“የሚፈልጉት የእምነት ቃል ነው” ማሰቃየት እና ጎጂ አያያዝ በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ፖሊስ ጣቢያ

የሪፖርቱ ይዘት ባጭሩ 

አንዱ (ፖሊስ) በያዘው ረዥም ጥቁር ዱላ ከኋላ ጭንቅላቴን መታኝ ከዚያ አይኔን በጨርቅ 
አሰረኝ፤ በመቀጠል ወደ ቢሯቸው ወሰዱኝ፤ ይህንን ያደረጉት መርማሪዎቹ ናቸው…ደጋግመው 
በጥፊ መቱኝ፡፡ የምነግራቸውን ለመስማት መርማሪዎቹ ዝግጁ አይደሉም፤ በጥቁሩ ዱላ እና 
በጥፊ ደግመው መቱኝ። እዚያው ክፍል እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ አቆዩኝ፤ በጣም ተዳክሜ 
ነበር። ከዚያ ወደ ታሰርኩበት ክፍል መለሱኝ እና ሌላ ሰው ወሰዱ፡፡ በሁለተኛው ቀን 
ምርመራ ድብደባው የባሰ ነበር። የሚፈልጉት ጥፋተኛ ነኝ ብየ እንዳምን ነው ፡፡ 

በ2003ዓ.ም ዓመት አጋማሽ ማዕከላዊ ታስሮ የነበረ ጋዜጠኛ - ናይሮቢ፣ ሚያዚያ 2004ዓ.ም 
በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ መሃል ከአንድ ሆቴል እና አንድ የኦርቶዶክስ ቤቴክርስቲያን አጠገብ በመላ ሃገሪቱ በጣም 
ታዋቂ የሆነ አንድ ፖሊስ ጣቢያ ይገኛል።ይህም የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ሲሆን በተለምዶ ማዕከላዊ 
በመባል ይታወቃል። ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የተቃውሞ ሰልፍ አደራጆች፣ በብሄር የተደራጁ አማፅያንን 
ይደግፋሉ የሚባሉ ሰዎች እና ሌሎችም በርካታ የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች ሲያዙ በቅድሚያ የሚወሰዱት ወደ ማዕከላዊ 
ነው፡፡ ማዕከላዊ ከገቡ በኋላ ምርመራ ይካሄድባቸዋል። በአብዛኞቹ ላይ ደግሞ ሁሉም ዓይነት እንግልት እና በደል 
የሚደርስባቸው ሲሆን ይህም ማሰቃየትን ይጨምራል፡፡ 
በማዕከላዊ የሚገኙት መርማሪ ፖሊሶች ታሳሪዎች ጥፋታቸውን እንዲያምኑ፣ እንዲናገሩ ወይም ሌላ መረጃ እንዲያወጡ 
የሚያደርጉት በሃይል የማስፈራራት መንገድን በመጠቀም ሲሆን ይህም እስከ ማሰቃየት እና ሌላ ጎጂ አያያዝ እስከ መፈጸም 
ይደርሳል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ እስረኞች ከጠበቃ እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናገኙ አይፈቀድላቸውም፡፡ እስረኞቹ 
የመርማሪዎቹን ፍላጎት ለማሟላት በሚያደርጉት ትብብር መጠን በቅጣት ወይም በማበረታቻ መልክ የውሃ፣የምግብ፣
የመብራት እና የሌሎች አስፈላጊ ነገሮች አቅርቦት ሊከለከሉ ወይንም ሊፈቀድላቸው ይችላል፡፡ 
ይህ ሪፖርት ከ2002 ዓ.ም እስከ 2005 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በማዕከላዊ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን፣ ህገወጥ 
የምርመራ ዘዴዎችን እና የታሳሪዎችን ሁኔታ የሚዳስስ ነው፡፡ ለዚህ ሪፖርት ሂዩማን ራይትስ ዎች ከ35 በላይ ቀድሞ 
ማዕከላዊ ታስረው የነበሩ ግለሰቦችን እና ቤተሰቦቻቸውን ቃለ መጠይቅ አድርጓል፡፡ ምንም እንኳ ሂዩማን ራይትስ ዎች 
ማዕከላዊን መጎብኘት ባይችል እና ይህም ሁኔታውን በቀጥታ ለመታዘብ እና በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን 
ለማነጋገር እንዳይችል ቢያደርገውም የዚህ ሪፖርት አዘጋጆች በተለያዩ መንገዶች የተመረጡት የቀድሞ ታሳሪዎች የሰጧቸውን 
መረጃዎች በተናጠል በተደረጉ ቃለ መጠይቆች ለማመሳከር ችለዋል። 
በኢትዮጵያ በፖሊስ እና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ስለሚፈጸሙ በዘፈቀደ የማሰር፣ የማሰቃየት እና ጎጂ አያያዝን የተመለከቱ 
ወቀሳዎችን መስማት አዲስ አይደለም፡፡ ሆኖም በተለይ ከአወዛጋቢው የ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት 
ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት፣ የመደራጀት እና የመሰብሰብ መብቶች ላይ የሚያደርገውን ገደብ በማጠናከር ተቃውሞን ለማዳፈን 
የሚያስችሉ በርካታ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ይህም የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎችን፣ ጋዜጠኞችን እና ሌሎች ለመንግስት 
ያልወገነ ድምፅ የሚያሰሙ ወገኖችን ይዞ ማሰር፣ እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ሥራ እና የመገናኛ ብዙሃን ነፃነትን 
በእጅጉ የሚገድቡ ህጎችን በሥራ ላይ ማዋልን ይጨምራል፡፡

ሙሉ ሪፖርቱን ከታች ካለው ሊንክ ላይ ተጭነው ያንብቡ
http://www.hrw.org/sites/default/files/reports/ethiopia1013ar_sumandrecs.pdf

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር