«የልፋታችንን ዋጋ አላገኘንም» - ቡና አምራች አርሶ አደሮች « ቡናን በጥራትና በብዛት ማምረት ግድ ነው» - የሲዳማ ዞን ግብይትና ኅብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ


አርሶ አደሮቹ እንደሚናገሩት ቀደም ሲል አንድ ኪሎ እሸት ቡና
እስከ 13 ብር ድረስ ሸጠው ነበር፤ አሁን ግን ተመሳሳይ መጠን
ያለውን ቡና በአምስት ብር ብቻ ለመሸጥ ተገድደዋል፤
በሲዳማ ዞን ዳሌ ወረዳ የአዋዳ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪው አርሶ አደር ተፋዬ ወቴ ከቡና ሌላ በማሳቸው እንስትም በቆሎም ያመርታሉ። ይሁንና ሰፋ ያለው መሬት በቡና የተሸፈነ ነው። ከዚህ መሬት በየዓመቱ የሚያገኙት የገንዘብ መጠን እንደ ቡና ገበያ ዋጋው መለያየቱን ይናገራሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት ፤ቀደም ባሉት ጊዜያት የቡና ምርታማነት ከፍ ያለ ቢሆንም በመሀል ደግሞ መቀነስ ታይቶበታል። ነገር ግን በአካባቢው ያሉ የግብርና ባለሙያዎች የቡናን ችግኝም ሆነ ዛፍ እንዴት መያዝ እንደሚገባ በሰጡት ትምህርት አሁን ላይ ለውጥ ይታያል። ምርቱ ቢኖርም የገበያ ሁኔታው አሳሳቢ ሆኗል።
በተለይ በተጠናቀቀውና በተያዘው ዓመት የቡና ዋጋ ከሚጠበቀው በታች ዝቅ ማለቱን የሚያመለክቱት አርሶ አደር ተስፋዬ ዘንድሮ አንድ ኪሎ እሸት ቡና በአምስት ብር ለመሸጥ መገደዳቸው የልፋታቸውን ዋጋ እንደሚያሳጣቸው ይገልፃሉ። ዋጋው ከፍና ዝቅ የማለቱ ጉዳይም እንዳሳሰባቸው ነው የሚጠቅሱት።
«እኛ የምንፈልገው የተጋነነ ትርፍ አይደለም። ከሁለት ዓመት በፊት የነበረው የቡና መሸጫ ዋጋ ከአምናና ከዘንድሮው ይሻል ነበር። ቢያንስ አንዱን ኪሎ እሸት ቡና እስከ 13 ብር ድረስ ሸጠናል። ነገር ግን ትርፍ አጋብሰናል ማለት ሳይሆን ለድካማችን የተሻለ ዋጋ ነበር የሚያስብል ነው። ስለዚህም የክልሉና የዞኑ ቡና ግብይት በዚህ ጉዳይ ላይ ተነጋግረው የልፋታችንን ዋጋ የምናገኝበትን መፍትሄ ቢያመቻቹ መልካም ነው» ይላሉ አርሶ አደር ተስፋዬ።
በአሁኑ ወቅት አንድ ኩንታል ጤፍ በአካባቢው በ1300 ብር እየተገዛ ትልቅ ዋጋ ተከፍሎበት እየተመረተ ያለው ቡና በኪሎ አምስትና ስድስት ብር መሸጡ ያስቆጫቸዋል። ይሁንና ያመረቱትን በቀላሉ ምንም የትራንስፖርት ወጪ ሳያወጡ በቅርብ ላለው ጎይዳ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር ማስረከብ መቻላቸው አንዱ መልካም ነገር እንደሆነ ይገልጻሉ። እርሳቸውም የማህበሩ አባል ናቸው። ማህበሩ የቡና መፈልፈያ ያለው ሲሆን የገበያ ሰንሰለቱም ከበፊቱ የተሻለ ሆኖ እንዳገኙት ነው ያመለከቱት።
አርሶ አደር ተናኘወርቅ ገለታ የዚያው የአዋዳ ቀበሌ ነዋሪና የማህበሩም አባል ናቸው። ልክ እንደ አርሶ አደር ተስፋዬ ሁሉ እርሳቸውም በአንድ ሄክታር ተኩል መሬት ላይ ቡና በስፋት ያመርታሉ። ይሁንና ጊዜያቸውን ሰውተው በቡና ምርቱ ውጤታማ ለመሆን መድከማቸውን ሊክስ የሚችል ዋጋ እያገኙ አይደለም።
«በተለይም ዘንድሮ የአንድ ኪሎ እሸት ቡና ዋጋ ከድንች ዋጋ በታች መሆኑ አሳስቦኛል» የሚሉት አርሶ አደሯ፤ ለዚህ መፍትሄ እንዲፈለግለት ያመለክታሉ። በአንድ ነገር ግን ደስተኛ ናቸው። ምርታቸውን ወደ ማህበራቸው ወስደው ስለሚያስረክቡ የቡና ዋጋ ቢቀንስም ለመሸጥ ችግር እንደሌለባቸው ነው የተናገሩት።
የዳሌ ወረዳ ግብይትና ኅብረት ሥራ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጥላሁን እንደሚናገሩት፤ በወረዳው ስምንት መሰረታዊ የኅብረት ሥራ ማህበራት አሉ። በእነዚህም ውስጥ 838 ሴቶች እና20ሺ 892 ወንዶች አባላት ይገኛሉ። ካፒታላቸው ደግሞ 21ሚሊዮን 730ሺ ብር ሲሆን 17 የቡና መፈልፈያ ጣቢያ እንዲሁም 57 የግብይት ማዕከላት አላቸው። እነዚህ ማዕከላት የግል ባለሀብቶችንም ያካትታሉ።
በቡና ሽያጩ ቀደም ባሉ ጊዜያት ተጠቃሚው አርሶ አደሩ ሳይሆን ደላሎችና ባለሀብቶች እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ይሁንና ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ለውጥ የታየ ቢሆንም አሁን ደግሞ«በዓለም የቡና ገበያ ዋጋ ማሽቆልቆልና በሌሎችም ምክንያት አርሶ አደሩ ቡናውን በዝቅተኛ ዋጋ ለመሸጥ መገደዱ ስጋት እየፈጠረ ነው» ብለዋል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ አርሶ አደሩን መደገፍ የሚያስችል ሥራ ሊሰራ ይገባል። የዓለም የቡና ዋጋ በዚሁ ከቀጠለ አምራቹ አንድ ኪሎ እሸት ቡና በአምስት ብር መሸጡ ውጤታማ አያደርገውምና የተሻለ ገቢ ወደሚያስገኝ ምርት ሊሄድ ይችላል። ይህ ደግሞ ሲታሰብ መንግሥት እንደ አገር ሊያጣው የሚችል ብዙ ነገር አለና ዋጋ የማፈላለግ ሥራ ሊሠራ ይገባል። ልክ የክልሉና የዞኑ ዩኒየኖች የሚያደርጉትን የዋጋ ማፈላለግ ሥራ ሊደግፍ ይችላል።
የሲዳማ ሕዝብና ቡና የጠበቀ ቁርኝት ያላቸው መሆኑ መታሰብ አለበት። ቡና ለሲዳማ ሕዝብ ልብሱ፣ ምግቡ፣ መዝናኛውና ሁሉ ነገሩ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ባይ ናቸው። «አርሶ አደሩ ለቡና ምርቱ ጥራትም በመጨነቅ እየሠራ ሲሆን በብዛትም እንዲሁ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል» ብለዋል። ለዚህም ማሳያው የወረዳው የቡና ምርት ባለፉት ዓመታት 15ሺ ሄክታር ሲሆን አሁን ግን ወደ16ሺ ሄክታር አካባቢ እየደረሰ ነው።
የሲዳማ ዞን ግብይትና ህብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ አቶ ቡርቃ ቡላሾ በበኩላቸው እንዳመለከቱት፤ በዞኑ ባሉ 13 ወረዳዎች ቡና በብዛት ይመረታል። የግብይት ሥርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግም ግብ በማስቀመጥ እንቅስቃሴ ተደርጓል። በተለይ የገበያ ሰንሰለቱን ለማሳጠር ሰፊ ሥራ ተሠርቷል። በሁለት ዓመት ውስጥ በተደረገው ርብርብ ወደ 254 የመጀመሪያ ደረጃ የቡና ግብይት ማዕከላት መፍጠር ተችሏል። ስለዚህም በአሁኑ ወቅት በዞኑ ቡና በግብይት ማዕከላት ብቻ ነው የሚሸጠው።
«በአርሶ አደሮቹ የተነሳው ጥያቄ እውነትነት ቢኖረውም መፍትሄው ግን ቡናን በብዛትና በጥራት ማምረት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል» ይላሉ። እንደሚታወቀው አገሪቷ እየተከተለች ያለው የነፃ ኢኮኖሚ የግብይት ሥርዓት ነው።
ዋናው ቁምነገር የራስን ጥረት አክሎ በሄክታር ስምንት ኩንታል ይመረት የነበረውን በክልሉ ከፋ፣ ሸካና ቤንች ማጂ አካባቢ የታየውን ተሞክሮ በመውሰድ በሄክታር ወደ 20 ኩንታል ለማድረስ መሥራት ነው። ከዚህ ሌላ ደግሞ አርሶ አደሩ በድካሙ ልክ እንዲያገኝ እሴት ጨምሮ በመላኩ ላይ ሰፊ ሥራ መሥራትን ይጠይቃል። በጥራት በኩልም እንዲሁ በማለት ነው የገለጹት።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር