የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግር ዛሬም አልተፈታም

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 17 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት መቆራረጥ በመዲናችን አዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች እየተባባሰ የመጣ ችግር ሆኗል ።
ሃገሪቱ እያመነጨች ያለው የኤሌክትሪክ ሃይል በቂ የሚባል ቢሆንም የአገልግሎት ጥራት መጓደል ግን በብዙዎች ዘንድ ተደጋጋሚ ቅሬታን እያስነሳ ነው ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ችግሩ መኖሩን አምኖ ይቀበላል ፤ የኬርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ምህረት ደበበ እንደሚሉት ፥ የኤሌክትሪክ መቆራረጡ በማህበረሰቡና በሃገሪቱ ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ ነው።
ከዚህ ቀደም ለጣቢያችን ቅሬታቸውን ያቀረቡ አካላት በየአካባቢው የሚተከሉ የሃይል ማሰራጫ ትራንስፈርመሮች ጥራት የጎደላቸው መሆን የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞችም ፈጣን ምላሽ አለመስጠት፤ ከዚህም አለፍ ሲል እጅ መንሻ ይቀበላሉ ሲሉ ሮሮ ማሰማታቸው የሚታወስ ነው።
አቶ ምህረትም  በኮርፖሬሽኑ ውስጥ መልካም ስነ ምግባር የሌላቸው ሰራተኞች መኖራቸውን በማመን ቅሬታው ተገቢ መሆኑን ይቀበላሉ።
የሲቪል ሰርቪስ ሚንስቴርም ባካሄደው ጥናት  ህዝቡ ቅሬታ ከሚያሰማባቸው የፌደራል ተቋማት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ነው።
ችግሩ የኮርፖሬሽኑን አቅም እንደተፈታተነው ያመኑት ሃላፊው ጉዳዩ በመንግስት ደረጃ እየታየ መሆኑን ጠቅሰው ፥ ከዚህ ጎን ለጎንም ኮርፖሬሽኑ ማዕከላትን አደራጅቶ እየሰራ ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ ቀድሞ የነበሩ  አሁንም ያልተፈቱና ለኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ምክንያት የሆኑ እክሎች እንዳሉ ናቸው።
ከእነዚህ ውስጥ በስፋት እየተካሄዱ ያሉት የመንገድ ፣ የባቡርና የውሃ መስመር ዝርጋታዎች ተጠቃሽ ሲሆኑ ፥ እነዚህን መሰረተ ልማቶች ለመዘርጋት በሚደረገው ጥረት በርካታ የኤሌክትሪክ ምሶሶዎች እየወደቁ ነው።
ይህን ችግር ለመፍታትም ተቀናጅቶ ለመስራት በሚያስችል ደረጃ በመንግስት በኩል እየተሰራ ያለ ስራ መኖሩን አንስተዋል።
የሆነ ሆኖ አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች እየታየ ያለው የመብራት መቆራረጥ ውስብስብ ከመሆኑ አንፃር ፥ ችግሩ በዘላቂነት የሚፈታበትን ቁርጥ ያለ ጊዜ ማወቅ አልተቻለም ነው ያሉት አቶ ምህረት።
ይሁን እንጂ የችግሩ ምንጮች መታወቃቸው በራሱ አንድ የመፍትሄ አካል ነውና ወደ መፍትሄው ለመግባት አያስቸግርም።
የመፍትሄው አንድ አካል የሆነውና የአመራር ችግር ያለባቸውን አካላት ነቅሶ የማውጣቱና የጥራት ጉድለት ያለባቸው ትራንስፈርመሮችን የመለየቱ ስራም ተጀምሯል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር