ከቱሪስት ከተማነት እስከ ታላላቅ የስፖርት ውድድሮች መናኸሪያነት_ሀዋሳ

ከሃምሳ ዓመት በላይ ያስቆጠረችው የደቡብ ክልል መዲና ሐዋሳ ከኢትዮጵያ ከተሞች በቁንጅናዋ፣ በዕቅድ ከመከተሟም ጋር ተዛምዶ ለብዙ ነገር ትመረጣለች፡፡
ከቱሪስት ከተማነት እስከ ታላላቅ የስፖርት ውድድሮች መናኸሪያነት ትታጫለች፡፡ 
አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በሐዋሳ ስሙን መትከል የፈለገው በቢዝነስ ሥራ ብቻ አይደለም፡፡ በታላቁ ሩጫ ዓመት ጠብቆ የሚጐበኛትን የደቡብ መናገሻ፣ አሁን ደግሞ ለአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን ማራቶን መሽቀዳደሚያ አውራና ተመራጭ አድርጓታል፡፡ 
ኃይሌ በሐዋሳ ያልተለመደውንና በስሙ የተሰየመውን የማራቶን ውድድር በከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት አንበሽብሾታል፡፡ በሁለቱም ጾታ አሸናፊዎቹ እያንዳንዳቸው የ100 ሺሕ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ 
የመጀመሪያው ‹‹ኃይሌ ማራቶን›› ጥቅምት 10 ቀን 2006 ዓ.ም. በደቡቧ መናገሻ ሐዋሳ እንደሚደረግ ይፋ በሆነ በጥቂት ወራት ከ16 አገሮች ከ200 በላይ ተሳታፊዎች በውድድሩ ለመሳተፍ ቅድመ ምዝገባ ማከናወናቸውን የገለፀው ዝግጅት ክፍሉ፣ በሚቀጥለው ዓመት ከተወዳዳሪ ቁጥር ጀምሮ የተሻለና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ አበረታች ተሞክሮ ተገኝቷል ብሏል፡፡ 
በአገሪቱ ለታላላቅ አትሌቶች መገናኛ እንደሆነ የሚነገርለት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፣ በ10 ሺሕ ተሳታፊዎች ጀምሮ በአሁኑ ወቅት በተመሳሳይ የሩጫ ውድድሮች ከዓለም ምርጥ አሥሩ አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡ ዘንድሮም 37 ሺሕ ተሳታፊዎች ለማወዳደር ዝግጅቱን አጠናቆ እንደሚገኝ መገለጹ ይታወሳል፡፡ ውድድሩ ከአዲስ አበባ አልፎ በመላ አገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ተወዳጅና ተናፋቂ እስከመሆን ደርሷል፡፡ 
42 ኪሎ ሜትር 195 ሜትር የሚሸፍነው ማራቶን በአውሮፓና በሌሎች ታላላቅ አገሮች ካልሆነ እንዲህ እንደ አሁኑ በኢትዮጵያ ይደረጋል ተብሎ በማይታመንበት በዚህ ወቅት፣ በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሐዋሳ የተደረገው ‹‹ኃይሌ ማራቶን›› አቅም የሌላቸው ነገር ግን በምኞት ብቻ አውሮፓን ለሚያልሙ ተስፈኛ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትልቅ የምሥራች ስለመሆኑ በወንዶች የኃይሌ ማራቶን አሸናፊ ጉዲሳ ሸንተማ ተናግሯል፡፡
በዚሁ መሠረት ባለፈው እሑድ ጥቅምት 11 ቀን 2006 ዓ.ም. በሐዋሳ በተከናወነው ማራቶን በወንዶች የውድድሩ አሸናፊ ጉዲሳ ሸንተማ ከመከላከያ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 2 ሰዓት 15 ደቂቃ 23 ሰከንድ ፈጅቶበታል፡፡ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ደግሞ ተካልኝ ጠበሉ ከኢትዮጵያ ራነር ማኔጅመንት ሲሆን 2 ሰዓት 15 ደቂቃ 24 ሰከንድ ወስዶበታል፡፡ ሦስተኛ የወጣው ከኤችአይቪ ክለብ ተስፋዬ በቀለ ደግሞ 2 ሰዓት 17 ደቂቃ 25 ሰኮንድ አጠናቋል፡፡
በሴቶች መካከል በተደረገው ተመሳሳይ ውድድር አልማዝ ነገደ ከኢትዮጵያ ተገን 2 ሰዓት፣ 39 ደቂቃ፣ 50 ሰኮንድ አጠናቃ ስታሸንፍ፣ ሁለተኛ የወጣችው ዓባይነሽ ፀጋዬ በግል 2 ሰዓት፣ 40 ደቂቃ፣ 30 ሰኮንድ እንዲሁም ስንታዬሁ ጌታቸው በግል 2 ሰዓት 47 ደቂቃ 22 ሰኮንድ አጠናቃ ሦስተኛ ሆናለች፡፡ 
ሽልማቱን በተመለከተ በሁለቱም ጾታ አንደኛ ለወጡ አትሌቶች 100 ሺሕ ብር፣ ሁለተኛ ለወጡ ደግሞ 40 ሺሕ ብር፣ እንዲሁም ሦስተኛ ለወጣው 15 ሺሕ ብር መሆኑም ታውቋል፡፡ እንደ ዝግጅት ክፍሉ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከናወነው ‹‹ኃይሌ ማራቶን›› ርቀቱን ከሁለት ሰዓት፣ ከ12 ደቂቃ በታች የገባ አትሌት ቢኖር በሚል ተጨማሪ 100 ሺሕ ብር ሽልማት እንደሚሰጠው ጭምር ቀደም ብሎ ተነግሮ ነበር፡፡
ይህንኑ የሰሙ አንዳንድ ታዋቂና ታላላቅ አትሌቶች ጉዳዩ ቀደም ተብሎ መረጃው ደርሶ ቢሆን፣ በውድድሩ ከመሳተፍ ወደ ኋላ እንደማይሉ በቁጭት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በመጨረሻም ከ16 አገሮች ከመጡት የውጭ አገር ዜጐች ውስጥ 56 ተወዳዳሪዎች በማራቶን የተሳተፉ ሲሆን፣ ከአገር ውስጥ 37 አትሌቶች ተካፍለዋል፡፡ በዕለቱ በተደረገው የአምስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር 2500 ተሳታፊዎች እንዲሮጡ ተደርጓል፡፡ 750 ሕፃናትም በተመሳሳይ የተሳተፉበት የሩጫ ውድድር ተከናውኗል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር