የፀረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት በሀገር ውስጥ ሊመረት ነው

የፀረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት በሀገር ውስጥ ሊመረት ነው፡፡
በሀገር ደረጃ የኤች.አይ.ቪ (ኤድስ) ስርጭት እየቀነሰ ቢመጣም ተጠናክሮ መሰራት እንዳለበት ተጠይቋል፡፡
በኤች.አይ.ቪ(ኤድስ) ላይ የሚሰሩ የተለያዩ አካላት በጋራ የሰጡት መግለጫ ከገጠሩ ይልቅ በከተማ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመቆጣጠር በሰፊው መሰራት አለበት ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጤናና ስነ-ምግብ ኢኒስቲትዩትን በመወከል ዶ/ር ይበልጣል አሰፋ በተለይም በፀረ የኤች.አይ.ቪ መድሃኒት አጠቃቀም ላይ በሰፊው መስራት እንደሚፈልግ ነው የገለፁት፡፡
ዶ/ር ይበልጣል እንደሚሉት የፀረ የኤች.አይ.ቪ መድሃኒት አጠቃቀም እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም በተለይ በመረጃ አሰጣጥ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡
የጸረ ኤች.አይ.ቪ (ኤድስ) መድሀኒትን በ2007  መጨሻ ላይ በሀገር ውስጥ ለማምረት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም የኢትዮጵያ ጤናና ስነ-ምግብ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡
ቅደመ ዝግጅቱ ሲጠናቀቅም 5 የጸረ ኤች.አይ.ቪ (ኤድስ) መድሀኒት አምራች ፋብሪካዎች ወደ ስራ ሊገቡ እንደሚችሉም ተጠቁሟል፡፡
የፌደራል ኤች.አይ.ቪ (ኤድስ) መከላከያና መቆጣጠሪያ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ም/ዳይሬክተር አቶ መስቀሌ ሌራ እንደሚሉት ደግሞ የኤች.አይ.ቪ (ኤድስ) ስርጭቱ ለስራ በሚንቀሳቀሰው ወጣቱ ላይ ጎልቶ ይታያል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተወካይ ዶክተር ፍሬሕይወት መብራቱ በበኩላቸው እስከአሁን ድረስ ኤች.አይ.ቪ (ኤድስን) በተመለከተ የተሰራው ሥራ ውጤት አያሳ በመምጣቱ ጥረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በተለይም ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ እቅድ ተዘጋጅቶ ቫይረሱ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ እንደሚሰራም ነው የገለጹት፡፡
የኤች.አይ.ቪ (ኤድስ) ሥርጭትን በተመለከተ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች የበለጠ ተጋላጭ እንደሆኑ በመድረኩ ላይ ተንጸባርቋል፡፡ከዕድሜ አንፃርም ከ35-49 የሚሆኑት ወንዶች እንዲሁም ከ25-34 ዓመት የሚሆኑት ሴቶች ለኤች.አይ.ቪ ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸው ተነግሯል፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገሪቱ የኤች ኤይ ቪ ኤድስ በሽታ ስርጭት ከ7 ወደ 1.6 በመቶ ዝቅ ማለቱና በበሽታው የሚሞቱ ሰዎችም በ90 በመቶ ትልቅ መሻሻል ታይቷል ተብሏል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር