በሲዳማ ዞን የገጠር ቀበሌ ተደራሽ መንገድ ግንባታ እንቅስቃሴ ጥሩ ሆኖ በጥራት ላይ ትኩረት ብሰጠው




በሲዳማ  ዞን ውስጥ ከኣንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ገንዘብ መንገድ መስራቱ እየተነገረ ያለ ሲሆን ፤ የመንገዶቹ ጥራት ግን ትኩረት የተሰጠበት ኣይመስልም። ሰሞኑን የዞኑ መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ ይፋ ያደረገውን መረጃ ከታች ያንብቡ፦

አዋሳ መስከረም 19/2006 በሲዳማ ዞን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ በአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የገጠር ቀበሌ ተደራሽ መንገድ ግንባታ መካሄዱን የዞኑ መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ ገለጸ፡፡ በፕሮግራሙ ከ30 ሺህ ለሚበልጡ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠሩ ተገልጿል፡፡ የመምሪያ ኃላፊ አቶ ማቴዎስ ዳንኤል ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ሀገራዊና ክልላዊ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ተከትሎ በዞኑ ሁሉም የገጠር ቀበሌ ደረጃቸውን በጠበቁና ክረምት ከበጋ በሚያገለግሉ መንገዶች ለማገናኘት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡ ፕሮግራሙ በዞኑ ገጠርና ከተማ ፣በአምራችና አገልግሎት ሰጪ እንዲሁም በግብርናና ኢንዱስትሪ ዘርፎች መካከል የሚኖረውን ትስስር በማጠናከር አርሶ አደሩ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ ከምርቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዞኑ እስካሁን 927 ኪሎ ሜትር የገጠር ቀበሌዎችን ክረምት ከበጋ የሚያገለግል መንገድ መኖሩን ጠቁመው ሽፋኑን ከፍ ለማድረግ በበጀት ዓመት ከአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ባላይ መንገድ ግንባታ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡ የቀበሌ ተደራሽ መንገድ ግንባታ 25 በመቶ በህብረተሰብ ተሳትፎ የሚሸፈን በመሆኑ ከ154 ሺህ በላይ ህዝብ በስራው በመሳተፍ 850 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የጠረጋና ምንጣሮ ስራ ማከናወናቸውን ገልጸው ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ ከወጪ ማዳኑን አስረድተዋል፡፡ በዚሁ ስራ ከተሳተፉት የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል 31 ሺህ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ብለዋል፡፡ ትራንስፖርት በዞኑ እየተመዘገበ ላለውና በቀጣይነት ይመዘገባል ተብሎ ሊሚገመተው ኢኮኖሚያዊ እድገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ መምሪያው የቀበሌ ተደራሽ መንገድ ግንባታ ፕሮግራም ውጤታማ እንዲሆን ከ57 በላይ አማካሪዎችና አነስተኛ የስራ ተቋራጮችን በማደራጀትና በማሰልጠን ወደ ስራ እንድገቡ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ የቀበሌ ተደራሽ መንገድ ግንባታ ፕሮግራም ከመንገድ ተደራሽነት ዓላማው ጎን ለጎን ለስራ እድል ፈጠራ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ30 ሺህ ለሚበልጡ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ በመገንባት ላይ የሚገኘውን የገጠር ቀበሌ ተደራሽ መንገድ ግንባታ ስራ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት የተቀናጀ ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ኃላፊው የክልሉ መንግስት ከበጀት በተጨማሪ ዘጠኝ ከባድ ማሽነሪዎችን ጨምሮ ለግንባታው የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ 19 ወረዳና ሁለት የከተማ አስተዳደር 528 የገጠር ቀበሌዎችን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ከዋና መንገድ ጋር ለማገናኘት ከ2ሺህ 500 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ግንባታ እንደሚከናወን አቶ ማቴዎስ ተናግረዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Default.aspx?Lang=0

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር