የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ሁለተኛ ወጥቶ ተሸላሚ ሆነ


  • ዩኒቨርሲቲው የስራ አጥነትን ችግሮች ለማቃለል መንግስት እያከናወነ ያለውን ተግበር ለማገዝ በሀገረ ሰላምና ዳሌ ወረዳ 60 ስራ አጥ ወገኖችን በንብ ማነብ ቴክኖሎጂ ስልጠና በመስጠትና የንብ ማንቢያ ዘመናዊ ቀፎዎችን በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል
  •  በሲዳማና ጌዴኦ ዞኖች በሚገኙ የማልጋና ቡሌ ወረዳዎች አርሶ አደሩ የተሻሻለ ዝርያ ያለውን የቢራ ገብስ በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆን አዳዳስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ በተጨማሪ የሚመረተው የቢራ ገብስ ገበያ እንዲያገኝ ከአሰላ ብቅል ፋብሪካ ጋር የገበያ ትስስር መፍጠሩ ተገልጸዋል

ሃዋሳ ጥቅምት 22/2006 የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በማሀበረሰብ አቀፍ የምርምር ስራዎችና በሌሎች መስኮች ባከናወነው ተግባርና ባበረከተው አስተዋጽኦ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሁለተኛ ወጥቶ ተሸላሚ ሆነ። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሴፍ ማሞ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ባለፉት አራት ዓመታት ለተማሪዎች ተከታታይ የምዝና ስርዓት በመዘርጋቱ የተማሪዎች ውጤት መሻሻል አሳይቷል፡፡ ቀደም ሲል ዩኒቨርሲቲው በአንድ ሴሚስተር ሁለት ጊዜ ብቻ ፈተና ይሰጥ እንደነበር አስታውሰው ተግባራዊ ባደረገው የሞጁለር ትምህርት ስርዓት በሴሚስተር ከአራት በላይ ተከታታይ ፈተና በመስጠት የተማሪዎችን ዕውቀት መገምገም እንደተቻለም ጠቁመዋል፡፡ በዚህም በተለይ በከፍተኛ ደረጃ ይባረሩ የነበሩ የሴት ተማሪዎችን ቁጥር ከአንድ በመቶ በታች ዝቅ እንዲል ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው በአንድ መቶ ኪሎ ሜትር ዙሪያ የሚገኘውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ማህበረሰብ አቀፍ የምርምር ስራዎችን ለማከናወን 10 የቴክኖሎጂ መንደሮችን በመከለል በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ እንክብካቤና ሌሎች መስኮች የተለያዩ ምርምሮችን እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል። ዩኒቨርሲቲው ባከናወናቸው የምርምር ስራዎች ያፈለቃቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለአርሶ አደሩ በማውረድ ጥቅም ላይ እንዲያውላቸው የተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። እስካሁን ጤፍን በመስመር መዝራት የሚያስችል መሳሪያ፣ ዘመናዊ የንብ የማንቢያ ቀፎዎች፣ የወተት መናጫና የቃጫ ማዘጋጃ መሳሪያዎችን ማሰራጨት እንደቻለ ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው የስራ አጥነትን ችግሮች ለማቃለል መንግስት እያከናወነ ያለውን ተግበር ለማገዝ በሀገረ ሰላምና ዳሌ ወረዳ 60 ስራ አጥ ወገኖችን በንብ ማነብ ቴክኖሎጂ ስልጠና በመስጠትና የንብ ማንቢያ ዘመናዊ ቀፎዎችን በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል። በሲዳማና ጌዴኦ ዞኖች በሚገኙ የማልጋና ቡሌ ወረዳዎች አርሶ አደሩ የተሻሻለ ዝርያ ያለውን የቢራ ገብስ በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆን አዳዳስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ በተጨማሪ የሚመረተው የቢራ ገብስ ገበያ እንዲያገኝ ከአሰላ ብቅል ፋብሪካ ጋር የገበያ ትስስር መፍጠሩን ዶክተር ዮሴፍ ገልጸዋል። መልካም አስተዳደርን በማስፈን ዩኒቨርሲቲው ለመማር ማስተማርና ለስራ ምቹ እንዲሆን ለማድረግ ያከናወናቸው ተግባራት ውጤታማ መሆን እንደቻሉና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መካካል ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ ሁለተኛ በመውጣት ተሸላሚ መሆን እንደቻለ ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=13122&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር