አወዛጋቢው የይዞታ ረቂቅ መመርያ አስተያየት እንዲሰጥበት ለከተማ ልማት ሚኒስቴር ተላከ

ገወጥ ባለይዞታዎችን ሕጋዊ የሚያደርገው አወዛጋቢው ረቂቅ መመርያ አስተያየት እንዲሰጥበት ለከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተላከ፡፡
የ62 ሺሕ ባለይዞታዎች ቀጣይ ዕጣ ፈንታን የሚወስነው ይህ መመርያ በርካታ ውይይቶች ተካሂደውበት ለውሳኔ ቢቀርብም፣ በከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል መግባባት ላይ ባለመደረሱ ሲንከባለል ቆይቷል፡፡ 
በሕገወጥ ባለይዞታነት ከሚፈረጁት መካከል 44 ሺሕ የሚሆኑት መንግሥት ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች በሰነድ ክፍያ የሚፈጽሙ ሲሆኑ፣ 18 ሺሕ የሚሆኑት ደግሞ ምንም ዓይነት ሰነድ የሌላቸው ናቸው ተብሏል፡፡ 
የሊዝ አዋጁን እንዲያስፈጽም በወጣው ደንብ ሕገወጥ ባለይዞታዎች በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕጋዊ የሚሆኑበትና ከተሞች እንደነባራዊ ሁኔታቸው ሕጋዊ የማድረጉ ተግባር እንደሚከናወን ተደንግጓል፡፡
ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከ1988 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 2004 ዓ.ም. ድረስ በሕገወጥ መንገድ የተያዙ ይዞታዎችን ሕጋዊ ለማድረግ ረቂቅ መመርያ አዘጋጅቷል፡፡ ነገር ግን እስከ ኅዳር 2004 ዓ.ም. ድረስ የተገነቡ ቤቶችን ሕጋዊ ማድረግ በባለሥልጣናት መካከል አለመግባባት መፍጠሩን ምንጮች ይገልጻሉ፡፡
በሌላ በኩል በግንቦት 1997 ዓ.ም. ከተካሄደው ምርጫ በኋላ የከተማው አስተዳደር የሥልጣን ሽግግር በሚያካሂድበት ወቅት ከፍተኛ የመሬት መቀራመት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ የነበረው የከተማው ባለአደራ አስተዳደር ከዚያ በኋላም ሥልጣኑን የተረከበው የከተማው አስተዳደር ግብረ ኃይል በማቋቋም ሕገወጥ ያሏቸውን ግንባታዎች አፍርሰዋል፡፡ ባለሙያዎች እንደሚሉት ዕርምጃ በሚወሰድበት ወቅት ዕርምጃ ሊወሰድባቸው የሚገቡ፣ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች የተዘለሉ በርካታ ይዞታዎች በአዲሱ መመርያ ሕጋዊ የመሆን ዕድል አግኝተዋል፡፡ በወቅቱ የፈረሰባቸው ‹‹ሕገወጥ›› ባለይዞታዎች ላይ መጥፎ ስሜት ሊፈጥር ይችላል ይላሉ፡፡  
ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የመሬት ሥሪት ባለሙያዎች ረቂቅ መመርያው ሕገወጥነትን ያበረታታል በማለት ይከራከራሉ፡፡ በሌላ በኩልም የአዲስ አበባ ከተማ በ54 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ያረፉ ይዞታዎች በሙሉ ለመጨረሻ ጊዜ የአየር ፎቶግራፍ የተነሱት በኅዳር 2003 ዓ.ም. ነው፡፡ እስከ ኅዳር 2004 ዓ.ም. ባለው ጊዜ የተካሄዱ ግንባታዎች በምን እንደሚታወቁ የሚገልጽ ነገር አለመኖሩን ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ እስከ 1988 ዓ.ም. ድረስ ያሉ ሰነድ አልባ ይዞታዎች ሕጋዊ የሚሆኑበትና ካርታ የሚያገኙበት አሠራር ተዘርግቷል፡፡ ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ኅዳር 2004 ዓ.ም. ድረስ ያሉ በሕገወጥ ባለይዞታነት የተፈረጁ ባለይዞታዎችን ለማስተናገድ ነበር ይህ ረቂቅ መመርያ የተዘጋጀው፡፡ ረቂቅ መመርያው ከተዘጋጀ ከዓመት በላይ ቢሆንም ሙሉ ስምምነት ባለመኖሩ ሲንከባለል ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት አስተዳደሩ ረቂቅ መመርያው አስተያየት እንዲሰጥበት ለሚኒስቴሩ ልኳል፡፡
ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፣ የሊዝ አዋጅ የወጣው በኅዳር 2004 ዓ.ም. በመሆኑና ረቂቅ መመርያው አዋጁ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ያሉትን ማስተናገድ ስላለበት እስከ 2004 ዓ.ም. ድረስ ያሉትን ያስተናግዳል ተብሏል፡፡ ነገር ግን የሊዝ አዋጅ ከተሞች እንደደረሳቸው ነባራዊ ሁኔታውን አጣጥመው እንዲሠሩ ዕድል ስለሚፈቅድላቸው ጉዳዩ በድጋሚ ሊጤን እንደሚገባ እነዚሁ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር