ሁሉም ችግር በመንግሥት ስለማይሳበብ ኅብረተሰቡም የድርሻውን ይወጣ!

ሕገ መንግሥቱን፣ የተለያዩ ሕጎችን፣ ደንቦችንና መመርያዎችን በመከተል መንግሥት ሊፈጽማቸው የሚገቡ ተግባሮችና ሊፈታቸው የሚገባ ችግሮች አሉ፡፡
የሚጠበቅበትን ባለመፈጸሙና ችግሮችን ባለመፍታቱ  ብዙ መንግሥትን ጊዜ እንወቅሳለን፡፡ አሁንም ለወደፊቱም እየተከታተልን እንጠቁማለን፣ እንወቅሳለን፡፡ መብታችንም ግዴታችንም ነውና፡፡
ነገር ግን ሁሉም ችግር ወደ መንግሥት የሚወረወርና በእሱ የሚሳበብ አይደለም፡፡ የግል ዘርፉ፣ የሚመለከታቸው አካላትና በአጠቃላይ ሕዝቡ የድርሻቸውን ባለመወጣታቸው የሚከሰቱ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ መንግሥት የድርሻውን አልተወጣም ተብሎ እንደሚወቀሰው ሁሉ፣ የግል ዘርፉም የድርሻውን ሳይጫወት ሲቀር ሊወቀስና ሊመከር ይገባዋል እንላለን፡፡
ምን ማለታችን እንደሆነ ለማሳየት በርካታ ምሳሌዎች ለመጥቀስ እንችላለን፡፡ ለጊዜው በጥቂት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ እናተኩር፡፡ 
1.የግሉ ዘርፍ ግብር መክፈል አለበት መብትም ግዴታም ነው
በግል የሥራ ዘርፍ የተሰማራ ዜጋና የውጭ ኢንቨስተር ግብር መክፈል ያለበት ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ግብር ክፈል ስለሚል ብቻ አይደለም፡፡ ገና ከገቢዎች ጋር ግንኙነት ሳይፈጠር የሥራ ፈቃድ ሲወጣ ጀምሮ የግል ዘርፉ ግብር መክፈል እንዳለበት ያውቃል፡፡ ለማትረፍ እሠራለሁ፣ ካተረፍኩት ላይ እከፍላለሁ ብሎ ተዋውሎ ነው የሥራ ፈቃድ የሚወስደው፡፡ ስለሆነም ለምን ግብር ክፈል ተባልኩ የሚባል ነገር አይነሳም፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ግብር ካልተከፈለ ልማት የለም፡፡ መንግሥት የመንገድ፣ የሆስፒታል፣ የትምህርት ቤት፣ የስልክ፣ የኤሌክትሪክ፣ የውኃ፣ ወዘተ መሠረተ ልማቶችን ማከናወን የሚችለው በቂ በጀት ሲኖረው ነው፡፡ ለበጀቱ ትልቁ ድጋፍ ደግሞ ግብር ነው፡፡ ስለሆነም የግሉ ዘርፍ ግብር ካልተከፈለ ልማት የለም ብሎ ከልብ ማመን አለበት፡፡ ግብር እየከፈለ ልማትን በማፋጠኑም ኮራና ቀና ብሎ የሚሠራና የሚኖር ዜጋ መሆን አለበት፡፡ 
በግብር አከፋፈል ዙሪያ ግን በግሉ ዘርፍ በኩል ትልቅ ችግር አለ፡፡ ሕግ መጣስ፣ በጉቦ መሸፋፈን፣ መረጃን መደበቅና ማጭበርበር ይታያል፡፡ ይህ መቆም አለበት፡፡ መንግሥትን ይህንንና ያንን አልሠራህም ብለን እንደምንወቅሰው ሁሉ፣ ራሳችንም ከስህተታችን ነፃ መሆን አለብን ብሎ የሚያምን ግብር ከፋይ የግል ዘርፍ ልንፈጥር ይገባል፡፡ ባጭሩ የግሉ ዘርፍ በግብር አከፋፈል የድርሻውን ይወጣ፡፡ 
2.የግል ዘርፉና ሕዝቡ ከሙስና በመፅዳት ሙስናን ይታገል
ባለሥልጣናት ሙሰኞች ሆኑ ብለን መንግሥትን እንወቅሳለን፡፡ መውቀሳችን ትክክል ነው፡፡ መንግሥት ራሱን ከሙስና ያፅዳ፡፡ ነገር ግን ሙስና ሰጪና ተቀባይ ይጠይቃል፡፡ ባለሥልጣናትና የመንግሥት ሠራተኞች ሙስና ሲቀበሉ የሚሰጠው ኅብረተሰቡ ነው፡፡ እምቢ አልሰጥም፣ አገልግሎት ማግኘት መብቴ ነው ብሎ የሚከራከር ኅብረተሰብና ጠንካራ የግል ዘርፍ ሊኖረን ይገባል፡፡ የሙስና ተባባሪ ሳይሆን ሙስናን የሚዋጋና የሚያጋልጥ የግል ዘርፍና ኅብረተሰብ ያስፈልገናል፡፡ 
በአገራችን እየታየ ላለው የሙስና መስፋፋትና ሥር መስደድ የግል ዘርፉም ተጠያቂ ነው፡፡ ኅብረተሰቡም ተወቃሽ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር በመንግሥት እናሳብባለን፡፡ እኛም ተጠያቂ ነን ብለን እንመንና እንታገል፣ የድርሻችንን እንወጣ፡፡
3.ኅብረተሰብ በፅዳትና በአካባቢ ጥበቃ ድርሻውን ይወጣ
ሁሉንም ነገር መንግሥት እንዲያደርገው አንጠብቅ፡፡ ሠፈራችን ቆሽሾ መንግሥት አያፀዳውም እንዴ ብለን እንማረራለን፡፡ ደጃፋችን በራሳችን ቆሻሻ ሞልቶ እያለ መንግሥት አያነሳውም እንዴ እንላለን፡፡ በአካባቢያችን ያሉ ዛፎች ተበላሽተው፣ አበባዎች እየደረቁና እየረገፉ እያሉ ዞር ብለን አናያቸውም፡፡ ዛፎቻችን ለማገዶ ሲቆረጡና ሲወድሙ ደንገጥ ብለን አቁሙ አንልም፡፡ ይህ የኅብረተሰቡ ድክመት ነው፡፡ 
በእርግጥ ሁሉም ነገር በኅብረተሰቡ ይሠራል ብለን መንግሥትን ከኃላፊነት ነፃ አናደርገውም፡፡ ነገር ግን የመንግሥትን ድርሻ ማየት እንደምንፈልግ ሁሉ የራሳችንን ድርሻም እንወጣ፡፡ 
ምናልባት በእጅ የሚገፉ ጋሪዎች በየቀበሌው አሉ አይደለም ወይ የሚል ማስተዛዘኛ ይቀርብ ይሆናል፡፡ አዲስ አበባን በሚያክል ትልቅ ከተማ ለማፅዳት ጋሪ ተገዝቶ እናቶች ይግፉት ማለት አሳፋሪ ነው፡፡ የናይሮቢንና የአዲስ አበባን የፅዳት አሠራር ስናወዳድር የአዲስ አበባ አሳፋሪ ነው፡፡ ይቀየር! ይለወጥ! ኅብረተሰቡም የድርሻውን ይወጣ፡፡ 
4.በፀጥታና በደኅንነት ጉዳይ ኅብረተሰቡ የድርሻውን ያበርክት 
የአገር ደኅንነትና የፀጥታ ጉዳይ ይመለከተናል፡፡ የደኅንነት ሠራተኞችና ፖሊሶች አሉ አይደለም ወይ? ተብሎ የሚተው አይደለም፡፡ እነሱ እንደ መንግሥት የተሰጣቸውን የመከላከያ፣ የደኅንነትና የፖሊስ ኃላፊነቶች ይወጡ፡፡ ግን የኅብረተሰቡ ሚና በእጅጉ ከፍተኛ ነው፡፡
በወረዳና በክፍለ ከተማ ደረጃ ከመንግሥት ጋር በመተባበር የጥበቃ ኃይል ማቋቋም አስፈላጊ ነው፡፡ ተቋቁሞ የለም ወይ? ኮሙዩኒቲ ፖሊስ የሚል ማስታወቂያ በየቦታው ተለጥፎ የለም ወይ? የሚል መከራከሪያ ሊነሳ ይችላል፡፡ አዎን ተለጥፎአል፡፡ ነገር ግን የመንቀሳቀስ አቅም ያለው መሆን አለበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዝርፊያ በእጅጉ በዝቷል፣ አድማሱም ሰፍቷል፡፡ መሥሪያ ቤቶች የሚገኙባቸው ሕንፃዎች እየተሰበሩና እየተዘረፉ ናቸው፡፡ በየአካባቢው መኖሪያ ቤቶችም እንደዚሁ እየተሰበሩና እየተዘረፉ ናቸው፡፡ ይህ ችግር ለፖሊስ ብቻ አይተውም፡፡ አካባቢውን የሚጠብቅ ኅብረተሰብ ሊጠናከር ይገባል፡፡ በሕንፃ ውስጥ የሚገኙ ቢሮዎች በጋራ ጥበቃቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል፡፡ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ኗሪዎች በጋራ ጥበቃቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል፡፡
ማሳጅ ቤትና የእንግዳ ማረፊያ እየተባሉ እንደ አሸን እየፈሉ ያሉትም በፀጥታና በደኅንነት ዓይን ሊታዩ ይገባል፡፡ በዓለም ላይ በአብዛኛው ለወንጀል የሚጋለጠው ኅብረተሰቡ ነው፡፡ የፖሊስ ሚና ኅብረተሰቡ ከጠቆመ በኋላ ነው፡፡ እኛም ይህንን ባህል እናሳድግ፡፡
5. ኅብረተሰቡና የግል ዘርፉ በወጣቱ ትውልድ ላይ ኢንቨስት ያድርግ 
ማንም ዜጋ ወጣቱ ትውልድ ጨዋ፣ አዋቂ፣ አገር ወዳድ፣ ወዘተ እንዲሆን ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን ምኞት እንጂ ኢንቨስትመንት የለም፡፡ ኢንቨስትመንት የለም ስንል በስፖርት የዳበረ ወጣት ለመፍጠር ኢንቨስት እያደርግን አይደለንም፡፡ የመጫወቻና የመናፈሻ ሥፍራዎች ሁሉ ለግንባታ እየተሰጡ ናቸው፡፡ ወጣቱ ጨዋ እንዲሆን ብንፈልግም ትምህርት ቤቱና የመኖሪያ አካባቢው በመጠጥ ቤትና በማሳጅ ቤት እየታፈነ ነው፡፡ በቂ ቤተ መጻሕፍት አይቋቁሙለትም፤ በተገቢው መንገድ የመዝናኛ ማዕከልም አይሠሩለትም፡፡ የጫትና የሺሻ ቤቶች ግን ‹‹በሽበሽ›› ናቸው፡፡
በመሆኑም ለመጥፎ ጠባይ የሚዳረግ አካባቢ እየፈጠሩና እያጠናከሩ ጨዋ ትውልድ መጠበቅ አይቻልም፡፡ ይህ የመንግሥት ድርሻ እንዳለ ሆኖ ኅብረተሰቡም የድርሻውን ይጫወት፡፡
ብዙ መዘርዘር ይቻላል፡፡ ለማሳያ ግን ይህ በቂ ነው፡፡ መንግሥት ማድረግ የሚገባውን እንንገረው፡፡ ሁሌም እንዲፈጽም እንደሚገባው እንወትውተው፡፡
ግን ነገር ግን ኅብረተሰቡም ሁሉንም ነገር በመንግሥት ላይ ሳይወረውር የራሱን የድርሻውን ይወጣ!
6.በልማት ስም መቀለድ ይብቃ
 በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ከሚያካሂዳቸው በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ባልተናነሰ የግሉ ዘርፍም በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ ነገር ግን በልማት ስም የተረከቡትን መሬት አጥሮ በማስቀመጥ ወይም ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ በመስጠት ልማት የሚያደናቅፉ አሉ፡፡ በሕጋዊ መንገድ እየሠሩ ያሉ ዜጎች የአገርን የልማት ገጽታ ሲለውጡ፣ ለግል ጥቅማቸው ባደሩ ባለሥልጣናት ከለላ ሥር በልማት የሚቀልዱትን ሕዝቡና የግሉ ዘርፍ በቃችሁ ሊሉዋቸው ይገባል፡፡ ለዚህም መንግሥትን ብቻ ሳይጠብቅ ኅብረተሰቡ የራሱን ድርሻ ይወጣ!

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር