የስደት ውርደት በዛ! ሥራም ይፈጠር ኢትዮጵያዊነትም ይከበር

በሳዑዲ ዓረቢያ በኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላይ እየተፈጸመ ያለውና እየተስተጋባ ያለው አሰቃቂ ግድያና ድብደባ ይዘገንናል፣ ይሰቀጥጣል፣ ያቅለሸልሻል፡፡ አረመኔያዊ ነው፡፡ 
የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት የራሱን ሕግ ማስከበር እንዳለበት እናምናለን፡፡ በሕገወጥ መንገድ አገሪቱ ውስጥ የገቡትን ሰዎች ወደ አገራቸው ቢመልስ ወይም ቢያባርር ተቃውሞ የለንም፡፡ ጥያቄያችንና ተቃውሞአችን ግን በሕገወጥ መንገድ የገቡትን ኢትዮጵያውያን ለምን መለስካቸው?ለምን አባረርካቸው?የሚል አይደለም፡፡ ሕገወጦችን መቆጣጠርና ሕግን ማስከበር የማንም አገር መብትና ኃላፊነት ነውና፡፡
ግን! ነገር ግን! በሕገወጥ መንገድ የገቡትን ኢትዮጵያውያን በሕጋዊ መንገድ ወደ አገራቸው ይመልሳል ወይም ይቀጣል እንጂ፣ ግድያና ማሰቃየት ማካሄድ የለበትም፣ አልነበረበትም፡፡ 
እኛም እንደምንከታተለው የዓለም መገናኛ ብዙኃንም እያስተጋቡት እንዳለው፣ በመጀመሪያ ከኢትዮጵያ የሄዱት የቤት ሠራተኞች እንደ ባርያ እንጂ እንደ ነፃ ሰው አይታዩም፡፡ እንደ እንስሳና እንደ ባርያ ነው የሚቆጠሩት፡፡ በሕጋዊ መንገድ የገቡትም ጭምር፡፡ 
ከዚያም አልፎ በየቤቱ ፖሊስ እየገባ ሕገወጥ ናችሁ እያለ ሲገድልና አስከሬን በየጎዳናው ሲወረውር በግልጽ በሚስቀጥጥ ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ የሳዑዲ መንግሥት የራሱን ሕግ የማስከበር መብት እንዳለው ሁሉ፣ ማክበር ያለበትና የሚገደድባቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎች እንዳሉም ሊገነዘብና ሊተገብር ይገባዋል፡፡ 
በተለይም በዘፈቀደ አንዳንድ የሳዑዲ ዓረቢያ ተወላጆች የሚፈጽሙት ግፍ አልበቃ ብሎ፣ የመንግሥት የፀጥታና የፖሊስ ኃይል ቤት ለቤት እየገባ ግፍና ወንጀል በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ሲፈጽም፣ በማያወላዳ መንገድ ዓለም አቀፍ ሕግን መጣስ ነው፡፡
ሕግ መጣሱና ወንጀል መፈጸሙ አሳዛኝ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በባህልና በታሪክ የማይገናኙዋቸው አውሮፓና አሜሪካ ሄደው እንዲህ ዓይነት ግፍ አልተፈጸመባቸውም፡፡ ለዘመናት በታሪክ፣ በባህል፣ በቋንቋና በሥነ ልቦና ከሚቀራረቡት የሳዑዲ ዓረቢያ ሕዝብ ይህ ዓይነቱ ግፍ ሲደርስባቸው የሚፈጥረው ስሜት ውግዘት ብቻ ሳይሆን ምፀትም ነው፡፡ ሕዝባችን ከሳዑዲ ዓረቢያ ሰዎች ጋር ብቻ ሳይሆኑ ከሌላው ዓለም ሕዝብ ጋር በአገሩም ሆነ በውጭ በፍቅርና በመተሳሰብ መኖር የሚችል ነው፡፡
በሳዑዲ ዓረቢያ እየተፈጠረ ባለው አስደንጋጭ ድርጊት እንደ ኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ብዙ ልንማረውና ልንፈጽመው የሚገባን ነገር አለ፡፡  ከሁሉም በፊት እንደ መንግሥትም እንደ ሕዝብም ይህንን ድርጊት በይፋና በግልጽ ልናወግዘው ይገባል፡፡ አላስፈላጊ ረብሻና ግርግር በመፍጠር ሳይሆን ድርጊቱን በትክክል እንዳወቅነው፣ ሕገወጥና አረመኔያዊ እንደሆነና በጥብቅ እንደምናወግዘው በግልጽ መልዕክታችንን እናስተላልፍ፡፡  
በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎችን ከሳዑዲ ዓረቢያ ለማስወጣትና እየተፈጸመ ያለው ግፍ በአስቸኳይ እንዲቆም ላደረገው እንቅስቃሴ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ላልተወሰነ ጊዜ በቅጥር ሠራተኝነት ስም ወደ ውጭ መሄድ እንዲቆም ማድረጉም ትክክል ነው፡፡ ችግሮች እስኪጠኑና መልክ እስኪይዙ ድረስ፡፡ 
አሁን የተፈጠረውን አሳዛኝ ድርጊት ስናወግዝ ግን እንደ መንግሥትም እንደ ሕዝብም መስመር እንዳናልፍ ልንጠነቀቅበት የሚገባ ጉዳይ አለ፡፡ ተቃውሞው ይህ ግፍ እንዲፈጸም በፈቀደው አካል ላይ መነጣጠር አለበት እንጂ፣ በስሜታዊነት ከዘርና ከሃይማኖት ጋር በተሳሳተ መንገድ አዛምደን ‹‹ዓረቦች›› እንዲህ አደረጉንና ‹‹እስላሞች ገደሉን›› ወደሚል ቅስቀሳ እንዳንሄድ መጠንቀቅ ያሻል፡፡ ችግሩ የዘርና የሃይማኖት ጉዳይ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የእስልምናና የክርስትና አገር ሆና ከሌላው ሃይማኖትና ዘር ጋር በጋራ የምትኖር ታሪካዊ አገር ነች፡፡ አሁንም የውጭ ኢንቨስተሮችን በመሳብ አብራ ማደግ የምትፈልግ ናት፡፡ ግፍ የፈጸመውን አካል እናውግዝ፤ ጥላቻ ወደ ሕዝብ እንዳይሸጋገር እንጠንቀቅ፡፡ 
ከዚህ አልፎ ግን አስቸኳይና ዘላቂ ዕርምጃ እንድንወስድ ይህ አሰቃቂ አጋጣሚ ትምህርት ይሰጠናል፡፡ ኢትዮጵያዊነታችንን የሚያስንቀውንና የሚያዋርደውን ሕገወጥ ስደት እየፈጸምን፣ ኢትዮጵያዊነታችንን የሚያስንቅ ሕገወጥ ግፍ እየተፈጸመብን ነው፡፡ ይህን ለማስወገድና ለማስቀረት በቁርጠኝነት እንነሳ፡፡ ሥራችንና እንቅስቃሴያችን ኢትዮጵያችንን የሚያስከብርና በኢትዮጵያዊነታችን እንድንኮራ የሚያደርግ ይሁን፡፡ ለውርደትና ለግፍ የሚዳርገንን ስደት እናቁም፡፡ 
ይህንን ውርደትና ግፍ ለማስወገድ መደረግ ያለበት ነገር ግልጽና ግልጽ ነው፡፡ ሥራ መፍጠር!! 
ኢትዮጵያ ለራሷ ዜጐች ቀርቶ ለበርካታ የሌሎች አገሮች ዜጎችም ሥራ መፍጠር የምትችል አገር ናት፡፡ የግብርና ሀብታችን ለሚሊዮኖች ሥራ የሚፈጥር ነው፡፡ የቱሪዝም ሀብታችንም እንደዚሁ፡፡ የንግድ እንቅስቃሴያችንም በርካታ የሥራ ዕድሎች አሉት፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለሚሊዮኖች ሥራ ፈጣሪ ነው፡፡ የማዕድን ሀብታችን ከዜጐች ተርፎ ለማንም የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ከጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ ዘርፎች ጀምሮ እስከ ትላልቅ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የማዕድን፣ የንግድ፣ የቱሪዝም፣ ወዘተ ዘርፎች ለበርካታ ወገኖች የሥራ ዕድል ፈጥረው ስደትን የሚያስቀሩና ወደ ‹‹ተረት ተረት›› ሊቀይሩ የሚችሉ ናቸው፡፡ 
እናስ?
እናማ ለተግባራዊነቱ እንንቀሳቀስ፣ እንገስግስ፡፡ የስደት ውርደት በዛ ተንዛዛ! ሥራ እንፍጠር! ኢትዮጵያዊነታችን እናስከብር!! 
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/editorial

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር