መሬትን ሳያርሱ በማልማት በምርምር የተገኘውን ተሞክሮ ወደ አርሶ አደሩ ለማስፋት የሚያስችል መድረክ ተመሰረተ

ሃዋሳ ነሐሴ 8/2005 በወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ተቋም የሃዋሳ መለስተኛ የበቆሎ ምርምር ማዕከል መሬትን ሳያርሱ የማልማት ምርምር ስራ የተገኘውን ተሞክሮ ወደ አርሶ አደሩ ለማስፋት የሚያስችል የባለ ድርሻ አካላት የጋራ መድረክ ተመሰረተ ። መሬትን ሳያርሱ የማልማት ምርምር ስራዉን ወደ አርሶ አደሩ ለማስፋት እንዲቻል የጋራ መድረኩ የተመሰረተዉ ትናንት በሃዋሳ በተካሄደ ምክክር ላይ ነዉ ። በሀዋሳ የበቆሎ ምርምር መለስተኛ ማዕከል ዳይሬክተርና የምርምር ፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ጎሽሜ ሙሉነህ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩ ምርምሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ በሚገኙ አምስት ሀገራት እየተካሄደ ነዉ ። መሬትን ሳያርሱ በማልማት በምርምር በተገኘው ተሞክሮ የቦሎቄና በቆሎን ምርታማነት በማሳደግ በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል ያለመ ነው ብለዋል ። በክልሉ ሲዳማ ዞን በአንድ ወረዳ ከሁለት ዓመት በፊት በአምስት አርሶ አደሮች የተጀመረው መሬትን ሳያርሱ የማልማት የግብርና የምርምር ስራ በተጨማሪ በአራት ወረዳዎች በማስፋት ምርምሩ ውጤታማ እንደሆነም ተገልጧል ። የምርምር ማዕከሉ የቦሎቄና በቆሎ ተረፈ ምርት በማሳው ላይ እንዳለ በማቆየት የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ምርታማነትን ማሳደግ እነደሚቻልም መረጋገፈጡ ተገልጧል ። በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች እስካሁን እየተሰራበት ያለ መሬትን ሳያርሱ የማልማት ልማዳዊ አሰራር ቢሆንም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም ቢሰራበት ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ለአፈር ለምነት የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን አቶ ጎሽሜ ተናግረዋል። በደቡብ ክልል በሀድያ ሲዳማና ጉራጌ ዞኖች የሚገኙ የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ፣ የሎካ አባያ የቦርቻ የመስቃንና የምስራቅ ባድዋቾ ወረዳዎች በምርምሩ መታቀፋቸዉንና ባለፉት ሶስስት ዓመታት የተገኘው ውጤት አርሶ አደሩን በምርምሩ ለመታቀፍ እንዳነሳሳው ጠቁመዋል ። ከደቡብ ክልል ግብርና ምርምር ማዕከል ምርምሩ ከሚከናወንባቸው ወረዳዎችና ከግብርና ቢሮና ከአርሶ አደሩ የተውጣጡ አካላት ያሉበት መድረክ የተመሰረተዉ በምርምር ማዕከሉ የተገኘውን ተሞክሮ ወደ አርሶ አደሩ በማስፋት ተጠቃሚነት ለማሳደግ መሆኑም ተመልክቷል ። በደቡብ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሀዋሳ ምርምር ማከል የጥራጥሬ ዝርያ ማሻሻያ ተመራማሪና የእቀባ ግብርና ምርምር ተወካይ ድክተር ዳንኤል ዳውሮ በበኩላቸው እንዳሉት መሬትን ሳያርሱ በማልማት ዘዴ ከምርምሩ የተገኘውን ውጤት መሰረት በማድረግ ወደ አርሶ አደሩ ለማስፋት በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል። በዚህ ዘዴ መሬትን ደጋግሞ በማረስ ከሚገኘው ምርት የተሻለ ማግኘት የሚቻል ከመሆኑ በተጨማሪ የአርሶ አደሩን ጊዜ ወጪና ጉልበት የሚቆጥብ በመሆኑ በአብዛኛው አርሶ አደር ዘንድ ወደዚህ አመራረት ዘዴ ለመግባት ፍላጎት መኖሩን ጠቁመዋል። በሎካ አባያ ወረዳ በምርምሩ የታቀፉ አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር ዮናስ ላታሞ እንደገለጹት በምርምሩ ታቅፈው መሬት ሳያርሱ በማልማታቸው ቀደም ሲል በሄክታር ሲያገኙ ከነበረው ብልጫ ያለው ምርት ማግኘት እንደቻሉ ገልጸዋል። አርሶ አደሩ እንደገለጹት የምርምር ማዕከሉ ለአርሶ አደሮቹ በማሳቸው ላይ ከሚያደርግላቸው ሙያዊ ድጋፍና ክትትል በተጨማሪ የበቆሎና ቦሎቄ ምርጥ ዘር ማዳበሪያና የአረም ማጥፊያ ኬሚካል እንዳቀረበላቸው ጠቁመዋል። የዕቀባ ግብርና በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ የመሬት ለምነታቸው በቀነሰባቸው ደቡብና ሰሜን አሜሪካ አውስትራሊያና ኒውዝላንድ ተግባራዊ ተደርጎ ውጤት ማምጣት መቻሉ ተገልጧል ። በመሆኑም በኢትዮጵያ በደቡብ ፣በኦሮሚያና አማራ ክልል በሚገኙ የአፈር ለምነት በቀነሰባቸው 12 ወረዳዎች ምርምሩ እየተከናወነ እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል ።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር