የዝናብ ስርጭቱ በጥቅምትና ህዳር ወር የመከሰት እድሉ ሰፊ በመሆኑ የሲዳማ አርሶ አደር ጥንቃቄ ያድርግ


አዲስ አበባ መስከረም 30/2006 በመላው አገሪቱ ሰሞኑን እየታየ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ የዝናብ ስርጭት እየቀነሰ ቢሆንም በጥቅምትና ህዳር ወር የመከሰት እድሉ ሰፊ በመሆኑ አርሶ አደሩ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አሳሰበ። ኤጀንሲው እንዳለው ከመስከረም 20 ቀን ጀምሮ አብዛኛውን የሃገሪቱን ክፍል የሸፈነ የዝናብ ስርጭት እምብዛም ያልተለመደ ነው። በቀጣይም እንደባለፈው ሳምንት የተስፋፋ ዝናብ ባይጠበቅም በአንዳንድ አካባቢዎች ያልተጠበቀ ዝናብ ሊከሰት ስለሚችል የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ረገድ አርሶ አደሩ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል። የኤጀንሲው የሚቲዎሮሎጂ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተር አቶ ድሪባ ቆሪቻ በተለይ ለኢትዮጰያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት በመላው አገሪቱ ባለፉት ዘጠኝ ቀናት ከባድ የሚባል የዝናብ መጠን ተመዝግቧል። በተለይም በአማራ ፣ ኦሮሚያ ፣ ደቡብና ሃረሪ ክልሎች እንዲሁም በሶማሌ ክልል ሰሜናዊ አጋማሽ ድሬዳዋን ጨምሮ ይህ ያልተለመደ ዝናብ ያለማቋረጥ መዝነቡን ተናግረዋል። የአማራ መካከለኛው ምስራቅ፣ ደቡብ ኦሮሚያ እና የደቡብ ክልል ሰሜናዊ አጋማሽ ከበድ ያለ ዝናብን ያስተናገዱ አካባቢዎች እንደነበሩ አስታውቀዋል። በእነዚህ አካባቢዎች በ24 ሰዓት ጊዜ ውስጥ ከ40 እስከ 80 ሚሊ ሜትር ዝናብ መመዝገቡን ገልጸዋል። የወቅቱ ዝናብ ዘግይተው ለተዘሩ ሰብሎች ጥቅም እንደሚኖረው አቶ ድሪባ ተናግረው እርጥበቱ በተለይ ሽምብራና ምስር የመሳሰሉትን እህሎች ቶሎ ለመሰብሰብ ከማገዝ ባለፈ በቂ የእንስሳት መኖ እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል። በቆላም አካባቢ ለሚገኙ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ለመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ለግጦሽ የሚሆን ሳር ለማግኘት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አቶ ድሪባ ተናግረዋል። በተጨማሪ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ይከሰት የነበረውን ከፍተኛ የሚባል ቅዝቃዜና ውርጭ መጠን እንዳይከሰትና መጠኑን የመቀነስ ሁኔታን ስለሚያስከትል ጥቅም ይኖረዋል። በዚህም በአገሪቱ ቆላማና በስምጥ ሸለቆ አካበቢዎች ላይ የደረሱና ያልደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት ስለሚያደርስ በቀጣይ የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ከሚደርሰው ጉዳት እንዲጠበቁ ጥሪ አስተላልፈዋል። ባለፉት ሁለት ቀናት የዝናብ ስርጭቱ በመላው አገሪቱ የመቀነስና ወደ መደበኛው ፈር የተከተለ የመሆን አዝማሚያ ማሳየቱን ተጠቁሟል፡፡ የሚቲዮሮሎጂ ትንበያ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሃገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ የዝናብ ስርጭቱ በመጠንም ሆነ በሽፋን እየተስፋፋ እንደሚሄድ ይጠበቃል ብለዋል።
ምንጭ፦
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=12536&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር