የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰልፍ ክልከላ ቀጭን መስመር

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መስከረም 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ለሁለተኛ ጊዜ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በበርካታ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ገለጻ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሰልፍ የማድረግ ሕገ መንግሥታዊ መብት ዙሪያ የሰጡት ምላሽ ግን አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ 
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤጥ እቁባይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረበችው ጥያቄ የሚከተለው ነበር፡- ‹‹የትግል እንቅስቃሴአቸውን አገር ውስጥ እያደረጉ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ጊዜዎች በተለያዩ ከተማዎች ከመንግሥት ምላሽ ይፈልጋሉ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ሰላማዊ ሰልፎችን አድርገዋል፡፡ ምንም እንኳን ሰልፎቹን አስመልክቶ በመንግሥት ኮሚኒኬሽን በኩል የተሰጡ መግለጫዎች ቢኖሩም ሰላማዊ ሰልፉ ላይ ከቀረቡ ጥያቄዎች ‹ምላሽ ያሻቸዋል፣ አግባብነት አላቸው› ብለው መንግስትም በተለያየ መንገድ ከሚሰበስባቸው መረጃዎች የወሰዷቸው ጥያቄዎች አሉ ወይ›› 
ለጥያቄው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው ምላሽ ለብዙዎች የሚያረካ ነበር ለማለት ያስቸግራል፡፡ ይልቁንም ምላሹ ሌሎች ተጨማሪ በርካታ ጥያቄዎችን አስነስቷል፡፡ በመልሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን፣ መንግሥታቸው በጫና ሐሳቡን የሚቀይር እንዳልሆነ፣ ተመሳሳይ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ከተጠየቁ መንግሥት አንድ ቦታ ላይ እንደሚያቆመው፣ የፓርቲዎች መብዛት ሰልፉን እንዳበዛው፣ ሰልፉ የሚታወቀው ውጭ ባሉ የእቅዱ ባለቤቶች እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ 
ሰላማዊ ሰልፍ እንደ ሕገ መንግሥታዊ መብት
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ‹‹ተቃዋሚዎች ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸው መብት እንጂ ማንም በችሮታ የሰጣቸው አይደለም፡፡ እንደ መንግሥት ኃላፊነታችን ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ስለሆነ ያንን እንዲያስተናግዱ ማድረግ ነው፤›› በማለት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ሕገ መንግሥታዊ የዜጐች መብት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 30 ላይ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብትን አስመልክቶ የሚከተለውን ያሰፍራል፤ ‹‹ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡ ከቤት ውጭ የሚደረጉ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሰልፎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች በሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ለማድረግ ወይም በመካሄድ ላይ ያለ ስበሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ሰላምን፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥሱ ለማስጠበቅ አግባብ ያላቸው ሥርዓቶች ሊደነገጉ ይችላሉ፡፡››
ሕገ መንግሥት በተጨማሪም የወጣቶን ደኅንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስምን ለመጠበቅ፣ የጦርነት ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሰብአዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎችን ለመከላከል ሲባል በሚወጡ ሕጐች ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት ሊገደብ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያለው መብት በተለያዩ ምክንያቶች ሊገደብ መቻሉ የተገለጸ ቢሆንም፣ ሕገ መንግሥቱ ከመጽደቁ በፊት በሽግግሩ መንግሥት የወጣው የሰላማዊ ስብሰባና ሕዝባዊ ፖለቲካዊ ስብሰባዎች ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 3 (1983 ዓ.ም.) ጥቂት የገደብ ምክንያቶችን ብቻ ያስቀምጣል፡፡ 
ይኸው አዋጅ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ስለ ሰላማዊ ሰልፉ 48 ሰዓት አስቀድሞ በጽሑፍ ማሳወቅ፣ በማስታወቂያው ውስጥ ስለ ሰልፉ ባሕሪ፣ ስለሚወስደው ጊዜ፣ ይሳተፋል ተብሎ ስለሚጠበቀው የተሳታፊ ብዛት፣ ስለሰልፉ ዓላማና ሰልፉ ስለሚካሄድበት ቦታ ማካተት እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም እንደ ኤምባሲ፣ ቤተ ክርስቲያን፣ መስጊድና የገበያ ቦታዎች ከሚገኙበት 100 ሜትር ርቆ ሰላማዊ ሰልፍ መካሄድ እንደሚኖርበትም ተደንግጓል፡፡ 
ሕገ መንግሥቱን በቀጥታ ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ ከመሆኑ አኳያ አዋጁ የያዘው ድንጋጌ በተሻለ በሚመለከታቸው አካላት ቢታወቅም መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን የገደብ ምክንያቶች በመጠቀም የሽግግር ዘመኑን አዋጅ የመቀየር አዝማሚያዎች እያሳየ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜያት የተካሄዱት ሰላማዊ ሰልፎች ጥያቄዎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ጣልቃ የሚገቡና ብሔራዊ ደኅንነትን የሚጐዱ እንደሆኑ በመንግሥት መጠቀሱ ይታወቃል፡፡ ስብሰባዎችንና ሰልፎችን ለመከላከልም ‹‹በሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር ይፈጥራል›› የሚል ምክንያት የተጠቀመ ሲሆን ይህ የክልከላ ምክንያት በሕገ መንግሥቱ የተጠቀሰ ነው፡፡ ዝርዝር ሕጐች ከበላይ ሕጐች ጋር እስካልተጋጩ ድረስ በቅድሚያ ተፈፃሚነት ይኖራቸዋል፡፡ 
የአዲስ አበባ አስተዳደር ሰላማዊ ሰልፎችን የሚገዛ አዲስ ሕግ ማውጣቱን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢገልጹም፣ አስተዳደሩ ያወጣው መመሪያ አዋጅ ቁጥር 3/1983 ዓ.ም.ን ለማስፈጸም መሆኑን በመግለጽ አስተባብሏል፡፡ የአንድነት ፓርቲ አባላት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በዝግጅት ላይ በነበሩበትና በራሪ ወረቀቶችን በሚበትኑበት ጊዜ ተይዘው ሲታሰሩ ‹‹ፈቃድ የላችሁም›› እንደተባሉ ገልጸዋል፡፡ አዋጅ ቁጥር 3/1983 ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ለመንግሥት ኃላፊዎች ማሳወቅ ብቻ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ መመሪያው ግን ፈቃድ ቀድሞ ማግኘትን ቅድመ ሁኔታ ከማድረጉም ሌላ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 ላይ የተዘረዘሩትን የገደብ ምክንያቶች እንደሚያጣቅስ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የበታች ሕጐች የበላይ ሕጐችን የመዘርዘርና የመተንተን እንጂ አዲስና የሚጋጩ ድንጋጌዎችን መያዝ አይችሉም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጀመሪያው ዙር ጋዜጣዊ መግለጫቸው ስለ ብሔራዊ መግባባት ሲጠየቁ፣ ‹‹ብሔራዊ መግባባት የሚጀምረው በሕገ መንግሥቱ መግባባት በመፍጠር ነው›› ብለው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በአንድ አመለካከትና አስተሳሰብ ላይ ተጨፍልቆ የተፈጠረ ሕዝብ ያለባት አገር አለመሆኗን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ በኢትዮጵያ በሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ላይ ልዩነት ያላቸው ግለሰቦችና ፓርቲዎቸ ቢኖሩም በሕገ መንግሥቱ ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት አለ ብለው እንደሚያምኑ ገልጸው ነበር፡፡ 
የአዲስ አበባ አስተዳደርን ውሳኔ ፀረ ሕገ መንግሥት ያሉት ፓርቲዎች አስተዳደሩን ለመክሰስ እቅድ እንዳላቸው ያሳወቁ ሲሆን፣ ይህ ውሳኔ ፓርቲዎችን በአንዳንድ አንቀጾች ቅሬታ ያላቸው አካላት አልያም ሕገ መንግሥታዊ መግባባት ለመፍጠር ያለው ተግዳሮት አካላት ስለመሆናቸው ግን እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም፡፡ 
‹‹የተሰለቹ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች›› 
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚጠይቁት ጥያቄ የሚታወቅና አዲስ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ቤት ቁጭ ብሎ መጠየቅና አደባባይ ወጥቶ መጠየቅ ነው ልዩነቱ›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሰልፍ የመውጣት ዋናው ዓላማ ጥያቄዎቹን ለሕዝቡ ማሰማት በመሆኑ ሕዝቡ ስለሰማቸው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሒደቱ መሳካቱን አመልክተዋል፡፡ ‹‹ድምፃቸውን ማሰማትና ሕዝቡ እንዲያውቅ ማድረግ ችለዋል›› ሲሉ የቀጠሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጥያቄያቸው መንግሥታቸው ከ100 ጊዜ በላይ መልስ መስጠቱን ጠቁመዋል፡፡ 
ፓርቲዎቹ የተሰለቹና ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን የሚያቀርቡት ጫና ፈጥረው መንግሥት ሐሳቡን እንዲቀይር ለማድረግ አስበው እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ ‹‹በሒደቱ ውስጥ መንግሥት ትክክለኛና እውነተኛ የሆነ መሆን ያለበትን ምላሽ አስቀድሞ የሰጠ ስለሆነ አሁን ጫና ተፈጥሮበት የሚቀይረው ነገር የለም›› ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ በኢትዮጵያ ካሉት 99 የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ ሲተው ሌላው እየመጣ ተመሳሳይ ጥያቄ መጠየቁ መንግሥት በየእሑዱ ጥበቃ እያደረገ ወደ መሰላቸት እንደሚመጣ አመልክተዋል፡፡ 
‹‹ዴሞክራሲ ስለሆነ እንታገሳለን፡፡ የሆነ ሆኖ በጣም ብዙ ሥራ ያስፈታል፡፡ መታወቅ ያለበት አንድ ጥያቄ በተደጋጋሚ የሚጠየቅ ከሆነ እኛም አንድ ቦታ ስንደርስ ለዚህ ጥያቄ እኮ ብዙ ጊዜ መልስ ሰጥተናል፡፡ ጥያቄው ይህ ከሆነ ‹ሰልፉ ምንድነው ትርጉሙ› ብለን የምናቆምበት ደረጃ እንደርሳለን፡፡ ሰልፍ ለዘለዓለም የሚካሄድበት አገር ያለ አይመስለኝም፤›› በማለት መንግሥታቸው ሰልፎቹ ላይ ገደብ እንደሚያደርግ አሳስበዋል፡፡ 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሰመሩት ቀጭን የሰላማዊ ሰልፍ እገዳ መስመር በጥያቄዎቹ ተደጋጋሚነትና አሰልቺነት ላይ መመሥረቱ በርካታ የሕገ መንግሥት ምሁራንንና የፖለቲካ ተንታኞችን ትኩረት ስቧል፡፡ የዴሞክራሲ መገለጫ እስከሆነ ድረስ ድግግሞሹንና አሰልቺነቱን መንግሥት ሊቋቋምና ሊችለው እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ 
በአዋጅ ቁጥር 3/1983 ዓ.ም. መሠረት ስለ ሰላማዊ ሰልፉ ባሕሪ፣ የሚወስደው ጊዜ፣ የተሳታፊዎች ብዛትና ሰልፉ የሚካሄደበት ቦታ የሚገለጸው መንግሥት ለጥበቃ እንዲዘጋጅ ለማድረግ ነው፡፡ ተደጋጋሚ ሰላማዊ ሰልፍ ሲደረግ ጥበቃ ለማድረግ የጥበቃ ኃይሉ ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ መጥፋቱ የማይቀር ነው፡፡ ይህ ተገቢነት ያለው የሰላማዊ ሰልፍ ገደብ መሆን አይችልም ወይ ባሉት ጥያቄ የቀረበለት አንድ የደኅንነት ባለሙያ ‹‹ለግብር ከፋዩ ፍላጐትና ጥቅም ሰልፉ እስከተካሄደ ድረስ ወጪ ይበዛብኛል ብሎ መንግሥት ገደብ ሊያደርግ አይገባም፡፡ ሕዝቡ ሲሰለቸው ለሰላማዊ ሰልፉ አይወጣም፡፡ ይህ በራሱ ወጪን ይቀንሳል፣ ዴሞክራሲንም ያረጋግጣልም፤›› ሲሉ መልሰዋል፡፡ 
ፓርቲዎቹ መብዛታቸውም የፌዴራል ሥርዓቱ የሚያበረታታው በመሆኑ የሰላማዊ ሰልፎች መብዛት ከፓርቲዎች መብዛት ጋር በአሉታዊ መልኩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መነሣቱ ያልተዋጠላቸው በርካታዎች ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም መቶ ጊዜ መልሰናል፣ ‹‹99 ፓርቲዎች አሉ›› ለማለት የተጠቀሙበት አባባል፣ ከዚህ ቀደም ከኤርትራ ጋር ለመደራደር ‹‹50 ጊዜ ሞክረናል›› በማለት ከገለጹበት ሁኔታ ጋር ተዳምሮ የሚጠቅሷቸው ቁጥሮች ምሳሌዎች መሆናቸውን በግልፅ ስለሚያሳዩ ለሰሚዎች እንደ ትክክለኛ ቁጥር እየተወሰዱ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲጠነቀቁ አስተያየት ሰጪዎች መክረዋል፡፡   
ውጭ አገር የታቀዱ ሰላማዊ ሰልፎች
‹‹ሰልፍ የሚያደርጉበት ዕቅድ የራሳቸው ዕቅድ አይደለም፡፡ አቅደው የሰጧቸው   ባለቤቶች አሏቸው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ውጪ አገር ያሉት የዕቅዱ ባለቤቶች ለአገር ውስጥ ፈጻሚዎቹ ሥልጠና ሰጥተው እንዳሰመሯቸው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በዚህ መንገድ ብትሄዱ መንግሥትን ትጠረቅቃላችሁ ትወጋላችሁ፣ አጣብቂኝ ውስጥ ትከታላችሁ›› ብለው የተጀመረው ሰላማዊ ሰልፍ ሁለቱንም በማሰልቸት እንደሚጠናቀቅ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም የዕቅዱ ባለቤቶች በፈፃሚዎቹ ጥያቄዎቹን ለመንግሥት እንዲያቀርቡ መጠየቃቸውን ሁሉ አመልክተዋል፡፡ 
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መሰል ወቀሳዎችን  በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ማቅረባቸው የተለመደ ሲሆን፣ ለዚህ ወቀሳና ትችት ግን ምንም ዓይነት ማስረጃ አያቀርቡም፡፡ እነዚህን መረጃዎች እየተነተኑና እያረጋገጡ የሚያጠኑና የሚያሰራጩ ነፃ የሆኑ የምርምር እንዲሁም የሲቪል ማኅበራት በብዛት በማይገኙበት አገር መሰል ትችቶች በሥልጣን ተዋረዱ ዝቅተኛ ቦታ ላይ ባሉ ባለሥልጣናትም እንደ ምሳሌ እንዳይወሰድ አስተያየት ሰጪዎቹ ሥጋታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጥያቄዎቹን ካቀረበው ፓርቲ ይልቅ ጥያቄዎቹ ላይ አትኩረው ቢመልሱ የተሻለ ነበር ሲሉ አስተያየት የሰጡ ዜጐች የፓርቲውን ባህል ይቀይሩታል   ተብለው የተጠበቀ ቢሆንም በተቃራኒ እየተዋጡ እንዳይመጡ ያላቸውን ሥጋት ጠቁመዋል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር