የፍቼ ጫምበላላ በሃዋሳ ተከበረ

የሲዳማ ብሔር ባህል፣ ቋንቋና ታሪክን ጠብቆ በማስተዋወቅ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አስገነዘቡ፡፡
የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ፍቼ ጫምባላላና የብሔሩ 19ኛው የቋንቋና ባህል ሲምፖዚየም ትናንትናና ከትናንት በስቲያ በሃዋሳ በድምቀት ተከብሯል፡፡
የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ጫምባላላ ባህላዊ የአከባበር ሥነ ሥርዓትን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮለማስመዝገብ የቅድመ ዝግጅት ሥራ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ደሴ ዳልኬ እንደገለጹት፣ የሲዳማ ህዝብ ለረጅም ዓመታት ማንነቱ፣ ባህሉና ቋንቋው ተረስቶ መቆየቱን በማስታወስ ባለፉት 21 ዓመታት ሥርዓቱ ባመጣው መልካም አስተዳደር ባህሉና ቋንቋው ተክብሮ የመናገር፣ የመዳኘትና የመማር ዕድል ባለቤት ለመሆን በቅቷል፡፡
የብሔሩን ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክና ቅርስን በማጥናትና በማልማት የበለጸገና ያደገ ህብረተሰብ ለመፍጠርና የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የሲዳማ ብሔር ከሌሎች የሀገሪቱ ብሔረሰቦች ጋር አምባገነኑን ሥርዓት በመገርሰስ ልማት፣ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ባደረገው ትግል ያስገኘው ጣፋጭ ውጤት ለብሔሩ ቋንቋ፣ ባህልና ማንነት መከበር ጉልህ ድርሻ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡ በዚህ የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መጥቷል ብለዋል፡፡
የዞኑ ህዝብ ከሌሎች የክልሉና የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመቀናጀት የተጀመረውን የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
ቀደምት የሲዳማ አባቶች ባህላቸውን ለዚህ ትውልድ ሳይሸራረፍ ያስተላለፉት በባህላቸው ለመኖርና ቋንቋቸውን ለመጠቀም ምቹ ባልሆነበት ሁኔታ ውስጥ ነው።የብሔሩ ተወላጆች ይህን ባህል በመጠበቅና የሌሎችን በማክበር በድህነት ላይ የተጀመረው ትግል ውጤታማ እንዲሆን ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ በበኩላቸው የሲዳማ ብሔር የበርካታ ባህልና የራሱ ቋንቋ ባለቤት ቢሆንም በሀገሪቱ በነበረው መጥፎ ሥርዓት በቋንቋቸው ሳይጠቀሙ ለብዙ ዘመናት መቆየታቸውን በማስታወስ ከ1983 ወዲህ አስከፊው ሥርዓት በመገርሰሱና መልካም አስተዳደር በመላ ሀገሪቱ በመስፈኑ በቋንቋው የመጠቀም ፣ ባህሉን የማሳየት አኩሪ ድል መጎናፀፋቸውን ተናግረዋል፡፡
የሲዳማን ቋንቋና ባህል ለማሳደግ ባለፉት 21 ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች ከ1ኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት መልቀቂያ ፈተና የሲዳምኛ ቋንቋ እንደ አንድ ትምህርት መስጠት ከመቻሉም በላይ በኮሌጅና በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሲዳምኛ ቋንቋ በዲፕሎማና ዲግሪ ፕሮግራም በመሰጠት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
የፍቼ ጫምባላላ በዓልን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮለማስመዝገብ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ሚሊዮን የዞኑ ተወላጅ የሆኑ ከፌዴራልና ከክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮች፣ የሀገር ሽማግለዎችና ከ19 ወረዳና ሁለት የከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ነዋሪዎች ፊርማቸውን የማኖር ሥራ ይካሄዳል ብለዋል፡፡
የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ጫምባላላና 19ኛው የቋንቋና የባህል ስምፖዚየም ለሁለት ቀናት በሃዋሳ ከተማ ሲዳማ ባህል አዳራሽና ጉዱማሌ አደባባይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ አምባሳደሮች የሃይማኖት መሪዎችና ነዋሪዎች በተገኙበት በድምቀት ይከበራል፡፡
የሲዳማ ቋንቋና ባህል ዕድገትና ታሪካዊ አመጣጥ የሚያሳዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረጉ እንዲሁም የሲዳማ ቋንቋ ድረ ገፅ ምረቃ እንደሚከናወን ከወጣው መርሀ ግብር ለማወቅ ተችሏል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር