ወጣቱን በማብቃት ላይ መሠራት አለበት


የኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት ከ85 ሚሊዮን በላይ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አገሪቱ ካላት የሕዝብ ብዛት ውስጥ ከሁለት ሦስተኛ በላዩ ወጣቶች ናቸው፡፡
ይህ በሚገባ የሚሠራበት ከሆነ እጅግ መልካም አጋጣሚ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ምክንያቱም ወጣቶች የማኅበረሰቡ የጀርባ አጥንት መሆናቸውን በማስመስከራቸው ነው፡፡ 
ኢትዮጵያ እንደ አገር ይህንን የወጣት ኅብረተሰብ ፍሬያማ በማድረግ ልታተርፍበት ትችላለች፡፡ መንግሥት ይህንን በመገንዘብ የወጣቶች ፖሊሲ ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን መንግሥት የአገሪቱን ወጣቶች አቅም በሚገባ አደራጅቶ እየተጠቀመበት ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ይህን ግዙፍና ጠንካራ የሆነ የኅብረተሰብ አካል እንዴት ሊጠቀምበት እንደሚችል ማሰብ ይገባዋል፡፡ 
እንደ አሜሪካ ባሉ የዓለማችን ኃያላን አገሮች ወጣቶች ያላቸው ተፅዕኖ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለአብነት እንኳን በዓለማችን በሰፊው የሚታወቀው የፌስቡክ ማኅበረሰብ ድረ ገጽ መሥራችና ባለቤት ወጣት አሜሪካዊ ነው፡፡ የ29 ዓመቱ ማርክ ዘከርበርግ በፌስቡክ ድረ ገጽ በኩል ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን ማፍራት ችሏል፡፡ በዚህም ከአሜሪካ አልፎ በዓለማችን ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰብ አድርጐታል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ለዚህ ወጣት ጉዞ መሳካት በርካቶች እጃቸው አለበት፡፡ ለአብነት የፌስቡክን ባለቤት አነሳን እንጂ በአሜሪካ ለአገርም ሆነ ለሕዝባቸው ኩራት የሆኑ በርካታ ወጣቶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ወጣቶች ከአገራቸው አልፈው በዓለማችን ላይ እንደዚህ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ ያስቻላቸው ዓቢይ ጉዳይ ደግሞ፣ ለወጣቶች ምቹ የሆነ ፖለሲ በአገራቸው በመኖሩ ነው፡፡ ታዲያ እኛም እንደ አገር ከዚህ ልንማር የምንችላቸው ነገሮች አሉ፡፡ 
ኢትዮጵያ በፖሊሲ ደረጃ የወጣቶች ፖሊሲ ቀርፃ መንቀሳቀሷ የሚበረታታ ቢሆንም፣ የፖሊሲው ተግባራዊነት ግን ሊፈተሽ ይገባዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ወጣቶች በአገሪቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምኅዳር ውስጥ ብቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የማብቃት ሥራ መሠራት አለበት፡፡ አሁን አሁን መንግሥት ወጣቶችን በማደራጀት የተለያዩ ሥራዎች እንዲሠሩ እያደረገ ይገኛል፡፡ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንፃር ይህ ጅማሬ የሚበረታታ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም አገሪቷ ያላትን የወጣት ኃይል በሚገባ እየተጠቀመችበት ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ 
በሌላ በኩል በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የሚታዩት ወጣቶች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ መንግሥት ለወጣቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚንቀሳቀስ በየጊዜው ቢለፍፍም፣ በተግባር ያለው እውነታ ግን ከዚህ የሚቃረን ነው፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደተለመደው ‹‹የአዛውንቶች ክበብ›› ይመስላሉ፡፡ በዚህ አካሄድ ከቀጠልንም ወደፊት አገር ተረካቢ የሚሆኑ ወጣቶችን ለማፍራት ያስቸግረናል፡፡
መንግሥት ኢትዮጵያ በተወሰኑ ዓመታት መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮችን እንድትቀላቀል በማቀድ እየሠራ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግሥት በተለይ የአገሪቱ ጠላት ነው የሚለውን ድህነት ለማስወገድ ቆርጦ ተነስቷል፡፡ ይህን በማድረጉ ሒደት ውስጥ ግን ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል ዋነኛ ተዋናይ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በፖሊሲ ደረጃም የዕድገት የጀርባ አጥንት ሊሆኑ የሚችሉ ወጣቶች በሚገባ ሊካተቱ ይገባቸዋል፡፡ ይህም ማለት የወጣቶች ተሳትፎ ወረቀት ላይ ከመስፈር የዘለለ መሆን አለበት፡፡ 
ከዚህ ባሻገር በአገራችን የሚገኙ በርካታ ወጣቶች በውስጣቸው የያዙትን ራዕይ ወልደው ሊያሳድጉበት የሚችሉበት ዕድል ሊመቻችላቸው ይገባል፡፡ በርካቶች አገሪቱን ወደቀጣዩ ደረጃ ሊያሻግራት የሚችል ሐሳብ ኖሯቸው፣ የሚረዳቸው ባለማግኘታቸው ብቻ እየተጨናገፉ ይገኛል፡፡ ወጣቶች በአገራቸው የሚሠሩበት ከባቢ ባልተፈጠረላቸው ቁጥር ልባቸው ወደ ሌሎች አገሮች መሸፈቱ አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ አገሪቱን ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል፡፡ ከዚህም ባሻገር የኅብረተሰቡ አካል የሆኑት ወጣቶችን ላልተፈለገ ስደትና እንግልት ይዳርጋል፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታም የአገራችን ወጣቶችን የምዕራብ ዓለም አገሮች በመቀበል ሲጠቀሙባቸው አይተናል፡፡ በእነዚህ አገሮችም በተለያዩ ሙያዎች የታወቁ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለወጣቱ አመቺ የሆነ ፖሊሲ በመቅረፅ የወጣቶችን ስደት ማስቆም አለበት፡፡ 
ለወጣቶች ምቹ የሥራ ዕድል የመፍጠር ኃላፊነት ግን የመንግሥት ብቻ አይደለም፡፡ በተለይ የፋይናንስ ተቋማት ለሥራ ፈጣሪ ወጣቶች የተለየ የብድር ማዕቀፍ ሊያዘጋጁ ይገባል፡፡ ወጣቶች ብዙውን ጊዜ የፋይናንስ ተቋማቱ ለማበደር እንደማስያዣ የሚጠቀሙበት ኮላተራል ባይኖራቸውም፣ የሚያቀርቡት የሥራ ፈጠራ ሐሳብ አገርንና ሕዝብን የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ ብድሩን የሚያገኙበት መንገድ ሊመቻችላቸው ይገባል፡፡ ይህንንም በማድረጋቸው የበርካታ ወጣቶችን የሥራ የመፍጠር አቅም ማጐልበት ይችላሉ፡፡
ወጣቶችን የማብቃት ሥራ ሲሠራ ግን ሁሌም ትምህርት ቤቶች ወሳኙን ሚና ይጫወታሉ፡፡ የአገሪቱን ወጣቶች ቀርፀው የሚያወጡ ትምህርት ቤቶች በሚገባ ሊፈተሹ ይገባል፡፡ ትምህርት ቤቶች የልቀት ማዕከል እንደመሆናቸው መጠን ያለባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ ያሉበት መንገድ መገምገም አለበት፡፡ የአገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ ከብዛት ባለፈ በጥራት ላይ በመሥራት በርካታ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን ማፍራት ይገባዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ ወጣቶች በተገቢው መንገድ ሊዝናኑባቸው የሚገቡ የተለያዩ የመዝናኛ ማዕከላት በየሥፍራው መኖር አለባቸው፡፡ ያለበለዚያ ግን በየቦታው እንደአሸን በፈሉት ጫትና ሺሻ ቤቶች ጊዜያቸውን በማሳለፍ በአጭሩ ሊቀጩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ መንግሥት የአገር ተረካቢ የሆኑት ወጣቶች ሊዝናኑባቸው የሚገቡ ማዕከሎችን በመገንባት ሊታደጋቸው ይገባል፡፡
በአጠቃላይ ወጣቱን የማብቃት ኃላፊነት የቤተሰብ፣ የኅብረተሰብና የመንግሥት በመሆኑ፣ ሁሉም ተቀናጅተው ይህንን የሰው ኃይል ፍሬያማ በማድረግ አገሪቱን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል፡፡ ወጣቶችም በአገሪቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምኅዳር በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ዕድሉና መንገዱ ይመቻችላቸው፡፡ 
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/editorial/item/3477-%E1%8B%88%E1%8C%A3%E1%89%B1%E1%8A%95-%E1%89%A0%E1%88%9B%E1%89%A5%E1%89%83%E1%89%B5-%E1%88%8B%E1%8B%AD-%E1%88%98%E1%88%A0%E1%88%AB%E1%89%B5-%E1%8A%A0%E1%88%88%E1%89%A0%E1%89%B5

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር