በሃዋሳ ከተማ ይታይ የነበረው ወንጀል መቀነሱን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 29 ፣2006 (ኤፍ ቢ ሲ) ከዚህ ቀደም በሃዋሳ ከተማ ለነዋሪውና ወደ ከተማዋ ለሚገቡ ጎብኝዎች ስጋት ይሆን የነበረው የዘረፋና የንጥቂያ ወንጀል በአሁኑ ሰአት በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
የሃዋሳ ከተማ በተለይ ከዚህ ቀደም በራሱ በከተማው ነዋሪ ላይና ለጉብኝት በሚመጡ እንግዶች ላይ በሚከሰቱ የቅሚያና ዘረፋ ወንጀል ምክንያት ፤ በተለይ ደግሞ ከመሸ በኋላ በሰዎች ላይ ስጋትን የምትፈጥር ከተማ ለመባል በቅታ ነበር ።
ዘረፋ ፣ ንጥቂያ ፣ የነብስ ማጥፋት እና የሌሊት የቤት ዝርፊያ በብዛት ይስተዋሉ የነበሩ ወንጀሎች መሆናቸውን የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ለማ አሹራ ተናግረዋል።
በተለይም ወንጀሎች በከተማዋ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ለህብረተሰቡ አገልግሎትን በሚሰጡ ባጃጆች አማካኝነት እንደሚፈፀሙም ነው ዋና ኢንስፔክተር ለማ የሚናገሩት።
ከሁለት አመት ወዲህ ግን ፖሊስ ፣ ህብረተሰቡ እና የከተማው አስተዳደር ባደረጉት ጥረት ፥ ለወንጀሉ መበራከትና ለእንግዶች በሰላም ወጥቶ መግባት ስጋትን በመፍጠር አስተዋፅኦ ያደርጉ የነበሩ 5 ሺህ ባጃጆች በህግና ስርአት እንዲመሩ ማድረግ ተችሏል ።
ይህም ባጃጆችን በማህበር በማደራጀትና በስርአት በመመዝገብ ፥ ምሽት ከአራት ሰአት በኋላ ህመምተኛ ይዘውና ለአስቸኳይ ነገሮች ብቻ እንዲንቀሳቀሱ ማድረጉንም ይናገራሉ።
ለህብረተሰቡ የተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት መጀመር ለውጤቱ መገኘት ከፍተኛ አስተዋጽ እንዳደረገም ነው አዛዥ የተናገሩት።
ከከተማው ፖሊስ መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ፤ ዐበ200 ዓ.ም 1229 እንዲሁም በ2005 ዓ.ም ደግሞ 1 ሺህ 69 ወንጀሎች ተፈጽመዋል።
በ2005 ዓ.ም አንደኛ ሩብ አመትም 241 ወንጀሎች የተፈጸሙ ሲሆን ፥ በ2006 አመተ ምህረት በተመሳሳይ ወቅት ላይ ደግሞ 159 ወንጀሎች መፈጸማቸውን መረጃው ያሳያል ።
የከተማዋ ከንቲባ አቶ ዮናስ ዮሴፍ ፥ በከተማዋ ውስጥ ያለው የወንጀል ሁኔታ ከኢንቨስትመንትና ከስብሰባዎች ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ ።
እንደ አቶ ዮናስ ገለጻ ፥ ኢንቨስተሮች የከተማዋን የወንጀል ሁኔታ እንደመጀመሪያ መስፈርት አድርገው ይጠይቃሉ ። ይህን ሁኔታ ለማሻሻል በሚገባ ስሰተሰራ በአሁኑ ሰአት ወንጀል የከተማዋ ስጋት አለመሆኑን በመጠቆም።
የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው የነበረውን ስጋት በማንሳት በአሁኑ ሰአት ያለው ሁኔታ  ፍጹም አስተማማኝ መሆኑን ነው የሚመሰክሩት።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር