ሃዋሳ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት ከወሰንሰገድ ገ/ኪዳን (ጋዜጠኛ)

ወቅቱ ፦ከኣንድ ኣመት በፊት

እንደመነሻ

“አዳራሽ ተቀምጣ ስታበላ ሥጋ ስታጠጣ ጠጅ
ስዕል ትመስላለች የምኒሊክ ልጅ”

እንዲህ ሆነ፡-
ዕለተ እሁድ መስከረም 27 ቀን 2005 ዓ.ም ረፋዱ ላይ ድንገት ብድግ ብዬ ወደ ሃዋሳ መረሽኩ፡፡ የሁለት ቅን እና ትንታግ ወጣቶች (መስከረም እና ፍፁም) ደግነት ነው ወደ ሃዋሣ ያንደረደረኝ፡፡ የእንዳልክና የፀሃይም ደግነት የጉድ ነው፡፡
እነሆ ሃዋሳን ለሁለተኛ ጊዜ ረገጥኳት፡፡ ድንቅ ከተማ ናት፡፡ አውራጎዳናዎቿ የተወለወሉ ይመስላሉ፡፡ አንድ ወጥ የሆነ መልክና ስፋት አላቸው፡፡ እንደእኔ ዓይነቱን አልፎሂያጅ መንገደኛ “ሊያምታቱ” ይችላሉ፡፡ አቀያየሳቸውም አነጣጠፋቸውም ፍፁም ተመሳሳይ ስለሆነ ወደሌላ ቦታ መሄድ ያሰበ ሰው ተጉዞ ተጉዞ ራሱን እዚያው የተነሳበት ቦታ ሊያገኘው ይችላል፡፡ ስለዚህ ከከተማዋ አንድ ጥግ ወደሌላ ጥግ መሄድ የፈለገ ሰው፣ ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ቆም ብሎ እንደአሸን እየፈሉ ካሉት ትልልቅ ሕንፃዎች መሃል አንዱን በምልክትነት 
Posted on Ethiopiansemay.blogspot.com 

ሃዋሳ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት
ከወሰንሰገድ ገ/ኪዳን (ጋዜጠኛ)

እንደመነሻ

“አዳራሽ ተቀምጣ ስታበላ ሥጋ ስታጠጣ ጠጅ
ስዕል ትመስላለች የምኒሊክ ልጅ”

እንዲህ ሆነ፡-
ዕለተ እሁድ መስከረም 27 ቀን 2005 ዓ.ም ረፋዱ ላይ ድንገት ብድግ ብዬ ወደ ሃዋሳ መረሽኩ፡፡ የሁለት ቅን እና ትንታግ ወጣቶች (መስከረም እና ፍፁም) ደግነት ነው ወደ ሃዋሣ ያንደረደረኝ፡፡ የእንዳልክና የፀሃይም ደግነት የጉድ ነው፡፡
እነሆ ሃዋሳን ለሁለተኛ ጊዜ ረገጥኳት፡፡ ድንቅ ከተማ ናት፡፡ አውራጎዳናዎቿ የተወለወሉ ይመስላሉ፡፡ አንድ ወጥ የሆነ መልክና ስፋት አላቸው፡፡ እንደእኔ ዓይነቱን አልፎሂያጅ መንገደኛ “ሊያምታቱ” ይችላሉ፡፡ አቀያየሳቸውም አነጣጠፋቸውም ፍፁም ተመሳሳይ ስለሆነ ወደሌላ ቦታ መሄድ ያሰበ ሰው ተጉዞ ተጉዞ ራሱን እዚያው የተነሳበት ቦታ ሊያገኘው ይችላል፡፡ ስለዚህ ከከተማዋ አንድ ጥግ ወደሌላ ጥግ መሄድ የፈለገ ሰው፣ ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ቆም ብሎ እንደአሸን እየፈሉ ካሉት ትልልቅ ሕንፃዎች መሃል አንዱን በምልክትነት ማስተዋል አለበት፡፡ የሃዋሣ መንገዶች ፍፁማዊ አንድወጥነት አስገርሞኝ ዋዘኛ ጥያቄ የሰነዘርኩለት ወዳጄ “ሃዋሣ አዙሪት ነገር አለባት የሚባለው ለዚህ ነው” የሚል ምላሽ ነበር የሰጠኝ፡፡ የሆኖ ሆኖ ሃዋሳ አ/አበባን የምትስንቅ ፅዱና ውብ ከተማ ናት፡፡
ወደ ሃዋሣ ከመጓዜም በፊት ሆነ በጉዞ ላይ እያለሁ የ2005 ዓ.ም መጥባትን ተከትሎ በምድረ ኢትዮጵያ የተከሰተውን “ድንገቴ ለውጥ” እያሰላሰልኩና በደቡብ ህዝቦች መናገሻ ከተማ ይገጥመኛል ብዬ የማስበውን እየገመትኩ ነው የሄድኩት፡፡


ግምቶቼ
(1)ባልታሰበ፣ ባልተገመተና ባልተጠበቀ ሁኔታ አዲሱ ጠ/ሚ/ር የወጡባት ክልል ዋና ከተማ ናት፡፡ በዚህም የተነሳ ሃዋሳን በለውጡ ኩራትና ሞገስ ተሞልታ አገኛታለሁ ብዬ ገመትኩ፡፡
(2) በኢትዮጵያ ታሪክ የፌዴራል መንግስት ዋንኛ መንበረ መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ደቡብ ክልል የሄደበት ዘመን ነው፡፡ እናም የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ከወትሮው በተለየ መልኩ “ደስተኛ” ሆነው አገኛቸዋለሁ ስል ገመትኩ፡፡
(3) በዚህም የተነሳ የተሟሟቀ የፖለቲካ ውይይት የተጧጧፈባት፣ ድንገቴውን አዲስ ክስተት በተመለከተ ከሃሳብ ፍጭትና ክርክር ባሻገር አዲስ ራዕይ ከየአቅጣጫው የፈነጠቀባት፣ አዲስመንፈስ የረበበባት ከተማ ሆና አገኛታለሁ ስል ገምቼ ነበር፡፡ ሌላም ሌላም ግምቶች ደርድሬ ነበር፡፡ በሁለት ቀን ቆይታዬ ያስተዋልኩት ግን ግምቴ የተዛባ መሆኑን ነው፡፡ እንደው በጥቅሉ፣ ከጥቅሉም በጥቅሉ፣ በአዲሱ ጠ/ሚ/ር ኃይለማረያም ደሳለኝ ሹመት የሞቃትም የበረዳትም አትመስልም፡፡ እንዴት? ከአስተውሎቴ እያጣቀስኩ ላስረዳ፡፡

አስተውሎቴ
አዲስ አበባንና አዲስ አበቤን፣ በጥቅሉ የፖለቲካ ጉዳይ የሚኮሰንረንን፣ እንዲሁም ዴያሰፓራውን ጭምር ሰጣ-ገባ ውስጥ የከተተን፣ የጉዱ የሚያነታርከንና የሚያወዛግበን የአዲሱ ጠ/ሚ/ር ሹመት ጉዳይ (በኢህአዴግ አባባል መተካካትና ለውጥ)ሃዋሳዎችን ግድ የሰጣቸው አይመስልም፡፡ በሃዋሳ አራቱም አቅጣጫዎች ስዟዟር ጉዳዩን “ጉዳዬ” ብሎ በጭምጭምታ እንኳ የሚነጋገርበት አላገኘሁም፡፡ የክስተቱ ትኩስነት አላተኮሳቸውም፡፡ ይህ ሁኔታ ገርሞኝ እንደዘበት ሃሳብ የጠየቅኳቸው ሰዎች በአብዛኛው ስሜታቸውን የገለፁልኝ በሁለት መንፈስ ነው፡- አንድም በዝምታ፣ አንድም በቀዘዘ መንፈስ፡፡
ሃሳባቸውን ሊያካፍሉኝ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች የአዲሱ ጠ/ሚ/ር ሹመት በሃዋሳና በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ የ”ዝምታ” መንፈስ ያሰፈነበት “የተለየ” ምክንያት አለው ባይ ናቸው፡፡ ያ ምክንያት በርካታ ዓመታተን ያስቆጠረ ፖለቲካዊና ታሪካዊ ዳራ እንዳለው አስረጅ ያሉትን ያጣቅሳሉ፡፡ እኔም የነገሩኝን እጅግ በጣም አሳጥሬ (ጨምቄ)በቅደም ተከተል ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡ 

የመጀመሪያው፡- የሃዋሳ ከተማ አመሰራረት ነው፡፡ ሃዋሳ ከተማ የተመሰረተችውም ሆነ የተገበባችው በሲዳማ ዞን ውስጥ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ነባሮቹ ነዋሪዎች (ሲዳማዎች) ቁጥራችን ከ3 ሚሊዮን በላይ ስለሆነ ክልል የመሆን መብት ይሰጠን ሲሉ መጠየቃቸው የአደባባይ ምሰጢር ነው፡፡ ይህ ጥያቄአቸው በተለያየ ጊዜ እያገረሸ ሲከስምም ቆይቷል፡፡ ባለፈው አመት 2004ዓ.ም ነሐሴ ወር ጉዳዩ ሰጥአገባ አስነስቶም ነበር፡፡ በያዝነው ዓመት መስከረም ወር አጋማሽ የደቡብ ክልል መንግስት ባዘጋጀው ትልቅ ኮንፈረንስ የተነሳው ጥያቄ የደቡብ ክልል ብሔር ብሔረሰቦችን የማይጠቅም መሆኑን አስምሮበት ተጠናቋል፡፡ በዚህ ኮንፈረንስ ላይ የተገኙ ዕድምተኞች “አብዮታዊ ስብዕና በመላበስ” የጥያቄውን ፋይል እንደዘጉትና ወደፊትም እንደሚዘጉት በመገናኛ ብዙሃን ነግረውን እንደነበር ያስታውሷል፡፡ ይሁን እንጂ የጥያቄው ምላሽ ህዝቡን “አብዮታዊ ስብዕና ያላበሰው” አይመስልም፡፡
“ይህ እና ይህን መሰሉ ነባራዊ ሁኔታ” ይላሉ ሃሳባቸውን ያካፈሉኝ ሰዎች “አዲሱ ጠ/ሚ/ር ከደቡብ ክልል የወጣ ቢሆንም፣ ለእኛ ትርጉም የለውም የሚል ስሜት አሳድሯል፤ ሹመቱ ደስተኛ አላደረጋቸውም” ሲሉ በአፅንኦት ይገልፃሉ፡- አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ የወላይታ ብሄር ተወላጅ መሆናቸውን ጭምር እያጣቀሱ፡፡
ይህ አስተያየት ባለቅኔ ዮሐንስ አድማሱ “እንግዳ ዓለም” በሚል ርዕስ ከፃፈው ግጥም ውስጥ የሚከተሉትን ስንኞች አስታወሰኝ፡-
“ይህ ታላቅ አጎበር ከላይ ተዘርግቶ
ይህ ዓለም ከስሩ ምንጣፍ ተንሰራፍቶ
ውርውር ባዮቹ
አለን ተቀምጠን እኛ ነን ሰዎቹ፡፡…”

በነገራችን ላይ ይህ አስተያየት የደቡብ ክልል ሕዝቦችን በሙሉ ይወክላል ብዬ አላስብም፡፡ አይወክልምም፡፡ ምክንያቱም በአቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝን ሹመት በአዎንታዊ ሁነትነቱ የሚመለከቱ ብዙ ሰዎች አግኝቻለሁ፡፡ ይሁን እንጂ በቀና መልክ ከተቀበሉትም መሀከል ጥቂት የማይባሉት “ጥርጣሬ” ያላቸው መኖራቸውን ታዝቤያለሁ፡፡ እነኚህኞቹ በሹመቱ ጉዳይ ከመናገር ይልቅ ዝምታን የመረጡ ዓይነት ናቸው፡፡ የእነዚህን አመለካከት ነው በሁለተኛ ምክንያትነት ያስተዋልኩት፡፡

ምክንያታቸው እጅግ ጠቅለል ባለ ሁኔታ ሲገለፅ ሰውዬው ሥልጣናቸውን በአግባቡ መጠቀም አይችሉም የሚል ነው፡፡ ከደቡብ ክልል የወጣ ሰው የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ሥልጣን መያዙ ደስ ቢያሰኛቸውም፣ በሥልጣናቸው ይህ ነው የሚባል የወሳኝነት ሚና አይኖራቸውም፤ ሥልጣናዊ ኃይላቸው ለንቋሳ ነው፡፡ ከሥልጣነ- መንበራቸው ጀርባ ውጫዊ እና ውስጣዊ ተግዳሮት ስለሚገጥማቸው ሹመቱ ልብን በኩራት አይሞላም ባይ ናቸው፡፡
ለዚህ ፅሁፍ መንደርደሪያነት የነቀስኩት የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ቅኔን ያስታወሰኝ ይህ አሰተያየር ነው፡፡ ነጋድራስ ተሰማ ከአፄ ምኒሊክ እስከ አፄ ኃይለስላሴ ዘመን በነበረው ስርዓት ያገለገሉ ሹመኛ ናቸው፡፡ በዚያ ዘመን የሰሉ ትችቶችን በመሰንዘር የሚታወቁት ነጋድራስ፣ የንግሥተ-ነገሥታት ዘውዲቱ ሥልጣን ስማዊ እንጂ ገቢራዊ አለመሆኑን እንዲህ ባለ መልኩ ነበር የገለፁት፡፡
“አዳራሽ ተቀምጣ ስታበላ ሥጋ ስታጠጣ ጠጅ
ስዕል ትመስላለች የምኒሊክ ልጅ”
ነጋድራስ “ስዕል ትመስላለች” ሲሉ የንግስት ዘውዲቱ ውበት ድንቅ ነው ማለታቸው ነው፡፡ ይቀጥላሉ፡፡ ንግሥቲቱ ንግስቲቱ ያበላሉ፣ ይጠጣሉ፣ ለጋስ እና ደግ ናቸው ብለው የሚያወድሱ መስለው በትችት ይሸነቁጧቸዋል፡፡ እንዴት ቢሉ፣ ሥዕል ህይወት አልባ ነው፡፡ የሚታይ፣ የሚደነቅ እንጂ የማይናገር፣ የማይጋገር እና የማይሰራ ነውና፡፡ በሌላ አነጋገር ንግስቲቱ በሀገሪቷ የፖለቲካ አስተዳደር ቁንጮውን ሥልጣን ቢይዙም፣ ጎልኀተ የሚወጣ ተግባር ወይም የመሪነት ሚና የላቸውም ማለታቸው ነው፡፡ ለማንኛውም የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስተርነት ስልጣን እንዲሁ ጥርጣሬ ውስጥ የከተታቸው በጉዳዩ ላይ ዝምታን መምረጣቸውን ይናገራሉ፡፡

ሌሎችም የሃዋሳ ነዋሪዎች አሉ፡- በሰውዬው ሹመት የተደሰቱ፣ ግን ደግሞ የሚሆነውን ሁሉ በዝምታ ለማየት የመረጡ፡፡ የእነኚህኞቹ አስተያየት “ለየት” እና “ወጣ” ያለ ይዘት አለው፡፡ የሰውየው የጠ/ሚ/ርነት ሹመት “በአሜሪካ ተፅዕኖ እና እጅ ጠምዛዥነት የተገኘ ነው” የሚል አንደምታ አለው፡፡ ለዚህ አመለካከታቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈተ-ዜና ከተሰማበት ዕለት አንስቶ የተከሰተ አንኳረ አንኳር ሁነቶችን በቅደም ተከተል ያጣቅሳሉ፡፡
የአቶ መለስ ሞት በተሰማበት ዕለት አቶ በረከት ስምኦን የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን አቶ ኃ/ማርያም እንደሚይዙ መናገራቸውን፣ ነገር ግን የተባለው አለመሆኑን ወዘተ ያስታውሳሉ፡፡ የኋላ ኋላ ፓርላማው በአስቸኳይ ስብሰባ ሹመቱን ያፀደቀላቸው በአሜሪካ ቀጭን ትዕዛዝ ነው ባይ ናቸው፡፡

“… አሜሪካ ሰውዬው በሙሉ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ የተባበሩር መንግስታት ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ያደረገችው ለራሷ ጥቅም ነው፡፡ ለዚህም ማሳያው ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው የማታውቀውን የገንዘብ ዕርዳታ ከዓለም ባንክ እንድታገኝ መደረጉ ነው፡፡ ዓለም ባንክን የምታሾረው ደግሞ አሜሪካ ናት፡፡ዕርዳታውን ዋናውን ስልጣን ከተቀበሉ ጥቂት ቀናት ብቻ ላስቆጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ያስጨበጠችው፣ ሰውየው እንደአቶ መለስ በአሸባሪነት ጉዳይ ላይ ታዛዥ እንዲሆኑላት ነው፡፡ ህጋዊ ታዛዥ ለማግኘት ሲሉ ነው ሰውየው የሙሉ ጠቅላይ ሚኒስትርነት በአስቸኳይ እንዲያገኙ ስውር ሚና የተጫወተችው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ሙሉ ስልጣን ከያዙ በኋላ ሥልጣናቸውን የሚፈታተን ካለ፣ መፈንቅለ መንግስት ተካሂዷል በሚል ሰበብ በውስጣዊ ጉዳያችን ጣልቃ ለመግባት አስልታ የፈፀመችው ነው፡፡ … ወ.ዘ.ተ” ባይ ናቸው፡፡ በዚህና በዚህ መሰል ምክንያት የአቶ ኃይለማርያም ሹመት የማይሞቅም የማይበርድም ስሜት እንዳሳደረባቸው፣ ሰውየው በሁለት ኃይሎች የስቅዝ የተያዙ መሆናቸው እንደሚታያቸው፣ ይህም ዝምታን እንዳስመረጣቸው ይገልፃሉ፡፡
እንዲያም ተባለ እንዲህ፡- የደቡብ ሕዝቦችና ብሔር ብሔረሰቦች ዋና መዲና የሆነችው ሃዋሳ እና የአካባቢው ነዋሪዎች የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመት ብዙም ቁብ የሰጣቸው አይመስልም፡፡ የሚነጋገሩበትና የሚወያየዩበት አጀንዳቸው አላደረጉትም፡፡ በጣም ካልቀረቧቸው እና የጓደኝነት ሥሜት ካላደረባቸው ለማንም ምንም ማለት የሚፈልጉ አይደሉም፡፡ ስለጉዳዩ ቢያነሱባቸው፣ ምንም እንዳልሰማ ሆነው ፊታቸውን ያዞራሉ፤ ወይም ጥለውዎት ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ አዎ በሃዋሳ ያስተዋልኩት ያልጠበቅሁትን ነው፡፡ “የቀዘዘ”ችዋን ሃዋሳ፡፡ እነሆ በዚህ መልኩ ያገኘኋትን ሃዋሳ፣ ከሁለት ቀን ቆይታ በኋላ ቸር ክራሞት ተመኝቼላት ተሰናበትኳት፡፡ አአንባቢዎቼም እንዲሁ - ቸር ክራሞት!!
Posted on Ethiopiansemay.blogspot.com (ethiopian Semay facebook)


Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር