ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሆኑ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2006 ዓ.ም. ባደረጉት የጋራ ስብሰባ በቱርክ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ ያሉትን ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን በፕሬዚዳንትነት ሰየሙ፡፡
አዲሱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ፣ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ተገኔ ጌታነህ አማካይነት ቃለ መሐላ ከፈጸሙ በኋላ ሥልጣኑን የተረከቡት፣ በሁለት ዙር ለ12 ዓመታት ፕሬዚዳንት ከነበሩት ከአቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ነው፡፡ በዕለቱ ከሰዓት በኋላ የስድስት ዓመት የፕሬዚዳንትነት የሥራ ዘመናቸውን በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ አቀባበል ካደረጉላቸው በኋላ መጀመራቸው ታውቋል፡፡ 

በቀድሞው ወለጋ ጠቅላይ ግዛት አርጆ ወረዳ በ1949 ዓ.ም. የተወለዱት ዶ/ር ሙላቱ፣ የመጀመርያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአርጆና በአዲስ አበባ ከተሞች የተከታተሉ ሲሆን፣ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከቻይና ቤጂንግ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ኢኮኖሚ ፍልስፍና በ1974 ዓ.ም.፣ በዓለም አቀፍ ሕግ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በዚያው ዩኒቨርሲቲ በ1980 ዓ.ም. አግኝተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በ1983 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ ሕግ በዶክትሬት ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡

የኦሮምኛ፣የአማርኛ፣እንግሊዝኛ፣ቻይናኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ተናጋሪ የሆኑት ተሰያሚው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቆንስልነትና በዳይሬክተርነት፣ በጃፓንና በቻይና በባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት፣ በኢኮኖሚ ልማትና ትብብር ምክትል ሚኒስትርነት፣ በግብርና ሚኒስትርነትና በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤነት ያገለገሉ ሲሆን፣ፕሬዚዳንት እስከሆኑበት ዕለት ድረስ በቱርክ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲሠሩ ነበር፡፡ 

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በ1987 ዓ.ም. ሲመሠረት የመጀመርያው ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሲሆኑ፣ አዲሱ ፕሬዚዳንት ሦስተኛው የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡
አዲሱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ናቸው፡፡ ባለቤታቸው ወ/ሮ መዓዛ አብርሃ ነጋ ይባላሉ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር