በመጪዎቹ አስር ቀናት የክረምቱ ዝናቡ መጠንና ስርጭት ይቀንሳል-ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ አጀንሲ

አዲስ አበባ ነሐሴ 28/2005 በመጪዎቹ አስር ቀናት የክረምቱ ዝናቡ መጠንና ስርጭት እየቀነሰ እንደሚሄድ ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ አጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው ለኢዜአ እንደገለጸው በቀጣዮቹ አስር ቀናት የክረምት ዝናብ ሰጪ ክስተቶች ወደ ደቡብና ምዕራብ ማፈግፈግ ጋር ተያይዞ ከሰሜንና ከሰሜን ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የዝናቡ መጠንና ሥርጭት እየቀነሰ ይሄዳል። በአንፃሩ የክረምቱ ዝናብ በምዕራብ የሀገሪቱ አጋማሽ ክፍሎች ላይ ቀጣይነት ይኖረዋል። ኤንሲው እንደገለጸው በዚህ ወቅት በሚኖረው የተጠናከረ የፀሐይ ኃይል በመታገዝ በሚፈጠር የደመና ክምችቶች ሳቢያ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ነጎድጎዳማና አልፎ አልፎም በረዶ የቀላቀለ ዝናብ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሊፈጠር ይችላል። በቀጣዮቹ አስር ቀናትም ዝናብ ሰጪ የሚትዎሮሎጂ ገዕታዎች በሰሜንና ሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ ላይ አንጻራዊ የመዳከም አዝማሚያ ሊኖር እንደሚችል የኤጀንሲው ትንበያ ይጠቁማል። በዚሁ መሠረት የምዕራብ ትግራይና አማራ፣ ቤንሻንጉል-ጉሙዝ፣ ጋምቤላና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሰሜናዊ አጋማሽ፣ የምዕራብና የመካካለኛው ኦሮሚያ አብዛኛው መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይጠበቃል ። ኤጀንሲው በምሥራቅ ኦሮሚያ፣ድሬደዋ፣ሐረርና ሰሜን ሶማሌ ከመደበኛው ጋር የሚቀራረብ ዝናብ እንደሚኖራቸውም አስታውቋል። የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ከፊል ደመናማ የአየር ሁኔታ እያመዘነባቸው በተወሰኑ ቦታዎች ላይ አነስተኛ ዝናብ ማግኘት ይጀምራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጿል። ይህ ሁኔታ ለመደበኛ የእርሻ ሥራ እንቅስቃሴ አመቺ ሁኔታን ከመፍጠሩም በላይ በልዩ ልዩ የዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰብሎችና ቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎትን በማሟላቱ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የኤጀንሲው ትንበያ ያሳያል። የወቅቱን ዝናብ ተጠቃሚ ለሆኑት አርብቶና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለግጦሽ ሣርና ለመጠጥ ውኃ አቅርቦት የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ይገመታል።
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=11536&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር