የሸበዲኖና የአለታ ወንዶ አርሶ አደሮች የቡና ዋጋ መቀነስ አሳስቧቸዋል፤የአንድ ኪሎ እሽት ቡና ዋጋ ከድንች ዋጋ ጋር መቀራራቡ አርሶ አደሮቹን አሳስቧቸዋል

ቡና ልብሳቸው፣ ምግባቸው፣ ጌጣቸው፣ መዝናኛቸው እንዲሁም መድመቂያቸው እንደሆነ የሲዳማ ዞን አርሶ አደሮች ያለአንዳች ማመንታት ይናገራሉ። ቡና ሸጠው ቤታቸውን ይገነባሉ፣ ቡና ሸጠው ልጆቻቸውን ያስተምራሉ እንዲሁም ቡና ሸጠው ሀብት ንብረት ይቋጥራሉ። ቡና አፍልተው የሩቁንም ሆነ የቅርቡን ወዳጃቸውን እንዲሁም ዘመድ አዝማድን ያስተናግዱበታል።
ታዲያ በዞኑ ካሉት አርሶ አደሮች መካከል ቡና በማሳው አልያም ደግሞ በጓሮው ያልተከለ የለም ለማለት ያስደፍራል። ከማጀታቸውም ቢፈለግ የታጠበ አሊያም ደግሞ እሸት ቡና አይታጣም-አሁን ቡና የሚለቀምበት ወቅት ነውና።
በአገር አቀፍ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥሩ ስም ያለውን ቡና የሚያመርቱት የእዚህ ዞን ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደሮች ቀደም ባሉት ጊዜያት ምንም እንኳ ቡና የማምረቱን ሂደት በራሳቸው የአመራረት ስልት ማምረት ባያቋርጡም የምርቱ ተጠቃሚ አልነበሩም። ይልቁንም ይላሉ የዞኑ አርሶ አደሮች «እኛ በለፋንበትና በደከምንበት ነጋዴውና በመሀል ያለው ደላላ ምርቱ ላይ አያዋጣኝም ያዋጣኛል በሚል ድርድር ኪሳቸውን ሲሞሉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነበር» ይላሉ። ምንም እንኳ በዞኑ ያሉ አንዳንድ መሠረታዊ ማህበራት የተቋቋሙት በ1968ዎቹ ዓመተ ምህረት አካባቢ ቢሆንም አርሶ አደሩ የአሁኑን ያህል በወቅቱ ከማህበራቱ አለመጠቀማቸውንም ሳይገልጹ አላለፉም።
ከቡና ምርታቸውም ሆነ በማኅበር በመደራ ጀታቸው አሁን አሁን ይበልጥ ተጠቃሚ እያደረ ጋቸው መምጣቱን የሚጠቅሱት አርሶ አደሮቹ በተለይ የዓለም የቡና ገበያ የተረጋጋ ነው ተብሎ ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ሲሸጥ የነበረበት ዋጋ ለድካማቸው መልካም የሆነ ምላሽ የሚሰጥ እንደነበር ያመለክታሉ። አምናና አቻምና ግን «በድካማችን ልክ ያለማግኘታ ችንን እንቆቅልሽን ማን ይሆን የሚፈታልን» በሚል ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል።
አቶ ዶጎማ ዶና በሲዳማ ዞን በሸበዲኖ ወረዳ በፉራና አካባቢው የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማህበር አባል ናቸው። ማህበሩን ከተቀላቀሉ ወደ ስምንት ዓመት ይጠጋቸዋል። የቡና ማሳቸው አንድ ሄክታር መሬት ሲሆን፤ በየዓመቱም እንደመሬቱ አሰጣጥ ከ100ኩንታል እስከ 200ኩንታል ቡና ለማህበሩ ያቀርባሉ።
አርሶ አደሩ ከማህበሩ በብዙ እንደተጠቀሙ ይናገራሉ። ቡናቸው ሲደርስ በተቆረጠለት ዋጋ ለማህበሩ ያስረክባሉ። ከማህበሩ ታዲያ ቡናቸውን ሸጠው ገንዘብ ከማግኘት ባለፈም በዓመቱ መጨረሻ የትርፍ ክፍፍል ይደርሳቸዋል። ለአብነትም ሲጠቅሱ የዘንድሮውን የትርፍ ክፍፍል 18ሺ ብር ያህል ማግኘታቸውን ነው የሚያመለክቱት። ማህበሩ ተጠቀመ ማለት መልሶ ራሳቸውን ስለሚጠቅም በአካባቢያቸው ላሉት ነጋዴዎች ቡናቸውን እንደማይሸጡ ነው ያብራሩት።
እንደ እርሳቸው አነጋገር ማህበሩ ትርፋማ በመሆኑ መኪና መግዛት ችሏል። ማንኛውም በቀበሌው ነዋሪ የሆነና የማህበሩ አባል መሆኑ የተረጋገጠ ሰው ቢታመም በቀላሉ ወደ ጤና ተቋም እንዲደርስ ይደረጋል። አያድርገውና እንዳጋጣሚ ሆኖ ሕይወቱ ቢያልፍም አስከሬኑን ለመመለስም በሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከሚጠየቀው ከፍተኛ ገንዘብ ለመዳን ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
«እኔም በኑሮዬ በብዙ ተለውጫለሁ። በባንክ ያለኝ ካፒታል ወደ 60ሺ ብር ያህል ደርሷል። ልጆቼንም በማስተማር ላይ እገኛለሁ። ጥሩ መኖሪያ ቤት ከእነሙሉ ዕቃው አለኝ። አባላት ለማህበሩ ያለን ግንንቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ መሻሻል ታይቶበታል» ይላሉ።
ይሁንና አሁን ላይ ግን አንዳች ስጋት እንደገባ ቸው ነው የሚገልጹት። የቡና ዋጋ ከተጠበቀው በታች ዝቅ ማለቱ ግር አሰኝቷቸዋል። የለፉበትና ያለመሰልቸት የታገሉበትን ቡና እንደ አንዳች የማይረባ ምርት መሸጥ የሞራል ውድቀት ነው። በባለሙያዎች የሚሰጣቸውን ምክርና አገልግሎት ተግባራዊ በማድረግ የቡናው ጥራት ከወትሮ በተለየ ሁኔታ በጠበቁበት በእዚህ ወቅት ደግሞ ይበልጥ ከምርቱ ተጠቃሚ መሆን ሲገባቸው የምርቱ ዋጋ ማሽቆልቆል ስጋት ፈጥሮብናል ሲሉ ይናገራሉ።
በእዚሁ በሸበዲኖ ወረዳ ፉራ ቀበሌ ነዋሪና የማህበሩ አባል የሆኑት አርሶ አደር ደቀማ ደበሳ የሁለት ሄክታር መሬት ቡና ባለቤት ሲሆኑ፤ ከቡና ሌላ እንሰት፣ በቆሎ፣ ሸንኮራና ሙዝ ያመርታሉ። የፉራ አገልግሎት የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማህበር መስራች ከሆኑት መካከል አንዱ ናቸው።
እርሳቸውም ልክ እንደ አርሶ አደር ዶጎማ ሁሉ ማህበራቸው በርካታ አገልግሎት እየሰጠ ስለመሆኑ ይናገራሉ። ማህበሩ በደርግ ሥርዓት ሲቋቋም በግዴታ እንደነበር የሚያስታውሱት አርሶ አደሩ፤ዛሬ ግን በርካታ ጥቅም እናገኝበታል ነው የሚሉት። በተለይም የእህል ወፍጮ አገልግሎትን ጨምሮ የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማህበርም በመቋቋሙ ያልተገባ ትርፍ ከሚያጋብሱ ነጋዴዎች መዳን መቻላቸውን ያመለክታሉ።
«ዘንድሮ ከትርፍ ክፍፍሉ ወደ ሰባት ሺ አካባቢ አግኝቻለሁ። በማህበሩ ይበልጥ ለመጠቀም ደግሞ እኛ አርሶ አደሮች ቡናችንን ለሌላ ለማንም አናስረክብም። በአካባቢው ያለው ባለሀብት ቡናችንን በጣም ትንሽ በሆኑ የገንዘብ ልዩነት እንድናስረክብ ቢፈልጉም ያንን አናደርገውም» ይላሉ። ያም ሆኖ ግን አንዳንድ የማህበሩ ጥቅም ብዙም ያልገባቸው ጥቂት አባላት የ25 እና የ50ሳንቲም ልዩነትን በማየት ለባለሀብቱ እንደሚያስረክቡ ይጠቅሳሉ፤ ይህ እንዳሆን ግን የማህበሩን ጥቅም ለአባላቱ እየገለጹ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
ነገር ግን ይላሉ አርሶ አደር ደቀማ የቡና ዋጋ አሳሳቢ መሆኑን ለማመልከት «ቡናችን ጥራቱን ሳያጓድል እየተመረተ የዋጋው ዝቅ ማለት ግራ የሚያገባ ነው። በእርግጥ የቡናችንን ዋጋ የሚወስነው የዓለም የቡና ዋጋ መሆኑን በቂ መረጃ አለን። ይሁን እንጂ ይህንን ለማስወገድ መፍትሔ የለም ወይ የሚል ጥያቄ በውስጤ ይመላለሳል» ሲሉ ነው ምላሽ የሚሻ ጥያቄያቸውን የሚያነሱት።
በእዚሁ ሲዳማ ዞን የአለታ ወንዶ ወረዳ የሆሞቾ ጫዋ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ፍቅሬ ሸለሞ የሆሞቾ ዋኤኖ አገልግሎት ኅብረት ሥራ ማህበር አባል ናቸው። ምንም እንኳ በቡና ምርት ኑሯቸውን በተሻለ ሁኔታ መምራት ቢችሉም የልፋታቸውን ዋጋ አለማግኘታ ቸውን ግን ከመናገር አልተቆጠቡም። እንዲያውም ቡና ከአርሶ አደሩ በርካሽ ዋጋ እንደሚገዛና ወደ ማዕከላዊ ገበያ ሲቀርብ ደግሞ በውድ እንደሚሸጥ ማወቃቸውን ያመለክታሉ።
እንደ እርሳቸው አነጋገር ከአርሶ አደሩ የሚገዛበት ዋጋና በዓለም ለሽያጭ የሚቀርብበት ዋጋ ተቀራራቢ ይሁን ባይባልም መመጣጠን መቻል አለባቸው። የቡና ዋጋ አንዴ ዝቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከፍ እንደሚል ግንዛቤ ያላቸው ሲሆን፤ በእዚህ መሀል ግን መንግሥት የራሱን አማራጭ ሊወስድ ይገባል ሲሉ ነው የተናገሩት። «እኛ አርሶ አደሮች የደከምንበትን የልፋታችንን ዋጋ በአግባቡ ልናገኝ የተገባ ነው» ይላሉ።
አርሶ አደር በእነርሱ በኩል ጥራት ያለው ቡና በስፋት ለማቅረብ ቁርጠኞች መሆናቸውን ይናገራሉ። በባለሙያዎች የተሰጣቸውም ሥልጠና መኖሩን ገልጸው፤ የመሥራት ፍላጎታቸውም ከፍ ያለ መሆኑን ነው ያብራሩት። መንግሥት ደግሞ እነርሱ የሚጠበቅ ባቸውን በቁርጠኝነት ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን ተከትሎ ለቡና ዋጋ መውደቅ ምክንያት ናቸው የተባሉት ላይ መፍትሔ ለማምጣት መንቀሳቀስ አለበት ሲሉ ያሳስባሉ።
እሸት ቡና በአሁኑ ወቅት ለአንድ ኪሎ እስከ አምስት ብር ነው እንዲሸጥ የሚደረገው።ይህ ደግሞ ድካምን ገደል ይከታል የሚል እምነት አለኝ ይላሉ።ይህ ዋጋ በክልላችንም ሆነ በዞናችን ደረጃ መሻሻል የሚቻልበት መፍትሔ ቢገኝለት መልካም ነው።አንድ አርሶ አደር የድካሙን ዋጋ ያገኛል ተብሎ የሚታሰበው ቢያንስ የአንድ ኪሎ እሸት ቡና ዋጋ ከ10 ብር መውረድ አይገባውም ባይ ናቸው።
አቶ ለገሰ ላሚሶ የእዚሁ የአለታ ወንዶ ወረዳ የኦሞቾ ዋኤኖ አገልግሎት ኅብረት ሥራ ማህበር ሊቀመንበር ናቸው። ማህበሩ የተመሠረተው በ1968 .እንደሆነ ጠቅሰው፤ የአባላት ብዛትም 3955 መሆናቸውን ተናግረዋል። ማህበሩ አራት ቀበሌዎችን የያዘ ሲሆን፤ ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጋ ካፒታልም አለው።
ማህበሩ ለቀበሌዎቹ የበኩሉን አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛል።ለአብነትም ለትምህርት ቤት ግንባታ ለመንገድ ሥራ እና እንዲሁም ለሌሎች አገልግሎቶች ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው ያመለከቱት። ሦስት መኪና ያለው ሲሆን፤ ሕዝቡ የሚገለገልበት ወፍጮ ቤትም እንደሠራ ተናግረዋል።
አቶ ለገሰ በዞን ደረጃ ያለው ዩኒየን ብዙ እገዛ እያደረገላቸው እንደሆነ ይጠቁማሉ። በተለይ ገበያ ከማፈላለግ ጋር ተያይዞ እያደረገ ያለው አገልግሎት ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል። በአሁኑ ሰዓትም ቡናውን ወደ መዳረሻ አገራት በጥሬው ከመላክ እሴት ወደ መጨመሩ ለመሸጋገር በመንቀሳቀስ ላይ በመሆኑ ይህም ማህበራቱን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
ይሁንና ይላሉ ሊቀመንበሩ አንድ ስጋት ላይ የጣላቸው ጉዳይ እንዳለ በማመልከት።ይኸውም የቡና ዋጋ መውረድ ግራ እንዳጋባን ነው በማለት። በ2003 .ም አንድ ኪሎ ግራም እሸት ቡና በ15 ብር ይገዛ ነበርና ማህበሩም ሆነ ቡና አምራች አርሶ አደሩ ተጠቃሚ ነበር ይላሉ። ይህ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሎ አምና በስምንትና ዘጠኝ ብር ሲሸጥና ሲገዛ መክረሙን ያመለክታሉ። ዘንድሮ ይባስ ብሎ ከድንችም ዋጋ ባነሰ አንዱን ኪሎ እሸት ቡና በዞኑ ውስጥ በአምስት ብር የመገበያያ ዋጋ ሆኖ መቆረጡ በጣም አሳሳቢ ሆኗል ነው ያሉት።
በቡና ጥራት ምንም አይነት ችግር ሳይኖርብን እንዴት ነው በእዚህ ዋጋ የምንሸጠው የሚል አመለካከት ነው በአምራቹም ሆነ በማህበሩ እየተነሳ ያለው አስተያየት፤ገበያውን በተመለከተ ሕዝቡስ እስከ መቼ ያለቅሳል ሲሉም ይጠይቃሉ።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር