‹‹በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሥራ ይልቅ ለወሬና ለአሉባልታ ጊዜያቸው የሚያጠፉ አሉ››

አቶ ዱቤ ጅሎ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር
አገሪቱ በአትሌቲክሱ የምትሳተፍባቸው በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ከፊት ለፊቷ ይጠብቃታል፡፡
ወቅቱ ደግሞ የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያው ሩብ በጀት ዓመት ተጠናቆ ቀጣዩ የተጀመረበት ነው፡፡ ስፖርቱን በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ግን ዝምታን መርጧል፡፡ በሌላ በኩል በአንድም ሆነ በሌላ የሚመለከታቸው አካላት የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ዝምታ እንዳልወደዱት የሚናገሩ አሉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ተቋሙ ባለፈው መስከረም 22 እና 23 ቀን 2006 ዓ.ም. 17ኛውን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው ድሬዳዋ ላይ ባከናወነበት ወቅት፣ አገሪቱ እስከዛሬ ከተለመዱት የውድድር ዓይነቶች በተጨማሪ አዳዲስ የሜዳ ተግባራትን ጨምሮ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ዕቅድ እንዳላት፣ ለዚያ ደግሞ ከሙያተኞች ምርጫ እስከ አትሌቶች ምልመላ ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ስምምነት ላይ መድረሱ ነው፡፡ የአገሪቱ የስፖርት መገናኛ ብዙሃኑ እግር ኳሱ ላይ በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫ እስከ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የተጓዘበትን መንገድ ብቻ ትኩረት ማድረጉ አትሌቲክሱን ጨምሮ የተቀረው እንዲዘነጋ ሆኗል ይላሉ፡፡ ይህም ለስፖርቱ ዘርፍ አደገኛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እነዚህንና ሌሎች ጥያቄዎችን በመያዝ ደረጀ ጠገናውበኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ ዱቤ ጁሎ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ 
• የውድድር ዓመቱ ሩብ ዓመት ተገባዷል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እርስዎ ከሚመሩት የቴክኒክ ክፍል ጭምር ዝምታን መርጧል የሚሉ ቅሬታዎች ይቀርባሉ፡፡
 መግለፅ የምችለው ቴክኒኩን በተመለከተ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ባለፈው ዓመት በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ተደርገው በውጤት ደረጃም ቢሆን ጥሩ ነገር የተመዘገበበት ዓመት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዓለም ሻምፒዮና በታዳጊዎችና በዋናው ቡድን፣ በአፍሪካ፣ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተለያዩ የጎዳና ላይ ውድድሮች አበረታችና ጥሩ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ከዚህ ተነስተን ወደ ዘንድሮው የውድድር ወቅት ስንመጣ ድሬዳዋ ላይ በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ዕቅድ ወጥቷል፣ ዕቅዱ የሚተገበርበት ፕሮግራምም ተይዟል፡፡ በዕቅዱ መሠረት የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ይኼው በቴክኒክ ክፍሉ አስፈላጊ የሚባሉ ማስረጃዎች ተሰብስበውና ተዘጋጅተው ለውሳኔ ሐሳብ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቀርቧል፡፡ ሥራ አስፈጻሚው ውሳኔ ከሰጠ በኋላ የዘንድሮ ሥልጠና ይጀመራል፡፡ በዘንድሮው ውድድር እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች አሉ፡፡ በዚህ ደረጃ ሲታይ ዘግይተናል፡፡ ነገር ግን ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንገባለን የሚል ተስፋ አለኝ፡፡  
• በቅርቡ በሞሮኮ ራባት የሚደረግ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አለ፡፡ ከአራት ወር በኋላ ደግሞ በባሐማስ የሚከናወነው የዓለም የዱላ ቅብብል ይኖራል፡፡ ይኼ ውድድር ከዚህ በፊት ያልተለመደ ከመሆኑ አኳያ ከወዲሁ ዝግጅት የሚጠይቅ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ በዋናነት የቴክኒክ ክፍሉን የሚመለከቱ ናቸው፡፡
 እውነት ነው፡፡ እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ዓለም አቀፍ ውድድሮች ይጠብቁናል፡፡ በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት ያስፈልጋል፡፡ እንደተባለው ከአራት ወር በኋላ ባሐማስ ላይ የሚደረገው የዱላ ቅብብል ውድድር ከዚህ በፊት ተደርጎ የማያውቅ ነው፡፡ ውድድሩ 4በ800 ሜትር ወንድና ሴቶች፣ እንዲሁም 4በ1ሺሕ 500 ሜትር ወንድና ሴቶች የሚሳተፉበት ነው፡፡ ፌዴሬሽናችን በውድድሩ እንደሚሳተፍ ለዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) አሳውቋል፡፡ ውድድሩ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም አዲስ ነው፡፡ ስለሆነም አዲስ ዝግጅትና አዲስ ሥራ ይጠይቃል፡፡ የቡድን ውድድር በመሆኑ ማለት ነው፡፡ ለዚህም በቅርብ ቀን ውስጥ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞችና አትሌቶች ምርጫ ይከናወናል፡፡ ሌላው የዓለም 21 ኪሎ ሜትር በመጋቢት ወር የሚከናወን ውድድር አለ፡፡ እንደዚሁም የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር፣ የወጣቶች ኦሊምፒክና የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና በውድድር ዓመቱ የሚጠብቁን ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአህጉር ደረጃ የምሥራቅ አፍሪካና የአፍሪካ አገር አቋራጭ ውድድሮችም ይኖራሉ፡፡ ለዚህ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለእያንዳንዱ ሙያተኛ እንደየድርሻውና ሙያው ሥራውን በኃላፊነት እንደሚሰጥ እምነት አለኝ፡፡ ቴክኒክ ክፍሉ አስፈላጊውን አከናውኖ እቅዱን ለቦርዱ ሰጥቷል፡፡ ውሳኔውም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለሕዝብ ይፋ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የአትሌቶችና ብሔራዊ አሠልጣኞች ምርጫም ቀጥሎ የሚከናወን ይሆናል፡፡ ምርጫው ከዚህ በፊት እንደሚደረገው በሦስት ምድብ (ካታጎሪ) ታዳጊዎች፣ ወጣቶችና አዋቂዎች ተብሎ ነው፡፡ በዚያው መጠን የተመረጡ አትሌቶችን ለማሰባሰብ ጊዜ የሚጠይቅ ነገር በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች በዚህ ኅዳር ውስጥ ማጠናቀቅ የሚጠበቅበት ይመስለኛል፡፡ 
• ባለፈው በተከናወነው ጉባኤ ማኅበራት ማለትም የአትሌቶች፣ አሠልጣኞችና ሌሎችም አካላት በአዲስ መልክ ስለሚዋቀሩበት ሁኔታ ተነስቷል፡፡ በዚሁ ዘንድሮ እውን እንደሚሆን ጭምር የውሳኔ አቅጣጫ በጉባኤው ተቀምጧል፡፡ ይህን አሠራር ከቴክኒክ ክፍሉ ጭምር ፌዴሬሽኑ የሚደግፈው አለመሆኑ የሚናገሩ አሉ፡፡
 ማኅበራት የሚባሉት የፌዴሬሽኑ አጋር ናቸው፡፡ እነዚህም የአሠልጣኞች፣ የአትሌቶች፣ የዳኞችና የአትሌቶች ሥልጠና ኮሚሽን የሚባሉት ሲሆኑ፣ እንዲቋቋሙ ቅድመ ሁኔታዎች ተሠርተው ለሚመለከተው ክፍል ተላልፏል፡፡ እዚህ ላይ ግልፅ እንዲሆን የምፈልገው የአሠልጣኞችና አትሌቶች ማኅበር እንዲሁም የዳኞች ጭምር እንደ ማኅበር ቢቋቋም ችግር ያለው አይመስለኝም፡፡ የአትሌት ሥልጠና ኮሚሽን ግን መቋቋም የሚገባው በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስር ነው፡፡ ኮሚሽኑ እንዴትና በምን መስፈርት መቋቋም እንደሚገባው ፌዴሬሽኑ መመሪያውን ለክልሎች እንዲደርስ ከተደረገ በኋላ አገር አቀፍ ሥልጠና ኮሚሽን እንዲቋቋም የሚደረግ ነው የሚሆነው፡፡ ይኼው እውን ይሆን ዘንድ ፌዴሬሽኑ መመሪያዎችን ለክልሎች ልኳል፡፡ የሙያ ማኅበራት ከሚመለከተው መሥርያ ቤት እውቅና ካገኙ በኋላ በሙያ ማኅበርነት ይቋቋማሉ፡፡ ነገር ግን የሥልጠና ኮሚሽኖች ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሙያተኞችን መርጦ የሚያዋቅረው፣ ተጠሪነቱም ለፌዴሬሽኑ የሚሆን ነው፡፡ ኮሚሽኑ በፌዴሬሽኑ ስር የሥልጠና ልማትና ተያያዥ የአትሌቲክስ ፕሮጀክት ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ነው፡፡ ባለፈው መስከረም በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተጨማሪ ጥያቄ ክለቦች የጠቅላላ ጉባኤ አባል መሆን አለባቸው የሚለው ይገኝበታል፡፡ ሐሳቡ እንደ ሐሳብ መቅረቡ ክፋት የለውም፡፡ ነገር ግን መታየት ያለበት እግር ኳስ የራሱ ሕግ እንዳለው ሁሉ፣ አትሌቲክስም የራሱ ሕግ አለው፡፡ ስለዚህ የፌዴሬሽኑ አደረጃጀት የክልል ፌዴሬሽኖችን አደረጃጀት መሠረት አድርጎ በመሆኑ ክለቦች በጠቅላላ ጉባኤ ሊወከሉ የሚገባቸው በክልላቸው ነው፡፡ ለምን ከተባለ በአዲስ አበባ ከ40 በላይ ክለቦች አሉ፡፡ አማራና ኦሮሚያም እንደዚያው፡፡ ነገ ደግሞ ትግራይ ከ70 እና 80 በላይ ክለቦችን ሊመሠርት ይችላል፡፡ ሌሎችም በዚያው መጠን የክለቦቻቸውን ቁጥር የማያሳድጉበት ምክንያት አይኖርም፡፡ በዚህ መነሻነት ክለቦች የጠቅላላ ጉባኤ አባል ይሁኑ ቢባል የፌዴሬሽኑን ደንብና መመሪያ በየዓመቱ ማሻሻል ሊገባው ነው ማለት ነው፡፡
• ክለብ የሌላቸው ክልሎች ክለብ ያላቸውን እንደማስተዳደር ይቆጠራል የሚሉ አሉ፡፡
 አገሪቱ የምትተዳደረው በፌዴራል ሥርዓት ነው፡፡ ክለብ የሌላቸው ክልሎች አሉ ከተባለ ክለብ እንዲኖራቸው እገዛ በማድረግ ማደራጀትና ማብቃት ነው፡፡ ጥያቄው ተደጋግሞ ሲቀርብ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በዚህ ፌዴሬሽን ከአትሌት ተወካይነት እስከ አመራር ወደ አሥራ ስምንት ዓመት ያህል ግልጋሎት ሰጥቻለሁ፡፡ ጥያቄውም የቆየ ስለመሆኑ አውቃለሁ፡፡ ፌዴሬሽኑ በዓለም አቀፍና በአገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት መሠረት የሚሠራ ተቋም ነው፡፡ 
• የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እያንዳንዱን ነገር ለራሱ እንዲሚያመቸው ከሕግጋቱ ጀምሮ በልኩ አድርጎ እንደሚያዘጋጅ የሚተቹ አሉ፡፡
 አትሌቲክስን እያስተዳደረ የሚገኘው ፌዴሬሽኑ ለየት ያለ አደረጃጀትና አሠራር አለው፡፡ እያንዳንዱ የሚሠራው መሬት ላይ በተግባር የሚታይ ነገር ነው፡፡ ይህንን በግልጽ ለማስቀመጥ በውድድር ወቅት ፌዴሬሽኑ ከሥራ ውጤት ይኖራል፡፡ ካልሠራ ደግሞ ውጤት ያጣል፡፡ ስለዚህ የፌዴሬሽኑ ቢፒአርና ቢኤሲሲ መለኪያው ውጤት ይሆናል ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሌት ከቀን ካልተሠራና በአገሪቱ መደበኛ የሥራ ሰዓት ልሥራ ቢባል በርካታ ነገሮች የሚያመልጡ ነው የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር በየካቲት መጨረሻ ይከናወናል፡፡ የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮናም ሆነ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚከናወኑት በሐምሌና በነሐሴ ነው፡፡ በእኛ ፍላጎት አንድን ወደ ኋላ ሌላውን ደግሞ ወደፊት ለማድረግ አንዳች ሥልጣን የለንም፡፡ በእያንዳንዱ ውድድር ከዓለም ጋር ተፎካካሪ ለመሆን የግድ ቀንና ሌሊት መሥራት ይጠይቃል፡፡ ጊዜና ሰዓት እንጠብቅ ብንል አይሆንም፡፡ ስለዚህ በዚህ መነሻነት ፌዴሬሽኑ ‹‹በልኩ›› የሚባለው ነገር ውኃ የማይቋጥር ነው የሚሆነው፡፡ በእርግጥ እንደተባለው በልክ የሚለው በእውቀት ላይ ተመሥርቶ ከሆነ ያስኬዳል፡፡ 
• በልክ የሚለው ሐሳብ መነሻ የለውም እያሉ ነው፡፡ 
•መነሻ አለው የለውም፣ ክርክር ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሙያተኞች ሥራን መሠረት አድርገው በሚሠሩበት ጊዜ ቅር የሚላቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ስለ ሠራህ ለጥቅም የምትሠራ የሚመስላቸው አሉ፡፡ በግሌ በአትሌቲክሱ በመቆየቴና በሙያው ውስጥ ያለፍኩ በመሆኑ ስሜቱ ይሰማኛል፡፡ ለዚህም ነው ሰዎች ገብተው ብዙም ሳይቆዩ ሲሰናበቱ በቆዩበት ቤት ለረዥም ዓመት መሥራት የቻልኩት ስሜቱን ስለማውቀውና ስለገባኝ ነው፡፡ እዚህ ላይ የግንዛቤ ችግር ያለ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው በአንድ ሥራ ላይ በቆየበት መጠን ሥራውን ጤናማ በሆነ መንገድ ማስኬድ እንዲችል ከልምድ ጀምሮ ያዳብራል፡፡ ጤነኛ የሆነ ሰው አንድ ሰው በአንድ ሙያን በሚጠይቅ ቤት በቆየ  መጠን ምርታማና ውጤትማ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ 
• በፌዴሬሽኑ ከላይ ከቦርዱ ጀምሮ ችግሩ ያለባቸው ሰዎች ይኖሩ ይሆን?
 በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቀደም ሲል ጀምሮ በቦርዱ አልያም በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ላይ ችግሩ ብዙም አይደለም፡፡ ችግሩ ያለው ታችኛው አካል ነው፡፡ ቦርዱ በአጠቃላይ የአትሌቲክሱን ሕግጋት በቅርበት የሚያውቅና የሚረዳ ቢሆን ለስፖርቱ ውጤታማነት የተሻለ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡ በዋናነት ግን ከጽሕፈት ቤቱ ጀምሮ ከስር የሚደራጀው አካል ግን በተቻለ መጠን አትሌቲክሱን የሚያውቁ መሆን ይኖርበታል፡፡ 
• እርስዎ በሚሉት ደረጃ ችግሩ አለ እያሉን ነውን?
 አለ የለም ወደሚለው ድምዳሜ ከመድረሻችሁ በፊት፣ በፌዴሬሽኑ የተለያዩ ክፍሎች ማለትም የፋይናንስ፣ የአስተዳደር ቴክኒክና የመሳሰሉት አሉ፡፡ በእነዚህ ሁሉ መኖር የሚገባቸው ሰዎች በሙሉ የአትሌቲክሱ ሙያ እንዲኖራቸው ላይጠበቅባቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን ደግሞ እኔ የምመራውን ክፍል ጨምሮ ከስፖርቱ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ለድርድር መቅረብ የለበትም፡፡ ሙያተኞችና አቅም ያላቸው ሊሆን ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአብዛኛው ከተግባር ጋር የተገናኘ ሥራ የሚሠራበት ተቋም ነው፡፡ ከዓለም አቀፍ ግንኙነት ጭምር ማለት ነው፡፡ 
• ፌዴሬሽኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭነት ያለው ሙያተኛ አለው፤ የለውም የሚሉ ክርክሮች ይደመጣሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
 እዚያ ደረጃ ላይ የደረሱ ሙያተኞች አሉን ማለት የምንችልበት ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡ በአጠቃላይ የለንም ብንል ነው የሚቀረው፡፡ በእርግጥ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በውድድርና ሥልጠና ረገድ ጥሩ ነገር እየታየ ነው፡፡ በስፖርት ልማት ረገድ ግን ይቀረናል፡፡ ለምሳሌ በዚህ መልኩ በጎረቤት ኬንያ ያለውን ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ በኬንያ በርካታ አካዴሚዎች አሉ፡፡ ወደ እኛ ስንመጣ በመንግሥት ተገንብቶ በቅርቡ በይፋ ሥራውን የጀመረው የኢትዮጵያ ወጣቶች አካዴሚ ካልሆነ በስተቀር በግልና በማናጀሮች ደረጃ የለም፡፡ መኖር እንዳለበት የግድ ማመን ይኖርብናል፡፡ ይህንን አጠናክሮ መሥራት የሚችል እውቀት ያለው ማኔጅመንት ያስፈልጋል፡፡ ቀደም ሲል ከተሠሩ ሥራዎች ከጠንካራው ትምህርት በመውሰድ፣ ደካማውን ደግሞ በማረም ወደተሻለ የአሠራር ሥርዓት ከመሄድ ይልቅ የድክመት ቀዳዳ የሚሹ ሙያተኞች ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዝናል፡፡ በዚህ ደረጃ በራሴ ላይ የደረሰ ግን ደግሞ ወደ ዝርዝሩ አልገባም፤ አሁን በሥራ ላይ ያለው የፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወደ አመራር በመጣበት ወቅት ልገልጸው የማልችለው አስቸጋሪ ፈተና ገጥሞኛል፡፡ ፈተናው በተወሰኑ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በሳል አመራር ባይከሽፍ ኖሮ ሁኔታው ለስፖርቱም የማይበጅ ነበር፡፡ 
• አቀነባባሪውና የችግሩ መንስኤ ይታወቃል?
 እከሌና እከሌ መባባሉ አይጠቅምም፡፡ የሚጠቅመው የአመራሩ በሳልና ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ ቀጥሎ ለተቋሙም ሆነ ለስፖርቱ የሚጠቅሙ አቅሙና ችሎታው ላላቸው ሰዎች ሥራውን ቆጥሮ በመስጠት እንዲቀጥል ነው፡፡ ቤቱ የብሔር ብሔረሰቦች ቤት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው፡፡ አቅምና ችሎታ ያላቸው ሙያተኞችና አመራሮች የሚሠሩበት ቤት ነው፡፡ አቅሙ የሌለው አቅሙ በሚፈቅደው ቦታ ሊመደብና ሊሠራ ይገባዋል፡፡ እዚህ ላይ በፌዴሬሽኑ ቦርድ ላይ ከአቅም ጀምሮ ምንም ዓይነት ችግር የለም፡፡ እታች ግን ልንፈተሽ ይገባል፡፡ ከጽሕፈት ቤቱ ጀምሮ በየደረጃው የምንገኝ ክፍሎች በሙሉ በተገቢው መንገድ መገምገም ይኖርብናል፡፡ የምናገረው በውስጣችን ስላለው ችግር ነው፡፡ ይህ በሆነበት ደግሞ ስፖርቱን በምንፈልገው መጠን ልናሳድገውና ልንታደገው አንችልም፡፡ ማነው እየሠራ ያለው? ማነው እያወራ ያለው? ተለይቶ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ቦርዱ በጅምላ እየተሄደ ያለውን መለየት ይኖርበታል፡፡ ስፖርቱን ለማሳደግ 24 ሰዓት ሙሉ ቤተሰቦቻቸውን ሳያዩ በሥራ የሚጠመዱ አሉ፡፡ በዚያው መጠን ደግሞ ከሥራ ይልቅ ለወሬና ለአሉባልታ ጊዜያቸውን የሚያጠፉ አሉ፡፡ ይኼ ሊሆን አይችልም፡፡ ወቅቱ በምላስ የሚኖርበት ሳይሆን፣ ሠርቶ የሚኖርበት ሊሆን ይገባል፡፡ ከእንግዲህ አትሌትን ከአትሌት፣ ሥራ አስፈጻሚን ከሥራ አስፈጻሚ፣ ሙያተኛን ከሙያተኛ የሚያለያይና የሚያላትም አካሄድ መገታት ይኖርበታል፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ራሱንና ማንነቱን የሚያረጋግጥበት ውሳኔ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ለማንም ሲባል አይደለም፣ ለአገሪቱ አትሌቲክስ ሲባል ነው ማስተካከል ያለበት፡፡ ጣልቃ ገብነትም ከአንዳንድ አካባቢ ይስተዋላል፡፡ ራሱን መፈተሽ ያልቻለ ተቋም ማለትም ከዓለም ሻምፒዮና አጠቃላይ አሠራርና ከሽልማት አሰጣጥ በመነሳት ለስፖርቱ የማይበጅ ጣልቃ ገብነት እየተስተዋለ ነው፡፡ 
• ከአትሌቶች ኩብለላ ጋር ተያይዞ በፌዴሬሽኑ ላይ ወቀሳዎች ይቀርባሉ፡፡
 አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ካለ ወሳኙና ወሳኙ አካል ራሱ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ ሊወቀስና ሊተች የሚገባው በአሠራር ችግር አትሌቶች ዜግነታቸውን ለመቀየር ተገደው ከሆነ ተቋሙ መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ሌላው ሊታይ የሚገባው በአገሪቱ ብዙ አትሌቶች አሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ በዓለም ሻምፒዮናም ሆነ በኦሊምፒክ ማሳተፍ የሚችለው በእያንዳንዱ ውድድር ሦስት፣ ሦስት አትሌቶችን ነው፡፡ እነዚያን የሚመርጠው ደግሞ አትሌቶቹ ባላቸው ወቅታዊ ብቃትና ሰዓት ነው፡፡ በዚያን ሰዓት የመመረጥ ዕድል ከሌላቸው አንዳንዶቹ ዜግነት በመለወጥ የመወዳደር ዕድል ይኖረናል ብለው ስለሚያምኑ ዜግነት መቀየርን የሚመርጡ ይኖራሉ፡፡ ሌላውና ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ጥቅም ነው፡፡ በእርግጥ የግል ጥቅምን ብቻ በመመልከት አትሌቶችን የሚያስኮበልሉ እንዳሉ አይካድም፡፡ ለዚያ ደግሞ ማስረጃ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ መፍትሔው ውድድር በማብዛት ዕድሎችን መፍጠር፣ በአገሪቱ ሰፋፊ የስፖርት ልማት እንቅስቃሴ በመፍጠር የአትሌቶቹን አመለካከት መለወጥ ሲቻል ይመስለኛል፡፡ 
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/sport/itemlist/user/58-%E1%89%A0%E1%8C%8B%E1%8B%9C%E1%8C%A3%E1%8B%8D%E1%88%AA%E1%8D%96%E1%88%AD%E1%89%B0%E1%88%AD

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር