ተግባር! ተግባር! አሁንም ተግባር!

በተጠናቀቀው ሳምንት የአፍሪካ መገናኛ ብዙኃን ባለቤቶች፣ መሪዎችና ጋዜጠኞች በመዲናችን በአዲስ አበባ ባካሄዱት ስብሰባ የአፍሪካ ሚዲያ ያለፉት የሃምሳ ዓመታት ጉዞ ምን ይመስላል? ቀጣዩስ መሆን አለበት? በሚል አጀንዳ ላይ ተወያይተዋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ አትሂዱ፣ ይህንን ስብሰባ በኢትዮጵያ አታካሂዱ የሚለው የተለመደው የፅንፈኛ ዳያስፖራ ፖለቲከኞች ተቃውሞ በበረታበት አፍሪካውያን የለም ወደ ኢትዮጵያማ እንሄዳለን፣ በመወያየት እንጂ በማኩረፍና በጥላቻ አናምንም ማለታቸውና መምጣታቸው ለኢትዮጵያም፣ ለአፍሪካም፣ ለሚዲያውም ትክክለኛ ውሳኔ ነበር፡፡ ውጤታማም ነበር፡፡
በዚህ ስብሰባ ላይ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ተግባር በኢትዮጵያ በኩል ተከናውኗል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በስብሰባው የመክፈቻ ንግግራቸው መንግሥት የኢትዮጵያን ሚዲያ ለማሻሻልና ለመለወጥ ዝግጁ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ የለውጥ ዕርምጃ በቅርቡ እንደሚጀምር አብስረዋል፡፡ ተሳታፊዎችም በተስፋና በደስታ ተቀብለውታል፡፡ 
የሕዝብ ተሳትፎ እውን ሊሆን የሚችለው መረጃ ያለው ኅብረተሰብ ሲኖር እንደሆነ ገልጸው፣ መረጃ ያለው ኅብረተሰብ እውን የሚሆነውም ጠንካራ ሚዲያ ሲኖር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡ 
አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ሚዲያ ችግር በመገምገምና የመፍትሔ ሐሳብ በማስቀመጥ የሚወሰደው የለውጥ ዕርምጃ በዘፈቀደና በግምት የሚደረግ ሳይሆን፣ ከሚዲያ ባለሙያዎች፣ ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችና ከሚመለከታቸው አካላት በሚገኝ ገንቢ ሐሳብ መሠረት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው፣ ለውጡ በቅርቡ  በተግባር እንደሚጀመር ቃል ገብተዋል፡፡ 
የተገባውን ቃል በተግባር ለማየት በጉጉት እንጠብቃለን፡፡
በነገራችን ላይ ይህ የተገባው ቃል ማጠናከሪያና ተጨማሪ ማስተማመኛ እንጂ፣ ኢትዮጵያ ባፀደቀችው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት ሙሉ በሙሉ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ እንደሚከበር ቃል ተገብቷል፣ ሰፍሯል፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 የዓለም የፕሬስ ነፃነት አዋጅ አንቀጽ 19 ቃል በቃል ተቀብሎ ያሰፈረና ያፀደቀ ነው፡፡
በመሆኑም አሁን ጠቅላይ ሚኒስትራችን የገቡት ቃል ሕገ መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ ተግባር ላይ እናውላለን የሚል አስተማማኝ ንስሐና ውል አድርገን እንወስደዋለን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃንን እንለውጣለንና እናሻሽላለን ሲሉ እንደ መነሻ አድርገው የወሰዱት፣ በኢትዮጵያ ለውጥ እናመጣለን ሲባል ከኢኮኖሚው ልማት ጎን ለጎን የዴሞክራሲው ልማት እውን ሲሆን ነው በማለት ነው፡፡ ለዚህም የሕዝብ ተሳትፎ ሲረጋገጥ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡ እውነት ነው ለኢኮኖሚውም፣ ለፍትሑም፣ ለሰላሙም፣ ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶችም ወሳኝ የሆነው የሕዝብ ተሳትፎ እውን የሚሆነው፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና መረጃ የማግኘት መብት በተግባር ሲከበር ነው፡፡ 
ሌላው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት ቁም ነገር አለ፡፡ ‘አሁንም የሕዝቡን አስተያየት፣ አሁንም የባለሙያን አስተያየት፣ አሁንም የሚመለከታቸውን የሚዲያ አካላት የማሻሻያ ሐሳብ ለማዳመጥ ዝግጁ ነን፤’ ብለዋል፡፡ ‘ምከሩን፣ ውቀሱን፣ ሐሳብ ስጡን፣ እናሻሽላለን፤' ብለዋል፡፡ ‘በዚህም ተሳትፎአችሁን አሳድጉ እኛም በውይይትና በመቀራረብ ስለምናምን ለመቀራረብ እንመን፤' ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በስብሰባው የምክክር መድረክ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሐሳብ በማጠናከር በአስቸኳይ ለውጥ እንደሚመጣ ቃል ገብተዋል፡፡
እነዚህ ቃላት በአዳራሹ የተስተጋቡና በአፍሪካ የሚዲያ ማኅበረሰብ አባላት የተመዘገቡ ናቸው፡፡ የተገባው ቃል ተግባር ላይ ዋለ ወይ የሚል ጥያቄም በየጊዜው እንደሚነሳ ልብ ሊባል ይገባዋል፡፡ ዛሬ ተነግሮና ተወስቶ ነገ የሚረሳ ጉዳይ አይሆንምና ለተግባራዊነቱ አደራ እንላለን፡፡ 
ሁላችንም በመወያየትና ሐሳብ ለሐሳብ በመለዋወጥ እንመን፡፡ መንግሥትም በመገናኛ ብዙኃን ዘንድ መደረግ አለበት የሚለውን በግልጽ ያቅርብ፡፡ መገናኛ ብዙኃንም መንግሥት ማድረግና መለወጥ ያለበት ይህና ይህ ነው በማለት በግልጽ ያቅርቡ፡፡ ልዩነታችን እንዳለ ሁሉ በጋራ በምንስማማባቸው ጉዳዮች በጋራ እንራመድ እንላለን፡፡
‘አትሂዱ፣ አትወያዩ፣ አትቀራረቡ' የሚለው አመለካከት የኋላ ቀርና የደካማ ፖለቲከኞች መገለጫና መታወቂያ ነው፡፡ ችግራችንን በውይይት እንፈታለን ብለው እነአሜሪካ ከታሊባንና ከኢራን ጋር በሚወያዩበት ጊዜ ‘ኢትዮጵያ አትሂዱ፣ ከመንግሥት ጋር አትነጋገሩ' የሚል አቋም ደካማና የትንሽነት መገለጫ ነው፡፡ 
አፍሪካውያን ኢትዮጵያ እንሂድ በማለት የፅንፈኛ ተቃዋሚዎችን አላስፈላጊ ጫናና የስድብ ወርጅብኝ ንቀው በመምጣታቸው እናመሰግናለን፡፡ ኢትዮጵያ ላደረገችው መስተንግዶ ብቻ ሳይሆን፣ ሚዲያውን ለመለወጥና ለማሻሻል ለተገባው ቃል ምሥጋና እናቀርባለን፡፡
ግን! ነገር ግን! መሻሻሉን፣ መለወጡን፣ ማዳመጡንና መወያየቱን አደራ! ማረጋገጫው ደግሞ ተግባር! ተግባር! አሁንም ተግባር! ይሁን፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር