የከተማ መሬት ምዝገባ አዋጅን ለማፅደቅ የተቸገረው ፓርላማ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ይሁንታ ጠየቀ...የኣዋጁ መጽደቅ የሃዋሳን ከተማ የወደ ፊት እጣ ፋንታ ይወስነዋል


የከተማ መሬት ምዝገባ አዋጅን ለማፅደቅ የተቸገረው ፓርላማ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ይሁንታ ጠየቀ...ፓርላማው ይህንን ሕግ በማውጣት የክልል ከተሞችን መሬት መመዝገብና ማስተዳደር ለፌዴራል መንግሥት ሊሰጥ ይችላል
 
ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 51(5) እና 52(2) (መ) መሠረት ለፌዴራሉ መንግሥት መሬትና የተፈጥሮ ሀብቶችን የሚመለከቱ ሕጎችን የማውጣት ሥልጣን የሚሰጥ ሲሆን፣ ክልሎች ደግሞ በፌዴራሉ መንግሥት የሚወጡ ሕጎችን መሠረት በማድረግ መሬት የማስተዳደር ሥልጣን እንዳላቸው የሚደነግግ በመሆኑ፣ ፓርላማው ይህንን ሕግ በማውጣት የክልል ከተሞችን መሬት መመዝገብና ማስተዳደር ለፌዴራል መንግሥት ሊሰጥ ይችላል የሚለው አስቸጋሪ ጉዳይ እንደሆነበት አስረድቷል፡፡
 
ኣዋጁ ከጸደቀ በፌዴራል መንግስት ልተዳደሩ ከምችሉ የክልል ከተሞች መካከል ሃዋሳ ከተማ ይገኝበታል
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር የቀረበለትን የከተማ መሬትና መሬት ነክ ንብረቶች ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ በስፋት ሲመረምር ቢቆይም፣ አዋጁን ለማፅደቅ ፓርላማው ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን አለው ወይ የሚለው አጠያያቂ በመሆኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ይሁንታ እንዲሰጠው ጠየቀ፡፡ 
ረቂቅ አዋጁ ‹‹የከተማ መሬት ምዝገባ አዋጅ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ቢሆንም፣ የአዋጁ አጠቃላይ ይዘት ግን ዜጎች በመሬት ላይ ለሚገነቡት ቋሚ ንብረት የባለቤትነትና የመጠቀም መብት ዕውቅናና ዋስትና መስጠትን የሚመለከት ነው፡፡ 
ረቂቅ አዋጁ የከተማ መሬትን በተመለከተ ‹‹በማንኛውም ክልል የከተማ አስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚገኝ መሬት ነው›› የሚል ትርጓሜ የሚሰጥ ሲሆን፣ የአዋጁ ተፈጻሚነት ወሰንን በተመለከተ ደግሞ፣ ‹‹ይህ አዋጅ የከተማ መሬትን በሚመለከት በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ሁሉም ከተሞች ተፈጻሚነት ይኖረዋል›› በማለት አስቀምጧል፡፡ 
በተጠቀሰው ረቂቅ አዋጅ ላይ ፓርላማው ሰኔ 25 ቀን 2005 ዓ.ም. የመጀመሪያ ውይይት በማካሄድ ለዝርዝር ዕይታ ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶት ነበር፡፡ 
በረቂቅ አዋጁ ላይ ላለፋት ወራት ጥልቅ ምርመራ ሲያካናውን የቆየው ቋሚ ኮሚቴ ባለፈው ሐሙስ የመጨረሻ የውሳኔ ሐሳቡን ለፓርላማው አቅርቧል፡፡ የከተማ ማሬትና መሬት ነክ ንብረትን ለመመዝገብና ባለይዞታው በመሬቱ ላይ ላፈራው መሬት ነክ ንብረት የዋስትና ማረጋገጫ እንዲኖረው ለማድረግ የሚያስችሉ፣ እንዲሁም አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ሒደቱን የሚያግዙ ጠቃሚ ድንጋጌዎችን የያዘ ረቂቅ አዋጅ መሆኑን መገንዘብ እንደቻለ፣ ቋሚ ኮሚቴው በውሳኔ ሐሳብ ሪፖርቱ አስረድቷል፡፡ 
ነገር ግን የከተማ መሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች ምዝገባ መካሄድ ያለበት በፌዴራሉ መንግሥትና በክልሎች መካከል ያለውን የሥልጣን ግንኙነት በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠውን ድንጋጌ ባከበረ መንገድ መከናወን ይገባዋል ሲል ቋሚ ኮሚቴው በውሳኔ ሐሳቡ አስረድቷል፡፡ 
ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 51(5) እና 52(2) (መ) መሠረት ለፌዴራሉ መንግሥት መሬትና የተፈጥሮ ሀብቶችን የሚመለከቱ ሕጎችን የማውጣት ሥልጣን የሚሰጥ ሲሆን፣ ክልሎች ደግሞ በፌዴራሉ መንግሥት የሚወጡ ሕጎችን መሠረት በማድረግ መሬት የማስተዳደር ሥልጣን እንዳላቸው የሚደነግግ በመሆኑ፣ ፓርላማው ይህንን ሕግ በማውጣት የክልል ከተሞችን መሬት መመዝገብና ማስተዳደር ለፌዴራል መንግሥት ሊሰጥ ይችላል የሚለው አስቸጋሪ ጉዳይ እንደሆነበት አስረድቷል፡፡ 
በመሆኑም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62(3) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት አስተያየቱን በዝርዝር ቢሰጥ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ቋሚ ኮሚቴው እንዳመነበትና ይህንንም ሐሳብ ፓርላማው እንዲያፀድቀው ጠይቋል፡፡ 
በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ በርካታ የምክር ቤቱ አባላት የውሳኔ ሐሳቡን በመቃወም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ መሬትን አስመልክቶ ለፌዴራሉ መንግሥት የሰጠው ሥልጣን ሕግ ማውጣትን ብቻ መሆኑ ግልጽ ሆኖ ሳለ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተያየት ለምን ይጠየቃል? የፌዴሬሽን ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሕግ ሊወጣላቸው ይገባል ብሎ ወደ ፓርላማው ይልካል እንጂ ፓርላማው በምን የሕግ አግባብ ነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተያየት የሚጠይቀው? የሚሉ ሐሳቦች በበርካታ አባላት ተንፀባርቀዋል፡፡ 
‹‹በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚቀርብ ጉዳይ የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚያስፈልገው ሲሆን ነው ጥያቄ የሚቀርበው፡፡ ረቂቅ አዋጁ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጣረስ ከሆነ አዋጁን ማስተካከል ከእኛ የሚጠበቅ ነው፡፡ ማብራሪያ የሚያስፈልግ ከሆነ ደግሞ የሕገ መንግሥት ረቂቅ ላይ የተቀመጠውን ማብራሪያ መመልከት ነው፡፡ ስለዚህ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ግልጽ አይደለም ወይም ቋሚ ኮሚቴው ሥራውን በአግባቡ አልተወጣም፤›› ሲሉ አንድ የምክር ቤቱ አባል ጠይቀዋል፡፡ 
ሌላ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው ቋሚ ኮሚቴው ከዚህ ቀደም ይህንኑ አዋጅ በተመለከተ የውሳኔ ሐሳብ ሪፖርቱን ለፓርላማው አባላት በትኖ እንደነበርና ይህም የውሳኔ ሐሳብ ፓርላማው ይህንን ሕግ የማውጣት ሥልጣን እንዳለው የሚገልጽ እንደነበር በማስታወስ፣ ቋሚ ኮሚቴው አሁን ሐሳቡን እንዴት ሊቀይር ቻለ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ 
በተጠቀሰው ጉዳይ ላይ ምላሽ የሰጡት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ቀደም ሲል ከዚህ የተለየ የውሳኔ ሐሳብ ተበትኖ እንደነበር አስታውሰው፣ ነገር ግን ወደኋላ በመመለስ ድጋሚ ውይይት የተደረገበት መሆኑን፣ ይህ የሆነበት ምክንያትም አዋጁ በአገር አቀፍ ደረጃ ቢፀድቅ ከሚኖረው ጠቀሜታ አኳያ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም የቀድሞውን የውሳኔ ሐሳብ በመተው አሁን በቀረበው ሐሳብ ላይ ብቻ የተመለከተ ውይይት እንዲደረግ ምክር ቤቱን አሳስበዋል፡፡ 
ሌላ የምክር ቤቱ አባል በበኩላቸው አዋጁ ቢፀድቅ ሊኖረው የሚችለውን አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ፋይዳ እንደሚረዱ በመግለጽ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ግን ግልጽ አይደለም ብለዋል፡፡ 
‹‹የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ መሬትና መሬት ነክ ምዝገባ ማካሄድ መሬት ከማስተዳደር ጋር ያለው ግንኙነትና ስለመሬት አጠቃቀም ሕግ የማውጣት ሥልጣን እስከምን ድረስ እንደሚሄድ ግልጽ አይደለም፡፡ በመሆኑም ፌዴሬሽን ምክር ቤት ማብራሪያ ይስጥበት ነው የሚለው፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ይህንን ሲል ምን ማለቱ ነው? ሌላው ይህ ጥያቄ የተነሳው ከየት ነው? ቋሚ ኮሚቴው ባለድርሻ አካላትን ባወያየበት ወቅት የክልል መንግሥታትን በመጥራት ከእነሱ የተነሳ ነው? ፓርላማው ነው ጥያቄውን ማንሳት ያለበት ወይስ ባለቤቶቹ ናቸው? ይህንን ሳንመልስ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ማብራሪያ መጠየቅ የፓርላማውን ኃላፊነት አሳልፎ መስጠት ሊሆን ይችላል፤›› ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ 
በመጨረሻም ረቂቅ አዋጁን በማፅደቅ በአገር አቀፍ ደረጃ የመሬትና መሬት ነክ ምዝገባን በአንድ ወጥ ማካሄድ እንደተፈለገ፣ ነገር ግን ይህንን በቀጥታ ማድረግ ከክልሎች ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ጋር የሚቃረን መሆኑ በሌሎች አባላት ተብራርቷል፡፡ 
የተጠቀሰውን አዋጅ ለማፅደቅ የሚያስችል ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ መኖሩን የገለጹ ሌላ የምክር ቤቱ አባል፣ በድንጋጌው መሠረት የውሳኔ ሐሳቡ እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡ 
የፌዴራሉ መንግሥት አንድ ወጥ የሆነ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሕግ ማውጣትና መተግበር የሚችለው የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ይሁንታ ሲያገኝ እንደሆነ በሕገ መንግሥቱ መቀመጡን፣ የዚህ ረቂቅ አዋጅ ዓላማም አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር በመሆኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን እንደሚመለከት እኚሁ አባል አብራርተዋል፡፡ 
በመሆኑም ክልሎች አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብን ለመፍጠር በዚህ ረቂቅ አዋጅ መውጣትና መተግበር ላይ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በኩል ይሁንታቸውን ከሰጡ አዋጁ ሊፀድቅ እንደሚችል በስተመጨረሻ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ 
ፓርላማውም በዚህ ሐሳብ ላይ በመተማመን የውሳኔ ሐሳቡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በረቂቅ አዋጁ ላይ ይሁንታውን እንዲሰጥ በሚል ተስተካክሎ በሙሉ ድምፅ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መርቶታል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/news/itemlist/user/52-%E1%8B%AE%E1%88%90%E1%8A%95%E1%88%B5%E1%8A%A0%E1%8A%95%E1%89%A0%E1%88%AD%E1%89%A5%E1%88%AD

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር