የመስቀል በዓል በአለም ቅርስነት ተመዘገበ፤ የሲዳማ ፍቼ በኣልስ?

አዲስ አበባ ህዳር26/2006 ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በማይዳሰስና በማይጨበጥ ቅርስነት የመስቀል በዓልን በዓለም ቅርስነት አስመዘገበች፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ በተደረገው ስምንተኛው የተባበሩት መንግስታት የሳይንስ የትምህርትና ባህል ማዕከል/ዩኔስኮ/ ኢንታጀብል ባህላዊ ቅርሶች ጉባኤ የመስቀል በዓል በአለም ቅርስነት ተመዝግቧል። ይህም ኢትዮጵያ ለመጀመሪያው ጊዜ በአለም አቀፍ ደረጃ በማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ያስመዘገበችው ሲሆን አገሪቱ በአጠቃላይ በዩኔስኮ በተባባሩት መንግስታት የሳይንሰና የባህል ማዕከል ያስመዘገበቻቸው ቅርሶች ብዛት አስር አድርሶታል። በጉባኤውም በአለም አቀፍ ለመመዝገብ ከቀረቡ 31 የማይዳሰሱና የማይጨበጡ ቅርሶች መካከል የመስቀል በዓል አንዱ ሆኖ መመረጡ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ መሆኑ ቢታወቅም በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በየራሳቸው ባህል፣ ትውፊትና እምነት አካሄድ የሚከበር ሲሆን በሰሜን የአገሪቱ ክፍሎች መንፈሳዊ ይዘቱ እንደሚያመዝን ተናግረዋል። በበዓሉ ተለያይተው የሚኖሩ የቤተሰብ አባላት የሚገናኙበትና ማህበራዊ ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት፣ ወጣቶች ለጋብቻ የሚዘጋጁበትና የተጣሉ ሰዎች የሚታረቁበት በመሆኑ ከሀይማኖታዊ ትርጉሙ በሻገር የመተሳሰብ የወዳጅነት መንፈስ የሚጎለብትበት መሆኑን ተናግረዋል። ቅርሱ በአለም አቀፍ ቅርስነት መመዝገቡ ዓለማቀፍ እውቅናን ከማበርከቱ ባሻገር፣ የቱርስት መስህብነቱ ይጨምራል፣ ቅርሱ ከቀድሞ በተለየ አለማቀፍ ጥበቃ ይደረግለታል፣ ቅርሱ ባሕላዊ ይዘቱን ጠብቆና የማንነት መገለጫ ሆኖ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ያደርጋል ብለዋል። በተጨማሪም በአለም አቀፍ ደረጃ ቅርሱ እውቅና በማግኘቱ ከተለያ የአለም ክፍሎች አጥኚዎችና ተመራማሪዎች በመምጣት ቅርሱ በአለም አቀፍ ታዋቂነትን እንዲያተርፍ ያደርጋል ብለዋል። ከዚህ ሌላ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ አምስት ቅድመ እውቅና የተሰጣቸው ቅርሶችን እንዳሏት የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ከነዚህም ውስጥ ድሬ ሼህ ሁሴን፣ ሆልቃ ሶፉኡመር ዋሻ፣ የጌዲዮ ጥምር ባህላዊ ተፈጥሮአዊ መልከአ ምድር፣ መልከ ቁንጥሬ የአርኪዮሎጂ ሳይትና የባሌ ተራሮች ተጠቃሾች ናቸው። ኢትዮጵያ የበርካታ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህላዊ አገር እንደመሆኗ የበርካታ ባሕላዊ ቅርሶች ባለቤት እንደመሆኗ እስከ ቅርብ ጊዜ ቅርሶቿ እምብዛም ትኩረት አልተሰጣቸውም ነበር። ይሁንና ከቀርብ ዓመታት ወዲህ በተወሰዱ አንዳንድ እርምጃዎች ለባህላዊ ቅርሶቿ አለም አቀፍና አገር አቀፍ ትኩረት በመሰጠት ላይ መሆኑን ተናገረዋል። በአሁን ወቅትም በአገሪቱ በሚገኙ 66 የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህላዊ ቅርሶች በሀገር አቀፍ ቅርስነት በመመዝገብ በአምስት ቅጾች በማተም ለሚመለከታቸው አካላት እንዲሰራጭ መደረጉን አስታውሰዋል። ባለስልጣኑ የመስቀል በዕል በአለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ያለሰላሰ ጥረት ያደረጉ አካላትም በማመስገን በቀጠይ የአገሪቱ ቅርሶች አለማቀፍ ዕውቅናን እንዲያገን የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር