አገልግሎት አሰጣጥ ሲሳከርና ሲቋረጥ ከመንግሥት ማብራሪያና ይቅርታ ይጠበቃል

በማደግ ላይ ባሉትም ሆነ በበለፀጉት አገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ፣ የውኃ አቅርቦት መስተጓጎልና የኢንተርኔት አገልግሎት አለመኖር ያጋጥማል፡፡ መጠኑና ደግግሞሹ በእጅጉ ሊለያይ ይችላል እንጂ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን ከፍተኛ ሕዝባዊ ጥያቄ እያስነሳ ያሉ የአገልግሎት አቅርቦት መሳከርና መቋረጥ እያጋጠሙ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ውኃ ለቀናት መጥፋት የተለመደ እየሆነ ነው፡፡ ለሳምንትና ለወር ተቋርጦብናል የሚሉ አሉ፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል በቀን ሦስቴና አራቴ ይቋረጣል፡፡ መደበኛ ስልኮች ይቋረጣሉ፣ ሞባይል ስልኮች አይሠሩም፡፡ የኢንተርኔት አገልግሎትም ብርቅ እየሆነ ነው፡፡ የብሮደባንድ፣ የዋይፋይና የኢቪድዮ ኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ የተለመደ ሆኗል፡፡
ለተፈጠሩት ችግሮች ከአቅም በላይ የሆኑና ያልተገመቱ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ግን ቀርበው በግልጽ ማስረዳት አለባቸው፡፡ ችግሮቹ እስኪስተካከሉ ለሚያጋጥሙ የአገልግሎት መቋረጦች መንግሥት ሕዝቡን  በይፋ ይቅርታ መጠየቅ አለበት፡፡ 
በኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋት ምክንያት የበርካታ ፋብሪካዎች ማሽኖች እየተበላሹና ከባድ ኪሳራ እያስከተሉ ናቸው፡፡ ምርትም እየተቋረጠ ነው፡፡ በኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋት ምክንያት በርካታ የቤት ዕቃዎች እየተቃጠሉና እየተበላሹ ናቸው፡፡ ፍሪጆች፣ ቴሌቪዥኖችና የኩሽና ዕቃዎች እየተቃጠሉ ቤተሶበችን ለከፍተኛ ኪሳራ እያደረጉ ናቸው፡፡ በተደጋጋሚ፡፡
በዚህ ሰዓት ኢንተርኔት ከፍቼ መልዕክቶችን አያለሁ የሚል ሐሳብ ተረት ተረት እየሆነ ነው፡፡ በዚህም በርካታ የቢዝነስ ሥራዎች እየተስተጓጎሉ ናቸው፡፡ ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን በመቋረጡ ምክንያት በርካታ ቢዝነሶች እየተጎዱ ናቸው፡፡
ውኃ፣ ኤሌክትሪክና ስልክ በሌሉበት ሕመምተኞችንና ሕፃናትን መንከባከብ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ ችግር በቀና መንፈስ የሚረዳ ሕዝብ ማብራሪያ ሲያጣ እንዴት ነው ነገሩ የሚል ጥያቄ ያነሳል፡፡ 
እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ሲኖሩ መንግሥት ተገፍቶ ሳይሆን በራሱ ተነሳሽነት ምክንያቱን አጣርቶ ለሕዝብ ማስረዳት አለበት፡፡  ‹‹ኤሌክትሪክ የተቋረጠው ዛፍ ስለወደቀ ነው›› የሚለው ፌዝ ይቅር፡፡ በእውነት ለሁሉም የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር ምክንያቱ የዛፍ መውደቅ ነው? የሚወድቁ ዛፎች በኤሌክትሪክ መስመርና በትራንስፎርመር ላይ የሚያደርሱትን ለማወቅ በእውነት ‹‹አስማተኛ›› መሆን ይጠይቃል፡፡
ዛፍ ወድቆ ነው እየተባለ ከመሸፋፈን ይልቅ ሆን ተብሎ የሚፈጸም አሻጥር ካለ መመርመሩ ያስፈልጋል፡፡ በሙስና ምክንያት የማይሠሩ ትራንስፎርመሮች ተገዝተው እየፈነዱ ለመሆናቸው ማጣራት ያስፈልጋል፡፡ 
ከኃይል ማመንጫዎች ጀምሮ የሚዘረጉት የማስተላለፊያ መስመሮች በጥናትና በባለሙያ መከናወናቸውን ማየትና ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ችግር ቢኖርም መንግሥት ምን እንዳጋጠመ በትክክል መርምሮና አውቆ ለሕዝብ ማሳወቅ አለበት፡፡ ስለደረሰው ችግር ሕዝብ የማወቅ መብት አለው፡፡ መንግሥት የማስረዳት ግዴታ አለበት፡፡ 
ለሕዝብ መረጃ ከመስጠት ባሻገርም ይቅርታ መጠየቅ የሚባል ጨዋ አሠራር አለ፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ለተፈጠረ ችግር ይቅርታ መጠየቅ ግዴታም ጨዋነትም ነው፡፡ በተለይ እንደዚህ ዓይነት ይቅርታ ከመንግሥት ሲመጣ ሕዝባዊ ከበሬታ ያስገኛል እንጂ ምንም ጉዳት የለውም፡፡
እስኪሠራና እስኪስተካከል ድረስ ሕዝቡ እንዲታገስ ማሳሰቢያ መስጠት፣ እያደረሰ ላለው ኪሳራና መስተጓጎል መንግሥት ሕዝቡን ይቅርታ ይጠይቃል መባል አለበት፡፡ መንግሥት እንደዚህ ዓይነት ግንኙነት ሲፈጥር ነው የሚከበረውና የሚደመጠው፡፡ 
የቦሌ መንገድ ሲሠራ በተፈጠረው መዘጋጋት ምክንያት ሕዝብ ጥያቄ ያነሳ ነበር፡፡ መንገዱ ተሠርቶ ሲያልቅ ግን የተፈጠረው መዘጋጋት ለአገሩ እንደሆነ አምኖ፣ አሁን ደግሞ ለመጋቢ መንገዶች ግንባታ መንገድ ሲዘጋጋ የአጭር ጊዜ ችግር እንጂ በቀጣዩ ጥሩ ይሆናል እያለ በአዎንታ እየጠበቀ ነው፡፡ እየተባበረ ነው፡፡
ነገር ግን በኤሌክትሪክ፣ በውኃና በስልክ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር ሲፈጠር ዝም መባል የለበትም፡፡ ሕዝብ  በተለያዩ ጉዳዮች ከመንግሥት ጋር ሆኖ በትዕግሥት እንዲተባበር የችግሮችን ምክንያት የማወቅ መብቱ ይከበርለት፡፡ ለሚደርሰው  ችግርም ይቅርታ ይጠየቅ፡፡   
የጋራ ችግርን በጋራ ለመፍታት ሕዝባዊና መንግሥታዊ የትብብር መሠረት ይፈጥራልና፡፡ የአገልግሎቶች አሰጣጥ ሲቋረጥና ሲሳከር ከመንግሥት ማብራሪያና ይቅርታ ይጠበቃል! 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር