ሥራን የማይንቀው ዳያስፖራ

በጌታቸው ንጋቱ
ዘመን በተለወጠ ቁጥር የተቻለኝን ሁሉ በማድረግ በአገር ምድር ከዘመድ አዝማድ ጋር አዲስ ዓመትን ለማክበር ከምኖርበት አገር አቀናለሁ፡፡
ከአገር ከወጣሁ ጀምሮ አንድም ዓመት የዘመን መለወጫን ከኢትዮጵያ ውጪ አሳልፌ አላውቅም፡፡ ዘመድና ጓደኛም ስለ አሜሪካ ኑሮ ይጠይቃሉ፡፡ እኔም የተቻለኝን ሁሉ እመልሳለሁ፡፡ ከሁሉም ግን አንድ የሚገርመኝ ጥያቄ ከአንዲት ጓደኛዬ ነው የመጣው፡፡ ‹‹ኑሮ በአሜሪካ እንዴት ነው? መቼም አሜሪካ የሚኖር ሰው ምንድነው የምትሠራው አይባልም፡፡ ሁሉም ተጠግርሮ ነው የሚኖረው፤›› አለችኝ፡፡ 
ጓደኛዬ ስለ ሥራና የሥራ ክቡርነት ያላትን አመለካከት ለማረቅ ብሞክርም ይህ የአንድ ሰው ብቻ ሳይሆን የብዙዎች የግንዛቤ ችግር ስለመሰለኝ ይህንን ለመጻፍ ተነሳሁ፡፡ 
1.ሥራ ክቡር ነው
ቢያንስ በሐሳብ ደረጃ ሥራ ክቡር ነው እንላለን፤ ነገር ግን ስንቶቻችን ነን ሥራ ክቡር ነው፤ ብለን በተሰማራንበት የሥራ መስክ ውጤታማ ለመሆን የምንጥረው የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ 
ሥራ ክቡር ነው የሚለው አባባል በሰሜን አሜሪካ በተግባር ላይ ውሎ የሚታይ አባባል ነው፡፡ የምትሠራው ሥራ ሳይሆን በምትሠራው ሥራ ምን ያህል ውጤታማ ነህ፤ ታክስህን በሥነ ሥርዓት ትከፍላለህ፤ የክሬዲት (ብድር) አጠቃቀምህ ምን ይመስላል፤ ሰላማዊና ጠንካራ ሠራተኛ ነህ ወይ? የሚለው ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ 
አንዳንዶች ከአገር ወጥተው ኑሯቸውን በአሜሪካ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ታክሲ በማሽከርከራቸው፤ ሆቴል በማስተናገዳቸው ወይም ‹‹ፓርኪንግ ሎት›› ውስጥ በመሥራታቸው ከአገር ቤት ባሉ ጓደኞቻቸው ትችት ሲሰነዘርባቸው ስሰማ አንዳንዶች ስለ ሥራ ባላቸው ግምት አዝናለሁ፡፡ 
ከቅርብ ሳምንታት በፊት በመሀል ዋሽንግተን ዲሲ አንዲት ወጣት ነጭ አሜሪካዊት በባር ውስጥ ታስተናግዳለች፡፡ ከተስተናጋጇ ጋር ስለ ሥራና ኑሮ ማውጋት ጀመረች፡፡ አስተናጋጇ አሜሪካ ውስጥ ተወልዳ ያደገች የስድስተኛ ዓመት የሕክምና ሳይንስ ትምህርቷን በጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ እየተማረች እንደሆነና መመረቂያዋ መድረሱን አወጋችን፡፡ የሕክምና ዶክተር ሆና ሆስፒታል መሥራት ብትጀምርም በአስተናጋጅነት መሥራት እንደምትፈልግም ነገረችን፡፡ እኔና ኢትዮጵያውያን ጓደኞቼ ይህንን ጠንካራ የሥራ ባህል አደነቅን፡፡ በአሜሪካ ምንም ሥራ ምን ኃላፊነትን መወጣትና ሥራን ማክበር የራሱ ዋጋ አለው፡፡ 
2.ዳያስፖራ በሥራ ክቡርነት ያምናል
ምንም እንኳን አገር ቤት ያሉ ጓደኞች ስለ ሰሀን ማጠብና ስለ አሜሪካ ሥራ ሊቀልዱ ቢሞክሩም ዳያስፖራው በአሜሪካ ጠንካራ ሠራተኛና ሕግ አክባሪ ነው፡፡ 
ከአገርና ቤተሰብ ድህነት ጋር በተያያዘ አሜሪካ ገብቶ የራሱን ኑሮ ከማሸነፉ በፊት ቤተሰብን መርዳት ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ሌት ተቀን ይሠራል፣ ይማራል፡፡ አገሩ ገብቶ ለመሥራትና ለመለወጥ የአቅሙን ይጥራል፡፡ 
በዋሽንግተን ዲሲ፣ ሜሪላንድና ቨርጂኒያ አንዲሁም በሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች በታላላቅ የመንግሥት ኃላፊነት፣ በሕክምና ባለሙያነት፣ በኮምፒዩተር ሳይንቲስትነት፣ በሥራ ፈጣሪነት በሁሉም የሥራ መስክ ጠንካራነቱን ያሳየ ዳያስፖራ ነው፡፡ 
በአገሪቱ (አሜሪካ) ነጭ፣ ለጥቁር፣ ለሂስፓኒክ ወይም ለኤዥያን ተብሎ የሚመረጥ ሥራ የለም፡፡ መጀመሪያ የውኃ፣ የስልክ፣ የቤት መክፈል አለበት፡፡ ስለዚህ በሁሉም የሥራ መስክ ጠንክሮ ሁሉም ይሠራል፡፡ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ይህንን ጠንካራ የሥራ ባህል ተቀብለው የራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ 
3.የአእምሮ ፍሰት አሳሳቢ ነው
መጀመሪያ ደረጃ፣ ሁለተኛ ደረጃ፣ ዩኒቨርሲቲ የማውቃቸውን ጓደኞቼን በየቀኑ፣ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች በሚገኙ ከተሞች ሳገኝ በጣም የሚያሳስበኝ ምን ዓይነት ሥራ እየሠሩ ነው የሚለው ሳይሆን፣ አገራችን ኢትዮጵያ ምን ያህል አምራችና ወጣት ኃይሏን እያጣች ነው የሚለው ነው፡፡ 
በሲያትል ማይክሮሶፍት፣ በጐግል፣ በዋሽንግተን ዲሲ መንግሥታዊ ባልሆኑና በአሜሪካ የፌዴራል መንግሥት መሥርያ ቤቶች ተቀጥረው መሥራት ብቻ ሳይሆን እጅግ ውጤታማ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ስመለከት ኢትዮጵያ ካላት በከፍተኛ ደረጃ የተማረ ጥቂት የሰው ኃይል ላይ ምን ያህሉ ከአገር እንደወጣና ምን ያህል እየጎዳን እንደሆነ እንወያያለን፡፡ 
በመሆኑም በአገሪቱ ያለው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ሁነቶች እንዲቀየሩ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ማበረታቻ ቢደረግ መልካም ይሆናል፡፡ 
4.ሥራን የሚንቅ ሰው ስኬታማ አይሆንም
ኢትዮጵያ እየኖሩና እየሠሩ፤ እጅግ ስኬታማ የሚሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ የግድ ስኬታማ ለመሆን ማስተርስ ዲግሪ መሥራት ወይም አሜሪካ መሄድ አያስፈልግም፡፡ አሜሪካም ሄደው አሜሪካ ተወልደው ካደጉ፣ ከተማሩት በላይ ውጤታማ ሆነው ትውልደ አሜሪካውያንን ቀጥረው፣ አሠርተው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ 
ኢትዮጵያም ኖሩ አሜሪካ በተለያዩ ምክንያት ስኬታማ የማይሆኑ ይኖራሉ፡፡ የትም ይኑር የት ሥራ ሳይንቅ፣ ሥራን አክብሮ የሚሠራ ስኬታማ መሆኑ አይቀርም፡፡ ዋናው ነገር የምትኖርበት አገር ብቻ ሳይሆን ለሥራ ያለን ክብርና ጠንካራ ሠራተኛነታችን ብቻ ነው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር