ኢትዮጵያን ለቀጣይ ስድስት ዓመታት የሚያገለግሏት ፕሬዝዳንት ሰኞ ይመርጣሉ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 24 ፣ 2006 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጪው ሰኞ የህዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች በሚያካሂዱት የጋራ ስብሰባ የ2006 በጀት ዓመት የስራ ዘመናቸውን በይፋ ይጀምራሉ ።
በዚሁ  እለት  ላለፉት 12 ዓመታት ኢትዮጵያን በርዕሰ ብሄርነት የመሯት ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስም የምክር ቤቶቹ በይፋ መከፈትን ያበስራሉ።
በመክፈቻው እለትም ፕሬዚዳንት ግርማ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ በመሆናቸው በክብር ይሰናበታሉ ።
ምክር ቤቱም በዕለቱ ከሚያከናውናቸው መርሃ ግብሮች መካከል እሳቸውን የሚተካ አዲስ ፕሬዝዳንት መምረጥ ይሆናል ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት ፥ ከተሰናባቹ ፕሬዚዳንት  ንግግር በኋላ  የአዲስ ፕሬዝዳንት እጩ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ድምፅ ይሰጥባቸዋል ።
በሀገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት ለፕሬዝዳንትነት እጩ የማቅረብ ስልጣን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሆን ፥ የሃገሪቱ ርዕስ ብሄር ለመሆን እጩው የግድ የምክር ቤቱ አባል እንዲሆን አይጠበቅበትም።
በመሆኑም የምክር ቤት አባል ያልሆነም ርዕሰ ብሄር ሊሆን ስለሚችል በእጩነት ሊቀርብ እንደሚችል ነው አፈ ጉባኤው ያስረዱት ።
ምክር ቤቱ ምርጫውን ካከናወነ በኋላም አዲሱ ፕሬዝዳንት ወንበራቸውን ከተሰናባቹ ፕሬዝዳንት በመረከብ ለኢትዮጵያ ህዝብ ንግግር በማድረግ ስራቸውን ይጀምራሉ።
የአዲሱ ፕሬዝዳንት ንግግርም የዓመቱ ዋና ዋና ስራዎችን በማካተት በመንግስት የወደፊት ስራዎች ላይ ያተኩራል ተብሎ ይጠበቃል።

ተሰናባቹ  ፕሬዚዳንት
ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ላለፉት 12 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን በፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል።
በእነዚህ የስራ ዘማናቸው ታዲያ በህገ መንግስቱ ከተሰጣቸው ስልጣንና ተግባር በተጨማሪ በተለያዩ መስኮች የሰሯቸው ተግባራት አሉ።
በአካባቢ ጥበቃና ቀይ መስቀልን ጨምሮ በተለያዩ ማህበራት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ በዋቢነት የሚነሱ ናቸው።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር