ሥልጣን ማገልገያ እንጂ መገልገያ አይደለም

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆን ኦፍ ኬኔዲ ባንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፡፡ ‹‹መጠየቅ ያለብህ አገሬ ለእኔ ምን ሠራችልኝ ብለህ ሳይሆን እኔ ለአገሬ ምን ላደርግ እችላለሁ ብለህ መሆን አለበት፡፡››
ይህ የፕሬዚዳንቱ ንግግር በመላው ዓለማችን በበርካቶች የሚታወቅና ጥልቅ መልዕክት የያዘ ነው፡፡ ዛሬ የፕሬዚዳንት ኬኔዲን ንግግር ያነሳነው ስለእሳቸው ለማውራት ሳይሆን፣ ከዚህ ታዋቂ ንግግራቸው ጀርባ ያለውን ቁም ነገር ለመዳሰስ በማሰብ ነው፡፡
በርካቶች በሕይወት ዘመናቸው እንዲኖሩዋቸው ከሚፈልጉዋቸው ነገሮች መካከል አንደኛው ሥልጣን ነው፡፡ ሆኖም ግን በርካታ ሰዎች ሥልጣንን የሚፈልጉት በሥልጣን ውስጥ ያሉ ጥቅሞችን ለማግኘት ካላቸው ክፉኛ መሻት ነው እንጂ፣ በእውነት ሥልጣንን በሚገባ ተረድተውት ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ምንም እንኳን ሥልጣን ይዞ የሚያመጣቸው በርካታ ጥቅሞች ቢኖሩትም፣ ዋነኛ ዓላማው ከዚያ የዘለለ ነው፡፡ 
ሥልጣን አንድን ነገር ለመግዛት የሚያገለግል ኃይል ቢሆንም፣ ትክክለኛው ትርጓሜው ግን ተገቢ የሆነ ተፅዕኖን በማሳደር ነገሮችን በሥርዓት ለማስጓዝ የሚጠቅም ዘዴ ነው፡፡ ታዲያ ዛሬ የምናነሳው ጉዳይ በአገራችን በርካቶች ሥልጣንን የሚጠቀሙት ከምን አንፃር መሆኑን ለመፈተሽ ነው፡፡ በርካቶች የሥልጣንን ትክክለኛ ትርጓሜ ካለማወቅ የተነሳ በአገር እንዲሁም በሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ጉዳይ በጊዜው ሃይ ካልተባለ፣ ለባሰ ችግር ማጋለጡ አይቀሬ መሆኑ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ 
በአገራችን ያሉ አንዳንድ ባለሥልጣናትም ስለሥልጣን ምንነት ትክክለኛ ዕውቀት ስለሌላቸው ይህ ነው የማይባል ኪሳራ እያደረሱ ይገኛሉ፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሲሾሙ ልዩ ትኩረት የሚሰጡት በሥልጣን አማካይነት ስለሚገኘው ቤት፣ መኪና፣ ክብር፣ ገንዘብና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ነው፡፡ ነገር ግን ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ እንደሚሉት፣ በሥልጣን ውስጥ ካለው ኃላፊነት ይልቅ ሰለጥቅማ ጥቅሞቹ ማሰብ መዘዙ ኋላ ለራስም መትረፉ አይቀርም፡፡
ሕዝብ የመንግሥት ባለሥልጣናትን መርጦ ሲሾም፣ የሾማቸው ባለሥልጣናት ባላቸው ዕውቀትና የሥራ ብቃት፣ መልካም አስተዳደርና ፍትሕን ያሰፍኑልኛል የሚል ብርቱ እምነት አለው፡፡ ለዚህም ነው እንደ ኮንትራት የሆነውን ድምፅ ሰጥቶ በምላሹ ለሰው ልጆች አስፈላጊና መሠረታዊ የሆኑትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሥርዓቶች በተገቢው መንገድ እንዲመሩለት የሚጠብቀው፡፡ ስለዚህም አንድ ባለሥልጣን ሕዝቡ ከእሱ የሚጠብቀውን ማሟላት ምርጫው ሳይሆን ግዴታው መሆኑን ሊገነዘብ ግድ ይለዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር አንድ ባለሥልጣን በሥልጣኑ ሊቆይ የሚችልበት ብቸኛው መንገድ የመረጠውን ሕዝብ ሲያገለግል መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ማንም ባለሥልጣን ሕዝብን በኃይል መግዛት እንደማይችል በዓለማችን ያሉ ክስተቶች መቃኘት ብቻ ይበቃል፡፡ ስለዚህ የትኛውም ባለሥልጣን ስኬቱ የሚለካው ለሕዝቡ በሚሰጠው አገልግሎት እንጂ ባለው ኃይል አይደለም፡፡ 
ዛሬ ስለሥልጣን ስናወራ በሥልጣን ላይ ያለ ማንኛውንም ባለሥልጣንን ቢመለከትም፣ ነገር ግን ከሁሉ በበለጠ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ይመለከታል፡፡ ምክንያቱም እነሱ ባላቸው ሥልጣን በበርካቶች ላይ ተፅዕኖ ስለሚያሳድሩ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የመንግሥት ሥልጣንን እንደመያዙ መጠን ይህንን ጉዳይ በሚገባ ሊያጤነው ይገባል፡፡ ድርጅቱ የመንግሥት ባለሥልጣን አድርጐ የሚያቀርባቸው ግለሰቦች በሁሉም አቅጣጫ ሕዝብን የማገልገል ብቃት ያላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡
ቀደም ብለን እንዳነሳነው ሕዝብ ሊታዘዝና ሊገዛ የሚችለው ከላዩ ያሉት ባለሥልጣናት ለእሱ የሚሠሩ መሆኑን ሲያረጋግጥ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ባለሥልጣናት የቀንና የሌሊት ሐሳባቸው ሊሆን የሚገባው ሕዝቡን እንዴት እንደሚያገለግሉ እንጂ እንዴት እንደሚገለገሉበት መሆን የለበትም፡፡ ስለዚህ አንድ ባለሥልጣን ሲሾም ካለው የትምህርትና የሥራ ብቃት ባሻገር፣ ሕዝብን የማገልገል ብቃቱ ሊገመገም ይገባዋል፡፡ በመሆኑም ከሥልጣን በስተጀርባ ያለው ኃላፊነት ቅድሚያ ሊተኮርበት ይገባል፡፡ 
መንግሥትም የያዘው ሥልጣን ሰውን የሚገዛበት ሳይሆን ሕዝብን የሚያገለግልበት ዕድል መሆኑን መረዳት አለበት፡፡ ነገር ግን ሥልጣን የፈለጉትን ማስፈጸሚያ ሳይሆን ሕዝብን ማገልገያ መንገድ መሆኑን ተረድቶ እንደዚያው ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ መንግሥት ሕዝብን ባለው ኃላፊነት መሠረት ማገልገል ካልቻለ በቀጣይ ያለው ጉዞ እንደሚደናቀፍ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ምንም እንኳን በሥልጣናቸው ያላግባብ የሚጠቀሙ ባለሥልጣናትን ብንወቅሳቸውም፣ በመንግሥት ውስጥ ሕዝብን በቅን ልቦናና በታታሪነት የሚያገለግሉትን ማመስገን የግድ ይላል፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ቅንና ታታሪ ባለሥልጣናት አገልግሎት በሌሎች ስግብግብና ጥቅም ፈላጊ ባለሥልጣናት ተሸፍኖ ይገኛል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ካለበት ከፍተኛ ኃላፊነት አንፃር ባለሥልጣናት የሕዝብ አገልጋይ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡ ይህንንም በተለይ የሕዝቡን የልብ ትርታ በመስማት ማወቅ ይችላል፡፡ ስለዚህ ሥልጣን መገልገያ እንጂ መገልገያ አይደለም እንላለን፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር