‹‹የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ስድስት ዓመት ገለልተኛ ሆኖ ካገለገለ በኋላ ነፃ ሆኖ ሐሳቡን መግለጽ መቻል አለበት››

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ የመጀመሪያው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት
ከሽግግር መንግሥቱ በኋላ በኢትዮጵያ በሦስት ዙር (ተርም) ሁለት ርዕሰ ብሔሮች [ፕሬዚዳንቶች] ተሰይመዋል፡፡
ላለፉት 12 ዓመታት በሥራ ላይ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በ2005 ዓ.ም. የሥራ ዘመናቸው ያበቃል፡፡ በ2006 ዓ.ም. በመስከረም ወር መጨረሻ አካባቢ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ጉባዔ ሲከፈት ለሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት የሚያገለግሉ አዲስ ፕሬዚዳንት ይሰየማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ወደተንጣለለው ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ማን ሊገባ ይችላል የሚለው ጉዳይ እስካሁን ባይታወቅም፣ የተለያዩ የኅብረተሰቡ ክፍሎች የተለያዩ ሰዎችን ሰብዕና በመምዘዝ እየተነጋገሩ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲም በዚህ ጉዳይ ላይ መጠመዱ ተሰምቷል፡፡ ኢትዮጵያ ፓርላሜንታዊ ሥርዓት የምትከተል አገር ተደርጋ የኢፌዲሪ መንግሥት ሲመሠረት፣ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሆነው መንበሩን የተቆናጠጡት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ነበሩ፡፡ ከፕሬዚዳንትነታቸው ቆይታ፣ ከቤተ መንግሥት ሕይወትና ከቀጣዩ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አሿሿምና ተግባር ጋር በተያያዘ የአሁኑን የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶን ውድነህ ዘነበ አነጋግሯቸዋል፡፡ 
ሪፖርተር፡- የኢፌዲሪ መንግሥት ሲመሠረት የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሆነው የተሰየሙት እርስዎ ነበሩ፡፡  የተመረጡበት ሒደት እንዴት ነበር? የተጠቆሙ ሰዎችስ ነበሩ?
ዶ/ር ነጋሶ፡- በ1987 ዓ.ም. ከምርጫው በፊት ነው የሆነው፡፡ ሒደቱ አሁን ተለውጦ ከሆነ አላውቅም፡፡ የዚያን ጊዜ በሥራ አስፈጻሚ ተነጋግረን ሦስት ሐሳቦች ቀረቡ፡፡ አንደኛ ወ/ሮ ገነት ዘውዴ፣ ሁለተኛ ፕሮፌሰር ጀማል አብዱልቃድር [የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩ]፣ ሦስተኛ አምባሳደር ተከተል ፎርሲዶ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡ ወ/ሮ ገነት ንቁ የሴቶች ተወካይ እንድትሆን ምናልባትም የነበረውን ባህል ለመቀየር በሚል ነው ፕሬዚዳንት እንድትሆን ሐሳብ የቀረበው፡፡ ሌላው ፕሮፌሰር ጀማል በዕድሜ በሰል ያሉና የታወቁ ሰው ናቸው፡፡ እሳቸው ፕሬዚዳንት ቢሆኑ ተብሎ ሐሳብ ቀረበ፡፡ አምባሳደር ተከተል የበሰሉ ሰው ቢሆኑም በኅብረተሰቡ ዘንድ ብዙም የማይታወቁ በመሆናቸው ስለሳቸው ገኖ አልወጣም፡፡ 
ከዚያ በፊት የኢሕአዴግ የሥራ ክፍፍል እየተደረገ ነበር፡፡ በክፍፍሉ የኢሕአዴግ ሊቀ መንበርና የሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ከብዙ ልምድና ብቃት አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ 
ሪፖርተር፡- የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ አቶ መለስ እንዲይዙት አራቱም የኢሕአዴግ መሥራቾች ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ኦሕዴድ፣ ደኢሕዴግ፣ ብአዴንና ሕወሓት ስምምነት ላይ ደርሰን ነበር፡፡ ለብአዴን፣ ለደኢሕዴግ፣ ለኦሕዴድና ለሕወሓት ከተሰጠው ቦታ በተጨማሪ ለሌሎቹ ቦታዎች ማን ይመደብ የሚል ሐሳብ ነበረ፡፡ ለአፈ ጉባዔነት ቦታ ከሕግ ዕውቀታቸው በመነሳት በሽግግር መንግሥት ጊዜ በመንግሥት ሥልጣን ላይ የነበሩት አቶ ዳዊት ዮሐንስ ይሁኑ የሚል ሐሳብ ቀረበ፡፡ ለፕሬዚዳንትነት ደግሞ ከኦሮሞ (ኦሕዴድ) ቢሆን፣ በሌላ በኩልም ለፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሰው ያስፈልግ ነበር፡፡ እነዚህን ቦታዎች ማለትም ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ፕሬዚዳንት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ቦታዎችን እንከፋፈል የሚል ሐሳብ ቀረበ፡፡ ከዚህ አንፃር የኦሮሞን ሕዝብ ብዛት በማየት የፕሬዚዳንትነትን ቦታ ኦሕዴድ እንዲያገኝ ተወሰነ፡፡ ስለዚህ በተጨባጭ ሲመጣ ፕሬዚዳንት ማን ይሁን? የሚለው መታየት ጀመረ፡፡ ወ/ሮ ገነት ሴት ናት፡፡ ምንም እንኳ የታወቀች ቢሆንም በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ውስጥ ሴትን ፕሬዚዳንት አድርገን ብናስቀምጥ ተቀባይነታችን ምን ይሆናል የሚል ሐሳብ ቀርቦ ውይይት ተደረገ፡፡ በዚህም ወ/ሮ ገነትን ፕሬዚዳንት የማድረግ ሐሳቡን ለጊዜው እናቆየው የሚል ድምዳሜ ላይ ተደረሰ፡፡ እሷ ፕሬዚዳንት ካልሆነች ምን ዓይነት ቦታ ይሰጣት ተባለና ለአፈ ጉባዔነት ከአቶ ዳዊት ጋር ለውድድር ቀረቡ፡፡ ከብቃት አንፃር በሚል አቶ ዳዊት አፈ ጉባዔ ይሁኑ ተባለ፡፡ ለፕሬዚዳንትነት ፕሮፌሰር ጀማል እንዲሆኑ ሐሳብ ቢቀርብም እሳቸው መሆን እንደማይችሉ አንዳንድ ሐሳቦች በመቅረባቸው ውድቅ ተደረገ፡፡
ስለዚህ ፕሬዚዳንት ከኦሕዴድ ይሁን በመባሉ ሰው ተፈለገ፡፡ ዕድሜና የቋንቋ ዕውቀት፣ ቢያንስ የአገሪቱን ሁለት ቋንቋዎች የሚያውቅና ከውጭ አገርም ቢያንስ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቃት ያለው ይቅረብ ተባለ፡፡ በኦሕዴድ ውስጥ አብዛኛዎቹ ወጣቶች ናቸው፡፡ ከእኔ በዕድሜ የሚበልጥ አልነበረም፡፡ ከዚያ በፊትም በሕገ መንግሥት አርቃቂ ጉባዔ ወቅት ጉባዔውን የምመራው እኔ ነበርኩ፡፡ በዚህ ወቅት በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ አካላት ለእኔ ጥሩ አመለካከት ነበራቸው፡፡ ያም ብቻ ሳይሆን ጉባዔው በቴሌቪዥን ይተላለፍ ነበርና በተቻለኝ መጠን ውይይቱ ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ለማድረግ እሞክር ነበር፡፡ እነሻለቃ አድማሴ ዘለቀን ለመሳሰሉ ተፃራሪ አቋም ለነበራቸው ተሳታፊዎች ዕድል እሰጥ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎቹ ከኢሕአዴግ የተለየ ሐሳብ ነበራቸው፡፡ በዚህ ምክንያት በኢሕአዴግ አንዳንድ ወገኖች በኩል ሰዎቹ እንዳይናገሩ ዕድል የመንፈግ ፍላጎት ነበር፡፡ እኔ ግን የኢሕአዴግን ጫና ተቋቁሜ ዕድል እሰጣቸው ነበር፡፡ የመናገር መብት አላቸው በሚል ዕድል እሰጣቸው ነበር፡፡ ይህ ሒደት በቴሌቪዥን ይተላለፍ ነበርና በሕዝቡ ውስጥ ተቀባይነት አግኝቼ ነበር፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ነጋሶ ፕሬዚዳንት ይሁን የሚል ውሳኔ እኔ በሌለሁበት ተላለፈ፡፡ በዚህ መሠረት ከአቶ አባዱላ ገመዳና ከአቶ ኩማ ደመቅሳ ጋር አቶ ኩማ ቤት ተገናኝተን ይህንን ሐሳብ አቀረቡልኝ፡፡ 
ሪፖርተር፡- ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ የቀረበልዎትን ጥያቄ ወዲያውኑ ተቀበሉ?
ዶ/ር ነጋሶ፡- እኔ በዕድሜ ብልጫ ያለኝ ብሆንም ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊ መሆን እፈልግ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት በምትሆንበት ጊዜ ከፖለቲካ ተሳትፎ ትገደባለህ፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ ኃላፊነቶች ብዙም አልነበሩም፡፡ ስለዚህ ተከራከርኩ፡፡ የኦሕዴድን ሥራ ብሠራ ይሻላል አልኩ፡፡ ነገር ግን የድርጅት ውሳኔ ስለሆነ በድርጅቱ በኩል አገሪቱን አገለግላለሁ ካልክ የድርጅቱን ውሳኔ መቀበል አለብህ፡፡ በተጨማሪም አቶ መለስ ቢያንስ ካለህ የፕሬዚዳንትነት የሥራ ሰዓት 15 በመቶውን ነው የሚወስደው፡፡ የተቀረውን 85 በመቶ የድርጅት ሥራ ልትሠራ ትችላለህ፡፡ የኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚ ሆነህ ልትሠራ ትችላለህ የሚል ሐሳብ ስላመጡ፣ የፖለቲካ ሥራውን እያከናወንኩ የፕሬዚዳንትነት ሥራ መሥራት እችላለሁ ብዬ ተቀበልኩ፡፡ 
ሪፖርተር፡- የፕሬዚዳንትነት ቆይታዎ እንዴት ነበር? በሕገ መንግሥቱ ለፕሬዚዳንት የሚሰጡትን ኃላፊነቶች በሚገባ መወጣት ችለዋል ወይ?
ዶ/ር ነጋሶ፡- የፕሬዚዳንት ኃላፊነትና ተግባር በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 71 ተዘርዝሯል፡፡ አንደኛው በአዲስ ዓመት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤትን የጋራ ስብሰባ መክፈት ነው፡፡ ሁለተኛው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቁትን አዋጆችና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በነጋሪት ጋዜጣ ፈርሞ ማውጣት ነው፡፡ ሦስተኛው አገሪቱን በውጭ አገር የሚወክሉ አምባሳደሮችንና መልክተኞችን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት መሾም ነው፡፡ አራተኛው የውጭ አገር አምባሳደሮችንና ልዩ ልዩ መልዕክተኞችን የሹመት ደበዳቤ መቀበል ነው፡፡ አምስተኛው በሕግ መሠረት ኒሻኖችንና ሽልማቶችን መስጠት ነው፡፡ ስድስተኛው በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕግ በተወሰነው መሠረት ከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረጎችን መስጠት ነው፡፡ ሰባተኛው በሕጉ መሠረት ይቅርታ ማድረግ ነው፡፡ የፕሬዚዳንቱ ተግባሮች እነዚህ ናቸው፡፡ እነዚህን በተመለከተ ችግር አልነበረም፡፡ ኃላፊነቴን እወጣ ነበር፡፡ እክልም አልገጠመኝም፡፡ ነገር ግን ምናልባት ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛ ፕሬዚዳንቱ የአገሪቱ ምልክት ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ የአገሪቱ ወኪል ነው፡፡ ወደ ውጭ አገር ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ይንቀሳቀሳል፡፡ ይህ እንግዲህ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና አገሮችን መጎብኘት የሥራው አካል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በውጭ አገር ኢትዮጵያን ስትወክል ወደ ውስጥ ደግሞ ከሁሉም በላይ ሆነህ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በላይ ሆነህ አንድነትን የማጠናከር ጉዳይ አለ፡፡ 
ሌላው 85 በመቶ የኦሕዴድን ሥራ ሳከናውን 15 በመቶ ከሚሆነው ጊዜዬ የፕሬዚዳንት ሥራዬን እሠራለሁ፡፡ በወቅቱ የኦሕዴድ የድርጅትና የፕሮፓጋንዳ ኃላፊ ነበርኩ፡፡ በኢሕአዴግ ደግሞ የሚዲያ ኮሚቴ አባል ነበርኩ፡፡ እንደገናም ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ ስለነበርኩ ብዙ ጊዜ በሥራ ተጠምጄ ነበር፡፡ እናም ወደ ውጭ በመሄድና በአገር ውስጥም በመንቀሳቀስ የፕሬዚዳንትነት ሥራ ለመሥራት ያን ያህል አልነበርኩም፡፡ ሁለተኛ የውጩን በሚመለከት በደንብ የታሰበበት አልመሰለኝም፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ብዙም ያሰበበትና ዕቅድ የያዘበት አይመስልም፡፡ ውሳኔ የሚፈልጉ ስብሰባዎችም ባይሆኑ በዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓመታዊ ጉባዔ አለ፡፡ በዚያ ወይም በአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አፍሪካ ኅብረት) ጉባዔ ላይና ትላልቅ በዓላት ላይ መገኘትና በተለያዩ አገሮች ጉብኝት በማድረግ በኩል ታቅዶበት አልተሄደም፡፡    
ሪፖርተር፡- ከእርስዎ በኋላም ይህ ዓይነቱ ሥራ ታቅዶበት እየተሄደበት ነው ማለት ይቻላል?
ዶ/ር ነጋሶ፡- እንደሚገባኝ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የበላይነት የሚከናወን የአስተዳደር ሥራ አለ፡፡ በፕሬዚዳንቱ የበላይነት የሚከናወን የውክልና (የምልክትነት) ሥራ አለ፡፡ እነዚህን ለያይቶ የማስቀመጥ ችግር አለ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም ቦታ እንዲሄድ ይደረጋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ግን አይሄድም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላልቅ ስብሰባዎችም ላይ ሲገኝ ለአስተዳደር ሥራ ነው፡፡ በሌላ በኩል የአገር ውክልናን በተመለከተ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ትልቅ ትኩረት የተሰጠው አይደለም፡፡ ምናልባት የአሁኑን በተመለከተ እንዳለ ሆኖ፣ በአሁኑ ፕሬዚዳንት በኩል (አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ) የዕድሜና የጤና ጉዳይ አለ፡፡ ይኼም ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ፕሬዚዳንት የሚሆን ሰው በጣም ወጣት ያልሆነ፣ በጣም ያረጀም ያልሆነ፣ የጤናው ሁኔታ የተስተካከለ መሆን ይኖርበታል፡፡ አገርን መወከል የሚችለው ፕሬዚዳንት እስከሆነ ድረስ ማለት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ እኔ በዚያን ወቅት በድርጅት ሥራ ተወጥሬ ያን ያህል ባላከናውነውም ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት ቢታሰብበት ይሻላል እላለሁ፡፡ 
ሁለተኛ ደግሞ በሕግ በተወሰነው መሠረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ የውትድርና ማዕረጎችን ይሰጣል፡፡ እስከ 1993 ዓ.ም. ድረስ ይህ ተግባራዊ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን በኢሕአዴግ ውስጥ ችግሮችና መከፋፈሎች የተፈጠሩበት ወቅት ነበር፡፡ ከእኔም ጋር ጭቅጭቆች ነበሩ፡፡ አንድ ቦታ ላይ እነ ሌተና ጄነራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ [የቀድሞው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም] ከሥልጣን ሲነሱ፣ በወቅቱ ሜጀር ጄነራል የነበሩት አቶ አባዱላ ከመከላከያ ወደ ሲቪል ኃላፊነት ተቀየሩ፡፡ በፊት ግን እኔ ነበርኩ የሾምኳቸው፡፡ ሲነሱም ፕሬዚዳንቱ እኔ ነበርኩ ማንሳት ነበረብኝ፡፡ በአሠራሩ የነበረውም ኮሚቴው ይወስንና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀርባል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም አስተያየቱን አክሎ ወደ ፕሬዚዳንቱ ያቀርባል፡፡ ፕሬዚዳንቱም በቀረበው ሐሳብ መሠረት ያነሳል፡፡ ይህ በወቅቱ አልሆነም፡፡ እነዚህ እንደ ችግር ሊታዩ ይችላሉ፡፡  
ሪፖርተር፡- በሕገ መንግሥቱ ለፕሬዚዳንቱ የተሰጡት ኃላፊነቶች በቂ ናቸው ይላሉ?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ምን ዓይነት ሥርዓት ነው የምንከተለው የሚለው ይወስነዋል፡፡ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ከሆነ አንድ ነገር ነው፡፡ ፓርላሜንታዊ ከሆነ ሌላ ነገር ነው፡፡ የእንግሊዝን ከወሰድን አገሪቱን የሚወክሉት ንጉሡ ወይም ንግሥቲቱ ናቸው፡፡ በአስተዳደሩ ሥራ ውስጥ አይገቡም፡፡ የአስተዳደር ሥራው የሚሠራው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ያንን ከመረጥክ በዚያው ትሠራለህ፡፡ እንደ አሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ከተመረጠ ፕሬዚዳንቱ ምልክት ወይም ወኪል ብቻ አይደለም፡፡ የአስተዳደር ሥራውንም አጣምሮ ይሠራል፡፡ በሌሎች አገሮችም ለምሳሌ ጀርመን ቻንስለሩ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደራዊ ሥራ ይሠራል፡፡ ፓርላሜንታዊ ነው፡፡ ጣሊያንም እስራኤልም እንዲሁ ነው፡፡ እኛ የተቀበልነው የእነዚህን ፓርላሜንታዊ ሥርዓት የሚከተሉትን አገሮች ሥርዓት ነው፡፡ 
ፕሬዚዳንቱ ሥልጣኑ ይበቃዋል ወይም አይበቃውም ከሚለው አንፃር ምናልባት ወደፊት ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱን ከነጭራሹ ጉልበት አልባ የሚያደርገው የሕግ ጉዳይ ነው፡፡ በአዋጁ ፕሬዚዳንቱ አገሪቱን የሚወክል ከሆነ አንዱን ፓርቲ ወይም መንግሥትን ብቻ አይወክልም፡፡ ሕዝብንም ይወክላል፡፡ የአስተዳደሩን ሥራዎች የተለያዩ የመንግሥት አካላት እንዲሠሩ የሚያስችሉ ሕግጋት ይወጣሉ፡፡ ሕጎች በሚወጡበት ጊዜ አንዳንዴ ሕገ መንግሥቱን ይጥሳሉ ወይም የአገሪቱን የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚጎዱ ሆነው ሊወጡ ይችላሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱ እነዚህን ሕጎች በሁለት ሳምንት ፈርሞ እንዲያፀድቅ ይቀርቡለታል፡፡ የእኛ ሕግ ፕሬዚዳንቱ በፓርላማው የፀደቀው አዋጅ ሲደርሰው፣ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ፈርሞ መመለስ ይኖርበታል ይላል፡፡ ፈርሞ ካልመለሰ አዋጅ እንደሆነ ይቆጠራል ይላል፡፡ ስለዚህ አዋጅ ለፕሬዚዳንቱ የሚቀርበው ለስሙ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በቀረበው አዋጅ ቢስማማም፣ ባይስማማም ፈርሞበት ማሳለፍ ይኖርበታል ይላል፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ አንፃር እርስዎ የገጠመዎት አለ? እንዲፈርሙባቸው ከቀረቡልዎ በኋላ ያልፈረሙባቸው ወይም ተመሳሳይ ጉዳዮች አሉ?
ዶ/ር ነጋሶ፡- አሉ፡፡ አሁን በዝርዝር ወደ ውስጥ መግባት አስቸጋሪ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ነገሮች የነበሩበት አጋጣሚ አለ፡፡ ነገር ግን እምቢ ለማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ነው፡፡ ይህ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የጀርመን ፓርላሜንታዊ ሥርዓት ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ይህ አዋጅ ይህ አንቀጽ ልክ አይደለም ሊል ይችላል፡፡ በድጋሚ እንዲታይ ማድረግ ይችላል፡፡ ሁለተኛ ቀደም ሲል ያልታሰበበት፣ ወይም ትኩረት ያልተሰጠው ግን ሊታሰብበት የሚገባ የምለው፣ ፕሬዚዳንቱ በሚመረጥበት ጊዜ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የምክር ቤቱን ወንበር ይለቃል ነው፡፡ ወንበሩን ከለቀቀ ለምን ያህል ጊዜ ነው የሚለቀው የሚለው አልተመለሰም፡፡ በእርግጥ ፕሬዚዳንት ሆኖ አገሪቱን እንዲወክል ሲደረግ ገለልተኛ መሆን ይገባዋል፡፡ የሥልጣን ዘመኑ እስኪያልቅ ድረስ ማለት ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሥልጣኑን ከለቀቀ በኋላ ወደ ፓርቲው መመለስ ይችላል? ወይም ሌላ ፓርቲ መቀላቀል ይችላል? ወይም ሌላ ፓርቲ ማቋቋም ይቻላል? ወይስ የፈለገውን መሆን ይችላል? የሚለው ጥያቄ አልተመለሰም፡፡ ፕሬዚዳንቱ አንድ ነገር ካልሆነ በስተቀር ለስድስት ዓመታት ይቆያል፡፡ ከዚያ በኋላ ተወዳድሮ ፓርላማ መግባት ይችላል ወይ? የሚለው ጥያቄ ግልጽ አይደለም፡፡ በተጨማሪም ኢሕአዴግ የፈለገውን ሰው ብቻ ፕሬዚዳንት እንዲሆን ማድረግ ይችላል፡፡ ኢሕአዴግን የማይቀበል ፕሬዚዳንት ሊሆን አይችልም፡፡ መሆን የነበረበት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ስድስት ዓመት ገለልተኛ ሆኖ ካገለገለ በኋላ ነፃ ሆኖ ሐሳቡን መግለጽ መቻል አለበት፡፡ በዚህ ጉዳይ ሕገ መንግሥቱ ሊሻሻል ይገባል እላለሁ፡፡ በዚህ ምክንያት እኔ የደረሰብኝን ማንም ሰው ያውቀዋል፡፡ 
ሪፖርተር፡- እርስዎ የኢሕአዴግ አባል ነበሩ፡፡ የፓርላማም አባል ነበሩ፡፡ ፕሬዚዳንትም ነበሩ፡፡ በግል ተወዳድረው ለፕሬዚዳንትነት የሚመጥኑ ሌሎች ሰዎች የሚሾሙበት መንገድ ስፋቱና ጥበቱ ምን ይመስላል?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ እኔ በነበርኩበት ወቅት ጥቆማውና ምርጫው በራሱ በኢሕአዴግ የበላይነት የሚካሄድ ነው፡፡ አሁን ለመቀየር አስበው ከሆነ በዝርዝር መቀመጥ አለበት፡፡ ማነው የሚጠቁመው የሚለው ሥርዓት ይዞ መታወቅ አለበት፡፡ አሁን ባለው አሠራር ኢሕአዴግ ነው ጥቆማውን ወደ ፓርላማ የሚያቀርበው፡፡ ለይስሙላ ግን ሌሎች ይጠቁማሉ፡፡ ለምሳሌ በ1997 ዓ.ም. ይመስለኛል ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ተጠቁመው ነበር፡፡ ግን አብዛኛው አባላት ኢሕአዴግ ስለሆኑ ጥቆማው ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ሌላ ፕሬዚዳንት ተዘጋጅቶ ነበርና ነው፡፡ መራጩ የምክር ቤት አባል የሚመርጠውን እንዲያውቅ ተደርጓል፡፡ በእኔ ጊዜም ይህ ተደርጎ ነበር፡፡ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ፕሬዚዳንት የሚሆነው ሰው ተወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ መሠረት መራጮቹ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡ የኢሕአዴግ አባላት በሙሉ ተሰብስበው እኔ እንደተመረጥኩ ተገልጾላቸው ለእኔ ድምፅ እንዲሰጡ ተነግሯቸዋል፡፡ ስለዚህ ይህ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ በጀርመን እንደሚደረገው የሕግ ባለሙያዎች፣ በፖለቲካ ውስጥ የታወቁ ሰዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ፕሮፌሰሮች ሳይቀሩ ያሉበት ኮሚቴ ይቋቋማል፡፡ የተቋቋመው ኮሚቴ ብቁ የሆኑ ሰዎችን ያፈላልጋል፡፡ የእኛ ሕገ መንግሥት በዚህ በኩል ዝርዝር ማስቀመጥ አለበት፡፡ ከፓርላማ የሚመረጥ ከሆነ መቀመጫውን ይለቃል ነው የሚለው፡፡ ይኼ በቂ አይደለም፡፡ ከፓርላማ ብቻ ሳይሆን ወይም ከገዥው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ከውጭም ሊቀርብ ይችላል የሚል ነገር መምጣት አለበት፡፡  
ሪፖርተር፡- ሕገ መንግሥቱ ከውጭ ሊመጣ እንደሚችል ያስቀምጣል እንዴ?
ዶ/ር ነጋሶ፡- የተዘረዘረው በአንቀጽ 70 ነው፡፡ የቀረበው ዕጩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ በ2/3ኛው ድምፅ ተደግፎ ከቀረበ ፕሬዚዳንት ይሆናል ይላል፡፡ በሦስተኛው አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ሦስት ላይ የምክር ቤት አባል ፕሬዚዳንት ሆኖ ከተመረጠ የተወከለበትን የምክር ቤት መቀመጫ ይለቃል ይላል እንጂ ሌላ ነገር አይልም፡፡
ሪፖርተር፡- ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውጭ የሚል አንቀጽ የለም እያሉ ነው?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ሕገ መንግሥቱን በምናፀድቅበት ወቅት በሚካሄዱ ስብሰባዎች ላይ ከውጭም ሊሆን እንደሚችል የተነሳ ሐሳብ አለ፡፡ በቃለ ጉባዔ ላይም ይገኛል፡፡ ከዚህ ውጭ በሕገ መንግሥት አልተዘረዘረም፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ ፕሬዚዳንት የሚያቀርበው ገዥው ፓርቲ በመሆኑ ከዚህ ውጭ የተዘጋ ነው?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ለስሙ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ፓርላማ ውስጥ ማነው ብዙ መቀመጫ የያዘው የሚለው ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ በመንግሥት በኩል ከውጭ ለመሾም ፍላጎቱ አለ ወይ? ኢሕአዴግ ራሱ አፈላልጎ እኮ ማቅረብ ይችላል፡፡ 
ሪፖርተር፡- እርስዎ ከኢሕአዴግ ጋር በፕሬዚዳንትነት ለስድስት ዓመታት ቤተ መንግሥት ቆይተዋል፡፡ ነፃነትዎ እንዴት ነበር? በመንግሥት በኩል ጣልቃ ገብነት ነበር?
ዶ/ር ነጋሶ፡- የፕሮቶኮል ጉዳይ አለ፡፡ ማንም እንደፈለገ ገብቶ ሊያየኝ አይችልም፡፡ የፀጥታ ጉዳይ አለ፡፡ ማነው የሚገባው የሚለው መጣራት አለበት፡፡ ከለቀቅኩ በኋላ ፈልገን ልናገኝህ አልቻልንም ያሉኝ አሉ፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ለእኔ ነግረው እንደዚህ ዓይነት ሰው ሊያይህ ይፈልጋል ሲሉኝ ይገባ ነበር፡፡ ትንሽ የተገደበ ነው፡፡ ሌላው ለመውጣት አትችልም፡፡ የዘመድህ ሠርግ አትሄድም፡፡ በሐዘንም ወቅት በጣም ጥቂት ቦታ ነው የሄድኩት፣ ያውም በድብቅ፡፡ ከዚህ አንፃር ካልሆነ በስተቀር ጥሩ ነበር፡፡  
ሪፖርተር፡- የቤተ መንግሥት ቆይታዎ አሰልቺ ነበር ማለት ነው?
ዶ/ር ነጋሶ፡- አዎ፡፡ አሰልቺ ነው፡፡ ወደ ውጭ አትወጣም፡፡ ቢሮ ከመግባትህ በፊት ግቢው ትልቅ ስለሆነ በእግርህ ትሄዳለህ፡፡ ግቢው ትንሽ ያስቸግራል፡፡ ግቢው ሁለት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ አንደኛው ፕሬዚዳንቱ የሚያርፍበት አካባቢ አለ፡፡ ሌላው የእንግዶች መቀበያና ማረፊያ አለ፡፡ በስተቀኝ ያለው የእንግዶች በስተግራ ያለው የፕሬዚዳንቱ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማግኘት ለሥራ የሚመጡ የአገር መሪዎች አሉ፡፡  ከፕሬዚዳንቱ ጋር የሚያገናኛቸው ነገር የለም፡፡ እዚያ ግቢ ውስጥ እነዚህ ሰዎች መኖራቸውን አንተ ላታውቅ ትችላለህ፡፡ የሚገርም ይሆንብሃል፡፡ በዚህ ምክንያት አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት የቤተ መንግሥቱን አገልግሎት ለመለያየት ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በፊት አስበን ነበር፡፡ እንዲያውም ፕላኑ ተነስቶ ነበር፡፡ የፕሬዚዳንቱ መኖሪያና ጽሕፈት ቤት ከሒልተን ወደ ላይ ስትወጣ ባለው ቦታ በመገንባት ላይ ነበር፡፡ የታችኛው ፕሬዚዳንቱን ለማግኘት የሚመጡና ለሥራ ጉዳይ የሚመጡ ሌሎች ሰዎች እንዲስተናገዱበት፣ እንግዳ በማይኖርበት ወቅት ሙዚየም እንዲሆን ታስቦ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከአፄ ምንሊክ ጊዜ ጀምሮ የተከማቹ ቅርሶች አሉ፡፡ በጣም ውድና አስደናቂ ዕቃዎች አሉ፡፡ ሕዝቡ ማየት አለበት፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ወይም ፕሬዚዳንቶች እንዴት ነበር የሚኖሩት የሚለውን ሕዝቡ ሊያይ ይገባል፡፡ ከታች በኩል ፍል ውኃ አለ ጥሩ ቦታ ነው፡፡ ለሠርግና ለሌሎች ሊውል ይችላል፡፡ ለደኅንነትና ለፕሮቶኮል ተብሎ ግላዊ ሕይወት መናጋት ስለሌለበት ከግምት እንዲገባ አስበን ነበር፡፡  
ሪፖርተር፡- ቤተ መንግሥቱ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ የተሰበሰቡ ቅርስ ሊሆኑ የሚችሉ ውድ መጠቀሚያ ዕቃዎች አሉት፡፡ ወደ ቤተ መንግሥት የሚገባ ፕሬዚዳንት በዕለት ተዕለት ኑሮው በእነዚህ ዕቃዎች ይጠቀማል? ወይስ ሌላ አዳዲስ ዕቃዎች ይገቡለታል?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ለምሳሌ ፕሬዚዳንቱ የሚቀመጠው በፊት ጃንሆይ የሚቀመጡበት መቀመጫ ላይ ነው፡፡ ቁሳቁሶቹ፣ መጻሕፍቱና ሰፋፊ ጠረጴዛዎቹ በሙሉ እንዳሉ ነው፡፡ መኝታውም እንደዚያው ነው፡፡ የምግብ ቤት ሁኔታውም እንዳለ ነው፡፡ እነዚህ ቁሳቁሶች እያሉ ሌላ ዕቃ መግዛት አስፈላጊ ነው ካልተባለ በስተቀር በቅርስነት መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ የአዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ፍላጎትም ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡ 
ሪፖርተር፡- ቤተ መንግሥቱ ውስጥ የተለያዩ የዱር እንስሳት አሉ፡፡ ነገሥታቱ እነዚህን የዱር እንስሳት ወደ ቤተ መንግሥት እንዳስገቡት ሁሉ፣ በእርስዎ የፕሬዚዳንትነት ዘመን ተጨማሪ እንስሳትን የማስገባትና የመንከባከብ ሥራ ነበር?
ዶ/ር ነጋሶ፡- አሁን እንጃ እንጂ እኔ በነበርኩበት ወቅት ኢሕአዴግ እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን ቅንጦት አድርጎ ነበር የሚያየው፡፡ ይመስለኛል ፕሬዚዳንት ግርማ ከጃፓን ጋር ተስማምተው አንድ መናፈሻ አሠርተዋል፡፡ የመዋኛ ገንዳ፣ ፍልውኃ፣ ሳውናና የመሳሰሉት አሉ፡፡ በፊት የነበሩ አዕዋፍ እየሞቱ ነበር፡፡ አንበሶች በዋሻ ውስጥ አሉ እኔ በነበርኩበት ወቅት ትኩረት አልነበረም፡፡  
ሪፖርተር፡- ለቤተ መንግሥት አስተዳደር የሚመደብለት በጀት በቂ ነው?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ምንድነው የምትፈልገው የሚለው ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ አንዳንዱ የተለየ ቅንጦት ሊፈልግ ይችላል፡፡ በእኔ ጊዜ አይበቃኝም ያልኩት ነገር የለም፡፡ አሁን በምናይበት ጊዜ የተለየ ነገር ይኖራል፡፡ የሰማሁት ግቢ ውስጥ አንድ ቤተ ክርስቲያን አለ፡፡ ኪዳነ ምሕረት ትመስለኛለች፡፡ እኔ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ስላልሆንኩ አልጠቀምበትም ነበር፡፡ አሁን እንደሰማሁት ቤተ ክርስቲያኑ እንዲታደስ ተደርጎ ፕሬዚዳንት ግርማ እዚያ ነው በዓል የሚያከብሩት፡፡ 
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ነገሥታት ሥርዓት ቤተ መንግሥት ውስጥ የማር ጠጅና የሰንጋ በሬ ጮማ አይጠፋም፡፡ እርስዎ ያጣጥሙ ነበር?
ዶ/ር ነጋሶ፡- እኔ በዚህ ዓይነት ነገር ውስጥ አላለፍኩም፡፡ እኔ የተለየ መንደላቀቅ ውስጥ በመግባት ጊዜ በማጥፋት አላምንም፡፡ እዚያ ውስጥ ሳልገባ እንዲሁ ቀለል ያለ ኑሮ የምኖር ሰው ነኝ፡፡ የኢሕአዴግ ጓደኞቼም እኔ ዘንድ አይመጡም ነበር፡፡ ስለዚህ ከቤተሰብ ያለፈ ነገር የለም፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር