳደር ታዬ፡- ፌዴራል መንግሥቱና ክልሎች ጣምራ ሥልጣን ያላቸው ቦታዎች አሉ፡፡ ሐሳቡ በአንድ ሕግና ማዕቀፍ በተመሳሳይ ሥርዓት የምትመራ አገር መገንባት ነው፡፡ የእያንዳንዱ ሰው ፍትሕ የማግኘት መብት እንዳይሸራረፍ ለማረጋረጥ ነው፡፡ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የማረም ሥልጣን ነው ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጠው፡፡ ይኼ ከመብት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ጉዳዩ በቅድሚያ በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቢታይም ከፍተኛ የአገሪቱ የዳኝነት አካል ይግባኝ የማለት ሥልጣን መስጠት አስፈልጓል፡፡ በአሜሪካም እኮ በሰርኪውት ፍርድ ቤት የታየው ጉዳይ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ይባላል፡፡ 
ሪፖርተር፡- ሕገ መንግሥቱ ብዙም ግምት የማይሰጠው ሥልጣን ለተሰጠው ፕሬዚዳንት የሥልጣን ገደቡን በሁለት የሥራ ዘመን ሲገድብ ብዙ ሥልጣን ያለውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሥራ ዘመን ገደብ ለምን አላስቀመጠም?
አምባሳደር ታዬ፡- የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ዘመን ክፍት የተተወበት ምክንያት ሥልጣን ላይ በምርጫ አሸንፈው ለሚወጡ ፓርቲዎች ምርጫ ለመስጠት ነው፡፡ በውስጥ ሕግጋታቸው ቢፈልጉ አንድ የሥራ ዘመን ሲፈልጉም ሁለት ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ በፓርላሜንታሪያዊ ሥርዓት የመሪው የሥራ ዘመን የሚወሰነው በፓርቲው በጎ ፈቃድ ነው፡፡ ለፕሬዚዳንት የሥልጣን ገደብ የሚቀመጠው ፓርላማው የሚያደርግበት ቁጥጥር የተወሰነ ስለሆነ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የፕሬዚዳንቱ የሥልጣን ዘመን ሁለት ዙር ብቻ እንዲሆን የተደረገው ፕሬዚዳንቱ የአገር አንድነት መገለጫ በመሆኑ ለዘለዓለም የሚቀመጥ አለመሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ይኼ ካለፈ ታሪክም ከመማር የመጣ ነው፡፡ መንግሥት የሚያቋቁመው ፓርቲ በፓርላማ ውስጥ ከፍተኛ መቀመጫ ያለው ነው፡፡ ብዙ ፓርቲዎች ተወዳድረው አንድ ፓርቲ ከፍተኛ መቀመጫ ያላገኘ እንደሆነስ? በዚህ ጊዜ ከፍ ያለ መቀመጫ ያላቸው ፓርቲዎች መንግሥት እንዲያቋቁሙ የሚጋብዘው ፕሬዚዳንቱ ነው፡፡ መመሥረት ካልቻሉም ሌሎችን በመጥራት የሥልጣን ክፍተቱን የሚሞላው ፕሬዚዳንቱ ነው፡፡ 
ሪፖርተር፡- እስካሁን የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ አልተደረገበትም፡፡ በአንድ በኩል የኢሕአዴግ ፍፁም የበላይነትና ግንባሩ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያን በበጎ ጎኑ ስለማያይ ማሻሻያ እንዳልተደረገ የሚገልጹ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሕገ መንግሥቱን ዲዛይን በማሻሻል ሥነ ሥርዓቱን እጅግ የተወሳሰበና ከባድ ስላደረገው ነው በማለት የሚጠቁሙ አሉ፡፡ የማሻሻያ ሥነ ሥርዓቱ አሁን ያለውን ቅርፅ እንዲይዝ ስታደርጉ ሐሳባችሁ ምን ነበር?
አምባሳደር ታዬ፡- መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች እስከነጭራሹ ሊሻሻሉ አይገባም የሚል ክርክር እንደነበር ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ሐሳባቸው መብቶች በሕገ መንግሥት ማሻሻያ ምክንያት እንዳይሸራረፉ ሥጋት ስለነበራቸው ነው፡፡ ለምሳሌ በኖርዌይና በግሪክ መሠረታዊ መብቶችንና ነፃነቶችን ማሻሻል አትችልም፡፡ ሕገ መንግሥት ምንጊዜም በከበደ ሥርዓት ነው መሻሻል ያለበት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሕገ መንግሥቱን ተዓማኒነትና ተገማችነት ለማረጋገጥ ነው፡፡ ወቅታዊ የሆኑ የመብት ጥያቄዎች ላይ ሕገ መንግሥቱ የማስተናገጃ በር መክፈት ነው እንጂ ያለበት ብረት ምሰሶ ሊሆን አይገባም፡፡ ሲሻሻል ግን በሰሞነኛ ጩኸት መሆን የለበትም፡፡ የሕገ መንግሥቱ መሠረት የሆኑት ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች ተወካይ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና ክልሎች ራሳቸው በሒደቱ እንዲሳተፉ መደረጉ አግባብ ነው፡፡ በቀላሉ ፓርላማው እንዲያሻሽለው ሊደረግ አይገባም፡፡ ፓርቲዎቹ በየቦታው መቀመጫ ለማሸነፍ ሊንቀሳቀሱና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚመለከት አጀንዳ ሊቀርፁ የሚገባውም ለዚህ ነው፡፡ በቅርቡ እዚሁ ጋዜጣ ላይ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ (ሰማያዊ) አማራጭ ሕገ መንግሥት እያዘጋጀ መሆኑን ስለመግለጹ አንብቤያለሁ፡፡ ይኼ የቅርንጫፍ ፖለቲካ ባህሪ ነው፡፡ ሰሞነኛ ጥያቄ እንጂ ዘላቂውን የሥርዓት ጥያቄ አይመስልም፡፡ ሕገ መንግሥቱን መቀየር የፈለገ ኃይል ወደ መራጩ ሕዝብ ሄዶ መዳኘት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የዕለት ተዕለቱን ነው የሚያየው፡፡ የፖለቲካ ባህሉ መሠረት እንዲይዝ ብዙ ትግል ይጠይቃል፡፡ 
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/interview/itemlist/user/46-%E1%88%B0%E1%88%88%E1%88%9E%E1%8A%95%E1%8C%8E%E1%88%B9

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር