‹‹ቢዝነስ ለመሥራት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አንደኛው ችግር ቢሮክራሲ ነው››

አቶ ሔኖክ አሰፋ፣ የፕሪሳይስ ኮንሰልት ኢንተርናሽናል ማኔጂንግ ዳይሬክተር 
ፕሪሳይስ ኮንሰልት ኢንተርናሽናል፣ ከስድስት ዓመታት በፊት የተቋቋመ በማኔጅመንት፣ በቢዝነስና በኢንቨስትመንት ዘርፎች የማማከር ሥራ ላይ የተሰማራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ነው፡፡
በአገር ውስጥ ከሚገኙ የግል ኩባንያዎች አንስቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙት ኤጀንሲዎችንና ድርጅቶችን የሚያማክረው ይህ ተቋም፣ 25 ቋሚ ሠራተኞች፣ ፕሮጀክት በመጣ ቁጥር እንዳስፈላጊነቱ የሚሠሩ 60 ባለሙያዎችና አሜሪካ፣ ካናዳ እንዲሁም ጀርመን አገር የሚገኙ የሥራ አጋሮች አሉት፡፡ መቀመጫውን አዲስ አበባና ኒውዮርክ ያደረገው ፕሪሳይስ ኩባንያን የመሠረቱትና ተቋሙን በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት የሚመሩት አቶ ሔኖክ አሰፋን ምዕራፍ ብርሃኔ አነጋግራቸዋለች፡፡ 
ሪፖርተር፡- ስለትምህርት ደረጃዎና ሲሠሯቸው ስለነበሩት ሥራዎች ይንገሩን፡፡
አቶ ሔኖክ፡- የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ያጠናቀቁት በካቴድራል ትምህርት ቤት ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ አሜሪካ ኒውጄርዚ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት ተምሬያለሁ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪዬንና ማስተርሴን እዚያው አሜሪካ ከሚገኘው ፎርድሃም ዩኒቨርሲቲ፣ ኢንተርናሽናል ትሬድ ኤንድ ፋይናንስና ኢኮኖሚክስ ላይ ሠርቻለሁ፡፡ ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ኒውዮርክ ከተማ ውስጥ ብሩክሊን በሚባል አካባቢ የሚገኘው ብሩክሊን ንግድ ምክር ቤት ውስጥ፣ አነስተኛ የብሩክሊን አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ለወጭ ገበያ ለማቅረብ በሚያስችላቸው ፕሮግራም ውስጥ ዓለም አቀፍ የንግድ ባለሙያ ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ በንግድ ምክር ቤቱ በነበረኝ የአራት ዓመታት ቆይታም፣ በጊዜው ከነበሩት ዳይሬክተሮች ውስጥ አንዱ ለመሆን በቅቼ ነበር፡፡ ከዚያም በተጨማሪ የንግድ ምክር ቤቱ የኒው ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ነበርኩ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2004 ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ውስጥ ምክትል ዋና ጸሐፊ በመሆን ለአንድ ዓመት ተኩል አገልግያለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትም ለሁለት ዓመት የቦርድ አባል ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2006 ወደ አሜሪካ ተመልሼ በግሌ የማማከር ሥራ መሥራት ጀመርኩ፡፡ መጀመሪያ ላይ ካገኘኋቸው የማማከር ሥራዎች ውስጥ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ውስጥ የአጭር ጊዜ የማማከርና የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አንዱ ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያ የሚገኘው የዓለም ባንክ ወደ ደቡብ ሱዳን ልኮኝ ሠርቻለሁ፡፡ ከዚያም እ.ኤ.አ. በ2007 መጀመሪያ ላይ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ ፕሪሳይስ ኮንሶልትን አቋቋምኩ፡፡ 
ሪፖርተር፡- ፕሪሳይስ መቀመጫውን ኒውዮርክና አዲስ አበባ ያደረገ ተቋም ነው፡፡ በሁለቱም ከተሞች እንዴት ነው የምትሠሩት?
አቶ ሔኖክ፡- ኒውዮርክ ውስጥ የከፈትነው እ.ኤ.አ. በ2010 ነው፡፡ የከፈትንበት ምክንያት ደግሞ ኢንቨስተሮች ከአሜሪካ አገር ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ሲፈልጉ፣ ከማን ጋር መሥራት እንችላለን የሚለውን እንዲያውቁና መተማመኛ እንዲኖር ስንል ነው፡፡ አሁን ላይ የኒውዮርክ ቢሯችን በተወካይ ደረጃ የሚሠራ ሲሆን፣ አጠቃላይ ሥራውን ግን እዚህ ነው የምንሠራው፡፡  
ሪፖርተር፡- ፕሪሳይስ የሚሰጠው ዋነኛ አገልግሎት ምንድን ነው? 
አቶ ሔኖክ፡- የምንሰጠው አገልግሎት ደንበኞቻችን ለሆኑት ቢዝነሶች፣ መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ኤጀንስዎች፣ ሥራቸው ላይ ትክክለኛ ውሳኔ ለመወሰን የሚያስችላቸውን ትክክለኛ መረጃና ዕውቀት እንዲያገኙ ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ አመዛኙ ሥራችን የነበረው ከዓለም አቀፍ ኤጀንሲዎች ጋር ነው፡፡ ከዓለም ባንክ፣ ከእንግሊዝ ተራድኦ ድርጅትና ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ጋር የግሉ ዘርፍ ልማት ወይም ዕድገት ላይ የማማከር ሥራ እንሠራለን፡፡ እነዚህ ኤጀንሲዎች የኢትዮጵያን የግል ዘርፍ እንዴት ማነቃቃትና ማሳደግ ይቻላል የሚሉት ጥያቄዎች ላይ መፍትሔ መስጠት ስለሚፈልጉ፣ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች ላይ በስፋት እንሠራለን፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥም የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚን እያማከርን ነው፡፡ ለውጭ አገር ኢንቨስተሮችና አገር ውስጥ ላሉ ታላላቅ ኩባንያዎች የማኔጅመንት፣ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የማማከር አገልግሎት እንሰጣለን፡፡  
ሪፖርተር፡- ዓለም አቀፍ ኤጀንሲዎቹ እዚህ መጥተው ለመሥራት ፍላጎት ሲያሳዩ እንዲሠማሩባቸው የምታማክሯቸው የሥራ መስኰች የትኞቹ ናቸው? 
አቶ ሔኖክ፡- በአሁኑ ጊዜ ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ሥራ ለመሥራት ትልቅ ፍላጎት አለ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ኢትዮጵያ እያደገ ያለ ኢኮኖሚ ስላላት፣ ገበያውም እየሠፋ እየሄደ ስለሆነና ኢኮኖሚዋም ከዓለም ጋር እየተሳሰረ ስለመጣ ነው፡፡ ስለዚህ የውጭ ኢንቨስተሮች መጥተው የኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ዘልቀን መግባት እንፈልጋለን፣ እዚህ ፋብሪካ ማቋቋም እንፈልጋለን፣ ነገር ግን ምን ላይ እንደምንሠራ ስለማናውቅ ያንን አጥኑና ንገሩን ይሉናል፡፡ እኛም እናጠናለን፡፡ ለምሳሌ አላቂ የሆኑ ምርቶችን መሸጥ በተመለከተ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ፍላጎት አለ፡፡ ስለዚህ እኛ ባቀረብንላቸው ጥናት መሠረት ለኢንቨስትመንታቸው የሚስማማቸውን መርጠው ለመሥራት ሲወስኑ፣ የተሟላ የቢዝነስ ዕቅድ ሠርተንላቸው ደረጃ በደረጃ እየተከታተልን እንመራላቸዋለን፡፡ ይህ ሥራችን ኢንቨስትመንትን የማማከር ሒደት ነው፡፡ ፋይናንስን በተመለከተ ደግሞ የቢዝነስ ባለቤቶች ለቢዝነሳቸው እንዴት ፋይናንስ እንደሚያደርጉ እናማክራቸዋለን፡፡ በተጨማሪም ገንዘብ ይዘው መጥተው ኢትዮጵያ ውስጥ እየሠሩ ካሉ ኩባንያዎች ላይ የባለቤትነት ድርሻ ወስደን ገንዘባችንን ኢንቨስት አድርገን አብረን ማደግ እንፈልጋለን የሚሉትን ደግሞ፣ እዚህ ካሉ ኩባንያዎች ጋር አገናኝተን ሥራዎቻቸውን እንዲቀጥሉ መንገዱን እናመቻቻለን፡፡ ለምሳሌ አንድ ኬንያ የሚገኝ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ በውኃ ሥራ ላይ ለተሠማራ ኩባንያ 12 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርጎ ሥራውን ቀጥሏል፡፡ ይህንን መሥራት ከበድ ይላል፡፡ ምክንያቱም ኢንቨስተሩ በቀላሉ ገንዘብ አይሰጥም፡፡ ባለቢዝነሱም በቀላሉ የባለቤትነት ድርሻውን አይሰጥም፡፡ 
ሪፖርተር፡- ዓለም አቀፍ ኤጀንሲዎችና ኩባንያዎች እዚህ ሲመጡ ሊሠሩባቸው ፍላጎት የሚያሳዩባቸው የንግድ ወይም የኢንቨስትመንት ዘርፎች የትኞቹ ናቸው?
አቶ ሔኖክ፡- እነዚህ ተቋሞች እዚህ መጥተው ኢንቨስት ለማድረግ ሲያስቡ፣ የታሸጉ ምግቦች፣ ማጠቢያ ምርቶች፣ የጥርስ ቡርሾች፣ የጥርስ ሳሙናዎችን ጨምሮ ቶሎ ቶሎ የሚሸጡና አላቂ የሆኑ ምርቶች ላይ መሰማራትን ይመርጣሉ፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ሁለተኛው ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላት አገር ስለሆነች ነው፡፡ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች የመሳሰሉት ምርቶች ላይም ለመሰማራት ፍላጎት ያሳያሉ፡፡ 
ሪፖርተር፡- የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚን እንዴት ነው የምታገለግሉት?
አቶ ሔኖክ፡- በብዙ መልኩ እናገለግላለን፡፡ ለምሳሌ የከብት መኖ ላይ የሚሠራ የግል ተቋም አለ፡፡ ተቋሙ ራሱ የፈጠራቸው አዳዲስ ሐሳቦችን አምጥቶ መኖ የማቅረብ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ ይህ ተቋም ገበያ ውስጥ ዘልቆ የሚገባበትን የፍራንቻይዚንግ ሞዴል እየሠራንለት ነው፡፡ ይህም ማለት አነስተኛና ጥቃቅን የሆኑ ፍራንቻይዞች በየክልሉ ተቋቁመው፣ ኩባንያው እያቀረበላቸው መኖው ወደ ገበሬው እንዲደርስ ለማድረግ እያማከርን ነው፡፡ ይህ ሲሆን የወተት ምርት እንዲጨምር ይረዳል ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ የወተት ምርታማነት ችግር አለ፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ ወተት የማምረት አቅም ስላላት፣ ያለውን ችግር ቀርፎ ትልቅ የወተት አምራች አገር እንድትሆን ማድረግ መቻል አለበት፡፡ ለምሳሌ ያህል አንዲት የኢትዮጵያ ላም በቀን የምትሰጠው የወተት መጠን በአማካይ 1.6 ሊትር ነው፡፡ የምትታለብበት ጊዜ ደግሞ በዓመት ስድስት ወር ነው፡፡ የአውሮፓ ላሞች ግን በቀን እስከ 40 ሊትር ይሰጣሉ፡፡ የሚታለቡበት ጊዜም ዘጠኝ ወር ይደርሳል፡፡ ይኼ ልዩነት በዝርያ፣ በመኖ፣ በሕክምናና በሌሎች ችግሮች አማካይነት የተፈጠረ ነው፡፡ ለዚህ መፍትሔ ለመስጠት ከአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት ጋር ለሦስት ዓመት የሚቆይ የሁለት ሚሊዮን ዶላር በጀት የተመደበለት ግብርና ተኮር (አግሪ ኢንኪዩቤሽን ቢዝነስ) ፕሮግራም ላይ ወተት፣ ሰሊጥና ማርን በተመለከተ በጋራ እየሠራን ነው፡፡ የዚህ ፕሮግራም ዓላማ ግብርና ነክ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ የግል ኩባንያዎች፣ ትክክለኛ የቢዝነስ ሞዴል ይዘው በጥሩ አመራር ተቋሞቻቸውን ካሳደጉ በኋላ፣ ዘርፉን እንዲያሻሽሉት ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ አርቲፊሻል ኢንሴሚኔሽን ላይ (በሰው ሠራሽ መንገድ የወንዱን እንስሳ የዘር ፈሳሽ ወስዶ ሴቷ ማህፀን ውስጥ ርቢው እንዲካሄድ መክተት) የሚሠራ ኩባንያ አለ፡፡ የኩባንያው አቅም ትንሽ ስለሆነ እኛ ከአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት ጋር ተረዳድተን ልናሳድጋቸው እየሠራን ነው፡፡ ይህን የምናደርገው ገበሬው ያለው ላም ጥሩ የወተት ምርትን ከሚሰጡ ጋር በማዳቀል ነው፡፡ በሰው ሠራሽ ሒደት ማዳቀል ቀርቶ ከአውሮፓ ላም እናምጣ ቢባል፣ ከባቢ አየሩ ስለማይመቻቸው ላሞቹ ይሞታሉ፡፡ አውሮፓውያኑ የሚታለበውን ወተት 40 ሊትር ያደረሱት ላሞችን እያዳቀሉ ነው፡፡ ስለዚህ ከአውሮፓ የወንዱ የዘር ፈሳሽ ይመጣና ከኢትዮጵያ ላም ጋር በርቢ እንዲቀላቀል ተደርጎ፣ 50 በመቶ የአውሮፓ 50 በመቶ የኢትዮጵያ ሆኖ የተዳቀሉ ላሞችን አበራክቶ የወተት ምርትን ማብዛት ነው፡፡ ሆለታ ላይ በዚህ መልኩ የተዳቀለች ቀነኒ የተባለች ላም አለች፡፡ ላሟ በቀን ከ25 እስከ 26 ሊትር ወተት ትሰጣለች፡፡ እንዲህ የበዛ ምርት እንዴት ማግኘት እንደሚቻል በተደረገው ምርምርና ተግባር አይተናል፡፡ ይህንን ወደ ንግድ መቀየር ነው፡፡ ሆለታ ላይ የአውሮፓውያን ላሞች ከኢትዮጵያ ጋር መዳቀል የጀመሩት የዛሬ 40 ወይም 45 ዓመት ነው፡፡ 98.6 ከመቶ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ላሞች ያልተዳቀሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ይህ እንዲሳካ መኖ ላይ፣ የማዳቀል ሥራ ላይና የተመረተው ወተት እንዴት እንደሚሰራጭ እናማክራለን፡፡ ሌላው ደግሞ አሜሪካ ውስጥ Center for International Private Interprise የሚባል ድርጅት አለ፡፡ ከእነርሱ ጋር ሆነን ንግድ ምክር ቤቶችን እንረዳለን፡፡ እነሱ ከእኛ ጋር ባላቸው ግንኙነት አማካይነት 47 የሚደርሱ ድርጅቶች ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ውስጥ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ስንሰጥ ቆይተናል፡፡ የቢዝነስ አሠራሩን ለማሻሻል የግል ዘርፉ ከመንግሥት ጋር መወያየት አለበት፡፡ መፈታት ያለባቸውን ችግሮች እንደ አገር አብረን መፍታት አለብን፡፡ ያን ለማድረግ ግን መጀመሪያ የንግድ ምክር ቤቶቹ አቅም መጎልበት አለበት፡፡ ከዚያም በተጨማሪ የአባላቶቹን አመለካከት፣ ችግርና ፍላጎት ለመንግሥት ለማቅረብ የንግድ ምክር ቤቶቹ አባላቶቻቸውን መወከል አለባቸው፡፡ እኛም እዚያ ላይ እየሠራን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አዳዲስ የሆኑ የቢዝነስ ሞዴሎችን ወደ ገበያ ለማቅረብና ወደ ንግድ ለመቀየር አብረን ከተለያዩ ከኩባንያዎች ጋር እየሠራን ነው፡፡ 
ሪፖርተር፡- ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከተመሰከረላቸው የሒሳብ አዋቂዎች ማኅበር (ACCA) ጋር በመተባበር የፋይናንስ ተደራሽነትን በተመለከተ ከባንክ፣ ከአምራቾችና ከሌሎች የንግድ ዘርፎች ከተውጣጡ የበላይ አካላት ጋር በየሦስት ወሩ የሚደረግ የቁርስ ላይ ፎረም አካሂዳችሁ ነበር፡፡ የፎረሙ ዓላማ ምን ነበር?  
አቶ ሔኖክ፡- የፎረሙ ዋና ዓላማ ታዳሚ ለነበረው የንግዱ ማኅበረሰብ መረጃን መስጠት ነበር፡፡ ባንክን በተመለከተ ምን አለ? ዓመታዊ የምርት ዕድገት እንዴት ነው? የዋጋ ግሽበት እንዴት ነው? የውጭ ምንዛሪ እንዴት ነው? የሚሉትንና የመሳሰሉት ነገሮችም የቀረበበት ነበር፡፡ ሌላው ዓላማ አንዱ ከሌላው የንግድ መስክ ጋር እየተገናኘ ሥራዎችን እንዴት አቀላጥፎ መሥራትና ማሻሻል እንደሚችል፣ እርስ በእርሳቸው ተዋወቀው እንዲገናኙ ማድረግ ነው፡፡ የፕሮግራሙ ሌላው ይዘት ደግሞ የቢዝነስ ማኅበረሰቡ ቢዝነሱን ሲሠራ ያለበትን ሁኔታ በመነጋገር፣ አዳዲስ አሠራሮችንና አዳዲስ ሐሳቦችን የሚለዋውጡበት፣ ፖሊሲን በተመለከተ ከመንግሥት ተቋማት ተወክለው ከመጡ ኃላፊዎች ጋር ቁርሳቸውን እየበሉ እንዲያወያዩ የሚደረግበት ፎረም ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ አሁን ባለበት ፍጥነት ወይም በበለጠ ፍጥነት እንዲያድግ ኢንቨስት ማድረግ አለብን፡፡ ኢንቨስት ለማድረግ ደግሞ ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ገንዘብ በሰፊው እንዲንቀሳቀስ ተደርጎ፣ ወሳኝ የሆኑ ኢንቨስትመንቶች ገንዘብ እንዲያገኙ ተደርጎ አገሪቱ ማደጓን የምትቀጥለው እንዴት ነው? የሚለውን ጥያቄ ለማስተናግድ የተዘጋጀ ፎረም ነው፡፡ ስለዚህ ለዚህ የቀረበው የመጀመሪያው ስሌት በባንኮች አማካይነት አገር ውስጥ ያለውን የገንዘብ ምንጭ የሚሰበሰብበት ዘዴን መፍጠር ነው፡፡ ሁለተኛው ስሌት ያንን የተሰበሰበ ገንዘብ ውጤታማ በሆነ መልኩ ኢንቨስት ማድረግ ነው፡፡ ሌላው ስሌት በመንግሥትም ትልቅ ቦታ የተሰጠው ደግሞ የቁጠባ ባህልን ማዳበር ነው፡፡ አንድ ገበሬ ትራስ ሥር 500 ብር ሲቀመጥ ለአገር አይጠቅምም፣ ገበሬውም ወለድ አያገኝበትም፣ ገንዘቡም አላግባብ ሊጠፋና ሊባክን ይችላል፡፡ ገበሬው ገንዘቡን ባንክ የማያስገባበት ምክንያት አገልግሎቱን እንደልብ በአቅራቢያው ስለማያገኝ ነው፡፡ ለዚህ መፍትሔ ለመስጠት ባንኮች በየቦታው ቅርንጫፎቻቸውን እየከፈቱ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ግን በጣም ሰፊ አገር በመሆኗ፣ የሕዝቦቿም ከፍተኛ ቁጥር በገጠር የሚኖር በመሆኑ፣ በእያንዳንዱ ቦታ ቅርንጫፍ ቢከፈት፣ ቅርንጫፎቻቸውን የሚያስተዳድሩበት ወጪ ስለሚበራከት አያዋጣቸውም፡፡ ስለዚህ ይህንን ለመታደግ ቅርንጫፍ ሳይከፈት ‹‹ቅርንጫፍ አልባ የባንክ አገልግሎት›› የሚል ዘዴን ስለመጠቀም በውይይቱ ወቅት ተንፀባርቋል፡፡ ይህንን የቴክኖሎጂ ስልት በመጠቀም (የዜድቲኢና የሁዋዌ የኔትዎርክ ማስፋፊያ ሲያልቅ የሞባይል ተጠቃሚ ቁጥር 50 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሏል) ገጠር ውስጥ ያለው ሕዝብ በቀላሉ ገንዘቡን በሞባይል ባንኪንግ ወደ ባንክ ማስተላለፍ ይችላል፡፡ በዚህ መንገድ የሚሰበሰበው ገንዘብ የባንክ ሥርዓት ውስጥ ሲገባ፣ ቢዝነሶች በብድር አማካይነት መዳበር ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ባንኮች ጋር ያለው ችግር ካላቸው የገንዘብ አቅም በላይ ደንበኛ ስላላቸው ማበደር አለመቻላቸው ነው፡፡ ስለዚህ በግብርም ይሁን በጡረታ እንዲሁም በሞባይል ባንኪንግ፣ መንግሥትና ሕዝቡ የሚያጠራቅሙት ገንዘብ ይኖራል ማለት ነው፡፡ ይህ ገንዘብ ለኢንቨስትመንት ይውላል፡፡ ፎረሙ ላይ የተነገረው ሌላው መንገድ ደግሞ፣ ከውጭ ቀጥተኛ የሆነ ኢንቨስትመንትን መሳብ ነው፡፡ ይህ መንገድ ውጭ አገር ያለውን ንዘብ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግ ነው፡፡ 
ሪፖርተር፡- በኢንቨስትመንትም ሆነ በአነስተኛ ደረጃ የቢዝነስ ሥራዎችን ከማስኬድ አኳያ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
አቶ ሔኖክ፡- ቢዝነስ ለመሥራት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አንደኛው ችግር ቢሮክራሲ ነው፡፡ አንድ ቢዝነስ ዓላማው ምርቱን ለገበያ ማቅረብ ነው፡፡ ነገር ግን ብዙውን ሰዓት ቢሮክራሲውን ለመወጣት ሲታገል፣ ውጤታማነቱና ምርታማነቱ ይቀንሳል፡፡ ቢዝነሱን የሚሠራው ሰው በየመንግሥት ቢሮው እየሮጠ ይህን አምጡልኝ፣ ይህን አድርጉልኝ እያለ የሚውል ከሆነ፣ የሚሠራበት ጊዜ ስለሚያጥር ውጤታማነቱ ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ትንንሾቹን ቢዝነሶች ያጠፋል፡፡ ትልልቆቹ አቅም ስላላቸው ተጨማሪ የሰው ኃይል ቀጥረው ይሠራሉ፣ ፉክክሩም ይቀንስላቸዋል፡፡ ከቢሮክራሲ ጋር አብረው የሚነሱት ጉምሩክ ላይ ያሉ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ የመብራት መቋረጥ፣ የሞባይል ኔትዎርክና የኢንተርኔት ችግሮች መፈራረቅም ተጨማሪ ችግሮች ናቸው፡፡ ደረጃቸው ይለያይ እንጂ እነዚህ ችግሮች ሁሉም ታዳጊ አገሮች ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ጥያቄው ለምን እነዚህ ችግሮች ኖሩ ሳይሆን እንዴት እየፈታናቸው እንሄዳለን የሚለው ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ጊዜ ቢፈጁም መስተካከል አለባቸው፡፡ ጊዜ እየሄደ በመጣ ቁጥር ተግዳሮቶቹ ዓይነታቸውን እየቀየሩ፣ ደረጃቸውንም ከፍ እያደረጉ ይሄዳሉ፡፡ ቢሆንም ግን ከሥር ከሥር አሠራሮች መስተካከል አለባቸው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት፡፡ 
ሪፖርተር፡- እስከዛሬ ድረስ ምን ያህል ኩባንያዎችን ወይም ዓለም አቀፍ ኤጀንሲዎችን አማክራችኋል?
አቶ ሔኖክ፡- በስድስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብዙ አማክረናል፡፡ ዓለም አቀፍ ኤጀንሲዎችን በተመለከተ ለምሳሌ ዓለም ባንክ፣ አፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ)፣ የእንግሊዙን የተራድኦ ድርጅት (ዲኤፍአይዲ)፣ የካናዳው ሲዳና የኔዘርላንድስ ኤስኤንቪ ይገኙበታል፡፡ እስካሁን በብዛት የሠራነው ከውጪዎቹ ጋር ነው፡፡ ከግሉ ዘርፍ ደግሞ ወደ 50 የሚጠጉ ኩባንያዎች ጋር ሠርተናል፡፡ 
ሪፖርተር፡- የምታማክሩበት ዋጋ እንዴት ነው?
አቶ ሔኖክ፡- ዋጋን በተመለተ የምለው ነገር ቢኖር ብዙ ሠራተኞች ስላሉን፣ ሰፊ ቦታ ይዘን ስለምንሠራና ወጪያችንም ሆነ የምንሰጠው አገልግሎት ከፍተኛ ስለሆነ የምናስከፍለው ዋጋ ርካሽ አለመሆኑን ነው፡፡ 
ሪፖርተር፡- ገንዘብ ኖሯቸው ምን መሥራት እንዳለባቸው የማያውቁ ሰዎች ቢመጡ ታማክሯችዋላችሁ?
አቶ ሔኖክ፡- እንደዚህ ዓይነት ደንበኞች በጣም ያጋጥሙናል፡፡ እኛ ግን ይህንን ሥሩ ብለን መንገሩ ላይ በጣም እንጠነቀቃለን፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንቨስትመንት አማራጭ ሞልቷል፡፡ እዚህ ያለው ገበያ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ሲመጡ ምንድን ነው የምታውቁት? ልምዳችሁ ምን ላይ ነው? ምንድን ነው ፍላጎታችሁ? የገንዘብ አቅማችሁ ምን ያህል ነው? የሚሉትንና ሌሎችንም ሁኔታዎች ባገናዘበ መልኩ ልናማክር እንችላለን፡፡ ይህን ሥሩ ብሎ ማለፍ ግን ኃላፊነት የጎደለው ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ ጊዜ ሰጥተን ተወያይተን ውሳኔ ላይ ልንደርስ እንችላለን፡፡ 
ሪፖርተር፡- ጥሩ ቢዝነስ ኖሯቸው ያንን ለማሳደጊያ ገንዘብ የሌላቸውንስ?
አቶ ሔኖክ፡- እንዲህ ዓይነት ደንበኞችም ይመጣሉ፡፡ ቢዝነሱን ጀምረውት ሁለት ሦስት አራት ዓመት ሠርተው ገበያው እንዳለ አሳይተው፣ ገበያውን መያዝ የቻሉ፤ ነገር ግን ቢዝነሳቸውን ለማሳደግ ያቃታቸው ኩባንያዎች አሉ፡፡ እንዲህ ዓይቶቹ ኩባንያዎች ገንዘብ የሚያገኙበትን ሁኔታ እናመቻቻለን፡፡ ገንዘብ እንደዚህ ያሉትን ኩባንያዎች ነው የሚፈልገው፡፡ 
ሪፖርተር፡- የቢዝነስ ሐሳቡ ኖሯቸው ሥራውን ያልጀመሩና ምንም ዓይነት ገንዘብ የሌላቸውንስ ገንዘብ  እንዲያገኙ ታመቻቹላችኋላችሁ?
አቶ ሔኖክ፡- እንደዚህ ዓይነት በጣም ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እጅግ በጣም ጥሩ የቢዝነስ ሐሳብ ያላቸው፣ ነገር ግን ገንዘብ የሌላቸው ሰዎች አሉ፡፡ አገልግሎታችን ውስን በመሆኑ ለሁሉም መድረስ አንችልም፡፡ ትልቁ ነገር ግን ሥራ ፈጣሪዎች ሁሌም ቢሆን ሐሳባቸውን ወደ ንግድ ቀይረው ሥራ የሚጀምሩበትን መንገድ አያጡም፡፡ የእኔም ምክር ገንዘቡን ከየትም ከየት አምጥተው ሥራውን ይጀምሩ የሚል ነው፡፡ 
ሪፖርተር፡- ፕሪሳይስ ወደፊት ወዴት ነው የሚያመራው? 
አቶ ሔኖክ፡- የፕሪሳይስ ዓላማ የምንሠራው ሥራ በሙሉ ልማት ላይ ያተኮረ፣ ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን መርዳት የሚችል ተቋም እንዲሆን ነው፡፡ ፕሪሳይስ በአገር ደረጃ ውጤታማ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነ አማካሪ ድርጅት ወደመሆንና አገልግሎቱንም የሚሰጥበትን አድማስ ወደ ማስፋት ያመራል፡፡ ማማከር ብቻ ሳይሆን እኛም ቢዝነስ ውስጥ የመግባት ፍላጎት አለን፡፡ ለምሳሌ አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ሪል ስቴትና ችርቻሮ ኢንዱስትሪ ውስጥ እየገባን አካሄዳችንን እያሰፋን ነው፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር