ዩኤን ኤድስ 2030 የኤድስ ማብቂያ ሊሆን ይችላል አለ

የተባበሩት መንግስታት የኤድስ ድርጅት (UNAIDS) ከቀናት በፊት የለቀቀው ሪፖርት እ.ኤ.አ በ2030 ኤችአይቪ ኤድስ በቁጥጥር ስር ሊውል የሚችልበት ዕድል መኖሩን አስታውቋል፡፡
ሪፖርቱ እንደሚያሳየው በህጻናትና አዋቂዎች አዳዲስ የኤችአይቪ ኢንፌክሽኖች ከ2001 ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንድ ሶስተኛ ቀንሰዋል፡፡ 
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ በኤችአይቪ የተያዙ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር 2.3 ሚሊዮን ሲሆን ይህ በ2001 ከታየው አዳዲስ ኢንፌክሽን 33 በመቶ መቀነሱን ያሳያል፡፡ በዚሁ ዓመት በቫይረሱ የተያዙ ህጻናት ቁጥር 260 ሺህ ሲሆን ከ2001 ጋር ሲነጻጸር የ52 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ የአዳዲስ ኢንፌክሽኖች ቁጥር የቀነሰው በስፋት እንዲዳረስ በተደረገው በፀረ-ኤችአይቪ መድሃኒት ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ 
የፀረኤችአይቪ መድሃኒት ተደራሽነት ከ2005 ወዲህ በኤችአይቪ ምክንያት የሚደርስ ህልፈተ ህይወትም 30 በመቶ እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ 
ከ2011 እስክ 2012 ባለው ጊዜ ውስጥ 20 በመቶ ለሚሆኑት ሰዎች (9.7 ሚሊዮን) ፀረኤችአይቪ መድሃኒት ተደራሽ መሆኑን የዩኤን ኤድስ ዳይሬክተር ሚሼል ሲዲቤ ገልጸዋል፡፡ ድርጅቱ በ2015፤ 15 ሚሊዮን ሰዎችን የፀረ-ኤችአይቪ ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ እንዳለው ይታወቃል፡፡ በሪፖርቱ እንደተመለከተው በ2012 ዓለም ላይ ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎች ቁጥር 35.3 ሚሊዮን ነበር፡፡ 
ከኤችአይቪ ህክምና ጋር በተያያዘ የታዩ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን መሠረት በማድረግ የዩኤን ኤድስ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሉዊስ ሎሬስ የኤችአይቪ ኤድስ ማብቂያ ከ2030 በፊት እንደሚሆን ግምታቸውን መስጠታቸውንም የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል፡፡ 
‹‹የኤችአይቪ ወረርሽኝ ማብቂያ ላይ መድረስ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ህክምናም አዳዲስ ኢንፌክሽኖችን የመቆጣጠሪያ ዘዴዎችም አሉን፡፡ ስለዚህም ያለምንም ጥርጥር መሻሻል እያስመዘገብን ነው›› ብለዋል፡፡ 
ምክትል ዳይሬክተሩ በተጠቀሰው ዓመት ኤድስ ሙሉ በሙሉ ይጠፋል ማለት ሳይሆን ዛሬ ላይ እንዳለው በወረርሽኝ ደረጃ አይኖርም ብለው እንደሚያምኑም ለኤኤፍፒ ገልጸዋል፡፡ 
እስካሁን ለኤችአይቪ ፈዋሽ መድሃኒት ባይገኝም ቫይረሱን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተለያዩ መድሃኒቶች ተገኝተዋል፡፡ በደም ውስጥ የቫይረሱን መጠን ዝቅ ለማድረግ፣ የጤንነት ሁኔታን ለማሻሻልና ኢንፌክሽኖችን ለመቀነስ የሚያስችሉ 25 ዓይነት ፀረ-ኤችአይቪ መድሃኒቶች በአሜሪካው ኤፍዲኤ (FDA) እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ 
በዓለም ላይ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ከሚገኝ 3.3 ሚሊዮን ህጻናት 90 በመቶ የሚሆኑት በሚገኙበት ሰብሰሀራ አፍሪካ በቫይረሱ ተይዘው የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ በሪፖርቱ ተቀምጧል፡፡   

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር