የግሉ ዘርፍ በሙስና የሚጠየቅበት ረቂቅ ሕግ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊፀድቅ ነው

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚቀጥሉት ሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ በግሉ ዘርፍ የሚካሄዱ የሙስና ተግባራት ዕርምጃ እንዲወሰድ የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ ተነጋግሮ ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ገለጹ፡፡
‹‹የሙስና ወንጀሎችን እንደገና ለመደንገግ የወጣ ረቂቅ አዋጅ›› በሚል የተዘጋጀው የፀረ ሙስና አዋጅ ከፀደቀ፣ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አንደኛው ክንፍ ፊቱን ወደ ግሉ ዘርፍ እንደሚያዞር እየተነገረ ነው፡፡ 
ለፀረ ሙስና ኮሚሽን የቀረበው የረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ እንደሚያስረዳው፣ ‹‹ሕዝባዊ ድርጅት›› የሚባሉት ከሕዝቡ የተሰበሰበ ገንዘብ ወይም ንብረት የሚያስተዳድሩ አካላት ሲሆኑ፣ በተለያዩ መንገዶች የሚቋቋሙ ማኅበራት፣ የአክሲዮን ኩባንያዎች፣ በአክሲዮን የተቋቋሙ ባንኮችና የኢንሹራንስ ተቋማትን ያጠቃልላል፡፡ 
ይህ የሕግ ረቂቅ ታኀሳስ 2005 ዓ.ም. ተዘጋጅቶ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለውይይት በቀረበበት ወቅት፣ ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ከተለያዩ አቅጣጫዎች በርካታ ጥቆማዎች መቅረባቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ 
ለፀረ ሙስና ኮሚሽን የቀረበው የጥቆማ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ነው የሚሉት ምንጮች፣ ኮሚሽኑ እየከናወነ ካለው በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ያነጣጠረ ሥራ ብዛት አንፃር ሊከብደው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ በዚሁ መነሻነት ኮሚሽኑ ሊኖረው ስለሚገባው አዲስ ቅርፅና የሰው ኃይል አደረጃጀት የኮሚሽኑ ኃላፊዎች ውስጥ ውስጡን መነጋገር መጀመራቸው ታውቋል፡፡ 
በአሁኑ ጊዜ ኮሚሽኑ ባለው የሰው ኃይል በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አለ በሚባለው የሙስና ወንጀል ላይ ምርመራ አድርጎ ክስ ለመመሥረት አስቸጋሪ እንደሆነበት፣ በዚህ የሰው ኃይል በግሉ ዘርፍ ሙስና ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ጫና ሊፈጥርበት ይችላል የሚል ሥጋት መፈጠሩን ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ 
በአሁኑ ወቅት ኮሚሽኑ ሊሰጡት የሚችሉትን ተጨማሪ ኃላፊነቶች ለመወጣት የሕግ ማሻሻያ በማድረግና በቀጣይነት ስለሚኖረው መዋቅር ይፋዊ ባልሆነ መንገድ እየመከረ መሆኑ ታውቋል፡፡ 
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህንን ረቂቅ አዋጅ በቅርቡ ያፀድቀዋል ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ የሚፀድቅለትን አዋጅ በመጠቀም በአዲሱ ዓመት አጋማሽ ወደ ግሉ ዘርፍ ፊቱን እንደሚያዞር ተጠቁሟል፡፡ ኮሚሽኑ አዘጋጅቶ ያቀረበው ረቂቅ አዋጅ ቀደም ሲል የሚያስጠይቁ አዳዲስ የወንጀል ዓይነቶችን በዝርዝር ይዟል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር