የደቡበ ክልል ሦስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሮች ከኃላፊነት ተነሱ

የደቡብ ክልልን ከሚመሩት አራቱ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሮች መካከል ሦስቱ ከኃላፊነት መነሳታቸውን ምንጮች ገለጹ፡፡
ለሦስቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መነሳት ከነሐሴ 15 እስከ 19 ቀን 2005 ዓ.ም. ከተደረገው ግምገማ ጋር የተያያዘ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮች፣ ለእያንዳንዳቸው መነሳት የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን ያስረዳሉ፡፡ ከኃላፊነታቸው ከተነሱት መካከል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ ከሆኑ አንድ ዓመት ያልሞላቸው አቶ ታገሠ ጫፎ ሲሆኑ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ አሰፋና በተመሳሳይ ማዕረግ  የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳኒ ረዲ ናቸው፡፡
የአቶ አለማየሁ አሰፋና የአቶ ታገሠ ጫፎ መነሳት የተጠበቀና ውስጥ ለውስጥ ሲነገር የቆየ መሆኑን፣ ያልተጠበቀው ግን የአቶ ሳኒ ረዲ ነበር በማለት አስተያየት የሰጡት የደኢሕዴን አባልና ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ የክልሉ ባለሥልጣን፣ ሦስቱም ሹማምንት የተገመገሙት በተለያዩ ችግሮች እንደሆነ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ ‹‹አቶ ታገሠ በአመራር ብቃት ማነስ በተደጋጋሚ ይተቹ እንደነበር ገልጸው፣ አቶ አለማየሁና አቶ ሳኒ ደግሞ አላስፈላጊ ‹‹ኔትወርክ›› በመፍጠር ብልሹ አሠራር በማስፈናቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡ 
በግምገማው የተሳተፉ ምንጮች ደግሞ በተለይ አቶ አለማየሁ ባለፈው ዓመት መጨረሻ አካባቢ በተወከሉበት ዳውሮ ዞን ከፍተኛ ተቃውሞ ሲነሳባቸው የኃይል ዕርምጃ እንዲወሰድ ማድረጋቸው እንደ አንድ ምክንያት መነሳቱን ያስረዳሉ፡፡
በሌላ በኩል የክልሉ የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑ አንዳንድ አስተያት ሰጪዎች ለሦስቱም ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከኃላፊነት መነሳት የአመራር ብቃት ማነስ ብቻ ሳይሆን የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ችግሮች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡ 
በሥነ ሕይወት ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በዓሣ ዕርባታ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙት አቶ ታገሠ ጫፎ እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ከ2000 እስከ 2003 ዓ.ም. መስከረም ድረስ ብቸኛው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የንግድ ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ፣ እንዲሁም ወደ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊነት እስከተዛወሩበት ህዳር 2005 ዓ.ም. ድረስ አራተኛው ምክትል ርዕስ መስተዳድር ሆነው ቆይተዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በላይ በኃላፊነት የቆዩበት ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ አንዳንድ ሠራተኞች፣ ‹‹ከአራት መቶ በላይ ሠራተኞች ያሉበትን ቢሮ ሲመሩ አንድም ቀን ሠራተኞችን ሰብስበው አናግረው ችግር የፈቱበት ጊዜ አልነበረም፡፡  ግንኙታቸው ከሥራ ሒደት ባለቤቶች ጋር ስለነበር ዕርምጃም የሚወስዱት ከነዚያ ሰዎች በሚያገኙት መረጃ ብቻ ነበር፤›› በማለት በርካታ ሠራተኞች ሳያውቁዋቸው እሳቸውም የሚያስተዳድሩዋቸውን ሠራተኞች በቅጡ ሳያውቁ መነሳሳታቸውን ይናገራሉ፡፡
እስከ መስከረም 2003 ዓ.ም. ድረስ የደኢሕዴን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመሆን የክልሉን የፖለቲካ እንቅሰቃሴን ሲመሩ የቆዩትና ከዚያ በኋላ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ መንግሥት ዋና ተጠሪ የነበሩት አቶ አለማየሁ አሰፋ፣ ‹‹ሜትሮ ፖሊታን›› የተሰኘውንና የሐዋሳ ከተማ አስተዳዳር 70/30 (ሰባ በመቶ ብሔር ብሔረሰቦች ተዋፅኦ፣ ሰላሳ በመቶ በሲዳማ ተወላጆች እንዲዋቀር) ባለፈው ሚያዚያ 2004 ዓ.ም. አዘጋጅተው ለውይይት ያቀረቡት መመርያ በተለይ በሲዳማ ተወላጆች ዘንድ ከፍተኛ ትችት እንዳስከተለባቸው ይታወሳል፡፡ ያም ብቻ ሳይሆን ከሲዳማ አርነት ንቅናቄ አፈትልኮ የወጣውን ያንን መመርያ የዞኑ ሕዝብ ዘንድ በመድረሱ በወቅቱ ከፍተኛ ውጥረት ተፈጥሮ ነበር፡፡ በቅርቡ የትምህርት ሚኒስትር የሆኑት የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የማረጋጊያ መግለጫ መስጠታቸው የሚታወስ ነው፡፡
አቶ አለማየሁ አሰፋና አቶ ሳኒ ረዲ ከሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባለፈው ሐምሌ 2005 ዓ.ም. ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሥራ አመራር ሁለተኛ ዲግሪ አግኝተው የተመረቁ ሲሆን፣ በአመራር ብቃት ማነስ ስለመገምገማቸው የተሰጠ አስተያየት የለም፡፡
     ሦስቱም ከኃላፊነት የተነሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሮች ለሰላሳ ስድስቱ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ከተዋጡት ዘጠኝ አባላት ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ባህር ዳር ከተማ ባደረገው ጉባዔ አቶ ታገሠ ጫፎና አቶ ደበበ አበራ በመተካካት መርህ መነሳታቸው ይታወሳል፡፡ አቶ ታገሠ ከንግድ ኢንዱስትሪ ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊነት ለወራት ብቻ ወደ መሩት ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ የተዛወሩት ከባህር ዳር ጉባዔ በኋላ መሆኑ አይዘነጋም፡፡
ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው የተነገረላቸው እነዚህ ሦስቱ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሮች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የካቢኔ አባላትም እንደሚኖሩበት ምንጮች ለሪፖርተር የገለጹ ሲሆን፣ በምትካቸው የሚሾሙትን ተተኪዎች አዲሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ በመጪው መስከረም 2006 ዓ.ም. በሚደረገው ጉባዔ ላይ ይፋ በማድረግ በምክር ቤቱ እንደሚያፀድቁ  ይጠበቃል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር