‹‹ሕዝቡ ብሶቱን የሚገልጸው ወደ ቤተ ክርስቲያንና መስጊድ እየሄደ ነው›› ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ፣ የግጭትና የፖለቲካ ተመራማሪ

ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ በኢትዮጵያ የግጭትና የለውጥ ታሪክ ተመራማሪ ናቸው፡፡ በርካታ የምርምር ሥራዎችም አበርክተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን ታሪክና ፖለቲካ ከሚተነትኑት መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በወቅታዊ የአገሪቱ ፖለቲካ በተለይ ደግሞ፣ በኢሕአዴግና በተቃዋሚዎች ግንኙነት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች መብዛትና በፓርቲዎች የርዕዮተ ዓለም ልዩነት፣ እንዲሁም ደግሞ የአዲሱን ትውልድ ኃላፊነት በተመለከተ የማነ ናግሽ ፕሮፌሰር ገብሩን አነጋግሯቸዋል፡፡  
ሪፖርተር፡- ባለፈው ምርጫ 90 የሚደርሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ መመዝገባቸው ይታወቃል፡፡ በዲሞክራሲ በበለፀጉ አገሮች ጥቂትና ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይስተዋላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ለፓርቲዎች መብዛት ዋናው ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ? በመካከላቸው ያለው ልዩነትስ የአስተሳሰብ ነው ወይስ?
ፕሮፌሰር ገብሩ፡- በፖለቲካ ፓርቲዎች መብዛት ዋና ምክንያት መስሎ የሚታየኝ የሥልጣን ጥመኝነት፣ ሥልጣን ላይ መቆናጠጥ፣ ከሥልጣን ጋር አብረው የሚመጡ ጥቅማ ጥቅሞችን ለመጨበጥ ነው፡፡ በተለይ ከአንድ መንግሥት ወደ ሌላ ሽግግር በሚደረግበት ጊዜ የዲሞክራሲ ልምድ በሌለበት አገር እንዲህ የፓርቲዎች እንደ አሸን መፈልፈል አስገራሚ አይደለም፡፡ እነዚህን ፓርቲዎች ምንድን ነው የሚለያያቸው? መሠረታዊ የሐሳብ ልዩነት ነው? የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ነው? ወይስ የግለሰቦች ልዩነት ነው? ትኩር ብለን ስናየው አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ከትናንሾቹ እስከ ትላልቆቹ ሁሉም በግለሰብ ዙርያ የተቋቋሙ ናቸው፡፡ ያ ግለሰብ እንደፈለገ ያስደንሳቸዋል፡፡ በእምነትና በዲስፕሊን ዙርያ የተዋቀሩ ፓርቲዎች አይደሉም፡፡
ቅንጅት ብቅ ብሎ ለመጥፋቱ አንዱና ዋነኛው ምክንያት ይኼ ነው፡፡ የግለሰብ ጥርቅም ነበር፡፡ በርዕዮተ ዓለም፣ በዲስፕሊንና በእምነት ፅናት የተዋሀዱ አልነበሩም፡፡ “It was a marriage of convienience” [ለጊዜያዊ ምቾት ያደረጉት ስምምነት] ነው፡፡ ወቅቱ ስለፈቀደ አንድ ፓርቲ ሥልጣን ላይ ስለነበር እሱን ለመገልበጥ ነው የተቀናጁት፤ ያንን ፓርቲ አሸንፈውት ቢሆን ኖሮ ምን ዓይነት መንግሥት እንደሚያቋቁሙ ትልቅ ጥያቄ ነው የሚያጭረው፡፡ 
ለፓርቲዎች መብዛት የርዕዮተ ዓለምና የመሠረታዊ ሐሳቦች ልዩነት ሳይሆን የግለሰቦች ውድድር ነው፡፡ እነዚህን ግለሰቦች ደግሞ የሚያወዳድራቸው ሥልጣን ነው፡፡ በየትኛውም ዓለም ለፖለቲካ ስትወዳደር ሥልጣን ለመያዝ ነው፡፡ ጥያቂው ሥልጣንን ምን ልታደርግበት ነው? ለአገር ጠቀሜታ፣ ለሕዝብ ጠቀሜታ፣ ለአገር ዕድገት፣ ለሕዝብ ብልፅግና በሚል ቀስቃሽ ሐሳብ የሚነሳሱ ግለሰቦች አሉ፡፡ ከእኔ በላይ ለአገር ከእኔ በላይ ለሕዝብ የሚሉ፡፡ እኔ እስካሁን እንዳስተዋልኩት፣ እንዳየሁትና እንዳነበብኩት እንደዚህ የሚያስቡ የአገራችን ፖለቲከኞች እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ሥልጣን ናፋቂዎች ናቸው፡፡ ያንን ሥልጣን ግን ለምን እንደሚያውሉት ግልጽም ባይሆንም፣ በእኔ ዕይታ ግን ለግል ጥቅም ነው፡፡ ሥልጣን ለሁሉ ነገር ነው የሚውለው፡፡ በሦስተኛው ዓለም በስፋት የሚታየው ራስን ለማበልፀግ ነው፡፡  
ሪፖርተር፡- ፓርቲዎች መብዛታቸው አንድ ነገር ነው፡፡ በዲሞክራሲ በበለፀጉ አገሮች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምና ልዩነት አላቸው፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች የሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም አላቸው ብሎ መናገር ይቻላል?
ፕሮፌሰር ገብሩ፡- የለም! አብዛኞቹ የተለያየ ርዕዮተ ዓለም (ዓለምን የሚመለከቱበት መነጽር) ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ አውሮፓን ስንመለከት ፓርቲዎቹ በርዕዮተ ዓለም ይለያያሉ፡፡ ለምሳሌ ኮሙዩኒስት ፓርቲ አለ፡፡ ሶሻሊስት ፓርቲ አለ፡፡ ሶሻል ዲሞክራትና ክርስቲያን ዲሞክራት ብለው ይለያያሉ፡፡ የእነዚህ ርዕዮተ ዓለም ግልጽ ነው፡፡ በመሠረታዊ ሐሳቦች ይለያያሉ፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ፖሊሲን በሚመለከት በጣም ይለያያሉ፡፡ በአሜሪካ በሪፐብሊካንና በዲሞክራት መከከል የርዕዮተ ዓለም ልዩነት የላቸውም፡፡ ልዩነታቸውን የምታየው በአገር ውስጥ በሚያካሂዱት ፖሊሲ ነው፡፡ የዲሞክራቶች ሶሻል ፕሮግራም (ፖሊሲ) ሰፊውን ሕዝብ የሚደግፍ ሆኖ ይታየኛል፡፡ በአንፃሩ የሪፐብሊካን የሀብታሞች ፓርቲ ወይም ደግሞ የዚሁ መደብ ተፅዕኖ ያለበት ፓርቲ ብንለው ትክክል ይመስለኛል፡፡ እነሱ አብዛኛውን ጊዜ ልዩነት የሚያሳዩት የውጭ ፖሊሲ በሚመጣበት ጊዜ ነው፡፡ በዚያም ጊዜ ከልዩነታቸው ይልቅ ተባባሪነታቸው ጎልቶ የሚወጣ ይመስለኛል፡፡
የሁለቱም ዓይነት አሠራር አሁን በአገራችን የለም፣ አይታይም፡፡ ስለዚህ አሁን በብዛት የሚታዩት ፓርቲዎች ሊሰባሰቡ የሚችሉት ትላልቆቹ ትንንሾቹን በመጨፍለቅ ሳይሆን ሊያቅፉዋቸው ሲችሉ ነው፡፡ ምናልባት የግለሰቦችን ጥቅማ ጥቅም ፍለጋ እሱን በተለያየ መንገድ መቀበል፡፡ በተለያየ ዘዴ ያንን ፍላጎት ያንን ጥማት የሚያስታግሱበት ዘዴ መፈለግ አለበት ማለት ነው፡፡ ይኼ ካልተቻለ ትላልቆቹ ፓርቲዎች የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ስለሌላቸው ኅብረ ብሔር የውህደት ፓርቲ ማቋቋም ባይችሉም፣ እንደ ግንባር ወይም ጥምረት በማቋቋም ሊሰባሰቡ ይችላሉ፡፡ እንዲህ እስካላደረጉ ድረስ ገዥውን ፓርቲ ለማሸነፍ ያላቸው ፍላጎትና ምኞት ህልም ሆኖ ሲቀር ይሰማኛል፡፡ 
ገዥው ፓርቲ በብዙ መንገድ ከብዙ ነገሮች አንፃር ስናየው በርካታ ድክመቶች እንዳሉበት ለማናችንም ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን በሌላ አንፃር ስታየው ጠንካራ ፓርቲ ነው፡፡ በደንብ የተደራጀ ፓርቲ ነው፡፡ አምነውበትም ይሁን ለጊዜው ተጠቃሚዎች የሆኑ ብዙ አባላትና ካድሬዎች አሉት፡፡ ድጋፋቸው ከእምነት ወይም ከልብ ወይም ከአፍ በእርግጠኝነት መናገር አልችልም፡፡ ግን ገዥው ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን የሥነ መንግሥትና የመንግሥት ኃይሎች ቁሳቁስ፣ ሚዲያ፣ ደኅንነቱ በቁጥጥሩ ስለሆነ እነዚህ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀላሉ ይገፉታል ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ፓርቲዎች ድክመቶቹን ግምት ውስጥ በማስገባትና ሕዝቡ ጉያ በመግባት፣ ወጣቱን በማሰባሰብ ከፍተኛ የሆነ ፕሮፓጋንዳ በመሥራት፣ ገንዘብ በማፈላለግ በሚቀጥለው የምርጫ ውድድር ባያሸንፉት እንኳን በዘለቄታው ግን በከፍተኛ ደረጃ ሊወዳደሩትና ሊያሸንፉት የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል፡፡ ለዚያ ግን ከፍተኛ እንቅስቃሴና ዝግጅት ያስፈልጋቸዋል፡፡
አቶ ልደቱ አያሌው መድሎት የሚለውን መጽሐፉን በአድናቆት ነው ያነበብኩት፡፡ ጥሩ ግምገማ አድርጓል፡፡ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ መሪ ፓርላማ ገብቶ ያስተዋለው ይመስለኛል፡፡ ባደረገው ግምገማ ሦስት ጠቃሚ ነገሮችን ጠቁሟል፡፡ አንደኛ ገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ምኅዳሩን መክፈት ወይም ማስፋት አለበት፡፡ ዲሞክራሲን ተጭኖታል፤ ረግጦታል፡፡ ሁለተኛው ተቃዋሚዎች ወቃሽ ብቻ መሆን የለባቸውም፡፡ መንግሥት በጎ ሥራ ሲሠራ በጎውን ማመስገንና መቀበል የሚወቀሰውንም መውቀስ፡፡ እነሱ እርስ በርስ ከመወቃቀስና ከመደቋቆስ ወደ አንድነት የሚያመሩበትን መንገድ መቀየስ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሦስተኛ ሕዝባችን በ1997 ዓ.ም. በተደረገ ምርጫ በመንግሥትም ሆነ በተቃዋሚዎች በተፈጠረው ስህተት ሞራሉ የተነካና ወደ ተስፋ መቁረጥ ገብቶ ራሱን ከፖለቲካ ዓለም የሚያገል መስሎ ይታየኛል፡፡ በመጨረሻ ወሳኙ ሕዝቡ ስለሆነ ሕዝቡ ቀጥተኛ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡ ራሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በገንዘብ መደገፍ፣ የፖለቲካ ፓርቱዎችንም የሚቆጣጠርበት ዘዴና ሁኔታ ለመፍጠር ከምንም ጊዜ በላይ መንቀሳቀስ አለበት ይላልና ጥሩ ግምገማ መስሎ ይታየኛል፡፡     
ሪፖርተር፡- ተቃዋሚዎች የኢሕአዴግ ጥንካሬ ከርዕዮተ ዓለም የመነጨ አይደለም ይላሉ፡፡ ምክንያታቸውም አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሌሎች የተለያዩ አስተሳሰብ ያላቸው ፓርቲዎች እንዲኖሩ አይፈቅድም፡፡ አላግባብ የመንግሥትን ሀብት በመጠቀም ራሱን በማጠናከርና በጥቅማ ጥቅም እየደለለ ነው አባላትን የሚመለምለው የሚሉ ስሞታዎች አሉ፡፡ ተቃዋሚዎች ለመዳከማቸውም እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚያነሱት አንዱ ይኼ ተፅዕኖ ነው፡፡ እንዴት ያዩታል?
ፕሮፌሰር ገብሩ፡- የፓርቲው ጥንካሬ ያልኳቸውን ጎኖች ቀደም ብዬ ዘርዝሬያለሁ፡፡ እንደ እኔ ግንዛቤ ደግሞ አንዱ ለኢሕአዴግ ጥንካሬ ምክንያት የተቃዋሚዎች ድክመት ነው፡፡ ተቃዋሚዎች በደከሙበት ሁኔታ ገዥው ፓርቲ የመንግሥት አውታሮችን ተቆጣጥሮ በሚገዛ ጊዜ እነሱ በበለጠ ሕዝብ ውስጥ ገብተው ከአሁን በፊት ካደረጉት በበለጠ መንቀሳቀስ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሁለተኛ መንግሥት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው መመርያው፡፡ የእነሱ ምንድን ነው? ተፃራሪና አማራጭ ርዕዮተ ዓለም ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ሕዝቡ በሚገባው ቋንቋና ዘዴ ማቅረብም አለባቸው፡፡
ገዥው ፓርቲ እኮ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ፍላጎት እንዳለው ግልጽ ነው፡፡ ፓርቲዎች እንዳይጠነክሩ ከውስጥም ከውጭም ተፅዕኖ በማድረግ ያደክማቸዋል፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት አይተናል፡፡ በተለይ በሦስተኛው ዓለም የተለመደ ነው፤ የተዳከመውን ጨርሶ ማጥፋት፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር መብዛት በአንድ በኩል የኢሕአዴግ ጨዋታ ሳይኖርበት አይቀርም የሚል ግምት አለኝ፡፡ በከፋፍለህ ግዛ መርህ በአንዳንድ ነገር ጥቅማ ጥቅም በማቅረብ አላስፈላጊ የሆኑ ልዩነቶችን በመፍጠር የፓርቲ መሪዎች እርስ በርሳቸው እንዲናቆሩ ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም የተቃዋሚ መሪዎች እርስ በርስ ሲዳቆሱ ለገዥው ፓርቲ ትልቅ እፎይታና ጉልበት ነው የሚሰጠው፡፡ 
ሦስተኛ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ራሱ ከሌኒስት የፓርቲ አደረጃጀት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይኼም በአንድ ፓርቲ ማዕከላዊነትን የማያጠናክር፣ ራሱን እንደ ቀዳሚ ፓርቲ ሕዝባዊና አገራዊ ተልዕኮ ያለውና ከእኔ በላይ ሁሉ ለአሳር የሚል ፓርቲ ነው፡፡ ይህ ፓርቲ በዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ሲመራ የዲሞክራሲ መድረኩን እንደሚያጠብ ከታሪክ የተማርነው ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ችግርም ይህ ነው፡፡ መለስ ራሱ ተናግሮታል እኮ፤ ‹‹ልማት ከዲሞክራሲ ጋር ግንኙነት ላይኖረው ይችላል›› በማለት፡፡ በተለይ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ይኼ ምን ማለት ነው? ለምሳሌ ደቡብ ኮሪያ ቻይና ይጠቅሙናል ከተባሉ በግልጽ የአንድ ፓርቲ አመራርና የአንድ ፓርቲ አሠራር ነበራቸው፡፡ በአብዛኛው ወታደራዊ አምባገነኖች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ አገሮች አሜሪካ ኮሙዩኒዝምን ለማጥፋት በደቡብ ኮሪያና በታይዋን ያፈሰሰችው ገንዘብ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ በኢትዮጵያ ይደገማል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ የማይመስል ነገር ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ስናየው ደግሞ ኮሪያና ታይዋን ትናንሽ አገሮች ናቸው፡፡ ኅብረተሰቡ በጣም ተመሳሳይነት (Homogenous) አለው፡፡ ኢትዮጵያ በጣም ሰፊ፣ ብዙ ቋንቋዎች፣ ብሔሮችና ባህሎች ያሉባት አገር ናት፡፡ ስለዚህ የእነሱን ተሞክሮ በቀላሉ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ቀላል ሆኖ አይታየኝም፡፡ 
ወደ ጀመርነው ወደዚህ ርዕዮተ ዓለም እንመለስና በተደጋጋሚ ተቃዋሚ ኃይሎች የሚሉት ነገር አለ፡፡ ወደ ሕዝቡ እንዳንቀርብ፣ ሠልፍ እንዳናደርግና ሁልጊዜ መንግሥት ጣልቃ ይገባል፡፡ አዳራሽ ማግኘት እንኳን ከባድ ነው፡፡ በአገሪቱ ቀርቶ በአዲስ አበባ እንኳን ለመንቀሳቀስ አልቻልንም፡፡ ሠልፍ ለማድረግ ፈቃድ ስንጠይቅ ያልሆነ ምክንያት እየፈጠሩ ይከለክሉናል ይላሉ፡፡ የዲሞክራሲ ባህርያት የሌሊት መንግሥት ነው ብለው ካመኑና በአምባገነንነቱ ካመኑ ሌላ ዘዴ ለምን አይቀይሱም? ለውጥ እኮ መስዋዕትነት ይጠይቃል፡፡ ወደ ሰሜን አፍሪካ ለምን ዘወር ብለው አያዩም? አሁን ደግሞ ዩክሬይንን ተመልከት፡፡ እምቢ ብለው ይኼውና ትልቁን አደባባያቸው ለሁለት ሳምንታት ያህል ተቆጣጥረውታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢያስፈራራቸው፣ ፖሊስ ቢልክባቸው አሁንም እዚያው እንዳሉ ነው፡፡ 
የእኛዎቹ ግን ሁልጊዜ የሚያሰሙት እንጉርጉሮና ዋይታ ነው፡፡ ከዚያ ትንሽ አለፍ ብሎ አንድ ጊዜም ይሁን እንጂ ሰማያዊ ፓርቲ ወጣ ለማለት ሞክሯል፡፡ የቅርብ ትዝታችን ነው፡፡ ሌሎችም ያንን በማየት አድርገዋል፡፡ ግን ምንድን ነው ‹‹ተከለከልን›› ማለት? እኔ ለአመፅ ተነሳሱ ማለቴ አይደለም፡፡ እምቢ በሉ ማለቴ አይደለም፡፡ ግን ልዩ ልዩ ዘዴ መፍጠር ይኖርባቸዋል፡፡ እዚህ ያሉት ተቃዋሚዎች የመረጡት ሰላማዊ ትግል ራሱ የተለያዩ ዘዴዎች እንደሚጠይቅ ከተለያዩ አገሮች የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡
በተለይ በፖለቲካ ዓለም በልመና የሚገኝ ነገር የለም፡፡ በልመና የሚቃና ነገር ያለ አይመስለኘም፡፡ ትግል ይጠይቃል፡፡ ትግል ደግሞ ከትንሹ እስከ ትልቁ የተለያየ መስዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ዓይነቱ መስዋዕትነት እነዚህ 90 ፓርቲዎች ምንኛ ዝግጁ መሆናቸውን የማውቀው ነገር የለም፡፡ እስካሁን የተከፈለ መስዋዕትነት የለም ማለቴ አይደለም፡፡ ብዙዎች ታስረዋል፣ ተሰደዋል፣ ሕይወታቸውን ያጡም ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ይህንን ዘንግቼው አይደለም፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን አሁን ካለው የፖለቲካ ሥርዓት የተሻለ ሥርዓት አመጣለሁ ወይም እገነባለሁ የሚል ኃይል የሚያካሂደው ትግል ያልተቋረጠና ረዥም ጊዜ የሚወስድ ነው ከሚል ነው፡፡ ትግሉ ለማስቀጠልና ወደ ግብ ለማድረስ ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡     
ሪፖርተር፡- ከዚህ በፊት ቅንጅትና ኅብረት (በ1997) ጠንካራ ጥምረት ሆነው መጥተው ነበር፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ቀጣይ ዕርምጃዎችን ተከትሎ በቀላሉ ነበር የፈራረሱት፡፡ ጥንካሬ ያላቸውን ስብስቦች ማየት አልተቻለም፡፡ በወቅቱ ‹‹ማንዴላ›› የሚል ስያሜ የተሰጣቸው መሪዎችም ነበሩ፡፡ ኢሕአዴግ ደግሞ በእውነተኛ ታጋዮቹ መስዋዕትነት ከፍሎ የመጣ እንደሆነ ይናገራል፡፡ የተቃዋሚ አመራሮችን ያብጠለጥላል፡፡ የኢሕአዴግ ታጋዮች የፈጸሙትን ዓይነት መስዋዕትነት መክፈል የሚችሉ ተቃዋሚ ታጋዮች ይኖራሉ?
ፕሮፌሰር ገብሩ፡- አንዳንድ ሰዎች እንደምታውቃቸው በብሔር ዙርያ የተሰባሰቡ ናቸው፡፡ አንዳንዳቹ ከየትም ከየትም ተጠናክረው ብቅ ያሉ ናቸው፡፡ የረዥም ጊዜ የትግል ተሞክሮ የሌላቸው ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ እኮ 17 ዓመት ሙሉ ታግሎ፣ ቆስሎና ደምቶ ትልቅ መስዋዕትነት ከፍሎ የመጣ ነው፡፡ ያንን መቀበል ይኖርብናል፡፡ እና እሱን ታግሎ ከሥልጣን ለማውረድ የሚፈልጉ ኃይሎች የእሱን የሚያህል የእምነት ፅናት ባይሆንም ቀናኢ ሕዝብ፣ በሕዝባዊነት የተመሠረተ የመንፈስ ፅናት ያስፈልጋቸዋል፡፡ የርዕዮተ ዓለም ጥራት ሊያስፈልግ ነው፡፡ አሁን በማንዴላ ዕረፍት ምክንያት በተለይ ከማንዴላ የምንማረው ምንድን ነው የሚል ነገር ከተቃዋሚ መሪዎች አንብቤያለሁ፡፡ ከማንዴላ የምንማረው ርዕዮተ ዓለሙን አይደለም፡፡ ሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ልክ ከእስር ቤት ሲወጣ አክ ብሎ ተፍቶ ጥሎታል፡፡ ከአንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች ምክር ተሰጥቶት እንደሆነም ይነገራል፡፡ እናም ከእስር ቤት እንደወጣ በቀዳሚነት ያስቀደመው እርቅ፣ ቀጣይነትና መረጋጋት የሚለውን ነው፡፡ 
በዚህም ምክንያት የነበረው ሥነ ሥርዓት በምንም ዓይነት እንዲናጋ አልፈለገም፡፡ ይኼውና ከጥቁሮች በጣት የሚቆጠሩ ቢሊየነሮች ሆነዋል፡፡ እነዚህ ጥቂቶች በእውነትም ከመጠን በላይ በልፅገዋል፡፡ አብዛኛው ግን ከነበረበት ሁኔታ አልተላቀቀም እንዳለ ነው፡፡ የምዕራባዊያን ሚዲያ በአንድ ነገር የፈጠረው ግለሰብ ነው፡፡ የእሱ አስተዋጽኦን ለማሳነስ አይደለም፡፡ ግን እሱን እንደ መልዓክ እንዲታይ ያደረገው የምዕራብ ሚዲያ ነው፡፡ ይህንን ያደረገበት ምክንያት የነበረው የካፒታሊስት ሥርዓት እንዳይናጋ በማድረጉ ነው፡፡ ግን የእኛ የተቃዋሚ መሪዎች ከማንዴላ የሚማሩት አንድ ትልቅ ነገር አለ፡፡ የመንፈስ ፅናት፣ የአቋም ፅናት፣ በአመኑበት ላይ መፅናት፡፡ ይኼ ሰውዬ አንድ ሦስተኛ ወጣትነት የሕይወት ዕድሜውን በእስር ቤት ነበር፡፡ በአካል በመንቀሳቀስ ለደቡበ አፍሪካ ትግል አስተዋጽኦ አላደረገም፡፡ ነገር ግን ትልቁ አስተዋጽኦ ለደቡብ አፍሪካ የጥቁሮች ትግል ተምሳሌትና ምልክት በመሆኑ ነው፡፡ ለፀረ አፓርታይድ ትግል እንደ ምሥል ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከዚያም አልፎ ወደ መጨረሻ ገደማ ከሮቢን ደሴት ወጥቶ ወደ አንድ የተሻለ ቦታ (ኬፕ ታውን) አምጥተውት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹አመፅን አወግዛለሁ ካልክ ነገ እፈታሀለሁ›› ይለዋል፡፡ በልጁ አማካይነት ደብዳቤ ይጽፍና በትላልቅ ሕዝባዊ ስብሰባ እንድታነብ ይላታል፡፡ የደብዳቤው ዋና መልዕክት ‹‹እንደዚህ የሚል ነገር ሰጥተውኛል፡፡ እምቢ ብያቸዋለሁ፡፡ ምክንያቴ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ የሁላችንም እስር ቤት ነች፡፡ እኔ ብቻየን አይደለም የታሰርኩት፡፡ እናንተም ሁላችሁም እስረኞች ናችሁ፡፡ እኔ ስፈታ እናንተ ነፃ ካልሆናችሁ ትርጉም የለውም፡፡ ሁላችንም ነፃ የምንወጣው ይህ የአፓርታይድ ሥርዓት ሲገረሰስ ብቻ ነው፤›› የሚል ነበር፡፡
በኋላ ዴክላርክ ፕሬዚዳንት ሲሆን የውጩና የውስጡ ግፊት በአፓርታይድ ኃይሎችና በኤኤንሲ መካከል ስምምነት ይደረጋል፡፡ ኤኤንሲ በወታደራዊ ኃይል የአፓርታይድ ሥርዓትን እንደሚያሸንፍ ይገነዘባል፡፡ የአፓርታይድ መንግሥት ደግሞ አሁን በተቃውሞ የተነሱት ውጫዊና ውስጣዊ ኃይሎች እንደማያሸንፉ ይገነዘባል፡፡ እዚህ መካከለኛው መንገድ ላይ ነው የተገናኙት፡፡ በሰላም በመወያየት ይህንን ችግር እንፍታ ብለው፡፡ ስለዚህ ‹‹One man one vote›› በሚል የምርጫ ሥርዓት ከ350 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ማንዴላ ተመርጧል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ጥቁሮች የምርጫ መብት የተሰጣቸው እ.ኤ.አ. በ1994 ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1948 ጀምሮ የመምረጥ መብት የነበራቸው ነጮቹ ብቻ ናቸው፡፡ ጥቁሮች የተገለሉ ነበሩ፡፡ ያ ስሙን ገናና አድርጐታል፡፡ ሦስተኛው ማንዴላን ገናና ያደረገው ከአንድ የምርጫ ተርም በኋላ አልፈልግም ማለቱ ነው፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ይኼ የተለመደ ባለመሆኑ ነው፡፡ ለዚህ ነው ነጮች እንደ መልዓክ ያደረጉት፣ ሰማይ የሰቀሉት፡፡ 
የእኛ መሪዎች ከማንዴላ ምንድን ነው የሚማሩት? ያመኑበት የመንፈስና የአቋም ፅናት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሁለተኛው ነገር ደግሞ ለሕዝብ መገዛትና የሕዝብ ወገናዊነትን አጥብቆ መያዝ፡፡ የራሱን ጥቅም በሁለተኛ ደረጃ በማስቀመጥ ከአገር በላይ ለአሳር ሲባል ነው፡፡ ብዙዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ግን ለራስ ጥቅም የሚንቀሳቀሱ የሥልጣን ጥመኝነት ያለባቸው ናቸው፡፡ ይኼ የእኔ እምነት ነው፡፡ ከዚህ በፊት ጋዜጠኞች በኢሕአዴግ መተካካት መደረግ አለበት ስትሉ በተቃዋሚዎችም መደረግ ነበረበት፡፡ ብዙዎቹ እኮ የፓርቲ አመራር ሆነው 20 ዓመታት የሞላቸው ናቸው፡፡     
ሪፖርተር፡- ሕዝቡ በተለይ ደግሞ ወጣቱ ከፖለቲካ ተሳትፎ የራቀ ይመስላል፡፡ በኢሕአዴግ ወይስ በተቃዋሚዎች ተስፋ የቆረጠ ይመስልዎታል?
ፕሮፌሰር ገብሩ፡- ሕዝቡ ከ97 ምርጫ ወዲህ በአጠቃላይ ስናየው ራሱን ከፖለቲካ ዓለም ያገለለ መስሎ ይታየኛል፡፡ ለምን? እኔ የሚመስለኝ የብሶት ማነስ፣ ባለው ሁኔታ የመደሰትና ምቾት ነገር አይመስለኝም፡፡ ከ97 በኋላ በሕዝቡ ውስጥ ፍርኃት የነገሠበት ሁኔታ ያለ ይመስለኛል፡፡ ፖለቲካና ኮረንቲ አንድ ናቸው የሚለውን አነጋገር በተደጋጋሚ እሰማለሁ፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ በፍርኃት ምክንያት ከፖለቲካ ራሱን አግልሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት የሚያደርግበት አንዳንድ ነገሮች አሉ፡፡ ኮንዶሚኒየም በመሥራት ወይም ኮንዶሚኒየም ይሠራል ብሎ ተስፋ በመስጠት፣ በተወሰነ መልኩም ቢሆን የውኃና የኤሌክትሪክ አቅርቦት የመንገድና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎችን እየተመለከተ ነው፡፡ ሕዝቡን ያባብላል፡፡ እነዚህ በጣምራ ሕዝቡ ፖለቲካዊ ተሳትፎውን እንዲቀንስ አድርገውታል፡፡ ሕዝቡ ብሶቱን የሚገልጸው ወደ ቤተ ክርስቲያንና መስጊድ እየሄደ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ሴቶች፡፡ ወጣቱ ደግሞ በተለያዩ ነገሮች ታስሯል፡፡ ችግሩ ይገባኛል መጫወቻና መዝናኛ ቦታ በሌለበት የውጭ አገር እግር ኳስ አምላኪ ቢሆን አያስደንቅም፡፡ ሌላው ደግሞ ቀደም ብሎ በደርግ ጊዜ የጀመረ ይመስለኛል፡፡ ብዙ አጉል ልማዶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ገብቷል፡፡ ወጣቱ የዚሁ ሰለባ ሆኗል፡፡ እነዚህ ነገሮች እስከ ትምህርት ቤት ድረስ ዘልቀዋል፡፡ 
ሥራ አጥነቱም አለ፡፡ ወጣቱ ተምሮ ጥቁር ካባ ተከናንቦ ከተመረቀ በኋላ ራሱንና ቤተሰቡን የሚደግፍበት ገቢ ከሌለው ወደሌላ መጥፎ ነገር የሚገፋፋው፡፡ አንዱ ችግር ይኼው ነው፡፡ ሁለተኛው ምኞታችን ተስፋን መሠረት ያደረገ የትግል መሣርያ ሆኗል፡፡ ኤርትራን ብትወስድ ለሥርዓቱ ብቸኛ ተቃውሞ የመግለጫ መንገድ መስዋዕትነት ነው፡፡ ኢሳያስም ሥልጣን ላይ ሊያቆየው የሚችለው ይኼው ነው፡፡ 
ሪፖርተር፡- እስካሁን እንደነገሩኝ ከሆነ ሥልጣን ላይ ያለው ኢሕአዴግ በተለይ ከ97 ምርጫ በኋላ የፖለቲካ ምኅዳሩን ሙሉ ለሙሉ በመቆጣጠር ለተቃዋሚዎች የማያፈናፍን አድርጎታል፡፡ የአንድ ፓርቲ ሥርዓትም እየገነባ ይመስላል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችም የሥልጣን ጥመኝነት ስላለባቸው፣ የተሻሉ ዲሞክራቶች መሆናቸውን ማረጋገጫ የለም፡፡ የትግል ፅናትም የላቸውም፡፡ በጥላቻም የተሰባሰቡ ናቸው፡፡ በሁለቱም ጎራ ተስፋ አስቆራጭ የሆነ ሁኔታ ይስተዋላል ብለዋል፡፡ ይህንን የአመራር ድክመት ከክፍተት ሊሞላ የሚችል ሌላ የትውልድ ጎራ ይታይዎታል?
ፕሮፌሰር ገብሩ፡- ገዥው ፓርቲ እየሸመገለ ነው፡፡ ተቃዋሚዎችም እየሸመገሉ ነው፡፡ እንግዲህ ይቺ አገር ነገ የሚረከባት ምን ዓይነት ትውልድ ነው የምትለው? ተረካቢውማ ያንተ ትውልድ ነው፡፡ ወደድንም ጠላንም የነገይቱ ኢትዮጵያ ተረካቢና መሪ የአሁኑ ትውልድ ነው፡፡ ቅድም የገለጽኩልህ የወጣቱን ደካማ ጎን ነው፡፡ ጠንካራ ጎኑን ደግሞ ላመላክት፡፡ ከፖለቲካ ትግል አንፃር አንዳንዶቹ በ97 ባዩት በማዘን አዳዲስ ፓርቲዎች በመፍጠር ላይ ያሉ አሉ፡፡ ለምሳሌ እንደሰማሁት ከሆነ በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው፡፡ ብዙዎቹ በቅንጅት በኋላም በአንድነትና በመድረክ ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚህ አዲስ አመራርና አዲስ ሥርዓት ያስፈልጋል ያሉ ይመስለኛል፡፡
በጋዜጠኝነት ዓለም የተሰለፉ ድፍረት ያላቸው፣ ሐሳባቸውን ጥርት ባለና ድፍረት ባለው መንገድ የሚያቀርቡ ደግሞ አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ አንተ ትመስለኛለህ፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጸሐፊዎች አሉ፡፡ የተዋጣላቸው ጸሐፊዎች፡፡ የአገሪቱን ፖለቲካ በማብጠርጠር ለሕዝብ የሚያቀርቡ ወጣቶች አሉ፡፡ በግጥም፣ በቴአትር፣ በሙዚቃ እሮሮዋቸውን፣ ተስፋቸውንና ዕይታቸውን ለሕዝብ የሚያቀርቡ ብዙ ወጣቶች እንዳሉ ደግሞ መዘንጋት የለብንም፡፡ የነገይቱ መሪዎች የሚፈልቁት ከእነዚህ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም፡፡ እንዲያውም ልብ እንበል፡፡ ኢትዮጵያ የወጣት ሕዝብ አገር ናት፣ አንዘንጋ፡፡ ከ50 በመቶ በላይ ከ30 ዕድሜ በታች ነው፡፡ ይኼ የሚያሳይህ የአገሪቱን ተስፋ ከሰብዓዊ ኃይል ምን ያህል ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ የሚያስፈልገው ጥሩ መሪ፣ የጠራ ርዕዮተ ዓለምና ጠንካራ ድርጅት ነው፡፡ ሁለትም ሦስትም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ በርካታ ፓርቲዎችን ማጥፋት ይኖርባቸዋል፡፡ እናም ተቃዋሚዎችም መተካካት አለባቸው፡፡ ወጣቱን ማስተማር አለባቸው፡፡ የአስተሳሰብ ጥራት ያለው፣ በውይይትና በንግግር ችግርን መፍታት የሚችልና ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ የሚያራምድ ትውልድ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ተቃዋሚዎች ይህንን መተካካት የሚያደርጉ ከሆኑ ጥሩ ነው፡፡ ወጣቶችን የማያቅፉ ከሆነ ደግሞ አዳዲስ የወጣቶች ፓርቲዎች ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡   
ሪፖርተር፡- ሥልጣን ላይ ያሉም በተቀዋሚነት ያሉም የ60ዎቹ በኃይል የሚያምን ትውልድ ውጤቶች ናቸው፣ የችግሩ አንዱ መገለጫ ይኼው ነው ይባላል፡፡ አሁንም የዛሬው ትውልድ የቀደመውን የኢትዮጵያ ታሪክ በራሱ እየተረጎመ የተለያዩ ጎራዎችን እየፈጠረ፣ ታሪክ ራሱን እየደገመ ይመስላል፡፡ በዘር ጥላቻ ላይ የተመሠረተ ሽኩቻ ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡ በዛሬው ትውልድ ላይ የጣሉት ተስፋ በዚህ ምክንያት አይደናቀፍም?
ፕሮፌሰር ገብሩ፡- እዚያ ውስጥ ከመግባቴ በፊት የፖለቲካ ፓርቲዎች መከፋፈል፣ በመድበለ ፓርቲ ስም የፓርቲዎች መብዛትና የሥልጣን ጥመኝነት የፖለቲካ ባህላችንን ኋላቀርነት ነው የሚያመለክተው፡፡ ይኼን ልናሰምርበት ይገባል፡፡ የዲሞክራሲ ባህል የለንም፡፡ ጃንሆይ ዙፋናዊና አምባገነናዊ ነበሩ፣ ከእሳቸው በኋላ የመጣ አምባገነናዊ ወታደራዊ መንግሥት ነበር፡፡ ሁለቱም በኃይል የሚገዙ የዲሞክራሲ ሽታ ያልነበራቸው ናቸው፡፡ እንግዲህ ወደድንም ጠላንም የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የተጀመረው በኢሕአዴግ ጊዜ ነው፡፡ መብዛታቸው የሚፈለግ ባይሆንም፣ ሥርዓቱ በመኖሩ ነው ይህን ያህል የፖለቲካ ፓርቲዎች የተፈጠሩት፡፡ ነፃ ፕሬሱንም የጀመረው ኢሕአዴግ ነው፡፡ ምንም እንኳን ሲፈልግ በትሩ ቢያነሳባችሁም፡፡ ከ97 በኋላ ግን እነዚህ ነገሮች ጠበዋል፡፡ 
አክራሪነቱ በሁለቱም በኩል ነው የሚታየኝ፡፡ በተቃዋሚዎችም በመንግሥትም፡፡ ይህ የሚያሳየን የመጣንበት የፖለቲካ ባህል ኋላቀር መሆኑን ነው፡፡ ይህንን ልናሰምርበት ይገባል፡፡ ስለዚህ በአንድ ትውልድ እንደ አውሮፓውያን እንሆናለን ማለት አይደለም፡፡ ገና ረዥም ጊዜ ያስፈልገናል፡፡ አሁን ባነሳኸው ጉዳይ ሁለት ዕይታዎች አሉ፡፡ በአንድ በኩል ከእኛ በላይ ኢትዮጵያዊ የለም ወይም የኢትዮጵያ ታሪክ ያልተቋረጠ የሦስት ሺሕ ዓመት ነው የሚሉ አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ብዙውን ቤተሰብ ሰብስባ የያዘች አገር እንጂ አንዱ የበላይ አንዱ የበታች ሆኖ ጨቋኝና ተጨቋኝ ያልነበራት አገር ነች ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የአገራችንን የመንግሥት ሥርዓት ወደ አክሱም ልንጎትተው ብንችልም፣ የዘመናይቱ ኢትዮጵያ ታሪክ ከ100 ዓመት ታሪክ የበለጠ አይደለም የሚሉ ናቸው፡፡
ይህንን በምሳሌ እናጠናክረው፡፡ ባለፈው ሳምንት የአፄ ምኒልክ መቶኛ ዓመት ተዘክሯል፡፡ በጋዜጦችና በመጽሔቶች ላይ አዎንታዊ የሆኑ ፍፃሜዎች ይዘረዘራሉ፡፡ ኢትዮጵያን በማዋሃድ፣ ወይም አዲሷ ኢትዮጵያን በመፍጠር፣ ዘመናዊ አስተዳደር ወዘተ፣ በመጀመር የመጀመርያ ናቸው፡፡ እንዲሁም ደግሞ አገራችንን ከቅኝ ገዥዎች ጋር ተዋግተውና ተሟግተው ያቆዩት ንጉሥ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል አዎንታዊ ገጽታው ትክክል ነው፡፡ እነዚህ ጸሐፊዎችና ተከራካሪዎች የሚዘነጉት ሌላ ገጽታ አለ፡፡ አፄ ምኒልክ የአሁኗን ኢትዮጵያን ማስፋፋቷን ይረሱታል፤ ግንዛቤ ውስጥ ሊያስገቡት አይፈልጉም፡፡ መስፋፋቱ ደግሞ በውዴታ የተደረገ አልነበረም፡፡ በኃይልና በጭፍጨፋ ነው፡፡ ይህንን ማወቅ የሚፈልግ የደቡብ ሕዝቦችን ሄዶ ማነጋገር ይችላል፡፡ ኦሮሞ፣ ወላይታ፣ ሃዲያ፣ ካፋ፣ ጉራጌ፣ ሐረሪ፣ ቤንሻንጉል እነዚህ በሙሉ በኃይል ተቀጥቅጠው ተሸንፈው የገቡ ናቸው፡፡ ከዚያ በኋላ የተጫነባቸው ደግሞ የጭሰኛ ሥርዓት ነው፡፡ የመጀመርያው ብሔርተኛ በመሆኔ ከእኔ በላይ ኢትዮጵያዊ ለአሳር የሚለው ወገን ይህንን ግንዛቤ ውስጥ አያስገባም፡፡ ስለዚህ የዚህ ወገን ትንተና እነዚህ ሕዝቦችን ያገለለ ነው ማለት ነው፡፡ 
ስለዚህ ምን መደረግ አለበት? የሚያስማማን እነዚህ ሁለት ገጽታዎችን ተቀብሎ በሚዛናዊነት ማስታረቅ ነው፡፡ የፖለቲካ እንቅስቃሴውም ከዚህ አንፃር መሆን አለበት፡፡ ስለአንድነትና ስለኅብረ ብሔራዊነት ስንነጋገር የብሔር ጭቆና፣ የአንድ ብሔር የበላይነት የብዙዎቹ የበታችነት፣ የሃይማኖት ልዩነት መኖሩን መቀበል አለብን፡፡ ሥራ ላይ ያለው የፌዴራል ሕገ መንግሥት እነዚህ ነገሮችን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ይመስለኛል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግን የአንድ ትውልድ ዕድሜ ነው ያለው፡፡ አቶ ልደቱ ሕገ መንግሥቱን አስመልክቶ የሰጠው ትንታኔ (በመድሎት) አሳማኝ ነው፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥቱ ብዙ እንከን የለውም፤ መሻሻል ባለባቸው ጥቂት አንቀጾች ላይ ነው መነጋገር ያለብን፤›› ይላል እኔም እስማማለሁ፡፡ በሪፖርተር ቃለ ምልልስ ያደረጉት አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ሰማያዊ ፓርቲ አዲስ ሕገ መንግሥት ማውጣቱን ገልጸው ወቅሰዋል፡፡ እኔም እስማማለሁ፡፡ ሁልጊዜ ስንደኸይ አንኖርም፤ ከዜሮ መጀመር አንችልም፡፡ እኔ በዕድሜ ሦስት ሕገ መንግሥቶች አይቼያለሁ፤ ከሁሉም የሚሻለው የአሁኑ ነው፡፡ ከታሪክ አንፃር የዘረዘርኩልህ አሁን በፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በግለሰቦች መካከል ብሔርን መሠረት ያደረጉ የታሪክ ሽሚያዎችና ክርክሮች መፍትሔው ይኼው ነው ለማለት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን በብሔር ያተኮሩ ኅብረ ብሔርነታችንን ያሳንሳሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኅብረ ብሔርተኞች አንዲት ኢትዮጵያ ምናምን እያሉ ብሔሮችን ያሳንሳሉ፡፡ መፍትሔው በሁለቱም ጫፎች መካከል ነው ያለው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ማጠናከር ይህንን ችግር የሚፈታ ይመስለኛል፡፡ 
ሪፖርተር፡- ከተቃዋሚ መሪዎች ቅድም ካነሱልኝ ኋላቀር የፖለቲካ ባህል በመገንዘብና በመገምገም የተሻለ ነው ብለው የሚያደንቁት አለ?
ፕሮፌሰር ገብሩ፡- [ረዘም ላለ ጊዜ ተንፍሰው ትንሽ ካሰቡ በኋላ] ከመሪዎች ጋር ልታጣላኝ ነው፡፡ የግሌ አስተያየት አይደለም? የተጻፈውን አነባለሁ፡፡ የሚናገሩትንም አዳምጣለሁ፣ እሰማለሁ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ከ97 ወዲህ የ20 ዓመቱ የአገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓትና ችግሩ ላይ መልካም ግንዛቤ ያለው፣ ያንን ግንዛቤውን ለሕዝብ በሚገባው ቋንቋ ያካፈለና በዚህም ምክንያት አክብሮት ያለኝ ለልደቱ አያሌው ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ካድሬዎችም እኔ በማላውቀው ምክንያት ብዙ ነገር ሲሉ እሰማለሁ፡፡ ብዙ ጥርስ ውስጥ እንደገባና ብዙ ሰው እንደሚያዝንበት አውቃለሁኝ፡፡ ግን ወጣትና ብሩህ አእምሮ ያለው ነው፡፡ በመናገር ችሎታ ማንም የማይወዳደረው ነው፡፡ እና መድሎት የሚለው መጽሐፉን አንብቤ በአድናቆት ነው ያቀፍኩት፡፡ ወደ ፖለቲካ ዓለም ደግሞ ይመለሳል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ መመለስም አለበት፣ አገሪቱ ትፈልገዋለች፡፡ ስህተት የማይሠራ ፖለቲከኛ የለም፡፡ በ97 ግን የእሱ ስህተት ቁልጭ ብሎ አልታየኝም፡፡ የ‹‹አረም እርሻ›› መጽሐፉን አንብቤያለሁኝ፡፡ እንዲያውም ያን ጊዜ መከራከሪያ ነጥቦች ነበሩት፡፡ አሁን የደረሱ ችግሮችን ያን ጊዜ ‹‹ተው ሕዝቡን ሞራሉን እንዳንሰብረው፣ ከፖለቲካ እንዳይርቅ›› ብሎ ነበር፡፡ ነብይ ነው አልልም፡፡ ሁኔታዎችን ግን ቀድሞ ማንበብ የቻለ ነበር፡፡ ጥሩ ግምገማ ስለነበረው ነው፡፡ በትሁትነቱ በሰው፣ አክባሪነቱ፣ በግልጽነቱና በሕዝባዊነቱ ደግሞ የማደንቀው መሪ ነጋሶ ጊዳዳ ነው፡፡ አሁን ካልቸኮሉ፣ መጀመርያ ከሕዝብ መማር አስፈላጊ መሆን ካልረሱ ምናልባት ከሰማያዊ ፓርቲ የማደንቃቸው አንድ ሁለት ወጣቶች ይኖራሉ፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/interview/item/4453-%E2%80%B9%E2%80%B9%E1%88%95%E1%8B%9D%E1%89%A1-%E1%89%A5%E1%88%B6%E1%89%B1%E1%8A%95-%E1%8B%A8%E1%88%9A%E1%8C%88%E1%88%8D%E1%8C%B8%E1%8B%8D-%E1%8B%88%E1%8B%B0-%E1%89%A4%E1%89%B0-%E1%8A%AD%E1%88%AD%E1%88%B5%E1%89%B2%E1%8B%AB%E1%8A%95%E1%8A%93-%E1%88%98%E1%88%B5%E1%8C%8A%E1%8B%B5-%E1%8A%A5%E1%8B%A8%E1%88%84%E1%8B%B0-%E1%8A%90%E1%8B%8D%E2%80%BA%E2%80%BA-%E1%8D%95%E1%88%AE%E1%8D%8C%E1%88%B0%E1%88%AD-%E1%8C%88%E1%89%A5%E1%88%A9-%E1%89%B3%E1%88%A8%E1%89%80%E1%8D%A3-%E1%8B%A8%E1%8C%8D%E1%8C%AD%E1%89%B5%E1%8A%93-%E1%8B%A8%E1%8D%96%E1%88%88%E1%89%B2%E1%8A%AB-%E1%89%B0%E1%88%98%E1%88%AB%E1%88%9B%E1%88%AA

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር