ሥራችሁም እንደ አፋችሁ ይሁን!


የሕገ መንግሥቱን የበላይነት በሚመለከት ሰሞኑን ጠቃሚና ዓበይት ቃላት ከባለሥልጣናት አንደበት ሲነገሩ እየተደመጡ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ኢሕአዴግና የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ሕገ መንግሥቱን በማክበር አርዓያ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡ ፓርላማውም ይህን መቆጣጠር አለበት በማለት በአፅንኦት ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ 
የመንግሥት መሪና ሥልጣን የያዘው ገዥ ፓርቲ ሊቀመንበር እንደመሆናቸው መጠን፣ እንደ ፓርቲም እንደ መንግሥትም ሕገ መንግሥቱን እናክብር ቁጥጥር ሊደረግብንም ይገባል ማለታቸው ጎሽ! የሚያሰኝ ነው፡፡ 
የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳም ተመሳሳይ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡ ፓርላማው ሕገ መንግሥቱ መከበሩን ሊቆጣጠር ይገባል ብለዋል፡፡ ኢሕአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲና እንደ መንግሥት መሪ በአርዓያነት ሕገ መንግሥቱን ሊተገብር ይገባል፣ ለሕጎች ተገዥ መሆን አለበት፡፡ ይህንን በተግባር ለመተርጎም የሚያዳግተው አይሆንም፣ አርዓያም ይሁን በማለት በአፅንኦት ገልጸዋል፡፡ 
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃንም በቅርቡ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ልዩ ስብሰባ እንዲዘጋጅ በማድረግ ለሁለት ቀናት በተደረገ ውይይት በአፅንኦት ያነሱት ጉዳይ አለ፡፡ መገናኛ ብዙኃን ስለሕገ መንግሥቱ ኅብረተሰቡን ማስተማር እንዳለባቸውና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን የማስተግበር የበላይ ኃላፊነት የተሰጠው ስለሆነ፣ በቅርብ እየተገናኙ ስህተትንና ጉድለትን እያሳዩ ሥራቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡ በተግባር ሥራ ላይ ያልዋለ ሕገ መንግሥት ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋም አስረድተዋል፡፡
በአጭሩ  ሲታይ ከመንግሥት መሪ፣ ከገዥው ፓርቲ ኃላፊ፣ ከተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔና ከፌዴሬሽን ምክር አፈ ጉባዔ ሕገ መንግሥቱና ሕጎች እንዲከበሩ ልዩ ትኩረትና ልዩ ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ በአፅንኦት ሲገለጽ ሰንብቷል፡፡ 
እንደ አፋችሁ ያድርግልን!
መናገር ቀላል ነው፡፡ አንቀጽ መጥቀስ አያስቸግርም፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠትም የተለመደ ነው፡፡ ሁሌም ችግሩ ተግባርና ተግባር ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሕገ መንግሥታችን የሰፈሩ መብቶችና የሕጎቻችን ፍሬ ነገሮች በደብዳቤዎች ሲጣሱና ሲደረመሱ እየተስተዋሉ ናቸው፡፡ በትግል የተገኙና ብዙ ክርክር የተደረገባቸው አኩሪ የሕገ መንግሥት አንቀጾች በቴሌፎን፣ በኔትወርኪንግና በሙስና እየተጣሱ ናቸው፡፡ 
ስለሆነም በግልጽ አንድ ጥያቄ ጠረጴዛ ላይ እንዲቀመጥ የሚያደርግ ሁኔታ ላይ ነን፡፡ 
ሕገ መንግሥት መከበር አለበትና ቁጥጥርም ይደረግ በሚለው ላይ ተቃውሞ የለንም፤ በዚህ ላይ ድጋፍ ነው ያለን፡፡ 
ግን ነገር ግን ፓርላማውም፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም፣ ገዥው ፓርቲም፣ መንግሥትም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሕግ የሚጥሱ ባለሥልጣናት ሲያጋጥሟቸው ዕርምጃ ለመውሰድ ቆራጦች ናቸው ወይ የሚለው ጥያቄ በሚገባ መፈተሽ አለበት፡፡ 
የኢሕአዴግም የመንግሥትም ችግር እዚህ ላይ ነው፡፡ በቃል የሚናገረውንና በመርህ አምንበታለሁ የሚለውን በተግባር አያሳይም፡፡ ሕጎች በባለሥልጣናት ሲጣሱ ዕርምጃ ለመውሰድ ድፍረት ያንሰዋል፡፡ 
ሕገ መንግሥቱንና ሕጎችን የሚጥሱ ባለሥልጣናትና ኔትወርኮች እንዳሉ መንግሥት በሚገባ ያውቃል፡፡ እከሌን አትንኩ ብለው የሚያዙ፣ እኬን አስቁሙ ብለው ቴሌፎን የሚደውሉ፣ ሕገወጦች ሕግ ሲጥሱ እንዳትነኩት የሚሉ፣ በሕጋዊ መንገድ የሚሠራውን አስቁሙት የሚሉ፣ ለመንግሥትና ለሕዝብ ካላቸው ታዛዠነት በላይ፣ ለሕገ መንግሥትና ለሕግ ካላቸው ከበሬታ በላይ፣ ለባለገንዘብና ለኔትወርክ ተገዥና ታዛዥ የሆኑ ባለሥልጣናት እንዳሉና ቁጥራቸውም በርካታ እንደሆነ ኢሕአዴግ ያውቃል፣ መንግሥት ያውቃል፡፡
ታዲያ ለምን ዕርምጃ አይወስድም? ለምን ሕገ መንግሥት የሕጎች የበላይ ነው ብሎ ቁጥጥሩን ጠበቅ አያደርግም? ኔትወርኩ የተወሳሰበ ነው፡፡ አባላቱ ብዙ ናቸው፡፡ መንግሥትም ኢሕአዴግም ድፍረት ያንሳቸዋል፡፡ ችግሩ ይህ ነው፡፡ 
የመረጃና የማስረጃ ችግር የለም፡፡ ዓይን የሚያስፈጥጡ መረጃና ማስረጃዎች በየአደባባዩ አሉ፡፡ ሕግ እየተጣሰ እንደሆነ በማያሻማ መንገድ ማሳያ አለ፡፡ ግራ የተጋባው ሕዝብም መንግሥት ለምን ዝም ይላል በማለት በየጊዜው ትዝብቱንና ቅሬታውን እየገለጸ ነው፡፡ የፍትሕ ያለህ እያለም ነው፡፡ አንድ ዜጋ ሕግ ጥሰሃል እየተባለ ሲቀጣና ሲንገላታ፣ ሌላው ሲጨፍርና ሲጋልብ በአደባባይ እየታየ ነው፡፡ 
ስለዚህ መንግሥትና ምክር ቤቶቻችን ሁለት ነገሮችን ያቀናጁ፡፡ ሕገ መንግሥትና ሕግ መከበሩን ጥብቅ ቁጥጥር እናድርግ ማለታቸውና ደፈር ደፈር እያሉ መናገራቸው በርቱ ተበራቱ ያሰኛል፡፡ ሕዝብም ከጎናችሁ ነው፡፡ ከጎናችሁም ይሆናል እንላለን፡፡፡ 
ግን በተግባር አውሉት እንላለን፡፡ ሕግ መጣስ የለበትም ከሚለው ጎን ለጎን የጣሰ ይቀጣል፣ በሕግ ይጠየቃል ማለትም አለባቸው፣ በተግባርም ያሳዩት፡፡ 
ጅምሩ ጥሩ ነው፡፡ ንግግሩ ጥሩ ነው፡፡ በተግባር አሳዩን፡፡ እንደ አፋችሁ ያድርግልን!
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/news/itemlist/user/58-%E1%89%A0%E1%8C%8B%E1%8B%9C%E1%8C%A3%E1%8B%8D%E1%88%AA%E1%8D%96%E1%88%AD%E1%89%B0%E1%88%AD

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር