ፊቼ እና ጫምባላላ - የሲዳማ ዓመት ዋዜማና መባቻ

የአንድ ማኅበረሰብ መገለጫና መለያ ከሆኑት እሴቶች አንዱና ዋነኛው ባህል እንደሆነ የመስኩ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡

የአንድ ማኅበረሰብ የኑሮ ዘይቤ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መርሕ እምነትና አስተሳሰብ የጥበብ፣ የአስተዳደር፣ የአለባበስና አመጋገብ ሥርዓት፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችና መገልገያዎች የባህል መገለጫዎች ሲሆኑ በዋናነት በሁለት የሚከፈሉት ቁሳዊና መንፈሳዊ ተብለው ነው፡፡ ቁሳዊ ባህል ታሪካዊ ቅርሶች በጽሑፍ የተቀመጡ ሕትመቶችና ሰነዶች ሕንፃዎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች የምርትና አገልግሎት መሳሪያዎችንና ሌሎች ተያያዥ ውጤቶችን ያጠቃልላል፡፡ መንፈሳዊ ባህል በሌላ በኩል የሃይማት (እምነት) ፍልስፍና፣ ርዕዮተ ዓለም፣ የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ ማኅበራዊ ክንዋኔዎች (ክብረ በዓላት) እና አመለካከቶችን ያካትታል፡፡ 

የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ፈቼና አዲሱ ዓመት ክብረ በዓል መንፈሳዊ (ኢንታንጀብል) ባህል ከሆኑት አንዱ ሲሆን፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሻገር የመጣ የብሔሩ ማንነት መገለጫ እንደሆኑ የሲዳማ ዞን ባህል ቱሪዝምና መንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ዓመታዊ መጽሔት ያሰፈረው መረጃ ያመለክታል፡፡ ሲዳማ የራሱ የሆኑ የቀን አቆጣጠር ያለው ሲሆን የአሮጌው ዓመት ማለቂያ እና የአዲሱ ዓመት መጀመሪያ  ትክክለኛ ዕለት የብሔሩ  ሊቃውንት (አያንቶ) ተወስኖ ይታወጃል፡፡ የፊቼ ጫምባላላ በዓል በዓለም መንፈሳዊ ቅርስነት ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን ቅድመ ምዝገባ የመጀመሪያ ዙር መረጃ የማሰበሰብ ሥራ መጠናቀቁን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ስለ ፊቼ እና ጫምባላላ መንፈሳዊ ባህል ምንነትና መገለጫዎቹን የክብረ በዓሉ ድባብ፣ የዘመን አቆጣጠር ምስጢራትንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እንደሚከተለው ተቀኝቷል፡፡ 

የፊቼ እና ጫምባላላ ምንነትና አመጣጥ 

በሲዳማ ፍቼና ጫምባላላ የማይነጣጠሉ የበዓሉ ሁነቶች ናቸው፡፡ ፊቼ የአሮጌው ዘመን መጠናቀቅ (ዋዜማ) ጫምባላላ የአዲሱ ዘመን (መባቻ) ብስራቶች ናቸው፡፡ ‹‹ፊቼ›› መጽሔት 2006 .. ዕትሙ፣ ፊቼና ጫምባላ ታሪካዊ  አጀማመር መቼ እንደሆነ በውል ባይታወቅም በዞኑ በሀቤላ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ከነበሩት ፊጦራ የሚባሉ ሰውዬ ሴት ልጃቸው ፊቾ አማካይነት መጀመሩን ለቅድመ ምዝገባ ጥናት የተሰበሰበው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

ፊቾ የምትባለው የአቶ ፈጠራ ልጅ ለአቅመ ሔዋን ደርሳ ባል ስታገባ የሞቀ ትዳር፣ የተትረፈረፈ ሀብት ስታገኝ በብሔሩ ባህል መሠረት እናት አባቷን ቅቤ፣ የተሠራ ቆጮና የረጋ ወተት ይዛ እየመጣች በየዓመቱ ‹‹ቀባዶ›› ተብሎ በሚጠራው ቀን  ትጠይቃቸው ነበር፡፡ ያመጣችውን ምግብ ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድና ጎረቤቶች ከበሉ በኋላ ከአባቷ ጋር ምርቃትና አድናቆታቸውን ይገልጹላታል፡፡ በእርግጥ በሲዳማ ባህል ልጆች የሚመገቡት ትላልቆቹና አዋቂዎቹ ከበሉ በኋላ ስለሆነ  የቀረውን የቤተሰብና የጎረቤት ልጆች አንድ ላይ ተሰብስበው ይመገቡና ደስታቸውን ጫምባላላ (የዚህ አይነት ጥጋብ ዞሮ ይምጣ) እያሉ በዘፈን ይግልጻሉ፡፡ መሰል የፊቾ ጥየቃ በዘላቂነት መታወስ እንዳለበት በመግለጽ አባቷ አቶ ፌጦራ በየዓመቱ ደስታና ፋሲካ የምትፈጥረው ልጃቸው የምትመጣበት ቀን የሲዳማ ፌቼ ተብሎ እንዲከበር ከአካባቢው ኅብረተሰብ ተቀባይነት አግኝቶ በጎሳ መሪዎች የዘመን መለወጫ እንዲሆን መወሰኑን የጥናቱ መረጃ ያስረዳል፡፡ ይሁን እንጂ የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ፊቼና የቀን አቆጣጠር ከፊቾ ታሪክ ጋር ስለመያያዙ ከአፈታሪክ መረጃ በስተቀር ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልገው ተጠቁሟል፡፡ በሌላ በኩል በዘመናት ደት የብሔሩ ሊቃውንት የየዓመቱን ዙር መሠረት አድርገው የቀን፣ የወርና የዓመት አቆጣጠር ዘዴን በመቀመር ፊቼ የሲዳማ የዘመን መለወጫ በዓል እንዲሆን መወሰናቸውን ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ተብራርቷል፡፡ ፊቼ ትርጉሙም የዘመን መለወጫ ድልድይ አዲሱ ዓመት የበረከት የደስታና ፍሥሐ ይሁንልን እንደማለት ነው፡፡ ከዋዜማ ቀጥሎ ያለው ቀን አዲስ ዓመት ወይም ጫምባላላ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ስለአለፈው ዓመት ለፈጣሪ ምስጋና፣ ስለቀጣዩ ደግሞ የመልካም ምኞት የሚገለጽበት የደስታና ፍንደቃ ዕለት ይሆናል፡፡ 

የፊቼና ጫምባላ መንፈሳዊ ባህል መግለጫ አጀቦች

 ፊቼ የአሮጌው ዓመት መጨረሻ የአዲሱ ዋዜማ እንደመሆኑ የብሔሩ ሊቃውንት የጨረቃና ኮከብ አቅጣጫና ቁጥር ተመልክተው የዘመን መለወጫ ትክክለኛ  ወሩንና ቀኑን ከወሰኑ በኋላ ለሕዝቡ ከአንድ ሳምንት በፊት በገበያ ይታወጃል፡፡ ይህም ላላዋ ይባላል፡፡

የዘመን መለወጫ ቀኑ ከታወጀ በኋላ የብሔሩ ባህላዊ መሪዎች (ዎማች) ለፊቼ ሳምንት ሲቀረው ከአንድ ወር በፊት የጀመሩት ጾምና የሱባኤ (የንስሐ) ጸሎታቸውን ያጠናቅቃሉ፡፡ በተጓዳኝ ሴቶች ለበዓሉ ማመቂያ ቅቤ፣ ቆጮ፣ ወተትና ቅመማቅመም ያዘጋጃሉ፡፡ ወጣት ወንዶች እንጨት ወጣት ሴቶች ለእናታቸውና ረዳት ለሌላቸው ጎረቤቶች የሚያቀርቡበትና የሚረዱበት ጊዜ ይሆናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ዋዜማን ከደረሱ በኋላ በእርጥብ ቅጠል የተዘጋጀ መሽሎኪያ (ሁሉቃ) ፀሐይ ስታዘቀዝቅ የቤተሰቡ አባላትና ከብቶች በዚያ ሾልከው እንዲያልፉ ይደረጋል፡፡ ይህም ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ በሰላም ተሸጋግረን ማለት ይሆናል፡፡ መሰል ትዕይንት በዞኑ ሁሉም አከባቢዎች በየደጁ የሚከናወን ሲሆን፣ በሐዋሳ ከተማ ሲዳማ ባህል አዳራሽ የሁሉም ጎሳ መሪዎችና አባቶች በተገኙበትም ይከናወናል፡፡ ከዚያም የበዓሉ ማድመቂያ ርችት ይሎኮስና በድምፅና ሕብርቀለማት ደስታ ይገለፃል፡፡ ባለፈው ሐምሌ 29 ቀን 2005 .. የተደረገው ይኸው ዓመታዊ ትዕይንት ነው፡፡ በእርግጥ የፊቼ ክበረ በዓል አጀቦች ከላይ ከተገለጹት በተጨማሪ በየአካባቢው ታላቅ ሽማግሌ ቤት ማታ ቆጮ በቅቤ በባህላዊ መመገቢያ ቀርቦ በዎማች ተመርቆ አንድ ላይ ተሰብስበው በመብላት ደስታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ሌላው ገጽታ ደግሞ ፊቼ በዕለት ከብት አለመታረዱ ነው፡፡ ቀድሞ የነበረ ሥጋ ካለ ከቤት ውጭ በእንስሳት ጉያ ያሳድሩታል፡፡ ይህም በፊቼ ክብረ በዓል የሲዳማ ብሔር ለከብት ያለውን ትልቅ ፍቅር የሚያሳይበት በመሆኑ የእንስሳትም ደስታ እንደሆነ ያሳስባል፡፡ 

ጫምባላላ

ጫምባላላ (ዞሮ መምጣት ማለት ነው) አዲሱ ዓመት የሚጀመርበት ልጆች ምንም ሥራ የማይሠሩበትና እየዞሩ የሚመገቡበት፣ ከብቶች ለዚህ ቀን ተከልሎ በቆየ ጥብቅ ውስጥ ተለቀው የሚግጡበት ቀን ነው፡፡ ልጆቹ ‹‹አይዴ ጫምባላላ›› (ዞረን መጣን) እያሉ ተስብስበው በየአካባቢው ሲዞሩ እናቶች ‹‹እሌ...እሌ..›› ወይም ‹‹ድረሱ....ድረሱ›› በማለት በቅቤ የተዘጋጀውን ቆጮ (ቡሪሳሜ) ያቀርቡላቸውና ይበላሉ፡፡ እስከ ጠዋቱ ሦስት ሰዓት መብላት መጠጣቱ ከቀጠለ በኋላ በየሕዝብ መሰብሰቢያ (ጉዱማሌ) ወጥተው የበዓሉን ስሜት ይገልጻሉ፡፡ ባለፈው ሐምሌ 30 ቀን 2005 .. ሐዋሳ ከተማ ከጧቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ ከሲዳማ ዞን 19 ወረዳዎችና  ሁለት የከተማ አስተዳደሮች በእግር በፈረስና በመኪና ሐይቅ ዳር ወደሚገኘው ጉዱማሌ የሕዝብ መሰብሰቢያ በሚተሙ እድምተኞች ጡሩምባና ዘፈን በአንድ እግሯ ቆማ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከረፋዱ አራት ሰዓት አካባቢ በፈረስ የታጀቡ ከተለያዩ አከባዎች የመጡ አረጋውያንና ጎልማሶች በዜማ የታጀበ ዘፈን እየዘፈኑ በጭፈራ (ቄጣለላ ወጣት ሴትና ወንዶች፣ ፋሮ ያላገቡ ሴቶች ሆሬ በተባሉ ባህላዊ ጭፈራዎች) የአዲሱን ዓመት አቀባበል አድምቀውታል፡፡     

የፊቼ በዓልና የቀን አቆጣጣር ምስጢራት

የፊቼ በዓል በየትኛው ቀንና ወር እንደሚውል የብሔሩ ባህላዊ ሊቃውንት ወይም አዋቂዎች /አያንቶ/ በጨረቃ ምልክትና ኮከብ ቆጠራ ስሌት ትክክለኛውን ዕለት ይወስናሉ፡፡ በሲዳማ ዞን በየወረዳዎቹና ከተማ አስተዳደሮች ሉዋ ተብሎ የሚጠራው አስተዳደራዊ መዋቅር ሥልጣን ያላቸው ማለትም ዎማ፣ ጋሮ፣ ሞቴ፣ ጋኔ፣ አማካይነት በአያንቶዎች የተገኘው የኮከብ ቆጠራና ጨረቃ ምልከታ ውጤት ይነገራቸዋል፡፡ በብሔሩ አስራ አራቱ ጎሳዎች ያሉት አያንቶዎች ለየአካባቢው ዎማዎች ይነግራሉ፤ እነሱም በተራቸው ለጎሳ መሪዎች (ሞቴ) በአጭር ጊዜ ውስጥ መልዕክቱን በማስተላለፍ የፊቼ በዓል የሚውልበት ቀን የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ በዘንድሮው በዓል በባህላዊ ጭፈራ (ቄጣላ) የፊቼ ጫምበላላን ክብረ በዓል ከፊት ሆነው ሲመሩ ከነበሩት አያንቶዎች አንዱ የሆኑትን አቶ ጋዱዳ ጋቢሶን ስለ ኮከብ ቆጠራና ጨረቃ ምልከታ በሪፖርተር ጋር አጭር ቃለ ምልልስ አድርገው የሚከተሉትን ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡

የጨረቃ ምልከታ ኮከብ ቆጠራ

እንደ አቶ ጋዱዳ ማብራርያ፣ በሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ከመድረሱ አንድ ወር አካባቢ ሲቀረው በየጎሳዎቹ የሚገኙት እሳቸውን ጨምሮ ታላላቅ አባቶች (ጪሜሳ) ስብሰባ ይቀመጣሉ፡፡ በዚያ ስብሰባ በዓመቱ ካሉት አስራ ሁለት ወራት በአሥራ አንደኛው ከእንግዲህ ጪሜሳዎች ወደ ዳስ በመግባት ለቀጣይ ተግባር ፊቼ ለመድረስ አንድ ሳምንት እስከ ሚቀረው ድርስ የንሥሐ ጸሎት ይደረጋል፡፡ በነዚህ ሠላሳ ቀናት መጪው ዓመት የሰላም፣ የበረከት፣ ከብቶች የሚረቡበትና ወተት የሚሞላበት ለሕዝቡ የደስታና የጤና እንዲሆን እንዲሁም አዝመራና የአየር ንብረቱ ተስማሚ እንዲሆን ይጸልያሉ፡፡ አቶ ጋዱዳ እንዳስረዱት በንሥሐ ጸሎት ጊዜ የትኛውም ጪሜሳ ሴት በፍጹም አትጠጋውም እነሱም እንደዚያው ርቀው ይቆያሉ፡፡ ምግብ የሚያቀርቡት ትናንሽ ልጆች ናቸው፡፡ ይህ መሰሉ እሳቤም ከኃጢአት እንዲርቁና ፈጣሪም ጸሎታቸውን እንዲሰማ ተብሎ  ነው፡፡

ስለ ኮከብ አቆጣጠሩና ጨረቃ ምልከታ አቶ ጋደዳ የሚከተለው ይላሉ፡፡ ‹‹በእርግጥ የኮከብ ምልክት ከታሪክ  አንፃር ካየነው  በጥንት ዘመን ኢየሱስ ክርስቶስም በኮከቦች እንቅስቃሴ ይመራ ነበር፡፡ በእኛ በሲዳማ ኮከብና የቀን አቆጣጠር አሥራ ሁለት ወራትን በመቁጠር የሚከናውን ሲሆን፣ ፊቼ ሳምንት ሲቀረው  የምልከታ ቀን (ላኦ) በየዓመቱ የምናወቃቸው ሃያ ሰባት ኮከቦች አሉ፡፡ እነዚያ ኮከቦች የሚታዩት በየወሩ በሃያ ሰባተኛው ቀን ሲሆን የተመለከትንበትን ቀን ከቆጠርን በሃያ ስምንተኛው ቀን  ይታያሉ ማለት ነው፡፡ 

በሲዳማ አንድ ወር ማለት አሥራ አምስት የጨለማና አስራ አምስት የጨረቃ ቀኖች ተቆጥረው ነው፡፡ ዓመቱ ከተጀመረ ዕለት ጀምሮ 12 ወር ማለቂያ አካባቢ የፊቼ በዓል ጨለማው ከማለቁ 11 ወይም 13ኛው ቀን ቀባዶ በዕለት እንዲውል ይደረጋል፡፡ እዚህ ላይ በሲዳማ ቀኖች ሁሉ ጥሩ ባለመሆናቸው ኮከቦቹን ከጨረቃ አንፃር ያሉበት አቅጣጫ በማየት ሁለት ወይም ሦስት ቀኖች ወደፊት ወደኋላ በማድረግ የግዴታ በቃባዶ ቀን እንዲሆን እንወስናለን፤ ቀባዶ ቀን እንዲውል የተፈለገበት ምክንያት ቀኑ ታሪካዊ በመሆኑና የሳምንቱ የተቀደሰ የመጀመሪያ ዕለት ስለሆነም ነው፤›› ይላሉ፡፡ እንደ አቶ ጋዱዳ ፊቼ የሚውልበትን ትክክለኛ ቀን ብቻ ሳይሆን በየወሩ ኮከብ ቆጠራና ጨረቃ ምልከታ ይደረጋል፡፡ ምክንያቱም አዲስ ቤት ለመሥራት፣ ሴት ልጅ ለማጨት፣ ጦርነት ካለ ለመዝመት፣ ስለአዝመራ ወቅቶችና ሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድርጊቶችን ለመከወን ትክክለኛ ቀንና ዕለት ይወሰናል፡፡

የሲዳማ ፊቼ - ጫምባላላ ከሙስሊም ጾም ጋር ይመሳሰል ይሆን?

ለዚህ ጥያቄ የሲዳማ አያንቶ የአቶ ጋዱዳ ምላሽ አውንታዊ ነው፡፡ ሆኖም አንድ አይነት ነው ማለት እንዳልሆነ ያሰምሩበታል፡፡ የሚመሳሰልውም ሲዳማም ሆነ የሙስሊሙ ጾምና ፍቺ በጨረቃና  ክዋከብት ሥርዓት (Lunar system) ጋር የተገናኙ በመሆኑ ነው፡፡ ‹‹ሁልጊዜ የሙስሊም ጾም የእኛን ፊቼ በዓል አንድ ወይም ሁለት ቀን ዘግይቶ ይውላል፡፡ አልፎ አልፎ በእኛ ቀን ጫምባላላ ቀን ሊውል ይችላል፤›› በማለት ካብራሩ በኋላ አንድ የሙስሊም ወዳጄ የጫምበላላ ማግስት ባነጋገርኩበት ቀን ‹‹ ለምሳሌ እኔ ባለኝ ተሞክሮና ምልከታዬ ጾማቸው ነገ (ሐሙስ) ሊፈታ እአንደሚችል ነግሬዋለሁ›› በማለት ስለዕውቀታቸው ገልፀዋል፡፡

የሲዳማ የቀን መቁጠሪያ እንዴት ይዘጋጃል?

የሲዳማ ዞን ባህል ቱሪዝምና መንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያ በየዓመቱ ከመደበኛው የኢትዮጵያ አቆጣጠር ጋር አያይዞ የዘመን መቁጠሪያ (ካሌንደር) ያሳትማል፡፡ እንዴት እንደሚያዘጋጅ የመምሪያ ኃላፊውን ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ፍላቴ ጠይቀን የፊቼ ጫምባላላ በዓል በየዓመቱ የሚውለው በተለያዩ ቀናትና ወር በመሆኑ የሚወሰነው በአያንቶዎች ጨረቃ ምልከታና ኮከብ ቆጠራ ነው ብለውናል፡፡ 

ነገር ግን አያንቶዎች ባላቸው የኮከብ ቆጠራ ጥበብና ተስጥኦ በትክክል ፊቼ የሚውልበትን ቀን በማወቅ እንደሚወስኑ ያብራሩት አቶ ወርቅነህ፣ ‹‹ለምሳሌ 2007 .. መቼ እንደሚሆን መዳረሻ ቀኖችን ከእነርሱ ስላወቅን የቀን መቁጠሪያውን ማዘጋጀት እንችላለን፡፡ ለትክክለኛው ቀን የአያንቶዎችን ውሳኔም እንጠብቃለን፤›› በማለት አክለዋል፡፡ 

ከዚህ ጋር በተገናኘ 2004 .. የሁላ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሸዋሌ አዱላ የተባሉት ምሁር 10 ዓመታት የፊቼ በዓል የሚውልበትንና የቀን መቁጠሪያውን አስልተው ማቅረባቸውንም አቶ ወርቅነህ ጠቁመዋል፡፡

ፊቼ - ጫምባላላን በዩሴስኮ በመንፈሳዊ ቅርስነት የማስመዝገብ እንቅስቃሴ

የሲዳማ ዞን ባህል ቱሪዝምና መንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ከፌደራልና ከክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋራ በመተባበር የፊቼ በዓል ከመስቀል በዓል ቀጥሎ  በመለያ ቁጥር 002 ቅድመ ምዝገባ ተደርጎለት 2005 .. ከግንቦት እሰከ ሰኔ ለአንድ ወር መረጃ የማስባሰብ ሥራ መሠራቱን የመምሪያ ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ገልጸዋል፡፡

ዩኔስኮ ባስቀመጠው ፎርማት (ICH-02) መሠረትም የምዝገባ ጥያቄውን ለመሙላት የሚያስችል ቅድመ ምዝገባ ጥናት መደረጉና በአሁን ወቅት የቀረው የክብረ በዓል አስር የፎቶግራና የቪዲዮ እንዲሁም የጽሑፍ ስነዶች እንዳቀርቡ በመጠየቁ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ ይህ ሥራም በመስከረም 2006 .. ለክልልና ፌደራል ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ከቀረበ በኋላ በጥር 2006 .. ለዩኔስኮ ተጠናቆ እንደሚቀርብ አስረድተዋል፡፡

 

ከሪፖርተር ጋዜጣ

 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር