የሃዋሳ ከተማ የጸጥታ ችግር ተቀርፎ ይሁን?

በሃዋሳ ፀጥታን የማስከበር ሥራ ለነዋሪው እፎይታ አስገኝቷል 

ብዙዎቹ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች በአካባ ቢያቸው በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ለብዙ ጊዜ ተቸግረዋል። በገዛ አካባቢያቸው በሰላም መውጣትና መግባት ያለመቻላቸውን ሲያስታውሱ ይማረራ። የፀጥታው ችግር የተፈጠረው ደግሞ በገዛ ወጣቶቻቸው መሆኑ የምሬታቸውን መጠን ከፍ ያደርገዋል።
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መዲና በሆነችው በሃዋሳ መሀል ክፍለ ከተማ የለኩ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ መሠረት ወንድሙ በቀበሌያቸውም ሆነ በክፍለ ከተማቸው ከእዚህ ቀደም ብዙ ፈተና ማሳለፋቸውን ይናገራሉ። ትንሽ መሸት ካለ ሰዎች እንደ ልብ ወዲያና ወዲህ መንቀሳቀስ ስለማይችሉ ያሰቡትን ማሳካት አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱን ያመለክታሉ።
«ጨለማን ተገን አድርገው የሚንቀሳቀሰውን ሰው ሰላምና ፀጥታ ማደፍረስ በአካባቢያችን የተለመደ ሆኖ ቆይቷል። ማንነታቸውንም ለመለየት ደግሞ ሰዎች ፍራቻና ስጋት ስለሚያድርባቸው በየጊዜው ወንጀል ይከሰት ነበር። ችግር የፈጠረውን ግለሰብ አሳልፎ ለሕግ የማቅረብ ድፍረቱም አልነበረም» ይላሉ ወይዘሮዋ።
ዛሬ ግን ይህ አስቻጋሪ ወቅት አልፏል። ለእዚህ ምክንያቱ ደግሞ የሰላምና የፀጥታ ችግር የሆነውን ጉዳይ ሕዝቡ በጋራ ስለመከረበት ነው። በፀጥታው መደፈር የታከተው ሕዝብ እርስ በእርስ በመወያየቱም ወደ መፍትሔ ሊመጣ ችሏል። መፍትሔ ሆኖ ለውጥ አምጥቷል ከሚባሉት መካከል አንዱ የኮሚኒቲ ፖሊሲንግ መቋቋም ነው በማለት ይገልጻሉ።
አሁን ሲያሰጋቸው የነበረው ችግር ሙሉ ለሙሉ መወገዱን የጠቀሱት ወይዘሮ መሠረት በሰላም ወጥተው መግባታቸው ለሥራቸውም ሆነ ለከተማዋ ልማት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ይናገራሉ። የአካባቢውም ነዋሪ የመንገድ ላይ መብራት በሁሉም ቦታ እንዲበራ ከቀበሌ ጋር በመነጋገር በመተግበር ላይ ይገኛል ብለዋል።
የእዚሁ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ተካ ተክሌም ቀደም ባሉት ጊዜያት አካባቢያቸውን ሌቦች ተዳፍረውት እንደነበር ያመለክታሉ። ይሁንና አሁን አሁን ትልቅ ለውጥ መምጣቱን አመልክተው፤ ከእዚህ ቀደም በሌብነት ሲያስቸግሩ የነበሩት ወጣቶች በተለያየ ሥራ ተጠምደው ሲያዩአቸውም በውይይት የመጣ ለውጥ በመሆኑ መደሰታቸውን ይናገራሉ። በተለይም የአካባቢው ወጣቶች ሥራ ላይ መሰማራታቸው ከእኩይ ተግባራቸው እንዲወጡ ከመርዳቱም በላይ ሕዝቡን እፎይ አሰኝቶታል ብለዋል።
ኮንስታብል በቀለ ዶኔ በክፍለ ከተማው የለኩ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ አገልግሎት የሚሰጡትም በቀበሌ ሁለት ፖሊስ ጣቢያ ነው። «ቀደም ባሉት ጊዜያት ስርቆት አይሎ ነበር። ሰዎችም በጣም ይቸገሩ ስለነበር ማጋለጥም ስጋት ሆኖ ቆይቷል። ይሁንና አሁን ከራሱ ከሕዝቡ ጋር በመወያየታችን ወደ ሰላም እና ፀጥታ መምጣት ችለናል» ይላሉ።
ከሕዝብ ጋር መወያየት በመቻሉ የፖሊስ ሥራም በእዚያው ልክ ተቃሏል ማለት ይቻላል ያሉት ኮንስታብሉ ሕዝቡ እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ የነበሩት ችግሮች መወገዳቸውን ነው ያመለከቱት። ሕዝብ በአንድ ጉዳይ መተባበር ከጀመረ ምንም ነገር ከቁጥጥሩ ውጭ እንደማይሆን ጠቁመው ድካማቸውንም ጭምር እያቀለሉላቸው በመሆኑ ሁሌም አብረው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ።
በሃዋሳ የመሀል ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መርክነህ ያዕቆብ በበኩላቸው የአንድ አገርም ሆነ ከተማ ሰላም መረጋገጥ ለልማትም ለእድገትም ቁልፍና ወሳኝ ጉዳይ ነው ይላሉ። ይህ ግን በክፍለ ከተማቸው በአንድ ወቅት ታጥቶ እንደነበር በማመልከት ችግሩን ለመፍታትና መፍትሔ ለማግኘት ነዋሪውን እንዳወያዩ ተናግረዋል።
እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለፃ የውይይት መድረኩ የአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን ዘላቂነት ነበረው። በየመድረኩም የህዝቡን ቅሬታ ማሰባሰብ ተችሏል። በእዚህም ወቅት ሕዝቡ ራሱ ሌቦችን እስከመደበቅ የተደረሰበት ጊዜ እንደነበርም ማወቅ የተቻለ ሲሆን በፖሊስ ዘንድም ችግሮች መንፀባረቃቸው አልቀረም። ስለዚህ ኅብረተሰቡ ከፍትሕ አካላት ጋር እንዲሠራ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን የተናገሩት አቶ መርክነህ በተለይም በኮሚኒቲ ፖሊሲንግ ላይ ጠንካራ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። በእዚህ አካሄድ መልካም ቅንጅት መፍጠሩን ጠቅሰው በተለይ በክፍለ ከተማው ያሉ ሦስት ቀበሌዎች ስድስት ቀጠና ተብለው ከተለዩ በኋላ በ35 ብሎክ በመደራጀታቸው ለሥራው ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ነው የገለፁት።
በእዚህም አሠራር ቀደም ሲል ተስፋ ቆርጦ የነበረው ሕዝብ ዛሬ ያለምንም ስጋት መንቀሳቀስ ችሏል። በሌብነት ሲፈረጁ የነበሩት ግለሰቦችም በሥራ ገበታ ላይ ይገኛሉ። ከእዚህ ቀደም በቀን ብቻ እስከ 40 እና ከእዚያ በላይ ወንጀሎች ይመዘገቡ ነበር። በ2oo5.ም ላይ ግን ምንም ዓይነት ወንጀል አልተፈፀመም። ሰላም ሰፍኗል። ይህ ደግሞ ትልቅ እፎይታን አስገኝቷል ነው የሚሉት።
የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ዮሴፍ ዮናስ በበኩላቸው ከተማዋ በተለያዩ ዘርፎች በየጊዜው በርካታ ለውጦችን በማስመዝገብ ላይ እንደመሆኗ በእዚያው ልክ ሰላሟና ፀጥታዋ ይከበር ዘንድ እየሠራን ነው ይላሉ። በተለይም የኮሚኒቲ ፖሊሲንግ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው ይህንንም ተሞክሮ ከአዲስ አበባ፣ከአዳማና ከቢሾፍቱ እንደወሰዱትም ነው ያመለከቱት።
እንደ ከንቲባ ዮሴፍ ገለፃ በየጊዜው ከሕዝቡም ጋር ሆነ ከፖሊሶች ጋር ውይይት ያደርጋሉ። ከሕዝቡም ሆነ ከፍትሕ አካላት የሚነሱ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል ስርዓት በመዋቀሩም ቀደም ሲል ይመዘገብ የነበረው ወንጀል ጨርሶ እየጠፋ ነው። በ24 ሰዓት ሪፖርት ውስጥ ምንም ዓይነት ወንጀል የማይኖርበት ጊዜያት እየበዙ ናቸው። ከፍትሕ አካላት እና ከሕዝቡም ጋር በተደረገው ጥረት ለውጥ መመዝገብ ችሏል። ዘንድም በተጨባጭ ጥፋት ታይቶባቸዋል የተባሉት የፖሊስ አባላትንም ከመቅጣት እስከማባረር የደረሰ እርምጃ እየተወሰደ ነው። 
http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/addiszemen/news/6677-2013-12-10-06-59-09

 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር