የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የማስፋፊያ ግንባታዎችን እያካሄደ ነው

ሐዋሳ ጥቅምት 23/2006 የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎችን የቅበላ አቅም ለማሳደግ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የማስፋፊያ ግንባታዎችን እያካሄደ መሆኑን ገለጸ። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮሴፍ ማሞ እንደገለጹት ይርጋለም ፣ ሀዋሳና ወንዶ ገነት በሚገኙ ካምፓሶች የሚካሄዱት የማስፋፊያ ግንባታዎቹ በ2007 የትምህርት ዘመን በመደበኛ ፕሮግራም የሚቀበሏቸው ተማሪዎች ቁጥር 30 ሺህ ለማድረስ ያስችላቸዋል፡፡ ከማስፋፊያ ግንባታዎቹ መካከል የመማሪያ ክፍሎች ፣ቤተ ሙከራዎች ፣የተማሪዎች ማደሪያና ቤተ መጽሀፍት እንዲሁም ለኢንጅነሪንግ ተማሪዎች የተግባር መለማመጃዎች ያሉት የቴክኖሎጂ ተቋም ዋና ዋናዎች መሆናቸውን አስረድተዋል። በተለይ የቴክኖሎጂ ተቋሙ በሁለት ምዕራፍ ተከፋፍሎ የመጀመሪያው ግንባታ የመማሪያ ክፍሎች ፣አዳራሾች ቤተሙከራዎች ፣ቢሮዎች የመመገቢያ አዳራሾችና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን አካቶ መያዙን ዶክተር ዮሴፍ አመልክተዋል። ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የተማሪዎች ማደሪያ ፣ የመመገቢያ አደራሽ ፣የቴክኖሎጂ ቤተ ሙከራዎች እንደሚገኙበት ጠቁመው ሁሉም ግንባታዎች አካል ጉዳተኞችን ግምት ውስጥ ያስገባና ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል። መንግስት በመደበው ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚገነቡት እነዚህ ማስፋፊያዎች ዘንድሮ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማዘጋጀት ስራቸው በመፋጠን ላይ እንደሚገኝ ዶ/ር ዮሴፍ አስታውቀዋል። የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተያዘው ዓመት 5400 አዲስ መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ በተለያዩ መስኮች ማስተማር እንደሚጀምርና በአሁኑ ወቅት ከ30ሺህ በላይ ተማሪዎች በመደበኛ፣ በማታና በተከታተይ የትምህርት ፕሮግራሞች እያሰለጠነ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=13163&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር