ለአክሲዮን ማህበራት የትርፍ ክፍፍል ግብር አዲስ መመሪያ ተግባራዊ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 13 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) የአክሲዮን ማህበራት የትርፍ ክፍፍል ግብርን አስመልክቶ አዲስ የአፈፃፃም መመሪያ ተግባራዊ ሆነ።
አዲሱ መመሪያ የትርፍ ክፍፍል ሳይደረግ በአክሲዮን ባለድርሻዎች ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንዲውል በቃለ ጉባኤ ከተወሰነ እና ይህንንም በህጋዊ መንገድ ማረጋገጥ ከተቻለ ከትርፍ ክፍፍል ታክስ ነፃ ያደርጋቸዋል መመሪያው ።
በመመሪያው መሰረት በሰነዶች ማረጋጋጫና በንግድ ሚኒስቴር ሳይረጋገጥ ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት ውሏል የሚል ምክንያት ቦታ የሌለው ሲሆን ፥ የትርፍ ክፍፍሉም እንደተፈፀመ ታሳቢ ተደርጎ 10 በመቶ የትርፍ ክፍፍል ታክስ እንዲከፍሉ ይደረጋል ነው ያለው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን።
ከሀምሌ 30 ጀምሮ ተግባራዊ በሆነው በዚህ መመሪያ ዙሪያ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ዛሬ ተወያይቷል።

የቀደሞው ንግድ ህግ ክፍተቶች
በ19 94 ዓ.ም የወጣው የንግድ ህግ ላይ ማንኛውም የአክሲዮን እና ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በየዓመቱ ከሚያገኘው ትርፍ እና ለአባላቱ ከሚያከፋፍለው ትርፍ ውስጥ 10 በመቶ ግብር እንዲከፍል ይደነግጋል።
ይህን ህግ በፍጥነት ተግባራዊ በማድረጉ በኩል በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን  የትርፍ ክፍፍል ግብሩንም እያሳወቀ በመክፈል ረገድ በንግዱ ማህበረሰብ በኩል በነበረው ክፍተት በሚገባ ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል ።
ህጉ የኩባንያዎቹ ትርፍ ለአባላት ሲከፋፈል ግብር እንደሚከፈል ይገልፃል ።
አብዛኛዎቹ የንግዱ ማህበረሰብ አባለት ደግሞ ይህን ትርፍ ለአባላቶቻችን እስካላከፋፈልን ድረስ የ10 በመቶ ግብርን መክፈል እንደማይገደዱ በመግለፅ ለካፒታል ማስፋፊያ አውለነዋል የሚል ምክንያት የሚያቀርቡበት ሁኔታ ነበር ።
የለም ኩባንያዎቹ አመታዊ ትርፍ በየጊዜው ለአባላቸው ያከፋፍላሉ ተብሎ የሚታሰብ ስለሆነ መክፈል አለባችሁ የሚለው እና የመንግስትን ግብር ከፍላችሁ ቀሪውን ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት አውሉት የሚለው ደግሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሃሳብ ነው።
በእነዚህ ሁለት የተለያዩ ምክንያቶችም ለረጅም ጊዜ የትርፍ ክፍፍል ግብር በአግባቡ ሳይሰበሰብ ቆይቷል።
ይህን የተጠራቀመ የትርፍ ክፍፍል ግብርን አስመልክቶ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ወለድና መቀጮውን በማንሳት ፍሬ ግብሩን ብቻ ከጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ መሰብሰብ ጀምሮ ነበር።
የዚህ ህግ ተርጓሚ እና የበላይ አስፈፃሚ የሆነው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርም በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አቋም የገለጸ ሲሆን ፥ ሚኒስትሩ አቶ ሶፊያን አህመድ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገራችን በተከናወነው የቢዝነስ ጉባኤ ላይ ያልተከፋፈለ የአክሲዮን ማህበር ትርፍ ግብር እንደማይከፈልበት ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎ በሁለቱም ወገኖች በግብር ሰብሳቢው እና ግብር ከፋዩ መካከል ለተፈጠረው የረዥም ጊዜ አለመግባባት መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል የአፈፃፀም መመሪያም ውጥቷል።

አዲሱ መመሪያ እና የንግድ ህጉ አተገባበር
ይህ የአፈፃፀም መመሪያ ከሀምሌ 30 ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ነው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዛሬ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ባደረገው ውይይት የገለፀው።
በዚህ መመሪያ መሰረት በየዓመቱ የትርፍ ክፍፍል የሚያደርጉ ድርጅቶች 10 በመቶ የትርፍ ግብር ሲከፍሉ ፥ አወዛጋቢ የነበረው እና የትርፍ ክፍፍሉን ሳያደርጉ ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት አውለነዋል ለሚሉ ኩባንያዎች ደግሞ ከትርፍ ግብር ነፃ ይሆናሉ።
ለዚህም ያገኙትን ትርፍ ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት ማዋላቸውን የአክሲዮን ባለድርሻዎቹ በመተዳደሪያ ደንባቸው ቃለ ጉባኤ ካፃደቁ እና ካፒታላቸውን በትክክል ስለማሳደጋቸው ከሰነዶች ማረጋገጫ እና ከንግድ ሚኒስቴር ህጋዊ ሰነድ ማቅረብ ከቻሉ መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ በከር ሻሌ ይናገራሉ።
 ይህን ህጋዊ ማረጋገጫ ሳያቀርቡ እና አመታዊ የትርፍ ክፍፍል ለአባላቶቻቸው ሳያደርጉ ለስራ ማስኬጃ አውለናል በሚል ምክንያት ከትርፍ ግብር ነፃ መሆን ግን አይቻልም ነው ያሉት።
 በመሆኑም ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት ማዋላቸውን በህጋዊ ሰነድ ማረጋገጥ የማይችሉ የአክሲዮን ማህበራት ለባለድርሻዎቻቸው እንዳከፋፈሉ ታሳቢ ተደርጎ የ10 በመቶ የትርፍ ግብር እንዲከፍሉ ይደረጋል ።
 መመሪያው አንድ የአክሲዮን ድርጅት የሂሳብ ዘመኑ ከተጠናቀቀ በኋላ ባሉት 12 ወራት ውስጥ ያገኘውን ትርፍ እንደሚያከፋፍልና ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንደሚያውል ከባለድርሻዎቹ ጋር እየተወያየ በየጊዜው ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እንዲያሳውቅ ያስገድዳል።
 የትርፍ ክፍፍሉን የሚያካሂድ ከሆነ በዚሁ ጊዜ ይከፍላል ፤ ለተጨማሪ ማስፋፊያ ካዋለም በህጋዊ ሰነድ እንዲያሳውቅ ይደረጋል ነው ያሉት አቶ በከር ።
 ከዚህ ባለፈ ግን ውዝፍ የትርፍ ግብር ለመክፈል ከዚህ ቀደም የተነሳው ቅጣትና ወለድ እንዳለ ሆኖ ቅድሚያ 25 በመቶ እየተከፈለ እንደየሁኔታው እስከ 3 አመት የእፎይታ ጊዜም መመሪያው ይሰጣል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር