የወጪ ንግድና የቡና ገበያ ዥዋዥዌ

የአገሪቷን የወጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግ በየዓመቱ የሚያዘው ውጥንና ትግበራው ዘንድሮም አልተጣጣመም፡፡ የ12ቱ ወራት የወጪ ንግድ ክንውን በ2005 ዓ.ም. ዋዜማ ላይ ሲወጠን አገሪቱ በ2005 በጀት ዓመት ታገኛለች ተብሎ የተጠበቀውን ያህል ብቻ ሳይሆን ከቀዳሚው ዓመት ክንዋኔ ጋር ሲነፃፀርም አንሶ ተገኝቷል፡፡
የ2005 በጀት ዓመት የወጪ ንግድ ገቢ ዕቅድ አምስት ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ተገኘ የተባለው ግን 3.08 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ አምና 3.2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ተገኝቶ ነበር፡፡

በበጀት ዓመቱ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ በተፈለገው ዕቅድ መጠን አለመስተካከሉ የአገሪቱ ዋና ዋና የወጪ ንግድ ምርቶች ገቢ በመቀነሳቸው ነው፡፡ በተለይ ከቡና የወጪ ንግድ ከተጠበቀው በታች የሆነ ገቢ ማስገኘቱ አንዱ ምክንያት ሆኗል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከቡና 1.2 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገኝ ታሳቢ የተደረገ ቢሆንም፣ የተገኘው ግን 746.4 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህ ገቢ በበጀት ዓመቱ ከቡና ይገኛል ተበሎ ከነበረው ገቢ በሁለት በመቶ አንሷል፡፡ ባለፈው ዓመት ተገኝቶ የነበረው ገቢ 832.9 ሚሊዮን ዶላር በመሆኑ በሁለቱ ዓመታት የተመዘገበው የውጭ ምንዛሪ ከ86 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቀንሶ ታይቷል፡፡

ከቡና የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከተጠበቀው መጠን በታች ይሁን እንጂ ለውጭ ገበያ የቀረበው የቡና መጠን ዕድገት አሳይቷል፡፡ በ2005 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ የቀረበው የቡና መጠን በ19 በመቶ አድጐ ወደ 200 ሺሕ ቶን የሚጠጋ ቡና ለገበያ ቀርቧል፡፡

በዚህን ያህል መጠን አድጐ የተላከው ቡና ለምን ገቢው ቀነሰ የሚለው ጥያቄ የተለያዩ ምክንያቶች የሚቀርቡበት ቢሆንም፣ ዋነኛ ምክንያቱ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና ዋጋ መቀነሱ ነው፡፡ በተለይ አገሪቱ የምትታወቅበት የዓረቢካ ቡና ዋጋ እስከ 30 በመቶ በማሽቆልቆሉ ነው፡፡

ከዚህም ሌላ በአገር ውስጥ የቡና ግብይት ሒደት ውስጥ ያልተፈቱ ችግሮች መኖራቸው፣ የቡና ወጪ ንግድ ወደተጠበቀው ደረጃ ከፍ እንዳይል አድርጐታል፡፡ የቡና አምራቾችም ሆነ አቅራቢዎች ምርታቸውን ለገበያ በሚፈለገው መጠን አለማቅረባቸው ከቡና ለሚገኘው ገቢ መቀነስ እንደ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡
  

የንግድ ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ ለገበያ መቅረብ ያለበትን ያህል የቡና ምርት እየቀረበ አለመሆኑን በመገንዘብ፣ በ2004 በጀት ዓመት የተመረተ ወይም ከራሚ የሚባለውን ቡና ለገበያ መቅረብ ያለበትን የጊዜ ገደብ ሦስት ጊዜ እስከማራዘም መድረሱ ይጠቀሳል፡፡

በማራዘሚያ ጊዜው ምርታቸውን ለማዕከላዊ ገበያ ያቀረቡ ያሉ ቢሆንም፣ ጥቂት የማይባሉ አምራቾች በበጀት ዓመቱ የነበረው የቡና ዋጋ ማሽቆልቆል በእጃቸው ላይ ያለውን ቡና እንዳያወጡ አድርጓል የሚለውም እምነት ለዘርፉ ከዕቅድ በታች ገቢ እንዲመዘገብ ማስቻሉን ይጠቅሳሉ፡፡ ከቡና ይገኛል የተባለው ገቢና የሚመዘገበው ውጤት መሳ ለመሳ መሆኑ የታየው ዘንድሮ ብቻ ሳይሆን ቀደም ባሉት ዓመታት ጭምር ነው፡፡

ከ2002 የበጀት ዓመት ጀምሮ በወጪ የቡና ንግድ ዕቅድና ክንውን መካከል ያለው ልዩነት ሲታይ ከመጥበብ ይልቅ እየሰፋ ነው፡፡ በ2002 የበጀት ዓመት 319,647 ቶን በመላክ 891.5 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የተላከው 53.87 በመቶ ብቻ ነው፡፡ በገቢ ደረጃም ይገኛል ተብሎ ከታሰበው ደግሞ በ48 በመቶ አንሷል፡፡

በገቢ ደረጃ ከዕቅድ ዘመኑ ይገኛል ተብሎ ከታሰበው ጋር ተቀራራቢ የሆነ ውጤት የተመዘገበው በ2003 ዓ.ም. ሲሆን፣ በዚህ በጀት ዓመት ከቡና የወጪ ንግድ 843.1 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 841.6 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት 99.8 በመቶ ማሳካት የተቻለበት ብቸኛ ዓመት ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

ይህም ገቢ የተገኘው በወቅቱ በነበረው ከፍተኛ የቡና ዋጋ ጭማሪ ሳቢያ እንጂ በበጀት ዓመቱ ይላካል የተባለውን ያህል መጠን ቡና በመላኩ አይደለም፡፡ በበጀት ዓመቱ ይላካል ተብሎ የነበረው የቡና መጠን 302,264 ቶን ሲሆን፣ የተላከው ግን 196,118 ቶን ብቻ ነው፡፡

ይህም በቡና ዋጋ መወደድ ሳቢያ ገቢው ማደጉን እንጂ በዕቅድ የተያዘውን ያህል መላክ ያለመቻሉን የሚያሳይ ነው፡፡ በ2004 በጀት ዓመትም በተመሳሳይ በዕቅድና በክንውን መካከል ሰፊ ልዩነት የታየበት ዓመት ነው፡፡ 

በ2004 በጀት ዓመት በቡና የወጪ ንግድ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ይገኛል ተብሎ ቢታሰብም፣ መንግሥትም ይህንኑ ማሳካት ሳይችል ቀርቷል፡፡ ይህ ዕቅድ የተያዘው የቀዳሚውን ዓመት የቡና ዋጋ ዕድገት ከግምት በማስገባት ሲሆን፣ ለመላክ የታቀደው የቡና መጠንም ከቀዳሚው ዓመት ይላካል ከተባለው የቡና መጠን እንዲያንስ መደረጉን ያሳያል፡፡

በወቅቱ ለውጭ ገበያ ይቀርባል ተብሎ የተያዘው 288,856 ቶን ሲሆን፣ ከዚህ ሽያጭ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ይገኛል ተብሎ ነበር፡፡ አፈጻጸሙ ግን እንደተጠበቀው አልሆነም፡፡ መላክ የተቻለው 169,392 ቶን ወይም 58.64 በመቶ ሲሆን፣ ገቢውም 832.9 ሚሊዮን ዶላር በመሆን 74.5 በመቶውን ብቻ ማሳካት ተችሏል፡፡

በሌላ በኩል በሦስት ዓመት ውስጥ ከተመረተ ቡና ውስጥ 35 ከመቶ የሚሆነው ብቻ ነው በዓለም ገበያ የቀረበው፡፡ በ2004 በጀት ዓመት የምርት ወቅት ልዩነት ያሳየ ቢሆንም፣ በሦስት ዓመት ውስጥ 65 ከመቶ የሚሆነው የቡና ምርት በአገር ውስጥ ፍጆታ መዋሉ ከፍተኛ የቡና ፍላጎት መኖሩን ያሳያል፡፡

ከ2002 እስከ 2004 ድረስ ባሉት ሦስት የበጀት ዓመታት ለወጪ ንግድ የሚቀርበውን የቡና ምርት 910,767 ቶን ለማድረስ ውጥን ተይዞ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በተጨባጭ ወደ ውጭ የተላከው የቡና ምርት መጠን 537,690 ቶን ሲሆን፣ ከዚህም የተገኘው ገቢ 2.2 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡ በዚህም ለመላክ ከታሰበው የቡና ምርት መጠን 59 በመቶ ሲላክ፣ ለማግኘት ከታሰበው ገቢ ውስጥ 77 ከመቶ ለማሳካት ተችሏል፡፡ የ2005 በጀት ዓመት ሲታከልበት ደግሞ ባለፉት አራት ዓመታት ከቡና ለማግኘት ከታሰበው ገቢ ማሳካት የተቻለው 74 በመቶ አካባቢ ብቻ ሲሆን፣ በምርት መጠን ደግሞ 60 በመቶ አካባቢ ብቻ ነው፡፡

ምንም እንኳ የቡና ምርት የወጪ ንግድ በዓለም አቀፍ ገበያ ውድድር፣ የዋጋ መውረድና መውጣት የሚወሰን ቢሆንም፣ በአገር ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች በተለይ ከአቅርቦት፣ ከቡና ጨረታ፣ ከመጋዘን አመቺነት፣ ከትራንስፖርትና ከባህር ትራንስፖርት ጋር በተያያዘ አገሪቱ በሦስት ዓመት ውስጥ ለማግኘት የወጠነችውን ገቢ እንዳታገኝ የራሳቸው ሚና እንዳለባቸው የሚጠቅሱ የጥናት ወረቀቶች አሉ፡፡

አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቡና አምራችነትዋ በሰባተኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ፣ ከአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚ የቡና አምራች አገር ነች፡፡ በ2004 የበጀት ዓመት አምስት መቶ ሺሕ ቶን ቡና በኢትዮጵያ መመረቱን የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ፡፡ ከዚህም ውስጥ ግማሽ የሚሆነው ምርት ጥቅም ላይ የዋለው ለአገር ውስጥ ፍጆታ ነው፡፡ በዚህም አገሪቱን በቡና ተጠቃሚነት ከአፍሪካ ቀዳሚ ያደርጋታል፡፡

በቡና አምራችነት የምትታወቀው ኢትዮጵያ፣ ከአጠቃላይ ሕዝቧ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከቡና አምራችነት ንግድ ጋር የተያያዘ ከመሆኑም በላይ ከወጪ ንግድ ምርቶች ውስጥ 27 ከመቶ ገቢ የሚገኘው ለዓለም ገበያ ከሚቀርበው የቡና ምርት ነው፡፡ ከዚህ በፊት ቡና ከአገሪቱ የወጪ ንግድ ወደ 60 ከመቶ የሚጠጋውን ገቢ ይይዝ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ የተለያዩ ምርቶች ለወጪ ገበያ እያቀረቡ በመምጣታቸው፣ በቡና ብቻ በአብላጫ ተይዞ የነበረው ገቢ በሌሎች እየተተካ ሊመጣ ችሏል፡፡

በዓለም ገበያ የታጠበ ቡና ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የምርት ገበያው በሦስቱ ዓመት ውስጥ ግብይት ከተካሄደበት የቡና ምርት ውስጥ የታጠበ ቡና አቅርቦት ተጨባጭ ለውጥ ሊያሳይ ሳይችል ዕድገቱ በ22 ከመቶ ነው የጨመረው፡፡ ስለሆነም ከቡና ምርት የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ በማሳደግ ለምርት ገበያው የሚቀርበው የታጠበ ቡና መጠን መጨመር ይገባዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ መጠቀስ ያለበት በ2004 የምርት ወቅት የዓለም አቀፉ የቡና ዋጋና የኢትዮጵያ ገበያ ዋጋ ከፍተኛ የዋጋ ልዩነት ያሳይ ነበር፡፡ በአገር ውስጥ የሚቀርበው ቡና ፍላጎቱ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ከዓለም ገበያ ዋጋ በላይ መሆን ችሎ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ የቡና ላኪዎችን የሚጎዳ ክስተት ሊፈጠር ችሏል፡፡ በመሆኑም በግብይት ሒደቱ ታሳቢ መደረግ እንደሚኖርበት በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ጠቁመዋል፡፡ 

በ2005 የበጀት ዓመት የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከቡና ሌላ ከዕቅድ በታች ውጤት የታየበት የወጪ ንግድ ምርት ወርቅ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ የተገኘው ገቢ 578.3 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህም ከአምናው በአራት በመቶ ቀንሷል፡፡

በወርቅ የወጪ ንግድ ገቢ መቀነስ እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው በቡና በበጀት ዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወርቅ ዋጋ መውረድ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን ከሌሎች ማዕድናት የተገኘው ገቢ 12.4 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ይህም አምና ከተገኘው በ48 በመቶ በልጧል፡፡

የቅባት እህሎች የወጪ ንግድም በተመሳሳይ ቅናሽ የታየበት ዘርፍ ሆኗል፡፡ ከቅባት እህሎች የተገኘው ገቢ በስድስት በመቶ ቀንሶ 440 ሚሊዮን ዶላር ሆኗል፡፡ በበጀት ዓመቱ ያስገኛሉ ተብለው በዕቅድ የተያዘላቸውን ገቢ ያህል ባያስገኙም፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ዕድገት ያስመዘገቡ የተወሰኑ ምርቶች ግን አሉ፡፡

በምሳሌነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት ውስጥ ጫት፣ ጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ውጤቶች ናቸው፡፡ ከባለፈው ዓመት ገቢ በ13 በመቶ ዕድገት ያስገኘው የጫት ምርት፣ ዘንድሮ 271.5 ሚሊዮን ዶላር አስገኝቷል፡፡ የቆዳ ውጤቶች 10 በመቶ፣ ጨርቃ ጨርቅ በ16 በመቶ የወጪ ንግድ ገቢያቸው ቢያድግም፣ እንደቡና፣ ወርቅና የመሳሰሉ ምርቶች ያስገኙት ገቢ መቀነሱ ለበጀት ዓመቱ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ ችሏል፡፡

ካለፈው ዓመት ክንውናቸው አንፃር ዕድገት የታየባቸው የቆዳና ጨርቃ ጨርቅ ዘርፎችም ቢሆን በበጀት ዓመቱ ይጠበቅባቸው ከነበረው ገቢ በታች አስመዝግበዋል፡፡ ከሁለቱ ዘርፎች ይገኛል ተብሎ የታሰበው ገቢ ከክንውናቸው ጋር ሲነፃፀር እስከ 30 በመቶ ቅናሽ መታየቱም ጥቅል የወጪ ገቢ ንግዱ ላይ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/business-and-economy/item/2808-%E1%8B%A8%E1%8B%88%E1%8C%AA-%E1%8A%95%E1%8C%8D%E1%8B%B5%E1%8A%93-%E1%8B%A8%E1%89%A1%E1%8A%93-%E1%8C%88%E1%89%A0%E1%8B%AB-%E1%8B%A5%E1%8B%8B%E1%8B%A5%E1%8B%8C

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር