ወደ ሀዋሳ የሚገቡ የኮንትሮባንድ እቃዎች እየተበራከቱ መጥተዋል - ነዋሪዎች

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 20 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) ወደ ሀዋሳ ከተማ የሚገቡ የኮንትሮባንድ እቃዎች መጠን በከፍተኛ ሁኔታ  እየጨመረ መምጣቱን የከተማዋ ነዋሪዎች ይገልፃሉ ።
ነዋሪዎቹ በዋናነት ከኬንያ ተነሰተው በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ከተማዋ  እየገቡ ያሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች ህጋዊ ነጋዴዎችን ከመጉዳቱም በላይ የንግድ ውድድሩ ላይ አሉታዊ ተጽህኖ እየፈጠረ እንደሚገኝም ነው የሚናገሩት።
እቃዎቹን ሰውሮ የማስገባት ስልቱ  በየጊዜው እየተቀያየረ መምጣቱን እና አንዳንድ የፍታሻ ጣቢያዎች ላይ የቁጥጥር ሂደቱ መላላቱን ነው ነዎሪዎች የሚጠቅሱት ።
እነዚህ እቃዎች በምንም መንገድ ይግቡ እንጂ ህገወጥ በመሆናቸው  መንግስት ከቀረጥ ማግኘት ያለበትን ከፍተኛ ገቢ በማሳጣት አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድሩ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
የንግድ ውድድሩ ላይ ሳንካ በመፍጠር ህጋዊውን ነጋዴ በማዳከም ከሚፈጥሩት ጫናም ባለፈ ፥  ተገቢውን ፍተሻ እና የጉምሩክ ሰርዓትን ተከተለው ወደ ገበያ ባለመግባታቸው  በሰው ጤና እና ንብረት ላይም የከፋ ጉዳት እንደሚያደርሱም ይታወቃል።
በተለይ ልባሽ ጫማና የተለያዩ ኤሌክቶሮኒክስ ውጤቶች  ከሌሎቹ የበለጠውን ድርሻ የሚይዙ ሲሆን ፥ ይህ በመሆኑም ህጋዊ መንገድን ተከትለው የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ሁኔታው ነገሮችን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው እና ጉዳዩ በአቋራጭ የመበልጸግ ስልት ተደርጎ እየተወሰደ በመሆኑም የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲወስድም ነው የጠየቁት።
የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪ ፅህፈት ቤት ሀላፊ በነዋሪው የተነሳውን ቅሬታ በመቀበል ፥ ችግሩን ለማስወገድ በዋናነት ህገወጥ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በሀገር ላይ የሚያደርሰውን ችግር ማሳወቅ ቀዳሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በእርግጥ ለውጦች እየመጡ እንደሚገኙ ያወሱት ሃላፊው ፥ በአሁኑ ወቅትም ይህንን ስራ ሲያከናውኑ የነበሩ ሀይሎችን ወደ ህጋዊ መስመር የማስገባት ስራም መጀመሩን ተናግረዋል።
በኢትዮጰያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ሀጎስ አባይ በበኩላቸው ፥በ2005 ዓ.ም በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ሀዋሳ ሊገቡ ሲሉ የተያዙ እና 62 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥረ ስር መዋላቸውን አስረድተዋል።
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት አመት በህገ ወጥ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴው ውስጥ ከተገኙት 90 ከመቶው የሚሆኑትን ማስቀጣት የተቻለ ሲሆን ፥ የፍርድ ሂደቱን በሀዋሳ ፣ ዲላ ፣ ሻሸመኔ ፣ ሮቤና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴው ሲፈጸም በተገኙባቸው አካባቢዎች እንደተከናወነም ነው የገለጹት።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር