የመንግሥትን አስቸኳይ ትኩረትና መፍትሔ የሚሹ ሰባት ዓበይት ችግሮች

ይበዛ ያንስ፣ ይሰፋ ይጠብ፣ ይረዝም ያጥር፣ ይሻል ይባስ እንደሆነ እንጂ ምንጊዜም በየትም አገር ችግሮች ይኖራሉ፡፡
ዋናው ጉዳይ ችግር መኖሩ አይደለም፡፡ ችግሩን ለይቶ፣ አውቆና ትኩረት ሰጥቶ መፍትሔ መስጠት ያለመቻል ካለ ነው የሚያሳስበው፡፡ መፍትሔ ያላገኘ ችግር እየተባባሰ ሄዶ አገርንና ሕዝብን ለአደጋ ይዳርጋልና፡፡ 
ይህ ስለሆነም ነው ሁላችንም እንደ ሕዝብና እንደ ዜጋ፣ በተለይም መንግሥት ኃላፊነት የተሸከመ አካል እንደመሆኑ መጠን በየጊዜው የአገር ችግሮችን እየመረመረ፣ እየገመገመና ቅደም ተከተል እያስያዘ ለችግሮች መፍትሔ መስጠት ይኖርብናል፡፡ 
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያችን እንደሌላው አገር ሁሉ የተለያዩ ችግሮች አሉ፡፡ ተገቢውን ትኩረት ካላገኙና አስቸኳይ መፍትሔ ካልተደረገላቸው በአገር ላይ አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ችግሮቹ ተለይተውና ታውቀው ልዩ ርብርብ ሊደረግባቸው ያስፈልጋል፡፡ የግድ ይላል፡፡
የመንግሥትን ትኩረትና መፍትሔ የሚሹ ወቅታዊ፣ ልዩና አስቸኳይ ዓበይት የኢትዮጵያ ችግሮች የምንላቸው የሚከተሉት ናቸው፡፡ 
1.ሰብሰብ፣ ጠንከርና ነቃ ያለ የመንግሥት አመራር ያስፈልጋል
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በሞት ሲለዩና አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሰየሙ ምንም ችግርና ብጥብጥ አልነበረም፡፡ ከዚያ በኋላም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ አገራችን እየተመራች ናት፡፡ ይህን የሚመለከት ችግር ስላለ አይደለም ሰብሰብ፣ ጠንከርና ነቃ ያለ መንግሥትና አመራር ያስፈልጋል እያልን ያለነው፡፡ ዓለም በኢኮኖሚ ቀውስ እየታመሰ ነው፡፡ እኛንም እየጐዳን ነው፡፡ ትላልቅና በርካታ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ሲደረጉ ከፍተኛ ፋይናንስ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በፊት ያልነበረ የሃይማኖት ግጭትና ልዩነት እየታየ ነው፡፡ ችግሩ ካልተፈታ አስጊ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ዕድገት የማይሹና የማይመኙ ጠላቶች በእጅጉ እየተፈታተኑን ናቸው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ጠንካራ መንግሥትና ጠንካራ አመራር የግድ ይላል፡፡ 
ገዥው ፓርቲ ውስጣዊ አንድነቱን ማጠናከር አለበት፡፡ በአደረጃጀቱ ምክንያት አራት አባል ድርጅቶች ቢኖሩትም ሲሠራና ሲንቀሳቀስ እንደ አንድ መሆን አለበት፡፡ እንኳን እየተራራቁ አንድ ተሁኖም ለመፍታት የሚያስቸግሩና የሚፈታተኑ ችግሮች እያጋጠሙ ናቸው፡፡ ጠላቶችና አንዳንድ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት ተጣሉና ተሰነጣጠቁ እንደሚባለው ሳይሆን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ተገቢና የሚጠበቅ አንድነት፣ መቀራረብ፣ የዓላማ ፅናትና ለመስዋዕትነት ዝግጁነት እየታየ አይደለም፡፡ መንግሥት ጠንከር፣ ሰብሰብና ነቃ ይበል እንላለን፡፡ 
2.አገር በሙስና እየተጨማለቀች ናት
ሙስናን ለመዋጋት ተጨባጭ እንቅስቃሴ እየታየ ነው፡፡ ሕጋዊ አሠራርን አጠናክሮ ትግሉ ይቀጥል እንላለን፡፡ ‘እንትና ይደናገጣል እከሌ ያኮርፋል’ ተብሎ የሚቆምና የሚቀዘቅዝ ትግል መሆን የለበትም፡፡ ሙስና ኢትዮጵያን እያጨማለቀ ነውና፡፡ የግድ የግድ የግድ መመታት አለበት፡፡ አጽንኦት የምንሰጠው ተጨማሪ ዕርምጃ ደግሞ አለ፡፡ ከስርቆትና ከዝርፊያ በኋላ ብቻ ዕርምጃ መውሰድ ሳይሆን፣ ከስርቆትና ከዝርፊያ በፊት ሙስናን የሚያስቆሙና የሚያጋልጡ አሠራሮች፣ ሕጐች፣ መዋቅሮችና የሥነ ምግባር ደንቦች ይጠናከሩ፡፡ በአስቸኳይ ሥራ ላይ ይዋሉ እንላለን፡፡ ለሙስና የሚያመች ሁኔታ እየፈጠሩ ሙስናን መዋጋት አይቻልም፡፡ ሙስናን መክሰስና መቅጣት አንዱ የትግል ዘዴ እንጂ ብቸኛው አይደለምና፡፡ ከአሿሿም ጀምሮ፣ ከቁጥጥር ጀምሮ፣ ከቅጥር ጀምሮ አሠራሩ ሁሉ ሙስናን የሚያስወግድ ይሁን፡፡ አደጋ ሲደርስ በአምቡላንስ ከመተማመን ይልቅ፣ አደጋና በሽታ እንዳይደርስና እንዳይዛመት በፀረ ሙስና የመጀመሪያ ዕርዳታና ክትባት እንመን፡፡ ለዚህ ልዩ ትኩረት ይሰጥ፡፡   
3.የመልካም አስተዳደር እጦት ሕዝቡን ተስፋ እያስቆረጠ ነው
አዎን ገዥው ፓርቲ መልካም አስተዳደር  አለመኖሩን እያመነ ነው፡፡ ዕርምጃም እወስዳለሁ እያለ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር  ይኑር ይስፋፋም እያለ ነው፡፡ በቃላት ላይ ችግር የለም፡፡ በተግባር ግን መልካም አስተዳደር እውን ሊሆን አልቻለም፡፡ የትም ሥፍራ፣ የትም መሥሪያ ቤት በማንኛውም ጊዜ መልካም አስተዳደር እየተጣሰ፣ ፍትሕ እየጠፋ፣ የሕዝብ ጩኸትና ጥሪ ተቀባይ አልባ ሆኗል፡፡ ሕገ መንግሥቱና የተለያዩ ሕጎች ተግባር ላይ የሚያውላቸው አጥተዋል፡፡ የሙስና ተጠርጣሪዎች ታሰሩ ቢባልም ፈጥረውታል የተባለው በደል ግን ሲስተካከል አይታይም፡፡ ይህ ችግር በእጅጉ አደገኛ ነው፡፡ ዜጋ አገሩን እንዲጠላና ተስፋ እንዲቆርጥ እያደረገ ያለ ችግር ነው፡፡ ከመንግሥት ቃላት ሳይሆን ተግባር ይጠበቃል!
4.የሃይማኖት ግጭትና መራራቅ ታሪካችንን፣ ማንነታችንና ደኅንነታችንን ለአደጋ እያጋለጠ ነው
ሃይማኖቶች በመርሀቸው አይጋጩም፡፡ ሁሉም ፍቅርን፣ መተሳሰብንና ሰላምን የሚሰብኩ ናቸው፡፡ ችግሩ ያለው እምነት ላይ አይደለም፡፡ ችግሩ ያለው የዚህ ሃይማኖት ጠበቃና አለኝታ እኔ ብቻ ነኝ፣ አንተ ወይም ያኛው አይደለም በሚል ሃይማኖትን ተገን በማድረግ በሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የክርስትና፣ የእስልምናና የአይሁድ እምነቶች በጋራ በሚኖሩበት አገር ውስጥ፣ ጋብቻ ፈጽመውና ተፋቅረው መኖር የሚችሉ የተለያዩ የሃይማኖት እምነት ተከታዮች ያሉበት አገር አለን እያልን፣ ጠንካራ የነበረን ሕዝብ ተጋጨ፣ ተፋጀ ወደሚል አሳፋሪ ታሪክ እየቀየርነው ነው፡፡ መንግሥትም ልዩ ትኩረትና ልዩ ጥንቃቄ እያደረገ፣ የሃይማኖት አባቶችም ተገቢውን ትምህርት እየሰጡና እንቅስቃሴ እያደረጉ፣ ምሁሩንና ዜጐችም የድርሻውን በሰላማዊና በአስተማሪ መንገድ እየተወጡ ካልተሄደ፣ ነገ ተቆጭተን ወደማናስተካክለው ውድቀት ይመራናል፡፡ መንግሥት የሃይማኖት አባቶችንና መሪዎችን፣ ሽማግሌዎችን፣ አስተማሪዎችን፣ ወዘተ. ተጠቅሞ ችግሩን ለመፍታት ይረባረብ፡፡ ሁሉም ዜጋ ድጋፉን ይስጥ፡፡ 
5.የኢኮኖሚና የቢዝነስ መቀዛቀዝ እያሳሳቀ የሚወስድ ጐርፍ እንዳይሆን ጠንቀቅ
የገንዘብ ችግር አለ፡፡ በጀት ማፅደቅ ቀላል ባይሆንም መልቀቁ እየከበደ ነው፡፡ ክፍያ አፈጻጸም ላይ እንኳን ግለሰብ መንግሥትም እየተቸገረ ነው፡፡ የግል ባንኮች እየተዳከሙ ናቸው፡፡ የብድርና የውጭ ምንዛሪ ችግርና እጥረት አለ፡፡ ግሽበትን ለመቆጣጠር የሚወሰደው ዕርምጃ የራሱን ችግር እየስከተለ ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ፣ የውኃ መጥፋት፣ የኔትወርክ አለመኖር፣ በሁሉም ዘርፍ ችግር እያስከተለ ነው፡፡ ገንዘብ ማሸሽና መደበቅ እየታየ ነው፡፡ ሌባው ሲፈራ ባይገርምም፣ ንፁኃን ሲሸማቀቁና ብታሰርስ እያሉ በመፍራት ከቢዝነስ እንቅስቃሴ ሲቆጠቡ እየታየ ነው፡፡ ይህን ችግር አምኖና ተረድቶ አስቸኳይ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
6.ሥራ አጥነት ከባድና አስጊ ችግር እየሆነ ነው
በኢሕአዴግ ጊዜ ብዙ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ መንግሥት የነበረውን የሥራ ዕድል እየዘጋ አይደለም፡፡ እየከፈተ ነው፡፡ ግን ከሕዝብ ብዛትና ከሚመረቁ ተማሪዎች አንፃር በቂ የሥራ ዕድል አልተፈጠረም፡፡ ሥራ ለማግኘት ወደ ዓረብ አገሮች የሚደረገው ስደት በአስፈሪ ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ወደ ወንጀል እየተገባ ነው፡፡ ለባለ ገንዘብ ራስን ለሽያጭ ማቅረብ እየተስተዋለ ነው፡፡ ይህ ችግር ካልተፈታ አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ያሰጋል፡፡ ልዩ ትኩረትና መፍትሔ ይደረግበት፡፡ የተራበ ሆድ አደገኛ ነውና፡፡ 
7.መቀራረብና መወያየት ባለመኖሩ ቀላል ችግሮች እየተካበዱ ናቸው
በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉ ችግሮች ኢትዮጵያዊያን ሊፈቱዋቸው የሚችሉ ናቸው፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ፣ በመንግሥትና በተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ፣ በመንግሥትና በሲቪል ማኅበረሰቡ፣ በመንግሥትና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች መካከል መቀራረብ፣ መወያየትና መመካከር ስለሌለ በቀላሉ የሚፈቱ ችግሮች እየተባባሱ ናቸው፡፡ ችግሮችን ለመንግሥት ማቅረብ አልተቻለም፡፡ መንግሥትም የሕዝብን ችግርና ስሜት ማወቅ አልቻለም፡፡ በዚህ ምክንያት ቀላል ችግሮች እየተካበዱና ወደማያስፈልግ አቅጣጫ እየተሸጋገሩ ናቸው፡፡ መንግሥት በአስቸኳይ ቲንክ ታንክ ያቅድ፣ የጋራ መድረክ ይፍጠር፣ የሕዝብና የመንግሥት፣ የመንግሥትና የባለሙያዎችን ግንኙነት ያጠናክር፡፡ መጠራጠርንና መራራቅን ወደ መቀራረብና መተማመን ይቀይር፡፡     
እየታዩ ያሉ አዎንታዊ ነገሮችን አንዘነጋም፡፡ እነዚህ ሰባት ነጥቦች ትኩረት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ፈጣን ዕርምጃ ይፈልጋሉ፡፡ ኋላ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር