የባንኮች የውጭ ምንዛሪ ግዢና አጠቃቀም ግልጽነት ይጐድለዋል

የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ከሚያገኝባቸው ምንጮች መካከል የውጭ ንግድ (Export) እና በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በባንኮች በኩል የሚልኩት ገንዘብ (Remittance) ዋናዎቹ ናቸው፡፡
መንግሥት የውጭ ንግዳችን እንዲያድግና ለገቢ ንግዳችን (Import) የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሰፊ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በዋናነት በቡና ላይ ተመሥርቶ የነበረው የውጭ ንግዳችን ዛሬ መሠረቱ ሰፍቶ አበባ፣ ቆዳ፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ የቅባት እህሎች፣ የቁም ከብቶችና ሌሎችም ተጨምረዋል፡፡ በውጭ ንግድ ላይ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች መሬት በአነስተኛ ዋጋ ከማቅረብ ጀምሮ ከውጭ የሚያስገቧቸው መሠረታዊ ዕቃዎች በአብዛኛው ከቀረጥና ታክስ ነፃ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ላኪዎች ገንዘብ ከባንኮች በአነስተኛ ወለድ ያገኛሉ፡፡ ከባንኮች ለሚበደሩት ገንዘብም መንግሥት ዋስትና የሚሰጥበት አግባብ አለ፡፡ ምርታቸውንም ተወዳዳሪ እንዲሆን ያለምንም ቀረጥና ታክስ ወደ ውጭ አገር ልከው እንዲሸጡ ይፈቀድላቸዋል፡፡
ታዲያ ይህ ሁሉ ማበረታቻ ተደርጎለት የሚገኝ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ላይ ክፍተት ይታያል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ አገር ገንዘቦች መግዣና መሸጫ ዋጋን ይወስናል፡፡ የየቀኑ የውጭ ምንዛሪ መግዣና መሸጫም ዋጋም በሬድዮና በቴሌቪዥን ከምንስማው ባፈነገጠ መልኩ ባንኮች ከመግዣ ዋጋ በተጨማሪ በመግዣና በመሸጫ መካከል ባለው ዋጋ (Mid rate)፣ አንዳንዴም በመሸጫ ዋጋ (Selling rate) ከላኪዎች (Exporters) እንደሚገዙ ይሰማል፡፡
በተለይ የዚህ ዓይነት የውጭ ምንዛሪ ግዢ በአገሪቱ የጠረፍ ከተሞች በኩል ከሚወጡ ዕቃዎች ሽያጭ በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ላይ እንደሚበረታታ ውስጥ አዋቂዎች ይገልጻሉ፡፡ አፈጻጸሙም ግልጽነት የጎደለው፣ ሙስና የተጠናወተው ከባንኮች የበላይ አመራር እስከ ጠረፍ አካባቢ ያሉ የቅርንጫፍ ኃላፊዎች የሚሳተፉበት መሆኑም ይገለጻል፡፡ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይህን አያውቅም ወይስ አሠራሩ ትክክልና የተፈቀደ ነው? ትክክልና የተፈቀደ ከሆነ በየቀኑ በሬድዮና በቴሌቪዥን ከምንሰማው ለምን ይጣረሳል? ማብራሪያ ቢሰጥበት ይጠቅማል፡፡
ሌላው ደግሞ ከላይ ከተጠቀሰው ሁኔታ ከፍተኛ ማበረታቻ ተደርጎለት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ላይ ያለው ክፍተት ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ በታዳጊ አገሮች ከፍተኛ እጥረት የሚታይበት ውድ ሀብት ነው፡፡ እጥረት ያለበት ሀብት ደግሞ በቁጠባና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን መርጦ መጠቀም የግድ ይላል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የውጭ ምንዛሪ ግልጽነት በጎደለውና ሙስና በተንስራፋበት ሁኔታ መሠረታዊ ለሆኑ ገቢ ዕቃዎች እየጠፋ መሠረታዊ ላልሆኑት ይመደባል፡፡ 
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዚህ ረገድም የቁጥጥር ሚናውን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም፡፡ እንዲያውም በአንድ ወቅት የባንኩ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው በወሬ ደረጃ ከሚሰሙት ያለፈ ማስረጃ ይዞ የሚቀርብ ሰው እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ በርካታ አስመጪዎች ለብዙ ወራት ተራ ጠብቀው የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻላቸው ለአንድ የአሜሪካ ዶላር እስከ አንድ ብር ከሃያ አምስት ሳንቲምና ከዚያም በላይ በመክፈል ለማግኘት ተገደዋል፡፡
ይህ ሳይወዱ ተገደው የገቡበት ሕገወጥ ተግባርን አጋልጠው ራሳቸውን እንዲወነጅሉ መጠበቁ ተገቢ አይሆንም፡፡ ይህን ከመጠበቅ የንግድ ባንኮች ግልጽነት ያለው የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ሥርዓት እንዲያሰፍኑና በዚሁ መሠረት ብቻ እንዲፈጽሙ ማድረጉ ይቀላል፡፡
የባንኮች ብልሹ አሠራር በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረው አደጋ ከፍተኛ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የንግድ ባንኮች አሠራር ከሙስና የፀዳ እንዲሆን ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ላይ ብቻ ሳይሆን በብድር አፈቃቀድ ላይ ያለው ችግር ቀላል ስላልሆነ አብሮ ሊያየው ይገባል፡፡
አጥፊዎችን ለጥፋታቸው ተጠያቂ ማድረጉ ተገቢና አስፈላጊ ቢሆንም፣ አስቀድሞ ግልጽነት ያለው አሠራር በማስፈንና በዚሁ መሠረት መፈጸሙን በመቆጣጠር ዜጎችንና የአገር ኢኮኖሚን መታደግ ያስፈልጋል፡፡ ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ ከአሁን ቀደም የአዋሽ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ላይ የቅጣት ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ አሁን ደግሞ በንብ ባንክ ሲሠሩ የነበሩ ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ሌሎች ተረኛ ይሆናሉ፡፡ እስከ ቅርብ ወራት (የባንኩ ፕሬዚዳንትና ቀጥሎም የዓለም አቀፍ ባንኪንግ መምርያ ኃላፊ ከሥራ እስከተወገዱ ድረስ) በንብ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ግዢና ሽያጭ ላይ የነበረው ሙስና፣ ፍፁም ድፍረት የተሞላበትና የቁጥጥር አካላትን (የብሔራዊ ባንክ ጭምር) መመርያና ሪፖርት በግልጽ የጣሰ እንደነበር ውስጥ አዋቂ ምንጮች በማስረጃ አስደግፈው ያቀርባሉ፡፡ ሕዝብ በተለይም ባለአክሲዮኖች ስለ ድርጅታቸው የማወቅ መብት አላቸውና በባንኩ ሲፈጸም ስለቆየው ሙስናና ከባንኩ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ዘርፎ ለዓመታት በየመን አገር ከቆየ በኋላ በቅርቡ በኢንተርፖል በኩል ተገዶ እንዲመጣ ስለተደረገውና አሁን በእስር ላይ ስለሚገኘው  ግለሰብና ተባባሪዎቹ ጉዳይ ጋዜጠኞች የሚመለከታቸውን ሁሉ አነጋግራችሁ በቂ መረጃ እንደምትሰጡንና ብሔራዊ ባንክም የቁጥጥር ሚናውን እንደሚያጠናክር ተስፋ እናደርጋለን፡፡
የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽንም ኋላ ሥራ እንዳይበዛበት ከአሁኑ በተለይ አክሲዮን ማኅበራትን መመርመር የሚያስችለውን የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖረው መግፋት ይኖርበታል፡፡ ቸር እንሰንብት!
(የኋላሸት ይልቃል፣ ከአዲስ አበባ)
*******************
መንግሥት በከተማ ውስጥ የቤት ኪራይን ለማናር የሚያደርገው ሚና
መንግሥት አገር ለማስተዳደር የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በማከናወን የሚያስፈልገውን ገቢ ከሚያገኝባቸው ዋና የገቢ ምንጮች አንዱ ግብር መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ግብር በተለያዩ ሁኔታ የሚሰበሰብ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በሚዲያ እንደምንሰማው መንግሥት ከተለያዩ የግብር ዓይነቶች የሚያገኘው ገቢ እየጨመረ ነው፡፡ የግብር ዓይነቶችን በማብዛትና አዳዲስ የግብር ስልቶችን በመንደፍ ከሌላ አገርም የአሠራር ዓይነቶችን እያስተዋወቅን ይገኛል፡፡ ከዚህም ውስጥ በቅርብ ተግባራዊ የሆነው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ግብር አንዱ ነው፡፡
የገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቱ በተቀናጀ ሁኔታ ግብር ከሚጠይቅባቸው መኖሪያ ቤቶች መካከል የኮንዶሚኒየም ቤቶች በመጀመሪያ ደረጃ ይጠቀሳሉ፡፡ ኮንዶሚኒየም ቤቶች በተወሰነ መልኩ በኮሚቴዎች የሚተዳደሩ ሲሆኑ፣  የገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቱ ከእነዚህ ኮሚቴዎች ጋር በመቀናጀት የተከራዮችን ማንነትና የሚከፍሉትን የክፍያ መጠን በማወቅ የራሱን የሆነ የግብር ተመን በማውጣት ላይ  ይገኛል፡፡ እንግዲህ እኔን የገጠመኝና ሌሎች ብዙ ሰዎችን ሊገጥማቸው ይችላል ብዬ ያሰብኩትን ችግር እነሆኝ እላለሁ፡፡ 
 በመጀመሪያ አንድ የግብር ከፋይ ግብርን ለመክፈል በሚሄድበት ጊዜ የሚያከራየው በስንት ሒሳብ እንደሆነ ይጠየቃል፡፡ መጠኑን ሲናገር፣ ትንሽ የሆነ ከመሰላቸው ሠራተኞቹ የማጣጣልና ተከራዩ ሆን ብሎ ግብሩን ለመቀነስ ያደረገው ስለሚስላቸው፣ ተመልሶ በሚኖርበት አካባቢ ካሉ ኮሚቴዎች ኪራዩን ትክክል መሆኑን ማረጋገጫ እንዲያመጣ ይጠየቃል፡፡ ማረጋገጫውን ካመጣም በኋላ ለመቀበል የማንገራገርና አከራዩንም በተለያየ ተፅዕኖ ውስጥ በመክተት ለማሳመን የመጣር ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህ እንግዲህ ተከራይና አከራይ በመመሳጠር የኪራይ መጠኑን በማሳነስ የግብር መጠኑን ዝቅ ያደርጋሉ ከሚል ግምት የመጣ ነው፡፡ 
ነገር ግን ይህ ድርጊት በኋላ የሚያስከትለውን የጎንዮሽ ጉዳትና በመሀል በበጎ አስተሳሰብ ቤታቸውን ያከራዩ አከራዮችና አቅም የሌላቸውን ተከራዮች ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ዘዴ መሆኑን ጉዳዩንና በትክክልና በጥልቀት ካለመመልከት የመጣ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ አከራዮችና ተከራዮች በመነጋገር የኪራዩን መጠን ዝቅ በማድረግ  ግብርን ለመቀነስ የሚያደርጉት ሙከራ እንደሚኖር መገመት አይከብድም፡፡ ነገር ግን ተከራይ በትክክል  ከሚከፍለው  ኪራይ በታች ውል ላይ አስፍሮ አከራዩን ለመጥቀም መሞከር ተገቢነት የሌለውና የአከራዩን ጥቅም ከአገር ጥቅም አስቀድሞ የአገሪቷን ገቢ በማሳነስ የራሱን የተከራይነት ዘመን ከማራዘም የዘለለ ምንም ጥቅም የለውም፡፡ 
ወደ ዋና ነጥብ ስመለስ መንግሥት የአከራዮችንና የተከራዮችን ባህሪ፣ ያላቸውን ግንኙነት ብስለት ወይም ስግብግብነት፣ የተከራዩን አቅም፣ ዕድሜ፣ የገንዘብ አቅም፣ የኑሮና የቤተሰብ ሁኔታ ግምት ውስጥ ሳያስገባ፣ እንደ መንደር ደላላ የአካባቢውን የቤት ኪራይ ግምት በማጠያየቅና በማስጠናት በካርቶችን እየጐዳ ነው፡፡ በዚህም አቅመ ደካማዎችን፣ በብዙ አቅጣጫ  ተቆራርጦ ጥቂት ብር እጃቸው ላይ የሚገባ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ ሴቶችን፣  የልጆች አሳዳጊ ቤተሰቦችን፣ በግለሰብ የቤት ኪራይ የተማረሩና በየጓሮ ከመኖር የወጡትን ዜጎች ሕልውና በሚፈታተን ሁኔታ፣ ለአከራዮች ይህንን ብቻ እንዴት ታስከፍላላችሁ አስተካክሉ በማለት ህልውናችንን እየተፈታተነ ይገኛል፡፡ እንደ ዜጋ በየወሩ  ከ13 እስከ 35 በመቶ የገቢ ግብር እየከፈሉና በየጊዜው  ከሚለዋወጠው የኑሮ ውድነት ጋር እየታገሉ በየሰበቡ በሚቆረጠው ደሞዛቸው  ሳይማረሩ፣ ለልማት ተባባሪ የሆኑ የግልም ሆነ የመንግሥት ሠራተኞች ቤት ሳይሰጣቸው፣ ለመንግሥት አንድም አስተዋጽኦ ሳያደርጉ  የቤት ባለቤት የሆኑ ግለሰቦች እንዳሉ የታወቀ ነው፡፡ እንግዲህ ምንም ዓይነት  የግብር ሆነ የሌላ ልማት አካል ሳይሆኑ የቤት ባለቤት  ለሆኑ ሰዎች የተረፈንን እየሰጠን በትዕግስት በምንኖርበት አገር፣ እንዴት መንግሥት ይህንን ብቻ ይከፍላሉ በማለት በጎ ሐሳብ ያላቸውን አከራዮችን ወሽመጥ ይቆርጣል? ይህ ከአንድ የመንግሥት አካል የሚጠበቅ አይደለም፡፡ መንግሥት ቢቻል የቤት ኪራይን በማረጋጋት የኑሮ  ውድነቱ አንድ አካል የሆነውን የቤት ችግር ለመቅረፍ መጣር ሲገባው፣ በዜጎች መካከል ያለመተማመንና  መልካም ያልሆነ ግንኙነት በመፍጠር ከአንድ ስግብግብ ደላላ ያልተናነሰ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው አካል በመሀል ተጎጂ የሆኑትን በጎ አከራዮችና በኢኮኖሚ አቅመ ደካማ የሆኑ ዜጎችን የማይጎዳ አካሄድ ወይም ዘዴ ቢጠቀም የተሻለ ይመስለኛል፡፡
(ታዛቢ፣ ከአዲስ አበባ)

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር