የዋጋ ንረት በነጋዴዎች እንደማይመጣ እንደገና በጥናት ተረጋገጠ

Written by  ዮሐንስ ሰ.
ግን ደንታችን አይደለም፤ ነጋዴዎችን ከማውገዝ ለአፍታም አንቆጠብም!
ታዋቂዋ የኢኮኖሚክስ ምሁር ዶ/ር ኢሌኒ ገብረመድህን በእህል ገበያ ዙሪያ ከ20 አመት በፊት ባደረጉት ሰፊ ጥናት የተገኘውን ውጤት በድጋሚ የሚያረጋግጥ አዲስ ጥናት ሰሞኑን በተካሄደው የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር ኮንፈረንስ ላይ ቀርቧል። ከጥናቶቹ ውስጥ ጎልቶ የሚታይ አንድ ሃቅ ቢኖር፣ በእህል ገበያ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችና ደላሎች በየፊናቸው ወይም ተመካክረው እንዳሻቸው የዋጋ ንረትን እንደማይፈጥሩ ነው። እንዲያውም፣ ነጋዴዎች የዋጋ ንረትን የሚፈጥርና ጉዳት የሚያደርስ ቅንጣት ያህል አቅም እንደሌላቸው ጥናቶቹ ያስረዳሉ። እንዲህ አይነቱ ሃሳብና መረጃ የማይዋጥላቸው ብዙ ኢትዮጵያውያን፣ ከገበሬ እህል ገዝቶ የሚያመጣ ነጋዴ ከደላላ ጋር ሆኖ፣ ያሰኘውን ያህል ዋጋ እየጨማመረ በሰፊ ልዩነት የሚሸጥ ይመስላቸዋል።
ከገበሬ የሚገዛበት ዋጋ ከወለል በታች በጣም ዝቅተኛ፣ ለሸማች የሚሸጥበት ዋጋ ደግሞ ከጣሪያ በላይ ከፍተኛ ነው ብለው ያምናሉ። ነጋዴው በሰፊ የዋጋ ልዩነት እጥፍ ሲያተርፍ፣ ከዚያም አልፎ የእጥፍ እጥፍ ዋጋ እየጨመረ ትርፍ ሲዝቅ በምናብ ይታያቸዋል። በተጨባጭ መረጃዎች እና በዝርዝር ጥናቶች ተደጋግሞ የተረጋገጠው እውነታ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። ነጋዴዎች ከገበሬ እህል የሚረከቡበት ዋጋ እና ለሸማች የሚሸጡበት ዋጋ ሲነፃፀር፣ በሁለቱም መካከል ሰፊ ልዩነት እንደሌለ ጥናቶቹ ከመግለፃቸውም በተጨማሪ፣ የዋጋ ልዩነቱ ከአመት አመት በእጅጉ እየቀነሰ መምጣቱን ያስረዳሉ። ታዲያ በእነዚህ ጥናቶችና መረጃዎች ምክንያት የአብዛኛው ሰው አስተሳሰብ የሚቀየርና በነጋዴዎች ላይ የሚሰነዘረው ውግዘት የሚረግብ እንዳይመስላችሁ። ቀድሞውንም፣ በጥናቶችና በመረጃዎች እጦት አይደለም ነጋ ጠባ ነጋዴዎች ላይ የእርግማን ዶፍ የሚዘንበው። በአብዛኛው የአገራችን ሰው፣ ነጋዴዎችን በክፉ የጥላቻ አይን መመልከት ይቀናዋል።
የጥናትና የመረጃ ክምር እየተደራረበ ተራራ ቢያክል እንኳ፣ ብዙ ሰው ከዚህ ጭፍን ጥላቻ ፍንክች ለማለት ፈቃደኛ አይደለም። ለነገሩማ፣ ነጋዴዎች የዋጋ ንረት አለመፍጠራቸውኮ… አዲስ የጥናት ግኝት አይደለም። ሁላችንም በየተሰማራንበት የሥራ መስክ ሁሉ፣ በእለት ተእለት ኑሯችን ዘወትር የምንናየው እውነታ ነው። መቼም፣ በአንዳች ምክንያት እቃ የሸጣችሁበት አጋጣሚ ይኖራል። ወይም ለምትሰሩት ነገር ክፍያ የተደራደራችሁበትን ጊዜ አስታውሱ። በተጨባጭ ያየነው ገጠመኝና በእውን የምንመራው ኑሮ ላይ ተመስርተን ጉዳዩን ስንመረምረው፣ የንግድና የግብይት ጉዳይ ያን ያህልም ውስብስብ አይደለም። በቃ!... ከገበያው ውጭ እንዳሻን የሸቀጦችን ዋጋ ወይም የአገልግሎቶችን ክፍያ ማናር እንደማንችል እናውቃለን። እንዲያም ሆኖ፣ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ነጋዴዎችን በጅምላ እንደ አጭበርባሪ የመቁጠር አባዜ ስለተጠናወተው፣ በተለይ የዋጋ ንረት በተከሰተ ቁጥር ነጋዴዎች ላይ እርግማን ለማውረድ ይሽቀዳደማል።
የተለመደ ነገር ነዋ። ይህም ብቻ አይደለም። የዋጋ ንረት ዋና መንስኤ ምን እንደሆነ ይታወቃል። የዋጋ ንረት የሚፈጠረው፣ መንግስት በገፍ እያተመ በሚያሰራጫቸው የብር ኖቶች ሳቢያ እንደሆነኮ እልፍ መረጃዎችና የሙያው አጥኚዎች በተደጋጋሚ ይመሰክራሉ። መንግስትም አልፎ አልፎ ተጠያቂነቱን በግልፅ አምኖ ሲቀበል ሰምተናል። እንዲያም ሆኖ፣ በኑሮ ውድነት የሚማረር አብዛኛው ዜጋ፣ በነጋዴዎች ላይ የቀሰረውን ጣት ለመመለስ አይፈልግም - ባህላችን ነዋ። … ይቅርታ! የጥናቶቹን ፍሬ ነገር በጨረፍታ ብቻ ጠቅሼ፣ ወደ አስተያየት ገባሁ። ግን፣ ችግር የለም። የጥናቶቹን ዋና ዋና ፍሬ ነገሮች አጠር አጠር አድርጌ መዘርዘሬ አይቀርም። እንዲሁ ሳስበው፣ ከጥንት እስከዛሬ በነጋዴዎች ላይ የሚዥጎደጎደው የማያባራ ውግዘትና እርግማን ስለሚገርመኝ ነው።
እስቲ አስቡት። “በመሰለኝ፣ አሰኘኝ” ስሜት የሚለፈፉ አሮጌ ዲስኩሮችን ዘላለሙን እየመላለስን ከምናመነዥክ፤ እስቲ ለአፍታ ያህል እውነታውን አስተውለን ለማሰብ ለማሰላሰል እንሞክር። በተጨባጭ መረጃዎች ላይ የተመሰረቱት ጥናቶች ውስጥ ተደጋግማ የተገለፀች አንዲት መረጃ ብቻ መዝዤ ልጥቀስላችሁ። የእህል ነጋዴዎች የተጣራ ትርፍ ምን ያህል ይመስላችኋል? ከጠቅላላ የሽያጭ ገቢ ውስጥ፣ ነጋዴዎቹ በአማካይ የሚያገኙት የተጣራ ትርፍ ከ5% በታች እንደሆነ ጥናቶቹ ያረጋግጣሉ። የአንድ ሺ ብር እህል ከሸጠ፣ የተጣራ ትርፉ ከ50 ብር በታች ነው። ተጨማሪ ትርፍ ለማግኘት ለምን ዋጋ አይጨምርም? አይችልማ። ከግራ እና ከቀኝ፣ ከፊትና ከጀርባ ተፎካካሪዎች ከበውታል። እንዳሰኘው የእህል ዋጋዎችን ማናር አይችልም። ጥናቶቹ ይህን እውነታ በግልፅ ቢያሳዩም፤ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ግን እንደወትሮው ነጋዴዎችን ከማውገዝ ወደ ኋላ አይልም። ‘ተምሯል’ የሚባለው የአገራችን ሰውም በአመዛኙ፣ ከልማዳዊው ቅኝት የፀዳ አይደለም። በተጨባጭ መረጃዎች ላይ የተመሰረቱትን ጥናቶች ባነበበ ማግስት፣ ያነበባቸውን መረጃዎች ከአእምሮው ያስወጣቸዋል፤ (ቃል በቃል መረጃዎቹን ከአእምሮው ውስጥ ማስወጣት እንኳ አይችልም። ግን በአእምሮው ውስጥ ብቅ ብርት እያሉ እንዳይታዩት ያዳፍናቸዋል)።
መረጃዎቹን “አውቆ ይረሳቸዋል” ብንል ይሻላል። እናም እንደ ተራው ሰው ሁሉ፣ አብዛኛው ምሁርም ምንም ያህል ጥናት ቢቀርብለት፣ ከጥንታዊው አስተሳሰብ ለመላቀቅ ፈቃደኛ አይደለም። እንደተለመደው ነጋዴዎችን እያወገዘ ይቀጥላል። የኋላቀርነት ባህል በቀላሉ አይነቀልም። ለሺ አመታት የዘለቀውና ስር የሰደደው የአገራችን ባህል፣ ለቢዝነስና ለንግድ ክፉ ጥላቻ አለበት። በኋላቀርነትና በድህነት ውስጥ እንደጨቀየን ለመኖር የተገደድነውም በዚሁ ባህል የተነሳ ነው። ስኬትን በሚጠላ ባህል ከድህነት መውጣት አይቻልማ። ለማንኛውም በመስኩ ባለሙያዎች ዘንድ ሊስተባበሉ ያልቻሉ ሦስት ጥናቶችን ነው የምጠቅስላችሁ። እስካለፈው አመት ድረስ የ25 ዓመታትን የእህል ገበያ ከሚዳስሱት ጥናቶች መካከል የመጀመሪያው፣ ኢትዮጵያዊ ምሁር ከውጭ አገር ባለሙያዎች ጋር በጋራ በሚቺጋን ዩኒቨርስቲ ትብብር ያካሄዱት ጥናት ነው። ምሁራኑ፣ ከ1979 እስከ 88 ዓ.ም ድረስ በአገራችን የእህል ገበያ ውስጥ የአስር አመት መረጃዎችን በማሰባሰብ ጥናት ለማድረግ የወሰኑት አለምክንያት አይደለም። ሁለት የኢኮኖሚ ስርዓቶችን ለማነፃፀር ነበር ፍላጎታቸው። የመጀመሪያዎቹ አራት አመታት የደርግ አገዛዝን ወቅት የነበረውን የእህል ገበያ የሚዳስሱ ናቸው። ገበያው፣ ስፍር ቁጥር በሌላቸው የመንግስት ቁጥጥሮችና ገደቦች፣ በዋጋ ተመኖችና በኬላዎች፣ በኮታና በራሽን ቢሮክራሲዎች የተተበተበ ነበር። ያው፣ “ህብረተሰቡ በአጭበርባሪና በስግብግብ ነጋዴዎች እንዳይበዘበዝ መንግስት ሰፊ ቁጥጥር ማድረግ አለበት” የሚባልበት ዘመን ነው። በዚህ አስተሳሰብም፣ የእህል ገበያው በመንግስት ቁጥጥር እንዲተበተብ ተደርጓል። ቀጣዮቹ 6 አመታት ደግሞ ከደርግ ውድቀት በኋላ፣ በኢህአዴግ ዘመን የእህል ገበያው ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም በከፊል ከመንግስት ቁጥጥሮች ነፃ እንዲሆን የተደረገባቸው አመታት ናቸው።
እና የመንግስት ቁጥጥሮችና የዋጋ ተመኖች በከፊል ሲሰረዙ፣ “ስግብግብ ነጋዴዎች” ነፃነት አገኘን ብለው የእህል ዋጋ እንዲንር አደረጉ? አጥኚዎቹ ምሁራን በበርካታ ከተሞች የአስር አመታት መረጃዎችን በማሰባሰብ ያቀረቡት ትንታኔ፣ ነፃ ገበያ በተወሰነ ደረጃ ሲስፋፋ የእህል ዋጋ ንረት እንደሚቀንስ ያሳያል (Jayne, Negassa, Myers. 1998. The effect of liberalization on grain prices and marketing margins in Ethiopia. MSU International Development Working Paper No. 68. Michigan State University)። ከጥናቱ ውስጥ አንድ ምሳሌ ልጥቀስላችሁ። በደርግ ዘመን ሻሸመኔ ላይ ከገበሬ በ66 ብር ተገዝቶ የሚመጣ በቆሎ፣ አዲስ አበባ ውስጥ በ100 ብር ይሸጥ ነበር። በመጣበትና በተሸጠበት ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት (marketing spread) 34 በመቶ ነው። ታዲያ፣ የትራንስፖርት፣ የመጋዘን፣ የማውረጃና የመጫኛ፣ ገዢና ሻጭ ለሚያገናኙ ደላሎች ሁሉ ወጪውን ሸፍኖ ነው፣ ነጋዴው በዚህ ዋጋ የሚሸጠው። በመንግስት ቁጥጥር በተተበተበው ገበያ ውስጥ ሸቀጦችና እያመጡ መስራት ብዙ ጣጣና ወጪ ነበረበት። የእህል ገበያው፣ በከፊል ከመንግስት ቁጥጥር ነፃ ሲሆንስ? በ1988 ዓ.ም የእህል ገበያ፣ ሻሸመኔ ውስጥ ገበሬው በ70 ብር ያስረከበው በቆሎ አዲስ አበባ ውስጥ በ90 ብር ገደማ ነው ሲሸጥ የነበረው።
በማምጫና በመሸጫ ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት ቀድሞ ከነበረው እየቀነሰ ከ22% በመቶ የማይበልጥ ሆኗል ማለት ነው። ነጋዴው፣ ለምን እንደቀድሞው ዋጋውን ከፍ አድርጎ በመቶ ብር አይሸጠውም? ለሸማቾች አዝኖ አይደለም። በተፎካካሪ ነጋዴዎች ስለተከበበ፣ ሸማቾችን መሳብ የሚችለው በገበያ ዋጋ ተወዳድሮና የተቻለውን ያህል ዋጋ ቀንሶ የሚሸጥ ከሆነ ብቻ ነው። በአጭሩ፣ ነጋዴዎች በአጭበርባሪነትና በስግብግብነት እየተወገዙ መንግስት በስፋት ቁጥጥር እያካሄደ በነበረበት ዘመን አዲስ አበባ ውስጥ በመቶ ብር እንገዛው የነበረ ሸቀጥ፣ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር እየላላ ሲመጣ ዋጋው ወደ ሰማኒያ ብር ወርዷል።
ለምሳሌ ያህል፣ በበቆሎ ንግድ የሻሸመኔንና የአዲስ አበባን ገበያዎችን ሁኔታ የሚያመላክት ምሳሌ ጠቀስኩላችሁ እንጂ፣ የምሁራኑ ጥናት በርካታ ከተሞችን ያካለለ ነው። መደምደሚያው ግን ተመሳሳይ ነው። የመንግስት ቁጥጥር ሲበራከት ዋጋ ይጨምራል፤ ቁጥጥሮች እየላሉ ነጋዴዎች በነፃነት የሚሰሩት ሁኔታ እየተስፋፋ ሲመጣ ደግሞ ዋጋ ይቀንሳል። ታዲያ፣ ነጋዴዎችን ምን ብንላቸው ይሻላል? “ያልተዘመረላቸው ጀግኖች” እንበላቸው? “ያልተወደሱ ቅዱሳን” ብንላቸውስ ይበዛባቸዋል? ይሄ ለብዙዎቻችን የሚዋጥልን አይደለም። እንዲያውም፣ ማንም ባለሙያ የፈለገውን ጥናት ቢያካሂድ፣ ብዙዎቻችን እንደተለመደው ነጋዴዎችን ከማውገዝና ከመኮነን ለመቦዘን ፈቃደኞች አይደለንም። ዶ/ር ኢሌኒ ገብረመድህን በ1994 ዓ.ም ወዳሳተሙት ሌላ ጥናት እንሸጋገር። ቀደም ካሉት የእህል ገበያ ጥናቶች ሁሉ በላቀ ጥልቀትና ስፋት የተካሄደው የዶ/ር ኢሌኒ ምርምር፣ አገሪቱን ከዳር እስከ ዳር ያዳረሰ፣ ከጤፍ እስከ በቆሎ በርካታ የእህል አይነቶችን የዳሰሰ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ከገበሬ እስከ ደላላ፣ ከጅምላ ነጋዴ እስከ ቸርቻሪ የገበያውን ተዋናዮች በብዛት ይፈትሻል።
ገበሬው የእህል ምርቱን ለገበያ የሚያቀርብበት ዋጋ እንዲሁም፣ ከተሞች ውስጥ በጅምላ አከፋፋዮች በኩል አልፎ በቸርቻሪዎች ለሸማች የሚሸጥበት ዋጋ በንፅፅር ሲታይ ልዩነታቸው ምን ያህል ነው? ከዶ/ር ኢሌኒ ጥናት የተገኘው ውጤት እንደሚያመለክተው፣ በ1988 ዓ.ም በነበረው የእህል ገበያ ውስጥ፣ ገበሬዎች በአማካይ በ78 ብር የሚሸጡት እህል፣ በከተሞች ገበያ ለሸማቹ በመቶ ብር ይቀርብ ነበር። በሁለቱ ዋጋዎች መካከል ያለው ልዩነት 22 በመቶ ነው። ከእያንዳንዷ መቶ ብር ውስጥ፣ ገበሬው 78 ብር ይወስዳል። 22 ብሯስ? ሰባት ብር ለትራንስፖርት ወጪ ይሆናል። ከዚያ በኋላ የምትቀረው 15 ብር ደግሞ፤ ደላሎች፣ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች፣ ጫኝና አውራጆች፣ ተላላኪና የግብይት ረዳቶች ይከፋፈሏታል። በአማካይ የግብይት ረዳቶችና ተላላኪዎች አምስት ብር ሲወስዱ፣ የደላሎች ድርሻ አንድ ብር ነው። የጆንያ፣ የማደሪያ፣ የመጋዘን ወጪ ወደ 4 ብር ይጠጋል። ስንት ቀረ? አምስት ብር ብቻ። ከዚህች አምስት ብር ነው ለአከፋፋዮችና ለቸርቻሪዎች ትርፍ የምትደርሳቸው። በዶ/ር ኢሌኒ ሰፊ ጥናት መሰረት፣ ከገበሬ እጅ ወጥቶ ሸማች እጅ ውስጥ እስኪገባ ባለው ሂደት ላይ ሁሉ፣ ከመቶ የሽያጭ ገቢ ውስጥ የነጋዴዎች ትርፍ ከ5 ብር አይበልጥም። እናላችሁ፣ የእህል ንግድ የዚህን ያህል ከባድ ስራ ነው። የእህል ነጋዴዎች ከአምስት በመቶ ባነሰ ትርፍ እንደሚሰሩ በጥናት መረጋገጡ፣ ለኛ ምናችን ነው? “በእጥፍ ላይ እጥፍ ዋጋ እየጨመሩ ይመዘብሩናል” እያልን እንደተለመደው ነጋዴዎችን ከማውገዝ አናርፍም! በመጨረሻ ሰሞኑን በኢኮኖሚክ ባለሙያዎች ማህበር አመታዊ ጉባኤ ላይ ከቀረቡት ጥናቶች ላይ አንዱን ላካፍላችሁ።
በአለማቀፍ የምግብ ፖሊሲ ጥናቶች ተቋም እና በኢትዮጵያ የልማት ጥናቶች ተቋም ትብብር በአራት ባለሙያዎች የተካሄደ ጥናት ነው (Ethiopia’s value chains on the move: The case for teff)። በጤፍ ምርትና ግብይት ላይ ያተኮረው ይሄው ጥናት፣ ዘንድሮ በስፋት የተሰበሰቡ መረጃዎችንና ከአስር አመት በፊት የነበረውን ሁኔታ በማነፃፀር ያቀርባል። በ1992 ዓ.ም ገበሬዎች የጤፍ ምርታቸውን በሚያስረክቡበት ዋጋና ነጋዴዎች ለሸማች በሚሸጡበት ዋጋ መካከል የነበረው ልዩነት 22% ገደማ እንደነበር ጥናቱ ይጠቅሳል - የትራንስፖርት፣ የማስጫኛና የማውረጃ፣ የደላላ ወጪዎች እንዲሁም የአከፋፋዮችና የቸርቻሪዎች ትርፍ በዚህ ውስጥ ይካተታል። ከአስር አመት በኋላስ፣ የነጋዴዎች ድርሻ ጨመረ ወይስ ቀነሰ? በገበሬዎች ማስረከቢያ ዋጋ እና በነጋዴዎች መሸጫ ዋጋ መካከል የነበረው ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ፣ በአምናው የጤፍ ገበያ ውስጥ እስከ 15% እንደወረደ ጥናቱ ያረጋግጣል። ከገበሬ በ85 የተገዛ እህል፣ ነጋዴዎች ለሸማች በመቶ ብር ይሸጣሉ ማለት ነው - ለዚያውም የደላሎችና የረዳቶች፣ የትራንስፖርትና የጫኝ አውራጅ ወጪዎችን ሁሉ ሸፍነው። እውነታው እንዲህ ከሆነ፣ ከምን ተነስተን ነው ነጋዴዎችን ቀን ከሌት የምናወግዘው? በቃ፣ ነጋዴዎችን መጥላት ባህላችን ስለሆነ፣ ነጋዴዎችን ከማውገዝ አናርፍም። ለመረጃና ለጥናት ደንታ የለንም።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር