የሲዳማ ዞን ኣስተዳደር ለወጣቶች የስራ እድል ፈጥራለሁ ኣለ

በሲዳማ ዞን ዘንድሮ ከ72 ሺህ የሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል 
ሐዋሳ ህዳር 20/2006 በሲዳማ ዞን በተያዘው ዓመት ከ72 ሺህ የሚበልጡ ስራ አጥ ወጣቶች በገጠር ስራ እድል ፈጠራ እና ልማት ፕሮግራም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የዞኑ ዋና አስተዳደሪ ገለጹ፡፡ የዞኑ የገጠር ስራ እድል ፈጠራና ልማት ጽህፈት ቤት ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂደዋል፡፡ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ አዱላ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ ከግል ኮሌጆችና አስርኛ ክፍል ላጠናቀቁ ዜጎች ሰፊ የስራ እድል ተዘጋጅቷል፡፡ ሃገራዊም ሆነ ክልላዊ የምጣኔ ሃብታችን እድገት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የገጠር ስራ እድል ፈጠራና ልማት እንቅስቃሴ ለማሳካት የሚያስችሉ ጠንካራ ስልቶች ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ በመሆኑ በየደረጃው የሚገኙ የባለድርሻ አካላት ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገሮች ተርታ ለማሰለፍ በመንግስት በኩል ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ልማታዊ እንቅስቃሴዎች አንዱ ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻል ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባዋል ብለዋል፡፡ ለዘርፉ ወቅታዊ ድጋፍና ክትትል ማድረግ በግብርና የሚመራው ክፍለ ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገርና ልማታዊ ባለሃብቶችን ለመፍጠር ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር ስራ አጥነትንና ድህነትን ለመቅረፍና ስራ ፈጣሪ ዜጎችን ለማፍራት ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም መረባረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ከመሰረቱ ለመቅረፍ የአመራርንና የባለሙያውን አመለካከት ከመቀየር አኳያ ከ100 ሺህ ለመበልጡ የዞን፣ የወረዳና ለቀበሌ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ይሰጣል ብለዋል፡፡ በዞኑ ግብርና መምሪያ የገጠር ስራ እድል ፈጠራና ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበበ ታደሰ በበኩላቸው የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ስራ አጥነትን ለመቅረፍ የገጠር ስራ እድል ፈጠራና ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብዋል፡፡ በዞኑ በተያዘው የበጀት ዓመት ከ72 ሺህ የሚበልጡ ወጣቶች በሰብል ልማት፣ በንብ ማነብ፣ ወተት ሃብት ልማት፣ እንስሳት ማድለብ እንዲሁም የገጠር ቀበሌ ተደራሽ መንገድ ግንባታ፣ ጥርብ ድንጋይ ንጣፍ፣ ሸንኮራ ልማት እና በሌሎችም ስራዎች ተደራጅቶ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልፀዋል፡፡ የስራ እድሉ ተጠቃሚ ከሚሆኑት መካከል ከ25 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው በመግለፅ ዘርፉን ለማጠናከር የብድር፣ የገበያ ትስስርና ክትትልን ጨምሮ በርከታ ድጋፎች እንደሚደረጉ አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ባለፈው የበጀት ዓመት በገጠር ስራ እድል ፈጠራና ልማት ፕሮግራም ከ63 ሺህ በላይ ስራ አጥ ወጣቶች በ1ሺህ 234 ማህበራትና በ6ሺህ 153 ቡድኖች በማደራጀትና ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=13988&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር