አምራቹ በቡና ዋጋ መቀነስ እንዳይጎዳ ማድረግ ያስፈልጋል

 ...ይህ በሲዳማ ቡና አምራቾች ላይ የተከሰተው ችግር የቡና ዋጋ በዓለም ገበያ ዋጋ የሚወሰን ከመሆኑ አኳያ የሌሎች ሀገሮች ቡና አምራች አርሶ አደሮችም ችግር ነው። ችግሩ ከቡና ጋር የጠበቀ ግንኙነት ላለውና ቡና ምግቡ፣ ልብሱ፣ መዝናኛው በአጠቃላይ የኑሮው ዋልታና ማገር ለሆነው የኢትዮጵያ ቡና አምራች ምን ያህል አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
የቡና ዋጋ እየቀነሰ መምጣት በአስቸኳይ የሚፈታ ካልሆነ የቡና አምራቾች የልፋታቸውን ዋጋ ወደ ሚያስገኙላቸው ዘርፎች ፊታቸውን እንዲያዞሩ የሚያስገድድ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋል፤ የግብይት ህብረት ሥራ ማህበራትም ይህንኑ ስጋት እያረጋገጡ ናቸው። ሀገሪቱም ከቡና በከፍተኛ ደረጃ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ እንዲቀንስ የሚያደርግም ይሆናል። ችግሩ በቡና ልማቱና ግብይቱ ሰንሰለት የሚሳተፈውን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ኑሮ እንዲናጋ ያደርጋል።

ኢትዮጵያ ለቡና ልማት በሰጠችው ትኩረት በቡና ተክል የተሸፈነው መሬትም ሆነ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል። ቡና ከሚመረትባቸው ክልሎች በተጨማሪ በአማራና በትግራይ ክልሎች ጭምር ቡናን በማምረት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው። ለቡና አምራቾች ወሳኝ ግብዓቶችን በማቅረብ ጭምር ድጋፍ እየተደረገ ነው።
አርሶ አደሩ ምርቱን በአቅራቢያው ለሚገኙ የራሱ የህብረት ሥራ ማህበራት እንዲያቀርብ የሚያስችል ሁኔታ በመፈጠሩም ምርቱ የደላሎችና ህገወጥ ነጋዴዎች ያለአግባብ መጠቀሚያ ከመሆን እየዳነ ነው። በአሁኑ ወቅት የቡና ግብይት የሚካሄድባቸው በርካታ የግብይት ማዕከላት ተቋቁመው እየሰሩ ናቸው። በተለይ አርሶ አደሩ ምርቱን ለህብረት ሥራ ማህበራት ማቅረብ በመቻሉ የቡና ዋጋ በሚወድቅበት ወቅት ምርቱን የሚያደርግበት እንዳያጣ የሚያስችሉት ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። በአብዛኛው በአውሮፓ ገበያ ተወስኖ የቆየው የቡና ግብይትም ወደ እስያ ሀገሮች እንዲገባ በመደረጉ ባለፈው ዓመት ከደቡብ ኮሪያ ብቻ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
2004 በጀት ዓመት169ሺ ቶን የታጠበና ደረቅ ቡና ወደ ውጭ በመላክ 832ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። በ2005በጀት ዓመትም ካለፈው ዓመት በ30ቶን ብልጫ ያለው ቡና ለዓለም ገበያ አቅርባለች። በቡና ዋጋ መቀነስ ሳቢያ ከእዚህ አቅርቦት740ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው ገቢ ያገኘችው።
ምንም እንኳ ሀገሪቷ ወደ ውጭ የምትልከው የቡና ምርትም በየዓመቱ ቢጨምርም በዓለም የተከሰተውን የኢኮኖሚ ቀውስ ተከትሎ የቡና ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መጥቷል። በዚህም ሀገሪቱም ሆነች ቡና አምራቹም ለተጎጂነት መዳረጋቸውን የተጠቀሰው መረጃ ያስገነዝባል ።
የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሲዳማ ዞን አርሶ አደሮችንና የግብይትና ህብረት ሥራ ማህበራትን ዋቢ ያደረገው የትናንቱ ዘገባችን እንደሚያመለክተውም፣ በዓለም የተከሰተውን የኢኮኖሚ ቀውስ ተከትሎ የገዥ ፍላጎት መቀዛቀዝ በመፈጠሩ ሳቢያ የቡና ዋጋ እያሽቆለቆለ መምጣት የቡና አምራቹን በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው ነው። የዞኑ ቡና አምራች አርሶ አደሮች የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ እየሆኑ አይደለም። አርሶ አደሮቹ ከሁለት ዓመት በፊት አንድ ኪሎ እሸት ቡና ቢያንስ እስከ 13 ብር ይሸጡ ከነበረበት ሁኔታ ባለፈውና በተያዘው ዓመታት ዋጋው እያሽቆለቆለ መጥቶ አንድ ኪሎ እሸት ቡና በአምስት ብር ለመሸጥ ተገደዋል።
ይህ በሲዳማ ቡና አምራቾች ላይ የተከሰተው ችግር የቡና ዋጋ በዓለም ገበያ ዋጋ የሚወሰን ከመሆኑ አኳያ የሌሎች ሀገሮች ቡና አምራች አርሶ አደሮችም ችግር ነው። ችግሩ ከቡና ጋር የጠበቀ ግንኙነት ላለውና ቡና ምግቡ፣ ልብሱ፣ መዝናኛው በአጠቃላይ የኑሮው ዋልታና ማገር ለሆነው የኢትዮጵያ ቡና አምራች ምን ያህል አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
የቡና ዋጋ እየቀነሰ መምጣት በአስቸኳይ የሚፈታ ካልሆነ የቡና አምራቾች የልፋታቸውን ዋጋ ወደ ሚያስገኙላቸው ዘርፎች ፊታቸውን እንዲያዞሩ የሚያስገድድ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋል፤ የግብይት ህብረት ሥራ ማህበራትም ይህንኑ ስጋት እያረጋገጡ ናቸው። ሀገሪቱም ከቡና በከፍተኛ ደረጃ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ እንዲቀንስ የሚያደርግም ይሆናል። ችግሩ በቡና ልማቱና ግብይቱ ሰንሰለት የሚሳተፈውን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ኑሮ እንዲናጋ ያደርጋል።
የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የቡና አምራቹ የልፋቱን እንዲያገኝ ለማድረግ እስከአሁን የተከናወኑ ተግባሮች ውጤታማ ቢሆኑም፣ ልማቱና ግብይቱ አርሶ አደሩንና ሀገሪቷን ተጠቃሚ እንዲያደርግ የሚከናወኑ ሥራዎች ቀጣይነት እንደሚገባ ይህ በዋጋ ላይ የተከሰተው ችግር ያስገነዝባል። በተለይ በዓለም የቡና ገበያ ላይ ሰፊና ዘላቂነት ያለው ሥራ መስራት እንደሚያስፈልግ የአርሶ አደሮቹ ጥሪ ማረጋገጫ ነው።
አሁን የአርሶ አደሩንና የሀገሪቷን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመፍትሔነት የተቀመጡት ሥራዎች አርሶ አደሮች የቡና ምርታቸውን እንዲያሳድጉ፣ ቡናን ለገበያ የሚያቀርቡ አካላት እሴት ጨምረው እንዲያቀርቡ የሚያስችሉ ተግባሮችን በስፋት ማከናወን ነው። የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋትና በምርት ጥራት ላይ መሥራትም ሌሎች ወቅቱ የሚጠይቃቸው ሥራዎች ናቸው።
አርሶ አደሩ በሄክታር የሚያመርተውን ምርት ለማሳደግ የሚያስችሉ ውጤታማ ተሞክሮዎችን ማስፋት ያስፈልጋል። ለዚህም በደቡብ ክልል ከፋ፣ ሸካና ቤንች ማጂ ዞኖች በሄክታር 20ኩንታል እየተገኘ ያለበትን ተሞክሮ በፍጥነት በሁሉም ቡና አምራች አካባቢዎች ማስፋት ጊዜ ሊሰጠው አይገባም።
ለአርሶ አደሩ ምርት በእሲያ ሀገሮች ገበያ ለማፈላለግ እንደተደረገው ውጤታማ ተግባር ያሉ ሥራዎችን በሌሎች የዓለም ክፍሎችም አጠናክሮ ማስቀጠል እንዲሁም የቡናን ጥራት ለማረጋገጥ እየተካሄዱ የሚገኙትን ሥራዎች ማጠናከርም ይገባል።
አጽንኦት ሲሰጠው የቆየው በቡናን ላይ እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በፍጥነት ወደ ተግባር መግባት ያስፈልጋል፤ ይገባልም።
ከእነዚህ ሥራዎች መካከልም ለዘንድሮ የሚደርሱትን ለዘንድሮ፤ የከርሞዎቹንና ቀጣዮቹንም እንዲሁ ለይቶ በማስቀመጥ በመሥራት የቡና አምራቹን ቅስም ሊሰብር የሚችለውን የቡና ዋጋ መቀነስ የሚያካክስ ተግባር ለማከናወን ፈጥኖ መንቀሳቀስ የግድ መሆን ይኖርበታል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር