የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረትና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲዎች ውህደት ፈፀሙ

አዲስ አበባ ነሐሴ 15/2005 የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረትና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲዎች ውህደት መፈጸማቸውን ትናንት አስታወቁ። የኢትዮጵያ ማሕበረ ዴሞክራሲ-ደቡብ ኅብረት አንድነት ፓርቲ (ኢማዴ-ደህአፓ) በሚል አዲስ ስያሜ ውህደቱን ይፋ ያደረገው ይኸው ፓርቲ የፀረ-ሽብር ሕጉን እንደሚቃወም አስታውቋል። የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጥላሁን እንደሻው ውህደቱን አስመልክቶ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት ሁለቱ ፓርቲዎች በአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ በነበራቸው የጋራ አቋም ራዕያቸውን በጋራ ለማሳካት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። የኢትዮጵያ ማሕበረ ዴሞክራሲ-ደቡብ ኅብረት አንድነት ፓርቲ (ኢማዴ-ደህአፓ) ሕጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ በማቅረብ ቦርዱ ሰኔ 3 ቀን 2005 ዓ.ም የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መስጠቱን ገልጸዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ውህደቱን በትናንትው ዕለት ይፋ ያደረገው ይኸው ፓርቲ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ በአገሪቱ ተግባራዊ የሆነውን የፀረ-ሽብር ሕግን እንደሚቃወም አስታውቋል። እንደ አቶ ጥላሁን ገለፃ የፀረ-ሽብር ሕጉ ሠላማዊ የሕዝቦች ተቃውሞን የማፈን ባህሪይ ስላለው ፓርቲያቸው እንደ ሌሎች የመድረክ አባላት ሁሉ ሕጉን ይቃወማል። ፓርቲው በማኒፌስቶው በግልጽ እንዳስቀመጠው የፀረ-ሽብር ሕጉ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚጋፋ በመሆኑ ሕጉን አጥብቆ እንደሚቃወም ገልጸዋል። በዚህም በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም ፓርቲው ከመፈለግ ባሻገር ትግል እንደሚያደርግ አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ማሕበረ ዴሞክራሲ-ደቡብ ኅብረት አንድነት ፓርቲ የኃይማኖት አክራሪነትን፣ የኃይማኖታዊ መንግሥት መቋቋምን እንዲሁም ኃይማኖትና መንግሥት አንዳቸው በሌላው ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እንደሚቃወም አስታውቋል። በአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠባብ እንደሆነ አቶ ጥላሁን ገልጸው መንግሥት በፓርቲውና በአባላቱ ላይ አፈና እና ጫና እያደረሰ እንደሆነም አመልክተዋል። በፍትህ ሚኒስቴር የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ በሥራ ላይ ያሉት የአገሪቱ ሕጎች ሽብርተኝነትን በበቂ ሁኔታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ባለመሆናቸው ጠንካራ የሕግ አቅም መፍጠር አስፈልጓል። ሽብርተኝነት ለኢትዮጵያ ሠላም፣ ደህንነትና እድገት ፀር እንደሆነና ለአካባቢዋና ለዓለም ሠላምና ደህንነትም ከፍተኛ ስጋት መሆኑንም አመልክተዋል። በመሆኑም ይህንን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ለማምከን የሚያስችል የተጠናከረ የምርመራና የክስ አቀራረብ ስልትና ሥርዓት በሕግ ማቋቋም በማስፈለጉ አዋጁ በአገሪቱ ሕግ አውጪ አካል ፀድቆ ተግባራዊ ሆኗል። አዋጁ አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደሚሉት ግለሰቦች ያለ በቂ ምክንያት የሚታሰሩበት ሳይሆን በሽብርተኛነት ሊያስጠረጥር የሚችል በቂ መረጃና ማስረጃ እንዲሰበሰብ የሚደነግግ መሆኑን ገልጸዋል። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስለ ሕጉ የሚያናፍሱት አሉባልታ ተገቢ ያልሆነ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘትና ለዜጎች ጥበቃ በሚያደርገው የደህንነት ሥራ ላይ ተጽእኖ ለማሳደር የሚደረግ ሕገ-ወጥ ተግባር መሆኑንም አመልክተዋል።
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=11076&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር